በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
የሰው ልጅ ታሪክ አለው። ታሪክ ደግሞ በጊዜና በዘመን ውስጥ ያልፋል። የእያንዳንዳችን ታሪክ ከውልደት የሚጀምር በሞት የሚጠናቀቅ የዘመን ሀቅ ነው። ይህ ተፈጥሯዊ እውነት ደግሞ የሰውን ልጅ ማረፊያ አድርጎ በተቀመጠለት የሥርዓት አውድ ውስጥ እየመጣ የሚሄድ ነው። ሀጂውን እየሸኘ..መጪውን እየተቀበለ በማይዛነፍ ፍጹም እውነት ውስጥ ይጓዛል..የሰውን ልጅ ጉዳይ አድርጎ።
ጊዜ ጌታ ነው..ጊዜ ፈራጅ ነው። ጊዜ መጽናናት መሻርም ሁሉንም ነገር ነው። በተፈጥሮ እውነት የጸና..በሚዛናዊነት ምህዋር ውስጥ ሳይንገዳገድ የቆመ እግዚአብሔራዊ ጽኑ ቃል እንዲህም ነው። የጊዜ ጌትነት ግን በራሱ የሚሆን ሳይሆን በሰው ልጅ የማሰብ አቅም የሚወሰን የአእምሮ ነጸብራቅ ነው።
የእያንዳንዳችን ትናንት የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ፣ የእያንዳንዳችን ድሮና ዘንድሮ፣ አምናና ካቻምና በዚህ በጊዜና በሰው ልጅ የጋርዮሽ መስተጋብር የተቃኘ ነው። የሰው ልጅ በጊዜ ውስጥ ባለታሪክ ነው። ጊዜ በሰው ልጅ ውስጥ ጉልበታም ነው። ጊዜና የሰው ልጅ እጅና ጓንት፣ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። ሁለት አካል አንድ ገጸ ሰብ፣ ሁለት ገላ አንድ ዓይነት መልክ። በተፈጥሮ እውቀትና ጥበብ ተሰናስለው የተደሩ የዳበሩም እንዲህ ዓይነት።
ለዚህም እኮ ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ነፍስና ስጋ ፍለጋ የምንዋትተው። ለዚህ እኮ ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከአምናው የተለየን ለመሆን በአዲስ እቅድና በአዲስ ምኞት የምንሳበው። ለዚህ እኮ ነው ዕድሜአችን የሚያሳስበን፣ሞታችን የሚያስጨንቀን።
አዲስ ዓመት እንደ ትርጉሙ አዲስ ነው። በውስጡ አንዳች ኃይልና ብርታት አለው። ለሰው ልጅ ሁሉ የሚሆን የመታደስ፣ የመበርታት መንፈስን በውስጡ ይዟል። ብዙዎቻችን ይሄን ኃይል እንፈልገዋለን። በዚህ ኃይል ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ለዚህም ዓመት ጠብቀን የምናቅድ፣ ዓመት ጠብቀን የምንጀምር፣ ዓመት ሲመጣ የምንበረታ በአጠቃላይ ለምንም ነገር አዲስ ዓመት የምንል ብዙዎች ነን።
ይገርመኛል የአዲስነት ስሜት የሚያድርብን አዲስ ዓመት ሲመጣና ሲቃረብ ነው። የመስራት የመለወጥ ፍላጎታችን የሚነሳሳው መስከረም ሊጠባ ጥቂት ሲቀረው ነው። ከአሮጌነት የምንወጣው፣ ከድሮነት የምንሸሸው ጳጉሜን ተሻግረን አበባየ ሆይ ሲባል የሚመስለን እልፍ ነን። ሕይወታችን፣ መኖራችን ትርጉም የሚያገኝ የሚመስለን በዚህ ጊዜ ነው። ለአዲስ ሕይወት የምንዘጋጀው ይሄን አዲስ ዘመን ታከን ነው። ሁሉ ነገራችንን ለአዲስ ዓመት አሳልፈን የሰጠን ነን። ዛሬን አናውቀውም። የአሁንን ኃይል አልተረዳነውም። የቆምንባት ቅጽበት የኃይል የለውጥ መጀመሪያ እንደሆነች ገና አልደረስንበትም።
ጥያቄ አንድ..አዲስ ዓመት ማለት ምን ማለት ነው? በአስተሳሰቡ ላልተቀየረ ማህበረሰብ አዲስ ዓመት ምኑ ነው? ከመጠበቅና ተስፋ ከማድረግ ላልወጣ ሰውነት አዲስ ዓመት ዋጋው ስንት ነው? ፍቅርን ለማያውቅ ይቅርታን ላልተማረ ልብ ጊዜ ዘመን ምኑ ነው? ለማይሰሩ እጆች፣ ለማያስቡ ጭንቅላቶች መጠበቅ ፋይዳው ምንድነው? አምናን እኮ በእልልታና በፌሽታ ተቀብለነው ነበር። ብዙ ልንሰራበት ብዙ ልናተርፍበት አውርተን ነበር። 2013 እኮ ብዙ ያቀድንበት ብዙ ያሰብንበት ዘመን ነበር ዛሬ ላይ አሮጌ ሆኖ ሲያልፍ ግን መጥፎና ዕድለ ቢስ እንደነበር አወራን። ምንም ያላተረፍኩበት ዓመት ነው ስንል ነቀፍነው።
