ባንዳ እናት አገሩን ክዶ ባእድን ወዶ ተላምዶ አገር የሚወጋ ዜጋ ነው፡፡ ባንዳ ለጥቅሙ የባእድ ክንድ ሆኖ መረጃ የሚሰጥ ጠላት ነው፡፡ ከወገን እየተጠጋ ወገኑን የሚወጋ የባእድ መሣሪያ ነው፡፡ ባንዳ ዕኩይ ስሙ ጎልቶ የወጣው በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ጦርነት ወቅት ነው ፡፡ ይላቅ ኃይለማርያም ሐበሻ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባንዳ በወረራ ወቅት ለጠላት ወግኖ ያገለገለ በሚል ይፈታውና ሥወ ቃሉ ጣሊያን መሆኑን
ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ጣሊያንን ደግፎ ኢትዮጵያን ነቅፎ ለተሰለፈ ባንዳና ከሀዲን ጉያ ይዞ ሰላምና ልማት አዳጋች መሆኑን በስነቃል እንዲህ ተገልጾ ነበር፡፡
ጠላትማ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው፣
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው።
ባለቅኔው ዮፍታሔ ንጉሤ ከጣሊያን ጦርነት በኋላ ለንጉሡ አፈ ቀላጤ ሆነው የተገኙ አንዳንድ ባንዳዎች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በግጥማቸውም
‹‹ ለጌሾ ወቀጣ
ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ለመጠጡ
ከየጎሬው ወጡ ››
ብለው ተቀኝተውባቸዋል፡፡ እሳቸው ጌሾ ወቀጣ ያሉት መጋደል የሚጠይቀውን የጦርነቱን ዘመን ነበር፡፡ በወቅቱ ሸሽተው በባንዳነት ለጣሊያን ያደሩ ጣሊያኖች ሲባረሩ ለአገሩ እንደተጋደለ ሆነው ከፊት ተገኙ፡፡ ለመጠጡ ለመጠጡ ከየጎሬው ወጡ ያሉትን ይህንኑ መሆኑን አንዳንድ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
ባለንበት በዚህ ወቅት ያልተደገፉ ወሬዎች የሚያሠራጩ ሰዎች አሉ፡፡ ከሰዎች ጋር ሲገናኙ እና ሥራዬ ብለው በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሬ ወለደ ዘገባዎች በማሠራጨት የስነ ልቦና ጥቃት ለማድረግ ሲፍጨረጨሩ ይታያል፡፡ እነዚህ የባንዳን ግብር በድረግብር (Network) የባጥ የቆጡን በማሠራጨት ሽንፈታቸውን በአሉባልታ ወሬ ለማካካስ ይፈልጋሉ፡፡
ከላይ እንደገለጽነው የባንዳ ግብሩ ጎልቶ የወጣው እና የታየው በጣሊያን የአምስቱ ዓመታት ወረራ
ነው፡፡ እነ አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉት ባንዳ ላለመሆን ነበር፡፡ ዘርዓይ ደረስ በሮም ተወስዶ በሀገራቸው ጀብዱ የፈጸመው ለሀገሩ ክብር ሲል ነው፡፡ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ በጣልያን ጦርነት በሲሲሊ ቢታሰርም ብርድ ልብስ ቆራርጦ ቀጣጥሎ አምልጧል፤ ማምለጤ በቃኝ ሳይል ታስረው የነበሩ ሌሎች እስረኞችን ለማስፈታት በድብቅ የእስር ቤት ጠባቂዎችን ገሎ ነፃ አውጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ በሠሩት መልካም ሥራ መወደስ መመስገን ሲገባቸው ሚዲያው ሁሉ የሚያወራው ጎጠኝነት የሚያቀነቅኑትን እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
አንዳንዶች ባንዳ የታየው በዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ነው ቢሉም ማስረጃዎች ግን የሉም፡፡ እንግሊዞች ዜጎቻቸውን ለማስፈታት ጦራቸውን ይዘው መቅደላ ተዋጉ፤ ንጉሡም እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸው ሰዉ፡፡ በወቅቱ ልዕለ ኃያል የነበረችው እንግሊዝ ንጉሡ ከሞቱ አገሪቱን መያዝ ትችል ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም እርስ በርሱ ቢሻኮት በአገሩ ጉዳይ እንደማይደራደር ስላወቁ መሣሪያቸውን ለራስ ካሳ ምርጫ ትተው አገሩን ለቀቁ ፡፡
