ማህሌት አብዱል
«የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ» በተሰኘው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው በስፋት ይታወቃሉ ።የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ።ተወልደው ያደጉት በድሬዳዋ ከተማ ነው። በሙያቸው ጸሐፊ-ተውኔትና የሥነ ጽሁፍ ምሁር ናቸው። እኚሁ የኪነጥበብና የታሪክ ሰው «ጓደኛሞቹ»፣ «ፍቅር በአሜሪካ» እና ሌሎችንም ቴአትሮችን ለመድረክ አብቅተዋል። በርካታ ግጥሞችንና መጽሐፍትንም ለአንባቢያን አድርሰዋል ።በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይታወቃሉ።
በአሁኑ ወቅት ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ታዋቂው የሥነ ጽሑፍ ምሁር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም «Heaven to Eden» እና «The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians» የሚሉ መጽሐፍትን በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትመዋል።
ሁለቱም መጽሐፎቻቸው (አማዞን) በተባለ የመጽሐፍ መሸጫ ድረ ገፅ ላይ ከተፈላጊ መጻሕፍት ተርታ ተሰልፎላቸዋል። «ላሟ» የተሰኘ ባለ ሁለት ገቢር ቴአትር ጽፈውም አጠናቀዋል። ከሰሞኑ ደግሞ «ኢትዮጵያ ግብፅን እንደፈጠረቻትና እንዳሰለጠነቻት» በሚል አዲስ መጽሐፍ ፅፈው አጠናቀዋል፡፡በእዚሁ መጽሐፍና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በድጋሚ የዘመን አንግዳችን አድርገናቸዋል ።ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ አዲስ መጽሐፍ እንዳሳተሙ ይታወቃልና እስኪ ስለ አዲሱ መጽሐፍዎ አጠቃላይ ይዘት ይንገሩንና ውይይታችንን በዚህ እንጀምር፤
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- የአዲሱ መጽሐፌ ርዕስ «ኢትዮጵያ ግብፅን እንደፈጠረቻትና እንዳሰለጠነቻት» ነው የሚለው፡፡አጠቃላይ ይዘቱ ግብፅ ዛሬ የምትኩራራበትና ሃብት የምታጋብስበት የቱሪዝም መስህብ ሁሉ የተሰራው በኢትዮጵያውያን መሆኑንና እንደአገር የፈጠረቻትና ያሰለጠነቻት ኢትዮጵያ መሆኗን የሚዳስስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ማስረጃዎት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ልክ ነሽ! እንደዚህ በድፍረት ለመናገር ማስረጃ ያስፈልጋል ።እኔ በቂ ማስረጃ ስላለኝ ነው ይህንን ለመናገር የደፈርኩት ።ለምሳሌ የዛሬ 250 ዓመት አካባቢ ግሪካዊው የታሪክ አባት ሄሮደተስ ከግሪክ ተነስቶ ወደ ግብፅ፣ ሱዳንና ሊቢያ አራት ጊዜ ተመላልሶ ፒራሚድ ውስጥ ያሉትን ካህናትና ፈርኦኖችን ፒራሚዱንም ሆነ እዛ ውስጥ የተሰሩት የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ከየት እንደመጡ ሲጠይቃቸው ከኢትዮጵያ ያመጡት መሆኑንና አጠቃላይ የሥልጣኔያቸው ምንጭ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው የነገሩት ።
ግብፅ ረግረግ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አሳሾችና አጥኚዎችን ካስጠኑ በኋላ ግብፅ ላይ መሰረት ጥለው ኪነ-ሕንፃውን መጀመራቸውን የዚሁ ባለታሪክ ምስክርነት ያስረዳል ።ከመጀመሪያው የፈርዖን ንጉስና ካህን ኦሳይረስ ጀምሮ እስከ 25 ዓመታት ድረስ የዘለቀ የኢትዮጵያውያን የዘር ሐረግ ግብፅ ውስጥ መኖሩን ነው ሄሮዶተስ የሚገልፀው ።
በተጨማሪም 330 ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች እንደነበሩና በተለይም 18ቱ የኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች እንደነበሩ በርካታ ማስረጃዎች መኖራቸውን ይመሰክራል ።ሄሮዶተስ እነዚህ ኢትዮጵያውያን የግብፅን ስልጣኔ ማምጣትና ፒራሚዱን መስራት ብቻ ሳይሆን ሃሮግላፊክስ የተባለ ስዕላዊ ፊደል በኢትዮጵያኖች የተሰራ ነው ይላል ።
ከሱ በኋላ የመጣውም ዲዌድሮስ የተባለው ሌላው ግሪካዊ ባለታሪክም ግብፅ ውስጥ ያለው ጥንታዊ ኪነ-ህንፃ በሙሉ የኢትዮጵያውያኖች ስራ ነው ብሎ ነው የሚናገረው ።ቅርፃ ቅርፁም፣ ሃውልቱም፣ ፒራሚዱም ሁሉም የእኛ እንደሆነ ነው የሚመሰክረው ።ከዚያ በኋላ የተነሱ ሌሎችም ተመራማሪዎችና የታሪክ ሰዎች እንደዚሁ የግብፅ ሥልጣኔ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሆኑን ነው ያረጋገጡት ።
