ትህነግ በለስ እየበላ ታግሎ በለስ ቀናውና በትረ ሥልጣን ጨበጠ፤ ዙፋኑን ተቆናጠጠ፤ ያኔ። ይሄንን በለስ ልግመጠውና ልሞክረው እንዴ ? ያሰኘኛል አንዳንዴ ። ምን ዋጋው አለው! ሁሉም ነገር በለስ እንደ መግመጥ ቀላልና አልጋ በአልጋ አልሆነም። በአሜሪካ እርዳታና አጋዥነት ሥልጣን የተቆናጠጠው አሸባሪው ትህነግ የደርግ ጦርን የደመሰስኩ እኔ ነኝ ሲለን ኖረ። እኛም ሰምተን ተቀበልን።
ሥልጣን ሲቆናጠጥ ‹ለሠፊው ሕዝብ ስለታገለ› ወያኔ የሚለውን ከውስጥ አረገና ኢህአዴግ የሚል ድርጅት ጨመረበት። ነገሩ ሰምና ወርቅ ሆነ። ወርቁ ማነው፤ ድረሱበት። የቱን ፓርቲ ነው እንደ ፈጣን ሎተሪ ሲፋቅ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የተባለው። ትህነግንም እንደዚያው በሉት። ኢህዴግ ሲፋቅ ትህነግ ነዋ። እናም በህወሓት ሥር ኢህዴንን /በኋላ ብአዴን የሆነውን/፣ ኦህዴድን እንዲሁም ደኢህዴድ እህት የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲቀፈቀፉ ተደረገ። በኢህዴግ ጥላ ሥር ያሉ የሶማሌ የአፋር የጋምቤላ እና የቤንሻንጉል ክልል ፓርቲዎችም ተመሥርተው አጋር ፓርቲ በሚል ታቀፉ። በእሱ መንገድ ተሰሩ።
አንዳንድ ሰዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚመሠርት ሲነግረን የነበረው ኢህአዴግ ከደርግ ጋር “በአምባገነንነቱና በፍርደ ገምድልነቱ አቻ ነበር” ይላሉ። እዚህ ላይ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተናገሩ የተባለውን ማስታወስ ይጠቅማል። ደርግ አብዮታዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል እያለ ያለ ፍርድ እየገደለ የሟቾችን ስም በሬዲዮ ይገልጽ ነበር። አብዮታዊው ደርግ ገድሎ በአደባባይ ሲያወራ ዴሞክራሲያዊ ኢህአዴግ ደግሞ የሚቀናቀኑትን ወይም ይቀናቀኑኛል ያላቸውን እየገደለ ከሟች ወዳጅና ዘመድ ጋር በመሆን የጠፋውን ለመፈለግ ‹‹ይጣጣር›› ነበር ሲሉ ዴሞክራሲያዊነቱን ተሳልቀውበታል።
ያ ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊ ነኝ ይል የነበረ መንግሥት መምራት ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ የሚል ነበር። እንደ ዘውዳዊ ሥርዓት በዘር ሐረግ ላይ የተንጠለጠለ ነበር። ታዲያ እኔ ብቻ መምራት አለብኝ የሚል ከሆነ፤ ከዘውዳዊው አገዛዝ በምን ተለየ? ዴሞክራሲያዊ የሚል መለያ ስለለጠፈ ይሆን? ምላሹን ለእናንተ ልተወው።
ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ነበር እንዴ? በአርባጉጉ ተገደሉ የተባሉትን አስታውሱ፤ መንበረ ስልጣኑ ሊገረሰስ አካባቢ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ የኢሬቻ በዓል እያከበሩ ባለበት ወቅት የተገደሉት ኦሮሞዎች፤ በአምቦ ከተማና የተለያዩ አካባቢዎች ደማቸውን የገበሩት ወጣቶች፣ በሀዋሳ ሎቄ አካባቢ የክልል ጥያቄ ባነሱ ሲዳማዎች በባህር ዳር ጎንደር የተፈጸመው ጭፍጨፋ ጸረ ዴሞክራሲያዊነቱን አጋልጠውበታል። ትህነጎች የዚህን ሁሉ ሰው ደም “ደመ ከልብ” (የውሻ ደም) አድርገው፤ለፍትህ የቀረቡ ሰዎች ግን አልሰማሁም፤ ገዳዮቹ ይደልዎ!(ይገባሃል) እየተባሉ ሲወደሱ የነበሩ ናቸው።
