አብርሃም ተወልደ
ዓለማችን የመልካም ሥነ ምግባር ሥርዓት የሚጣሱ ውሸት እና ውሸታሞች ጎልቶው የሚታዩባት እየሆነች ትገኛለች፡፡ ውሸት በዓለማችን ውስጥ ምን ያህል እንደ ሰለጠነ/ እንደ ሰየጠነ ቢባል ይሻላል/ ለማየት አንዳንድ መረጃዎችን መመልክት ይጠቅማል፡፡
ለምሳሌ ከግብር ከፋዮች መካከል ትክክለኛውን ገቢ አሳውቆ የገቢ ግብር ለመክፈል የሚዘጋጀው ምን ያህሉ ነው፤ በጣም ውስኑ ነው፤ ግለሰቦች ለብድር ጥያቄ ሲሉ የሚቀርቡት የሀብት መጠንና እውነተኛው የሀብት መጠን የሰማይና ምድር አይነት ልዩነት ሲኖረው ይስተዋላል፤ ብዙ ለመበደር ባለብዙ ሀብት/ማስያዣ ባለቤት/ ሆኖ ለመቅረብ የማይደረግ ሙከራ የለም፤ በዚህ አይነት ሁኔታ ባንኮች ብዙ አጥተዋል፤ …ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ እውነታዎች እንደ ግሰብም ሆነ ማህበረሰብ ምን ያህል ከእውነታ መራቅ እንዳለ ያመለክቱናል፡፡
ብዙዎቻችን የወጣንበትን ቤተሰብ ያደግንብትን አካባቢ እንመስላለን፡፡ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም፣ ሁልጊዜ እውነት ብቻ ማለት እንዳለባቸው፣ ከዋሹ ግን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚከተላቸው ያስጠነቅቋቸዋል ፡፡
በእርግጥም በዚህ ሕግ መሰረት ያደጉ ልጆች እውነት እንጂ ውሸት መናገር ይከብዳቸዋል፡፡ ትልቅ ትንሽ ሳይሉ ሰው ሲዋሽ እውነቱን በመናገር ለውርደት አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
ውሸት መናገር በማያስቀጣ እና በማያስቆጣ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ግን ልማድ ሆኖባቸው ያለአንዳች ምክንያት ወይም ምንም ዓይነት የሚያስጨንቅ ነገር ሳይደርስባቸው የሚዋሹበት ጊዜ አለ፡፡
መጥፎ ተክልም ዘር አለውና ውሸትም ዘር አለው። ከውሸት ዘሮች መካከል ደግሞ ያልሆኑትን አሊያም ራስን ከፍ አድርጎ መግለጽ አንዱ ነው፡፡ መዋሸትን አንዳንድ ሰዎች እንደ መዝናኛ እና እንደ ጊዜ ማሳለፊያም አድርገው የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፤ እንዲህ ያለ ክስተት በጉዞ ወቅት ስላጋጠመኝ እንጂ! እንደተለመደው ወደ ሥራ ለመሄድ በጠዋት ተነስቼያለሁ፤ በጠዋት አልኩኝ እንጂ በሌሊት ነው የተነሳሁት፤ ከተዘጋጃጀሁ በኋላ /ያው ጎህ ሲቀድ ስለሆነ ከቤት የምወጣው/ አስራ ሁለት ሰዓት ከሃያ ወጣሁ፡፡ ሲርቪስ ከምጠብቅበት አካባቢም ደርስኩ፤ ከሰርቪስ ጓዶቼ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ወደ ሰርቪሱ ገባን፡፡ ይሄኔ ነው የትዝብቴ መነሻ የሆነ ድርጊት ያገኘሁት፡፡
ሁለት እድሜያቸው ወደ አርባዎቹ የሚጠጉ የሰርቪስ ጓደኛሞች ናቸው፤ አንደኛዋ እኔ በምኖርበት የጋራ መኖሪያ ሰፈር የምትኖር ስትሆን፣ ወደ ሥራ የምንሄደው በአንድ ሰርቪስ ነው፤ ያለማቋረጥ ማውራት ልማዷ ነው፤ እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በሚያደርጉት ጨዋታ መሀል ከጎረቤቴ አያሌ ቅጥፈቶች አንዱ ጀሮዬ ገባ፡፡
በመጀመሪያ እሷ አይደለችም ብዬ ራሴን ላሞኘው ሞከርኩ፤ የሴትየዋን ህይወት እንደ ጎረቤት አውቀዋለሁ፤ የምታወራው በሙሉ የምትመኘውን እንጂ የኖረችውን አይደለም፤ የምትኖርበትን ኮንደሚኒየም ቤት ጨምሮ ሌላ ሁለት ኮንደምንየም ቤቶች ገዝታ እያከራየች መሆኗን ለጎደኛዋ ገለፀችላት፤ ልጆቿን “አሜሪካ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት” እንደምታስተምር ተተረተረች፤ የልጆቿ የትምህርት ቤት ክፍያም በሦስት ወር (በተርም) ለጆሮ የሚከብዱ ሺህ ብሮች መሆናቸውን አብራራች፡፡
ጨዋታቸው ለእኔ እየተወራ እስኪመስል ድረስ ኮለል ብሎ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም የማለዳው ደመናማ አየር ሰውን ጨብጥ አድርጎት ስለነበር ሰርቪሱ ውስጥ ፀጥታ ነግሷል፤ የሁለቱ እንስቶች ወግ እኔንም ጨምሮ ለተወሰንን ተሳፋሪዎች የተከፈተልን መዝናኛ ይመስል በሚገባ ይሰማ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዓይን በፊት ገጽታ ገለፃ እንግባባ ነበር፡፡