ጆርጅ ጀምስ የተባለ ጸሐፊም ‹‹የተሰረቀ ሌጋሲ›› ወይም ቱሩፋት ብሎ ነው ሥለግብፅ ጥንታዊ ስልጣኔ የኢትዮጵያ መሆኑን የፃፈው ። ሌሎችም ግብፅ ማለት ኢትዮጵያ መሆንዋን ጽፈዋል ።ከዚህ በተጨማሪም የራሳችን ታሪክም ከ19 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ግብፅ ላይ መንገሳቸውን እንረዳለን ።
ለምሳሌ ህንደኬን መጥቀስ እንችላን ።በግብፅ ፣ በሊቢያ እንዲሁም ዛሬ ሱዳን ድሮ ኑቢያ በሚባለው አገር የነገሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መኖራቸውን የተገኙ የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ ።ዛሬ ግን በተቃራኒው ልጆቻችን ተዋርደውና ደህይተው የአረብ አገልጋይ መሆናቸው የሚያሳዝን ነው፡፡
ሙዝሊቪያ የምትባለው ኢትዮጵያዊት ንግስትና አራቱ ልጆችዋ ከቁንጅናቸው ብዛት የታመመ ሰው አጠገባቸው ቢሆን ይድናል ተብሎ እንደአማልክት የሚሰገድላቸው እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል ።ከወንድም አፄ ዘዋሪ ብለን አክሱም ላይ ያነገስነው የህንደኬ ልጅ ግብፅን ሲያስተዳድር እንደነበር ተጠቅሷል።
ብዙዎቻችን ግብጽ እየተጠቀመች ያለችው በውሃችንና በአፈራችን ብቻ ነው የሚመስለን፤ ነገር ግን አሁን ድረስ የገቢ ምንጯ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገላት ያለው እኛ ኢትዮጵያውያንን በሰሩት የቱሪስት መስህብም ጭምር ነው ።
በዚህ ብቻ እንዳይመስልሽ አባቶች አስከሬንን ለማድረቅ ይጠቀሙበት የበረውን ‹‹መሚ›› የተሰኘውን ጥበብ ጭምር ባለቤት መስለው አውሮፓና አሜሪካ ቤተመዘክሮች በዚያ ጥበብ በደረቀው የአባቶቻችን አስከሬን ሳይቀር ገቢ እያገኙበት ነው ። ይህንን እውነት አሁን ያለነው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን እነሱም ማወቅ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በመጽሐፌም ላይ ይህንን ነገር ሁሉ ዘርዝሬ ነው የፃፍኩት ።
በሌላ በኩል ግብጽ አሁን ላይ በጦርነት አትችሉኝም እያለች ትፎክራለች ።ድሆች ናችሁም ትለናለች ።እውነታው ግን ይህ አይደለም ።በመጀመሪያ ደረጃ ደሃ አይደለንም ።በጣም ብዙ የተፈጥሮ ሃብት ነው ያለን ።ነገር ግን እርስ በእርስ ባለመስማማታችን በፈጣሪ የተሰጠንን ተፈጥሮን እንደማልማትና እንደመግራት እርስ በእርሳችን በመናቆር እና በመገዳደል በችግር እየኖርን እንገኛለን።
ዛሬ ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኖ ሥራ የሚሰራ ጠፍቶ ነው እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ ለአለም ትተርፋለች። ግብፆች መሳሪያ አለን ብለው ተሳለቁብን ።ነገር ግን ግብፅ በታሪኳ አንድም ቀን ኢትዮጵያን አሸንፋ አታውቅም ።
እስከዛሬ በገጠሟቸው ጦርነቶች ሁሉ በሽንፈት ወይም በሽሽት ነው የሚወጡት፡፡ለዚህ የቅርቡን እንኳን ብናነሳ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ጊዜ የነበረው የግብጽ ንጉስ አሸንፋለሁ ብሎ ፎክሮ መጥቶ ተዋርዶ ነው የሄደው ።በአፄ ቴዎድሮስ ዘመንም ቱርኮችና ግብፆች አንድ ላይ ሱዳንን ለመውረር መጥተው አፄ ቴዎድሮስ ከሱዳን ነፃ አውጪዎች የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር አብረው ቅኝ ገዢዎችን ከመሀዲዎች ጋር በመሆን ካርቱም ድረስ ሄደው ገርፈው ነው ያባረሯቸው።ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚያንፀባርቅ ግብፅን የሚያኮመሽሽና አንገታቸውን የሚያስደፋ መጽሐፍ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ግብፆች ከአረብ እንደፈለሱ ነው የሚናሩት?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ልክ አይደለም ።ግብፅ ከመስፋፋቱ ሶስት ሺ አመት በፊት እኛ የግብፅን ሥልጣኔ ቀድመን ጨርሰናል፡፡ይህም ፒራሚዶቹንና እዛ ውስጥ ያሉትን ቅርፆች እንዲሁም የኪነት ስራዎች በሙሉ የተሰራው በኢትዮጵያውያን ነው። ከደቡብ አረቢያ ፈልሰው አረቦች ወደ ግብፅ በሚመጡበት ሰዓት ከእስልምና በስተቀር ምንም ይዘው አልመጡም። ምክንያቱም በሲራራ ነጋዴነትና በከብት አርቢነት የተሰማሩ ሰዎች ናቸው እንጂ እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣኔ አልነበራቸውም ።
እነዚህ ሰዎች በእስልምና አሳበው ግብፅ ከገቡ በኋላ እኛ በገነባነው ስልጣኔ ውስጥ ነው መኖር የጀመሩት ።አስቀድሜ እንዳልኩሽ የእኛ አባቶች አስከሬን እንዳይፈርስ በሚያደርገውና ‹‹መሚ›› በተባለው ጥበብ የአረብ ነው እያሉና ቱሪስት እየሳቡ ገንዘብ ያተርፋሉ ።እኛም ይህንን ውለታ በዋልንላቸው ነው ዛሬ እዚህ መድረስ የቻሉት ። ይህንን እውነት እነሱም ሆነ እኛ አናውቅም።
ግብፅ በውሃችንና በአፈራችን ብቻ ሳይሆን እየተጠቀመችባቸው ያለችው በሰራነው ፒራሚድና ቅርሶቻችን በመሆኑ የዚህ ጥቅም ተጋሪ መሆን አለብን ብለን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መጠየቅ እንችላለን ።ይህንን እውነት ግብፆች እንዲያውቁትና እንዲደነግጡ ማድረግ ያስፈልጋል ።
‹‹ማን ላይ ተቀምጠሸ ማንን ታሚያለሽ›› እንደሚባለው ሁሉ ዛሬ ግብፅ ያደገችበት ዋነኛ የሃብት ምንጭ እኛ በመሆናችን እያደረገች ያለችውን ትንኮሳ ካላቆመች በውሃና በአፈራችን ብቻ ሳይሆን በቅርሶቻችንና በጥበቦቻችን ልንጠይቃት እንደምንችል ማስገንዘብ ይገባናል ። እርግጥ ነው ምንም እንኳን ይህንን የመሰለ አኩሪ ታሪክ ባለቤቶች ብንሆንም መቀበል የማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን አሉ ።
በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ትውልዱ የተቀረፀው ታሪክ የለህም ተብሎ በመሆኑ ታሪክ የለኝም የሚለው አስተሳሰብ አንገቱን አስደፍቶት ነው የኖረው ።በዚህ ምክንያት ትውልዱ ይህንን እውነት መቀበል አይፈልግም።ለዚህም ነው ማስረጃዬን በመጽሐፌ ላይ በተቻለኝ አቅም ሁሉ ለማካተት የሞከርኩት ።
አዲስ ዘመን፡- የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ግዛትም ሆነ ታሪክ ከቅኝ ግዛት ዘመን ወዲህ ያለው እንደሆነ የሚያወሱ አካላት አሉ፡፡በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ግብፅ ውስጥ ባሏት ቅርሶች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መክሰሷ ያዋጣታል ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡-
ተቀባይነት አገኘም፤ አላገኘም መጠየቅ መቻል አለብን ።እኛ ከእነሱ እናገኛለን ብለን ብቻ ሳይሆን ያንን ሁሉ የገነባነው እኛ መሆናችን እንዲታወቅልን ማድረግ መቻላችን በራሱ ትልቅ አንድምታ አለው፡፡የግብፅ አጠቃላይ ህይወት እኛ መሆናችንን በተጨባጭ እንዲያውቁት ያደርጋል ።የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉትም ወንዛችንም ሆነ ፒራሚዶቹ ከኢትዮጵያ ለግብፅ የተሰጠ ስጦታ እንጂ የገዛ ሃብታቸው አለመሆኑን ማስገንዘብ ይገባናል።
ይህንን ውለታ ውለን ሳለ ጭራሽ በገዛ ውሃችን አንዲት ጠብታ እንዳንጠቀም እያደረገችው ያለችውን ጥረት የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል ።እኛ እንደ ግብፅ በየአደባባዩ እንጩህ ካልን በታሪካዊ ማስረጃ ተደግፈን መብታችንን መጠየቅ እንደምንችል ማሳወቅ አለብን።
የኢትዮጵያውያን ጥበብ ግብፅ ላይ ፈሷል ።አረቦች በተዘጋጀ ባዶ ቤት ሰተት ብለው ነው የገቡት ።ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ትኩረት ለመሳብ በክስ ደረጃ መቅረብ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብፆች ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላታቸው አድርገው የሚቆጥሯት በአባይ ውሃ ብቻ ነው ወይስ ሌላም ስጋት ስላላቸው ነው?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እንዳልሽው ግብፆች በእርግጥ ውሃ እናጣለን የሚል ስጋት ስላላቸው ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ በጠላትነት የፈረጇት ።ምክንያቱም ውሃው ከእነሱ ተርፎ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር እንደሚፈስ ያውቃሉ፡፡እንዳውም እነሱ የውሃ እጥረት የለባቸውም ።ከዚህ የሚሄድላቸውን ውሃ ባክኖ እንዳይቀር ትንንሽ ግድቦች ገድበው ማስቀረት የሚችሉበት እድል አላቸው ።
እንኳን ዛሬ ይቅርና ናፖሊዮን ቦናፓርት ግብፅን በወረረበት ጊዜ የአባይን በከንቱ መባከን አይቶ ‹‹እኔ ብሆን ኖሮ ይህችን አገር ለረጅም ዘመን የምገዛት አንድም ውሃ ወደሜዲትራንያን ባህር አይገባም›› ብሎ ነው የተናገረው ።ስለዚህ በቂ ውሃ አላቸው ።እንዳውም አልፈው ተርፈው ለእስራኤል ይሸጣሉ ።