ለሃያ ሰባት ዓመታት በስመ ኢህአዴግ አገር ሲመሩ ፤ ዴሞክራሲያዊ ስለነበሩ ነው እንዴ ሰውን በዘር በሃይማኖት ሲከፋፍሉት የኖሩት? አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኘሁዋቸው አንድ ምሁር በአንድ ወቅት “አገር ሊመሩ ሳይሆን ሊመዘብሩ” የመጡ አካላት ናቸው ብለውኛል ። እውነታቸውን ነው። መዘበሩት እንጂ፡
“እነሱን የሚቃወም ወይም የሚቃወም የመሰላቸውን ሁሉ ‹ትምክህተኛ ጠባብና ነፍጠኛ› የሚል ታፔላ እየለጠፉበት ያሸማቅቁታል” ብለውኝ ነበር እኚሁ ምሁር። እነሱን የሚቃወም በጣም የሚታገል ቡድን እና ተሰሚነት ያገኘ ግለሰብ ካገኙ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲጥር አገኘነው ብለው እስር ቤት ይወረውሩታል። ግን እነሱ ከፌዴራል መንግሥት ውጪ ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ ለራሳቸው ምርጫ ያካሄዱ፣ለፌዴራል ስርአቱ አንታዘዝም ያሉ ናቸው።
‹‹የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ›› የሚለው የሚቃወማቸውን አካል የሚዘልፉበት አንድ አባባል ነበራቸው። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለው ሥልጣን ላይ እያሉ የሚያስቡት ብርና መሬት ብቻ ነበር። ደርግ የመሬት ከበርቴውን ሥርዓት ሲገረስስ የእነርሱ ደግሞ በሊዝ ታፔላ የመሬት ከበርቴውን ሥርዓት መልሰው ኢንቬስተር እንስባለን ብለው፤ገበሬውን ከእርሻ እና መኖሪያ ቦታው ያለ በቂ ካሳ አፈናቀሉት ፤ ‹ልማታዊ መንግሥት› ስለሆነ ግን እንቀበለው ብዬ ነው የማስበው።
ይህ ሁሉ ለምን ተነቃብን ብለው አኩርፈው መቀሌ ተቀመጡ። አሁንም የሚያረጉትን አሳጣቸው። ተመከሩ ተዘከሩ። መጥፊያቸውን ሰሜን እዝ ላይ አደረጉ። በሀግ ማስከበር ክፉኛ ተመቱ እዚያው ዋሻቸው ሸሽተው ገቡ። በዘመኔም ሆነ በታሪክ ይህን ሁሉ ዘመን አገር ሲመራ የነበረ አካል አልጋውን ለቆ በዋሻና በጥሻ ተደብቆ ለትግል የተሰማራ አላየሁም፤ ብዙዎቹ አገር ጥለው ይወጣሉ፤ አልያም ተይዘው ህጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፤ በቃ ፤ እኔ የማውቀው ይህን ነው።
ሁሌ የሚናገሩትን መልካም አስተዳደር ዴሞክራሲያዊ ስርአት ይሉት የነበረውን ቢተገብሩት ኖሮ አልጋቸውን ለቀው እንደገና ከሀ ለመጀመር ወደ በረሃ አይሄዱም ነበር። ሥራቸው ወደ ዋሻ አሸሻቸው። ምናልባት እትብቴ በተቀበረበት ልቀበር ብለው አስበው ይሆናል። ዋሾዎቹ ወደ ዋሻዎች ተሸሸጉ።
“አፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ” አይታውቅም የሚባል ነገር አለ። የተሸሸጉት ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ብለው ምቾታቸውን ብቻ ሲያስቡ የነበሩት ዋሾዎቹ፣ በአገር ጉዳይ ቀልድ በማያውቀው በትግራይ ሕዝብ ስም ወጣቱን ኮረዳይቱን ለጦርነት እየማገዱ ሥልጣኑን ሲቆናጠጡ፤ ቀለዱበት እንጂ ምንም ያተረፉለት ነገር አልነበረም። ወደ ሁለት ሚሊየን የሚሆን የትግራይ ህዝብ የሴፍቴኔት እየተሰፈረለት እነሱ ግን ሃያ ሰባት አመት ሙሉ የሀገር ሀብት ወደ ውጪ ሲያሸሹ ነበር።