ይህች (ቀጣፊዋን ማለቴ ነው) ሰው ከጓደኛዋ ምን ማግኘት እንደፈለገች ባለውቅም አንድ የማውቀውን ግለሰብ ቤት እኔው በምንኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤት ሰፈር ተከራይታ እንደምትኖር አውቃለሁ፡፡ ልጆቿም ቢሆኑ በአካባቢው በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት እንጂ እሷ ባለችው ትምህርት ቤት ስለአለመማራቸው እኔ ህያው ምስክር ነኝ፡፡
ሴትዮዋ በዚህ አላበቃችም፤ የውሸት መአቷን ታወርደዋለች፤ አንዳንዱን ለእናንተ ለተከበራችሁ አንባቢዎቼ ሰለማይመጥን እዚህ አልጠቅሰውም፤ ባለቤቷ ከውጭ ያመጣላት የወርቅ ፤ የእጅ ሰዓት፣ የቦርሳ የአልባሳት ብዛት ለቁጥር ይታክታል፤ በትግራይ በተካሄደው ሰላም ማስከበር ከተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት በየቀኑ ስምንት መቶ ሺውን ደመሰስነው እንዳለው ግለሰብ ነው የሆነችው፡፡
ባለቤቷም እዚያው ኮንደሚኒየም አብሯት ያለ ነው፡፡ በደላላነት ይሰራል፤ ሴትየዋ እንዳለችው ውጭ የሚመላለስና ለሷ ወርቅ የሚያግዝም አይደለም፡፡ የማይደርስ የለም ከሰርቪሱ የምትወርድበት ቦታ እና ጊዜ ደርሶ ወረደች፤ ተቀባይነትን ለማግኘት ሲባል ይህን ያህል ይዋሻል እንዴ!
ይህን ቅኝቴን በደንብ አድርጎ ሊገልጽልኝ የሚችል አንድ ሃሳብ እንካችሁ፤ አንድ ጊዜ አንዲት ስለራሷ ትልቅነት ብዙ ማውራት የምትወድ ወጣት በሏ እና እርሷ ስላሳለፉት ጥሩ ጊዜ ለጓደኛዋ ትነግራታለች፡፡ ባለቤቷ ፓይለት እንደሆነ በመግለጽ ‹‹አንድ ቀን በአውሮፕላን ሊያንሸራሽረኝ ፈልጎ ጠዋት ከቦሌ ተነስተን እየበረርን ሰበታ አረፍን” ትላታለች፡፡
የምታዳምጣት ጓደኛዋ “እንዴ !…አንቺ ሰበታ
አውሮፕላን ማረፊያ አለ እንዴ?“ አለቻት፤ ልጅቷም፤ “ሰበታ አልኩኝ ወልቂጤ ማለቴ ነው” ትላታለች፡፡ አሁንም ጓደኛዋ “አንቺ! አሁንስ አበዛሽው !…ወልቂጤ ደግሞ የአውሮፕላን ማረፊያ የታለ” በማለት ትገልፃለች። የፓይለት ባለቤት ነኝ ባይዋ አሁንም መዋሸቷን ትቀጥላለች፡፡ “ሆለታ ማለቴ ነው” አለቻት፡፡
በዚህ አይነት ብዙ ከተሞችን ስትጠራ ቆየች፡፡ በመጨረሻም ጓደኛዋ “… ዛሬ አታርፊያትም እውነቱን ሳትናገሪ …” አለቻት ይባላል፡፡ ይህ ታሪክ እንደ ተረት የሚነገር ይሁን እንጂ፣ ከተነገረው በላይ ነገርን አተልቀው በማውራት ትልቅነታቸው እዚያ ውስጥ ያለ ይመስል የሚያወሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡
አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ሁነቶች እየተከሰቱ ያሉት ጉዳዮችም እንዲሁ ናቸው፤ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ይለግማል በዳገት” ይባላል፡፡ የሌለንን የማይገባንን አውርተን ከማህበረሰቡ እንዳንገለል መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡
ማህበረሰቡ ከእኛ ብዙ ይጠብቃል፤ የሚጠበቅብንን ለማድረግ እንድንችል፤ የምንችለውን ብቻ ማድረግ አለብን፡፡ ያልሆነውን ማውራት ነገም አብሮ በሚኖር ማህበራሰብ ውስጥ በኋላ ደብቁኝ ደብቁኝን ያስከትላል፡፡
“እውነት” ብዙ ጠቃሚ ጓደኞች አሉት… መተማመን፣ እምነት፣ ሐቀኝነት ዋስትና፣ ጽናት …የመሳሉት፡፡ በተቃራኒው “ውሸት” ደግሞ የራሱ ተባባሪዎች አሉት፤ አለመተማመን፣ ጥርጣሬ፣ ግጭት ቁጣና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
”እውነት” እውነት ባልሆነ ነገር ሲተካ የውሸት ተባባሪዎች ብቅ ይላሉ፡፡ በውሸት ምክንያት በሰዎች መካከል መተማመን ሲጠፋ የሰው ግንኙነት የተበላሸ ወይም የፈረሰ ይሆናል፡፡ ውሸት ባለበት የቤተሰብ አንድነት ይፈርሳል፤ የመንግሥት አስተዳደር መሰረትም ይናጋል፡፡ ስለዚህም የሆነውን እንሁን፤ እሱንም እናውራ!!
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013