ኢትዮጵያ ውሃ ልታሳጣኝ ነው እያለች በየአደባባዩ የምትከሰን ውሸቷን መሆኑን ይህ ሁኔታ ያረጋግጥልሻል፡፡ከዚያ ይልቅ የሚያሰጋቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ካደገች በቀጠናው ኃያል ትሆናለች የሚል አስተሳሰብ ነው ያላት ።በአፍሪካ አገራት ላይ ተፅዕኖ ትፈጥራለች የሚል ስጋት ነው ግብፅ ያላት ።
በዚህ ምክንያት ግብፅ የፖለቲካ ተቀባይነቷን ታጣለች የሚል ፍርሃት አላቸው ።በመሆኑም ግብፆች ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡበት ከዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ ምንም እንኳን ገማል አብዱልናስር ፓንአፍሪካኒዝም ቢልም ሌሎቹ መሪዎች ኢትዮጵያን እንደጠላት ነው የሚያዩዋት።
ግብፆች ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ሲሉ አረብ አገር ናት እያሉ ቀጠናውን ሲያምሱ ነው የኖሩት። አንድ ወቅት ላይ እንዳውም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሊያቃጥሉ ሲሉ በግብፅ የኢትዮጵያ አታሼ የነበረው የአርበኛው የራስ መስፍን ልጅ ጃራ መስፍን ግብፃውያን የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዳያቃጥሉ አራቱን በጥይት መታቸው ።በየጋዜጣው ‹‹ዲፕሎማቱ ተኩሶ ግብጾችን መታቸው›› ተብሎ ተወራ ።
ከዚያ እንዳይገሉት ብሎ ወደአገሩ መጣ ።ይሁንና ወደ አገሩ ሲመጣ የጠበቀው ምስጋና ሳይሆን ወቀሳ ነበር።ንጉሱ ድሬዳዋ ቤተመንግሥት ድረስ ጠርተውት ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲጠይቁት ‹‹ያስተማራችሁኝ ለሰንደቄና ለአገሬ እንድዋደቅ ነው›› የሚል ምላሽ ነው የሰጣቸው ።እሱ ይህንን ቢልም በወቅቱ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሰዎች በሁኔታው ባለመደሰታቸው ከሥልጣኑ አነሱትና ሌላ ቦታ መደቡት፡፡
ግብፆች በተለይም ላለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲተነኩሱና ለኢትዮጵያ ጠላት ሁሉ ገንዘብ ጭምር እየከፈሉ አገራችን እንድትተራመስ ሲያደርጉ ነው የኖሩት ።
በተለይም የአገራችንን ገፅታ የሚያጠለሹ ሚዲያዎችን በማደራጀት ሰፊ ስራ ሲሰሩ ነበር ።ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ሲሉ ነፃ አውጪ ነን ላሉት ሁሉ ገንዘብ ሲከፍሉ ነው የኖሩት።አሁንም በመተከል አካባቢ ሰዎች እንዲገደሉና እልቂት እንዲፈፀም ያደረጉት እነሱ ስለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለኝም ።
ሱዳንም እንድትወረንና ጦርነት እንድትቀሰቅስ የገፏት እነሱ ናቸው ።በእርግጥ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሠላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ነው የሚፈልጉት ።በተለይም ዶክተር አብይ ስላስታረቃቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት መግጠም የሚፈልጉ አይመስለኝም ።ይልቁንም የሱዳንን መከላከያ የሚመራው ጀኔራል ግን ከግብፅ ገንዘብ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ለመውጋት የተነሳ ይመስለኛል ። ኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ስላለባት አቅሟ ተዳክሟል በሚል የተደረገ ወረራ መሆኑ እሙን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሱዳኖች የወረሩት መሬት በተጨባጭ የኢትዮጵያ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ አለ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡– በተጨባጭ አለ ።አሁን የወረሯት ትንሽ መሬት ይቅርና መላው ሱዳን የኢትዮጵያ እንደነበር ነው ታሪክም ሆነ የተፃፉ ሰነዶች የሚያሳዩት። ካርቱምን ጨምሮ መርዌ የሚባለው ስፍራ የእኛ ነበር። በነገራችን ላይ መርዌ የሚለው ቃል መርሃዊ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ነው ።
መርሃዊ ማለት ድምፁ የሚያምር ማለት ነው ።በመሆኑም መርዌ አሁን ሱዳን ቀድሞ ደግሞ ኑቢያ የምንለው ቦታ መናገሻ ስፍራ ነበር ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ አካል ነበር ።በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን እነ አፄ ቴዎድሮስ ሱዳን ውስጥ ገብተው የሱዳን ነፃ አውጪ የነበሩትን ደርቡሾችን በማገዝ ግብፆችን ከቱርክ ወረራ ታድገዋቸዋል ።