ስለ ባንዳ ስናነሳ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ደጃች.ኃይለሥላሴ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ በላይ ግደይ ኢትዮጵያ ሀገሬና ትዝታዬ 1990 ዓ.ም በሚል በጻፉት መጽሀፋቸው ‹‹…መቀመጫቸው መቀሌ ሆኖ በአዲግራት በኩል ይዋጋሉ ተብለው የነበሩት የእንደርታና ክልተ አውላዕሎ ገዥ የነበሩት የደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከኢጣሊያ ተስማምተው በዛላምበሳ በኩል ለመጣውና ጠቅላ ሰፈሩ አዲግራት ለነበረው የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ለጄኔራል አማሊዮ ዶቦኖ እዳጋ ሐሙስ ሄደው መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም እጃቸውን ሰጡ ፡፡
ከእናት አገራቸው ከድተው ወደ ወራሪው ጣሊያን መግባታቸው እንኳን የትግራይ ሕዝብ ይቅርና ፤አሽከሮቻቸው ስላልደገፉት 200 ያህሉን ብቻ አስከትለው ነበር ወደ ጠላት ሠፈር በሹክሹክታ
የገቡት፡፡… ይሁን እንጂ “አገራችን ለወራሪ ጠላት አሳልፈው ከመስጠት ይልቅ አስቀድመው ከዐፄ ኃይለሥላሴ ጋር በመዋጋት ዘውዱን ለመመለስ መሞከር ነበረባቸው” ሲል የትግራይ ሕዝብ ተችቷቸዋል፡፡” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
መጽሐፉ በጎንደር የኢጣሊያ ቆንሲል የነበረው በሲኞር ፖሌራ በተሠራው የተንኮል ፕሮፓጋንዳ ምክንያት እነ ራስ ጉግሳ ወሌና ራስ ኃይሉ ተክለ ኃይማኖት ከኢጣሊያኑ ጋር ውስጥ ውስጡን እየተስማሙ ንጉሡ በእንደራሴነት ይመሩት በነበረው መንግሥት ላይ ያምጹ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ሲል ያስረዳል፡፡ በርዕሳችን ባንዳ የታሪክና የሀገር ባለእዳ እንዳልነው የጠቀስናቸው ሰዎች እና አሁን የባንዳነት ግብር የሚፈጽሙ አሸባሪዎች ስማቸውና ዕኩይ ታሪካቸው በጥቁር መዝገብ ተጽፎ ይኖራል፡፡
የውጪ ወራሪ ለማስገበር ሲመጣ ለነገሥታቱ አልገብርም ያለ የአካባቢ ገዥ ሁሉ ቅድሚያ መቀመጫዬን ብሎ ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ ቅሬታውን ረስቶ ሀገሩን ከውጪ ወራሪ ሲከላከል ኖሯል፡፡ ባልሠለጠነው ዘመን አገሩን ማስቀደም እንዳለበት ቀድሞ የተገነዘበ ሥልጡን ዜጋ ነበር፡፡ አሁን ግን በሰለጠነው ዘመን እየኖሩ ባልሰለጠነ እሳቤ የሚዳክሩ የህዝብን ሰላም ለማደፍረስና አገር ለማፍረስ የሚጥሩ ባንዳዎች እያየን ነው፡፡ በዘመናችን በመንግሥት አሸባሪነት የተፈረጁ ሸኔን ወያኔን የመሰሉ ባንዳዎች የአገር ሰላም እያደፈረሱ ነው፡፡
በኦሮሚያ ወለጋ አካባቢና በቤንሻንጉል መተከል የምንሰማው ግጭት ውስጥ ጸጥታ አስከባሪ ሆነው የዜጎች ሰላም መጠበቅ እያለባቸው ከቦታው ለቀው ሌላ ቦታ እንዲሄዱ እየተነገረ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል ቆስለዋል፡፡ የመንግሥት ሰላም አስከባሪ ዋነኛ ሥራው ዜጎችን መጠበቅ ነው፡፡ ለጠላት መረጃ እየሰጡ ሰላማዊ ዜጎች እንዲጠቁ የሚያደርጉ ይጠየቁ፡፡ በርግጥ ለፍርድ የቀረቡ እና የተፈረደባቸው እንዳሉ ሰምተናል ግን አሁንም፤ ከውስጥ ሆነው እንደ ባንዳ የሚያገለግሉትን ለመመንጠር ጥረት ይደረግ ፡፡
ልጆችሽ ልጆችሽ ሳይሆኑ ቢቀሩ
አገር ለማጽናናት ሰዎች አፈሩ ደርሷል
የዋይታሽ ቃል ራማ ከበሩ
ጊዜ አለው ሊመለስ የደስታሽ ክብሩ
በ19 29 ባለቅኔ ዮፍታሔ ንጉሤ ከገጠሙት የተወሰደ ነው፡፡ በእርግጥም በአዲሱ ዓመት በግፍ የተገደሉት እመው አበው አእሩግ ህፃናት እምባቸው በአዲሱ ዓመት ይታበሳል፡፡ ሰላም ለአገራችን፡፡
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም