ኃይለማ ርያም ወንድሙ
በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960 አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለንባብ ካበቃቸው ዘገባዎች መካከል ጥቂቶቹን ይዘን ቀርበናል፡፡
መኪና ሲጠብቅ ውሃ
ወሰደው
አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ)፡- በወንዝ ውስጥ የቆመ ላንድሮቨር መኪና ይጠብቅ የነበረ ሰው በውሃ ሙላት ተወሰደ፡፡
አደጋው የደረሰው በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ፤ ስልጤ ወረዳ ግዛት ውስጥ መጋቢት ፴ ቀን ፲፱፻፷ ዓ.ም ነው፡፡
መጋቢት ፳፱ ቀን አቶ ዘውዴ ወልደ ሰንበት የተባሉት ሰው ላንድሮቨር መኪና እየነዱ ላዶ የተባለውን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ፤ጭቃው መኪናውን ስለያዘባቸው፤ ረዳታቸውን ገብረዮሐንስ የተባለውን ሰው እንዲጠብቅ አድርገው ሄዱ፡፡
በዚሁ ዕለት ሌሊት በጣለው ዝናም ምክንያት ወንዙ ሞልቶ መኪናውን ይጠብቅ የነበረው ሰውና በመኪናው ውስጥ የነበሩት ጥቃቅን ዕቃዎች ተወሰዱ፡፡
የአካባቢው ሕዝብ ባደረገው ፍለጋ፤ ሚያዝያ ፯ ቀን፷
ዓ.ም ገርቢ በር በተባለው ቦታ፤ ላይ የዚሁ ሰው አስከሬኑ ተገኝቷል፡፡ ሲሉ የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ክንፈ ንጉሤ ባስተላለፉት ዜና ማረጋገጣቸውን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል ትናንት ገለጠ፡፡
(ሚያዝያ 23 ቀን 1960 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ሁለት የዳለቻ ሰዎች
በመብረቅ ሞቱ
አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ)፡- ሚያዝያ ፫ ቀን ፷ ዓ.ም ከቀኑ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ፩ ሰዓት ተኩል ድረስ በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ በዳለቻ ምክትል ወረዳ ግዛት በጣለው በረዶ የተቀላቀለበት ዝናም ፤ ሁለት ሰዎች በመብረቅ ተመትተው ወዲያውኑ ሲሞቱ አንድ ሰው ቆስሏል፡፡
እንዲሁም በዚሁ ጊዜ አሥራ ሁለት ፍየሎች ከሜዳ እንደተሰበሰቡ መሞታቸውን የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ ሌተና ኰሎኔል ክንፈ ንጉሤ ገልጠዋል ሲል የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል አመለከተ፡፡
(ሚያዝያ ፮ ቀን ፷ ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
መብረቅ ቤት አቃጠለ
አሰበተፈሪ፤ (ኢ.ዜ.አ)፡- ሚያዝያ ፳፮ ቀን ባለፈው ቅዳሜ በአሰበተፈሪ በጣለው ዝናም ምክንያት የጣለው
መብረቅ የወይዘሮ ሶፍያ ዳውድን የሣር ክዳን ቤት አቃጠለ፡፡
በዚሁ በአሰበተፈሪ ከተማ የሚገኙ የደጃዝማች ወልደገብርኤል አባ ሰይጣን ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት ፹፯ኛ የዳግማዊ ምኒሊክ እስካውት ተማሪዎች በሥፍራ ደርሰው ቃጠሎው ወደ ሌሎች ቤቶች እንዳይዛመት ተከላክለዋል። በሰውና በሌላ ንብረት ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩ ታውቋል፡፡
(ሚያዝያ 29ቀን 1960 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
በአንድ ትከሻ ሁለት ጭንቅላት
ጐሬ (ኢ.ዜ.አ)፡- በጐሬ አውራጃ በዱረኒ ወረዳ በወረቦ ም/ግዛት ልዩ ስሙ ዱዱ ሮብ ገበያ ከተባለው ቀበሌ የአቶ አጥናፍ ጀምበሬ ላም ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፷ ዓ.ም ሁለት አንገት ሁለት ጭንቅላት ከሻኛዋ ላይ ጐን ለጐን ሆኖ ለያንዳንዱ ጭንቅላት ሁለት ሁለት ዓይንና ሁለት ሁለት ጆሮ አራት አራት እግር ያላት ግንባረ ቦቃ ጥጃ ወልዳለች፡፡ የተወለደችውም ጥጃ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መሞቷን አቶ መኰንን ወልደ መድኅን የዱረኒ ወረዳ ገዢ ገለጡ፡፡
(ሚያዝያ 29 ቀን 1960 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ያልተመረመሩ ከብቶች ያረዱ በስድስት ወራት እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ (ኢዜአ)፡- አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ የተባሉ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በመጋዘናቸው ውስጥ ሽታው የአካባቢውን ህዝብ ጤና የሚያውክ ርጥብና ደረቅ ቆዳ ከማጠራቀም አልፈው ጤንነቱ ያልተመረመረ ከብት በዚሁ ግቢ ውስጥ ከህግ ውጪ እየደጋገሙ በማረዳቸው በስድስት ወር እስራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሆኑን ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተገኘው ዜና ገለጠ፡፡
አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ በአካባቢው ኗሪና በጠቅላላው ህዝብ ጤንነት ላይ ጠንቅ የሚያስከትሉትን ድርጊቶች የፈጸሙት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ፭ ጊዜ መሆኑንና በዚህም ከ፳ ብር እስከ ፩፻፶ ብር ተቀጥተው እንደነበረ ዜናው ገልጧል፡፡
አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ ፍርድ ቤት ቀርበው የሰጡት የመከራከሪያ ማስረጃ ‹‹በገዛ ርስቴ ላይ የፈለግሁትን ብሰራ አልከለከልም›› የሚል ብቻ እንደነበረና ፍርድ ቤቱም በገዛ ርስት ላይ ተቀምጦ ህዝብን የሚጎዳ ስራ መስራት በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልጦ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር ፰ -፯፻፳፬ በተከሳሹ ላይ የ6 ወር እስራት መፍረዱን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የማስታወቂያ ክፍል ገልጧል፡፡
አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ የእስራት ጊዜያቸውን እንደጨረሱ የቆዳ መጋዘናቸውን የህዝበ መኖሪያ ከሆነው አካባቢ አንስተው ለኢንዱስትሪ በተመደበው ቀበሌ ካላዛወሩ በቀር ባሉበት ቦታ ላይ እንዳይገለገሉበት ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ጥብቅ ትእዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013