በዚያ ጦርነት ነው አፄ ቴዎድሮስ ‹‹መይሳው ካሳ ከቱርክ ይዋጋል እንኳን ከአንበሳ›› ብለው የፎከሩት ።አፄ ፋሲልም በተመሳሳይ ያንን አካባቢ ግብር እያስገበሩ ይገዙ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል ።
እንደነገርኩሽ በቅኝ ግዛት ዘመን እንግሊዞች በፈጠሩት ሴራ እስካሁንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካለል ስለቆየ ነው እንጂ መሬቱ በተጨባጭ የእኛ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያትትና ግብፅ ኢትዮጵያን በገጠመቻቸው ጦርነቶች ሁሉ መሸነፏን የሚገልፅ ምዕራፍ በዚሁ መጽሐፌ ላይ ተካቷል ።በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ግብጾች ጦርነት ቢገጥሙ ሊያሸንፉን እንደማይችሉ ስለሚያውቁ ነው ሱዳኖችንም ሆነ ሌሎቹን እያነሳሱብን ያሉት ።
እነሱ መሳሪያ ስላላቸው በመሳሪያ የሚያሸንፉን መስሏቸዋል ።ግን መሳሪያ ብቻውን አይዋጋም ።የአገር ፍቅር ወኔና ጥበብም ያስፈልጋል። የእኛ ጉብዝና እንደተጠበቀ ሆኖ እግዚአብሔርም ለራሱ ዓላማ ኢትዮጵያን የመረጣትና የሚወዳት አገር በመሆንዋ ግብፆች መጥተው ሲያጠቁን ዝም ብሎ አያይም ።ደግሞም እነሱ ዘመናዊ መሳሪያ አለን ቢሉም እድሜ ለዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያም የዘመናዊ የጦር ትጥቅ ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ግብፅ የምትመካባቸው መሳሪያዎች እኛም ጋር አይጠፉም ።ምርጥ ምርጥ ተዋጊ አብራሪዎችም አሉን ።በጅቡቲም በኩል ያለፈው መንግስት ምንም እንኳን ወደብ አልባ ቢያደርገንም ከጅቡቲ ጋር ተዋውለን ከፈረንሳይም ጋር ተስማምተን የጦር መርከበኞችን አሰልጥነን ጠንካራ ኃይል ለመፍጠር እየተሞከረ ነው ።
ስለዚህ ባህሩ ባይኖረንም መርከቦችና ሰዎቹ አሉን ።ከዚህ አንፃር ተስፋ አለን ብዬ ነው የማምነው።የመከላከያ ሰራዊታችን በአዲስ መልክ መደራጀቱ ለዚህ ጠቃሚ ነው ። ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው የአንድ ብሔር ተፅዕኖ ወይም አመራር ነበር ።አሁን ግን የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ኢትዮጵያዊ መልክ እያየዘ ነው የሚገኘው።
ስለዚህ ይህ ሁሉ ዝግጅት ለግብፅ የሚመቻት አይደለም፡፡እነሱ የሚመኩበት መሳሪያ ቢኖርም እኛ የአቅማችንን ያህል እንሳተፋለን።ደግሞም ያን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጠው ይመጣሉ የሚል እምነት የለኝም ።ምክንያቱም እዚህ ሳይደርሱ በረሃ ላይ ነው የሚያልቁት ።ከዚህ በፊትም ሞክረው አልተሳካቸውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንደአንድ አገሩን እንደሚወድ ኢትዮጵያዊ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በግብፅ መደለያ ተታለው በገዛ አገራቸው ላይ ጉዳት እያደረሱ ላሉ አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት አለዎት?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡– እንደሚታወቀው በየዘመኑ አገራቸውን የሚክዱ ባንዳዎች አይጠፉም።እነዚህም በግብፅ ተታለው ለአገራቸው ውድቀት የሚሰሩ አካላት ባንዳና ከሃዲዎች ናቸው ።በግብፅ ተከፍሏቸው አገራቸውን የካዱ ሰዎች አሁንም በአገር ውስጥ አሉ ።አሁን ያለው መንግስት ታጋሽና ቸልተኛ ሆኖ ነው እንጂ በሞት ሊቀጡ የሚገባቸው ሰዎች ናቸው ።በእውነቱ እነዚህን ሰዎች መምከር አትችይም፡ ።
ምክንያቱም ለገንዘብ ብለው አገር የሚከዱ፣ ኢትዮጵያን የማይወዱ፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌላቸው ባንዳዎች ናቸው ።ምንአልባት ልትመክሪያቸው የምትችያቸው በየዋህነት ተታለውና ባለማወቅ የገቡበትን ሰዎች ነው ።
ለምሳሌ ግን ዲጂታል ወያኔ እንደሚባሉት ሁሉ ገንዘብ እየተከፈላቸው ስራቸው ይሄ የሆነ አሉ ።እነሱ ያልሆኑትን ስም ይዘው አንዱን ብሔር ከሌላኛው ለማጥፋት ይሰራሉ።አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ሲያጣሉና ሲያባሉ ነው የኖሩት ።አሁን ከጁንታው መውደቅ በኋላ በእርግጥ በጀታቸው ስለቀነሰባቸው እንቅስቃሴያቸውም በዛው ልክ ቀንሷል ።