ሰኔና ሐምሌ ገመገም ላይ ቆመው 2013 ለኔ ጥሩ ጊዜ አልነበረም የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ተስፋ ያደረጋችሁት አዲሱ ዓመት ያሰባችሁትን እንደሚሰጣችሁ ዋስትናችሁ ምንድነው? ጊዜ በሰው ልጅ ነው የሚፈጠረው። የምትፈልጉትን ጊዜ አሁን ላይ መፍጠር ትችላላችሁ። ከጊዜ ባርነት ውጡ..ከቻላችሁ ጊዜ የእናተ ባሪያ እንዲሆን ተቆጣጠሩት። ካልቻላችሁ አትጠብቁት..ወዳለበት ሂዱ።
ከትጋት ስትጎድሉ ለምንም ነገር ጊዜን መጠበቅ ትጀምራላችሁ። በትጋት ስትሞሉ ለምንም ነገር ጊዜ እናንተን መጠበቅ ይጀምራል።
ጊዜን መጠበቅና በጊዜ መጠበቅ ሁለት የተለያዩ እውነቶች ናቸው። ልክ ለምንም ነገር አዲስ ዓመትን እንደሚጠብቁት እና ለምንም ነገር ዛሬ የተሻለ ቀን ነው ብለው እንደሚያምኑት ሁለት ጉራማይሌ ነፍሶች ዓይነት። ትጉ ነፍሶች የሚፈልጉትን ዘመን ዛሬ ላይ ይፈጥሩታል። ታካች ነፍሶች ደግሞ በመንቀፍ፣ በመጠበቅ ውስጥ ይቆማሉ።
ብዙ ዛሬዎችን፣ ብዙ አሁኖችን፣ ብዙ ነገዎችን ዘላችሁ አዲስ ዓመትን አትጠብቁ። ለተጋ ልብ ለበረታ አእምሮ ሁሌም ስኬት ሁሌም አዲስ ዓመት አለ። አዲስ ዓመት ለእናንተ ብሎ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። መጥቶ እንዲሄድ የተፈጥሮ ግዳጁን እየተወጣ ነው። እኛ ነን ከተፈጥሮ የራቅነው። እኛ ነን ማስተዋል የጎደለን..በጊዜ ሀቅ ውስጥ ቆመን እንኳን መማር አልቻልንም። ለመማር ዝግጁ ብንሆን ጊዜ የሚያስተምረን ብዙ ነበረው።
የሚሰማ ጆሮ የሚያስተውል ልብ ቢኖረን ኖሮ የጊዜን ሹክሹክታ እናደምጠው ነበር። ጊዜ ህላዊ ኖሮት መናገር ቢችል ኖሮ ..እባካችሁ አትጠብቁኝ እኔ ለሰው ልጅ የሚሆን ምንም የለኝም..ለበረቱ እየመጣሁ የምሄድ ነኝ የሚላችሁ ይመስለኛል። ‹ከኔ ይልቅ ዛሬና ነገ የላቀ ዋጋ አላቸው። አስራ ሁለት ወራትን አልፋችሁ፣ ሀምሳ ሁለት ሳምንታትን ትታችሁ፣ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን ሽራችሁ አትጠብቁኝ በአሁናችሁ ላይ በርትታችሁና ተልቃችሁ ጠብቁኝ ይላችሁ ነበር። ምኞታችሁ መልካም ጊዜ ከሆነ እጆቻችሁን በሥራ ልቦቻችሁን በትጋት ጥመዱ። ካልሰራንበት ካልበረታንበት አዲሱ ዓመትም እንደ አምናና ካቻምና ርባና ቢስ ሆኖ ነው የሚያልፈው።
አዲስ ዓመት የዛሬ አብራክ ነው። ብዙ ዛሬዎች ተቆጥረው ነው የምንቦርቅበትን አዲስ ዓመት የሰጡን። ለምንድነው ዛሬአችንን አዲስ ዓመት አድርገን የማንቀበለው? ለምንድነው አዲስ ዓመት ሲመጣ የምናገኘውን ኃይልና ብርታት በቆምንባት ዛሬ ላይ የማንፈጥረው? አትሸወዱ..አዲስ ዓመት የቀናት ጥርቅም ነው። አትሳቱ አዲስ ዓመት የሳምንታት የወራት ሂደት ነው። ለመለወጥ ካልተጋችሁ የሚሰጣችሁ አንዳች ነገር የለም። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ የአዲስ ዓመት መምጣት ብቻውን ዋጋ ይሰጠናል ብዬ አላስብም። ጊዜ በተለይም አዲስ ዘመን በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ዋጋ የሚኖረው የአሁንን ወይም ደግሞ የዛሬን ዋጋ ስናውቅ ብቻ ነው። አምና አዲስ ያልነው ዘንድሮ አሮጌ ብለን ሸኝተንዋል። ምንም አላተረፍንበትም። ስለዚህ ከዘመን ቁራኛነት ወጥተን ዛሬን አዲስ ዓመት እናድርግ። በተለወጠ ልብ በተለወጠ ሀሳብ እናፍራበት እያልኩ ላብቃ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014