በቅርቡ የቡድኑ አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ በቢቢሲ ሀርድ ቶክ የባጥ የቆጡን ሲዘባርቅ ነበር። ንግግሩ ራሱ የአሸባሪው ትህነግ የመሞቻው ቀን እንደደረሰ በሚገባ ይናገራል። ቡድኑ ለ17 ዓመታት በትግል ትግራይን መሠረት አድርጎ ሲታገል እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱን ደግሞ በስመ ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት ሲመራ በአጠቃላይ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የትግራይን ሕዝብ ቀለደበት። ግለሰቦች ከበሩበት የሚሰሩትን አጡበት እንጂ የትግራይ ህዝብ ያገኘው የለም።
አሁንም ከሀገራዊው ለውጥ ወዲህ በትግራይ መሽጎ ይህን ህዝብ ሌላ ትውልድ እንዲገብር እያረገው ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ በቃኝ ሊለው ይገባል። ጭቁኑ የትግራይ ሕዝብ ተነገደበት አንጂ አንዳች ያተረፈው ነገር የለም። ትግራይን በደርግ በሻዕቢያ ብሎም በዘመናችን የጦር አውድማ ከመሆን አላዳናትም ተሳለቀባት ።
አንዳንዶች ወያኔ ሲባል ትግራይ ብለው የሚያስቡ ካሉ የተሳሳቱ ናቸው። ሚዲያውም በዚህ ላይ አበክሮ ሊሠራ ይገባል። አሁንም በትግራይ ጥሻ ውስጥ ተሸሽጎ ያለው አመራር ነኝ የሚለው የአሸባሪ ቡድን የትግራይ ታዳጊዎችን ሀሽሽ እያስወሰደ ለጦርነት እየማገደ ነው። ይሄ መቼም ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ የተደረገ አይደለም።
ኢትዮጵያን ሲመሩ ከቆዩት አመራሮች አንዱ የሆነው ጌታቸው ረዳ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦልም መውረድ ካለብን እንወርዳለን›› የሚል ጸያፍ ንግግር አሰምቷል። አሁንም በድጋሚ ከአፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ አያስታውቅም የሚለውን አባባል ለመድገም እንገደዳለን። ከዚህ መዘላበድ ውስጥ የተገባው ያንኑ ሀሽሽ ወስዶ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አይከፋም። ከምቾት ዓለም ወጥተው አሁን ጌታቸውና አጋሮቹ በሀዘንና በሰቆቃ በዋሻ ተሸሽገው ነው ያሉት። ንግግሩ ግን ፈገግ አሰኝቶኛል። ሲኦል የመሰለ ቦታ ወርዶ “ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲኦልም እንገባለን” ማለቱ። ያለበትን ዋሻ ገነት አድርጎ ስሎት እንደሚሆን እገምታለሁ።
እንደ ዋሹ መዝለቅ የለም። ውሸት ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ መልሶታል። እንደገናም ከመቀሌ የተፈጠረበት ዋሻ መልሶ ከቶታል። አሁን ደግሞ የጣር ውሽት ላይ ነው። ግብአተ መሬቱ ሲፈጸም ሁሉም ነገር ያበቃለታል። ውሸት እስከ መቃብሩ ትህነግ።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013