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቱን ሕዝባዊ አንድነት ለመመለስ ታሪክ ምን አይነት ፋይዳ አለው ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- በተደጋጋሚ እንደሚባለው ወያኔዎች ለ27 ዓመታት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ አገር ሲያተራምሱ ሕዝብና ሕዝብን ሲያባሉ ነው የኖሩት ።በተሳሳተው መንገዳቸው ሄደው ብዙ ጥፋት አድርሰዋል ።ሙስና፣ አድሏዊ አሰራር፣ ዘረኛ አስተሳሰብ ዘርግተው ሕዝብን በግፍ ነው ሲመሩ ነው የኖሩት ።
የራሳቸውን ወገን ብቻ እየደገፉ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ደግሞ እያገለሉ የኖሩበት ዘመን ከየትኛውም ጊዜ በላቀ በጭካኔውና ክፋቱ የላቀ ነው ።በዚያ ዘመን የተፈጠረውም ሙሉ ትውልድ ጥላቻን አርግዞ እንዲኖር በማድረግ የባከነ ዜጋ ፈጥረዋል ብዬ ነው የማምነው ።በተለይም የሙስናው አሰራር ስር ሰዶ አገሪቱን ለከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ ዝቅጠት አድርሶታል ።
ዛሬም ድረስ ትተውት ያለፉት የብልሹ አሰራር ዱካው አገርን ወደኋላ በማስቀረት ላይ ነው የሚገኘው ።በህወሓት ዘመን ትውልዱ ግብረገብ እንዳይኖረውና ኢትዮጵያዊነቱን እንዲጠላ የተሰራው ሴራ ታሪክ የማይዘነጋው ነው። ለዘመናት የቆየውን አኩሪ ታሪካችንን የመሳፍንት መስፋፋት ታሪክ ነው እያሉ ወጣቱን እያሳቱ ነው የኖሩት ።የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ዘመን ብቻ እንዳለው ነው የሚደሰኩሩት።
እነሱ ይህንን ቢሉም በተጨባጭ የተፃፈ ማስረጃ እንደሚያሳየው አገራችን ከ600ሺ ዘመን በላይ የላቀ ታሪክ ባለቤት ናት ።የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እስከ ፍልስጤም የነበረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኩሽ መንግስት እንዲሁም ከዚያ ሰለሞናዊ ተብሎ የቀጠለበት ገናና ታሪክ ያለን ኩሩ ሕዝቦች ነን።ከንጉስ ሰብታህ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ድረስ በደንብ ተመዝግቦ የተቀመጠ ታሪክ አለን ።
ታዲያ ያንን ታሪክ ወዴት ገደል ሊከቱት ነው? ከየትስ አምጥተው ነው የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ነው ያለን የሚሉት? ።ስለዚህ የማይሆን የውሸት ታሪክ ነበር ሲያስፋፉ የኖሩት ። አሁን ግን ይህንን ሁሉ ለመቋቋም የታሪክን ውዥንብርም ሆነ የማንነት ቀውስ ለማዳን መንግሥት የሚጠበቅበት ስራ አለ ።
በተለይም ትክክለኛውን ታሪክ ፅፎ ለትውልዱ ማስተማር፣ የሚያኮራ ታሪክ እንዳለው በማሳወቅ አገሩን እንዲጠብቅ ማነሳሳት ይገባል፡፡አንቺ አንዳልሽው ይህንን የቀደመ ገናና ታሪካችንን ለትውልዱ ማስተማራችን በወያኔ ሴራ የተበረዘውን አንድነታችንን ለማጠናከር ያግዘናል የሚል እምነት አለኝ ።
በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልንገርሽ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያገናኘን ነገር ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች መሆናችን ነው ።እንደሚታወቀው አባታችን ኢትዮጵያ መላውን አፍሪካ ልጆቹን ልኮ ተስፋፍቶ ገዝቶ ነበር ።ድፍን አህጉሪቷም ትጠራ የነበረችው ኢትዮጵያ ተብላ ነበር ።
ይህንን እውነት የሚያሳዩ ካርታዎች አሉ ።የዛሬ 150 ዓመት የነበሩ ባህርተኞች አገር ሲያስሱ ይዘዋቸው የነበሩት ካርታ ኢትዮጵያ የሚል ነበር፡፡ከዚያ በኋላ ደግሞ አፋሮች መርከብ ሰርተው በዓለም ዙሪያ የሚነግዱ ስለሆኑ ነው አፍሪካ የሚለውን ስያሜ ከአፋር ያገኘችው ።ይሄ ሁሉ በታሪክ መመዝገብ መቻል አለበት ።
ከዚህም ባሻገር ህንድ ውቅያኖስም ሆነ አትላንቲክ ውቅያኖስ የኢትዮጵያ ባህር ነበር የሚባለው ።ስለዚህ እኛ ትልቅ ነበርን፤ እንሆናለንም ።ጣሊያኖች አገራቸውን አንድ ያደረጉት ተረት ፈጥረው ነው ።እኛ ግን አንድ የሚያደርገን እውነተኛ ታሪክ አለን ።አንድ ሕዝብ ነን ።
ይህችን አገር ለማቆየት ሁላችን ብዙ ትግል አድርገናል ።ሁላችንም የኢትዮጵያ ዘር በመሆናችን አንድ ነን ።ምንአልባት በቋንቋ ብንለያይም በደም አንድ ነን ።ደግሞ በቋንቋ ብንለያይም የስጋ ዝምድናችንን አያግድም ።ለምሳሌ ጥቁር አሜሪካኖች ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ቢሆንም በዘር ግን አፍሪካዊ ናቸው ።
እንግሊዘኛ ስለተናገሩ እኛ እንግሊዞች ነን ማለት አይችሉም ።በመሆኑም የምትናገሪው ቋንቋ ዘርሽን አይለውጠውም ።በመሆኑም ታሪካችንን ለይተን ማወቃችን ለአንድነታችን ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ ።ለዚህ መንግሥትን እዚህ ላይ የምመክረው አንድ የሚያደርገንና እውነተኛ የሆነውን ታሪካችንን እናስተምር፣ እናስፋፋ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጁንታው መውደቅ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ተስፋ ይዞ ይመጣል ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ ወያኔዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ በስህተት ጎዳና ነው ሲመሩ የነበሩት፡፡እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ታሪክ እምብርት የሆነችውን ትግራይን ለመገንጠል ከሚል መነሻ የማያዋጣ አካሄድ ነበር ሲከተሉ የኖሩት ። ትግራይ ኢትዮጵያ ታሪክ ማህተም ናት ።የኢትዮጵያ ነገስታት ከመጀመሪያውም ጀምሮ አክሱም የነገስታቱ መናገሻ ከተማ ነበረች ።ክርስትና ከመስፋፋቱ ጀምሮ ነገስታትም ሆነ ካህናት የሚሾሙት ከአክሱም እንደነበር ይታወቃል ።
ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሊቢያ ለግብፅና ሌሎችም አገራት ንጉሶች ይሾሙ የነበሩት ከአክሱም ነው ።ይህንን ድፍን የትግራይን ታሪክ ትተሽና እንዳልነበረ ቆጥረሽ አዲስ ታሪክ ልትፈጥሪ አትችይም ።
እነሱ ኢትዮጵያ ያላት የ100 ዓመት ታሪክ ነው ሲሉ የአክሱምንም ታሪክ እየፋቁ ነው ማለት ።ይህንን የሚሉት ፈፅሞ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ስለሌላቸው ነው ።ቢኖራቸው ኖሮ ይህንን ታሪክ ይዘው ነው የሚጓዙት ።
ስለዚህ በዚያ በተሳሳተው መንገዳቸው ትግራይን እንገነጥላለን ብለው ሄዱ።በደርግ ዘመን ብዙ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው ይታወቃል ።በተለይም ይህ አጥፊ አስተሳሰባቸው የትግራይ ሕዝብ ስላልተቀበለው ነው የከሸፈባቸው። ይህ አልሳካ ሲላቸው ኢህአዴግ ብለው በመሰረቱት ድርጅት አገር የመከፋፈል ስራ ነበር ሲሰሩ የነበሩት።
ሲመጡም መሪ የሌለው አገር ስላገኙ ነው ዛሬ ድረስ መቆየት የቻሉት ።ሲጀምሩ የነበራቸው ዓላማ ከመላው ኢትዮጵያ ሃብት ዘርፈው ወደ ራሳቸው አካባቢ ለማከማቸትና ሲጠናከሩ ለመገንጠል ነበር።እስከዛሬ ድረስ ለኢትዮጵያ የእኔነት ስሜት ኖሯቸው አያውቅም ።ነገር ግን የሚቃወማቸው ጠንካራ ፓርቲ ስላልነበረ የሚጠሉትን አገር ሲመሩ ነው የኖሩት ።
በዚህ በተሳሳተ መንገዳቸው አገር ሲያተራምሱና ሕዝብ ሲጨቁኑ ኖረው የለውጥ ኃይል ከመጣ ወዲህ የሰረቁትን ይዘው በሰላም እንዲኖሩ ቢጠየቁም አልሰማም ብለው መቀሌ ላይ መሽገው ነው ሁለት ዓመት የቆዩት ።
በዚህ ጊዜም በሰላም የሚኖረውን የትግራይ ሕዝብ እየበደሉና እያስፈራሩት ነው የኖሩት።እነዚህ ኃይሎች ለትግራይ ሕዝብ በፊትም አሁንም የፈየዱለት የለም ።እንደምታውቂው ደግሞ ለመቀሌ ውሃ ዝርጋታ የተዋጣውን ገንዘብ ቅርጥፍ አድርገው ነው የበሉት፡፡
እነሱ በፊትም ቢሆን የጠቀሙት ሕዝቡን ሳይሆን ካድሬውንና የእነሱን አገልጋይ የሆኑትን ብቻ ነው ።ሌላው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በስቃይ ነው የኖርነው ።ከኢትዮጵያውያን ጉሮሮ ነጥቀው ሃብት ሲያግበሰብሱ፣ መሬት ሲዘርፉ፣ ሲሸጡ ሲለውጡ አልፎ ተርፎም በውጭ አገራት ባንኮች ገንዘብ ሲያከማቹ ነው የኖሩት ።
የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ያደረሱትም የትግራይ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ወደ ጦርነት ይገባል ብለው ነበር ።ግን መጨረሻ ላይ ከዚህ ጦርነት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት አልቻሉም ።በተለይ የትግራይ ሕዝብ ይጠቀማል እንጂ ይጎዳል ብዬ አላስብም።የተረጋጋ ነገር ከተፈጠረለት ልማቱም ይመጣል ።
እነሱ በእርግጥ የትግራይን ሕዝብ ቢወዱት ኖሮ የልማት አውታሮችን እያጠፉ አይሄዱም ነበር ።ሕዝቡን ምሽግ ያደረጉት መንግስት ሕዝቡን ገደለ ለማሰኘትና የፖለቲካ ጩኸት ለማስገኘት ነው ።
ነገር ግን በእግዚአብሄር ቸርነትና በሰራዊታችን ጥበብ ብዙ ሰው ሳይጎዳ በድል ለማጠናቀቅ ተችሏል ።ህወሓት ከራሱ በስተቀር ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ደንታ የለውም ።ስለዚህ የጁንታው ኃይል መወገድ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ተስፋን ይፈነጥቃል ብዬ ነው የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመቶ አመት ታሪክ የፖለቲከኞች ትርክት ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ምንመሰለሽ፤ መቶ አመት ሲሉ ዋና አላማቸው አፄ ምኒሊክን ለመኮነን ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ነው ። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ሲበዘብዙ የኖሩትን አገር ያገኙት አፄ ምኒሊክ ገንብተው ትተውላቸው በመሄዳው ነው ።ንጉሱ የዘረጉትን መሰረተ ልማት እየተጠቀሙ እሳቸውን መኮነን እነዚህ ሰዎች በልቶ ካጅ መሆናቸው ማሳያ ነው። ልክ እንደማንኛውም ሰው ነቀፌታ ቢኖርባቸውም እንኳን የሰሩት መልካም ስራ ይበልጣል ።
አሁን የሚታየው ዘመናዊ ነገር ሁሉ መሰረት የጣሉት አፄ ምኒሊክ ናቸው። እሳቸው በጀመሩት ላይ ነው ሁሉም እየቀጠለ የመጣው ። ስለዚህ ማንላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ እንደሚባለው እሳቸው በገነቡት አገር ላይ ቆሞ የእሳቸውን ኃጥያት ማብዛትም ሆነ ታሪክ እንዳልነበረ መቁጠር ለማናችንም አይበጀንም፡፡
በነገራችን ላይ ዶክተር አብይ የእሳቸውን ፈለግ የተከተለ ነው የሚመስለኝ ።ይህ ሁሉ ፈታኝ ሁኔታ ባለበት በዚህ ጊዜ ተፈጥሮ 27 ዓመት ያላየነውን ነገር ያመጣልን ጠንካራ መሪ ነው ።በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚችል መገመት አያዳግትም ።
አዲስ ዘመን፡- ላለፉት ዓመታት ሲዘራ የኖረው የጎጠኝነት አስተሳሰብና የአንድነቱ ኃይል ሊያስታርቅ የሚችል ነገር አለ ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ መጥፋት ወይም መዳን ነው ።ላለመጥፋት ከተፈለገ ያለን አማራጭ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን መመስረት ነው ። አባቶቻችን እስከአሁን ያቆዩልን ኢትዮጵያ የምትባል ግዛት ብታንስም አለች ።ስለዚህ በዚህ መሰረት በእኩልነት ላይ በተመሰረተ መልካም አገር ገንብተን መሄድ ጠቃሚ ነው ብዬ ነው የማምነው።
ይህም ማለት በሃሳብ ልዕልና ተቀራርበው መስራትና አገራቸውን ማሳደግ የማይችሉበት ሁኔታ ይኖራል ብዬ አላምንም ።ነገር ግን በጎሳ ላይ ተመስርተው የተደራጁ ፓርቲዎች ለዚህች አገር ያስፈልጋታል ብዬ አላምንም እንዳውም ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ነው የሚያመዝነው ።
በነገራችን ላይ ዶክተር አብይ ብልፅግናን ሲመሰርቱ ቀድሞ በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን በጎሳ ላይ የተመሰረተ መከፋፋል ለማጥፋት ሲሉም ጭምር ነው ።እኔ እንዳውም የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ እንዲለው ነግሬው ነበር ።ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በራሱ ትርጓሜው ቢጫ ወርቅ ለእግዚአብሄር የተሰጠ ማለት ነው ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ቢጨመርበት ኃይል ይኖረዋል የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው ።ሌሎችም እንዲሁ ከዘረኝነትና ከጎሳ አስተሳሰብ ወጥተው በኢትዮጵያ ላይ ያጠነጠነ ድርጅት ቢመሰርቱና ከሌላው ጋር ተቀናጅተው ቢሰሩ ለሁላችንም መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው ትውልድ ከአድዋ ምን መማር አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡– አድዋ የአንድ ብሔር ወይም አንድ ጎሳ ድል አይደለም ።የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ወይም ነገዶች በአንድ ላይ ሆነው በንጉሱ በአፄ ምኒሊክ መሪነት እንደእናት ታምነውና ቃላቸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሁሉ የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር የዘመተበት ጦርነት ነው ። አባቶቻችን ባሪያ ሊያደርገን የመጣብንን ነጭ ወራሪ ድል የነሱት በሕብረት ነው።
በባርነት እንዳንኖርና ዛሬ ደረታችንን ነፍተን ለመንቀሳቀስ የቻልነው በአድዋ ላይ ድል በመንሳታችን ነው ።ቅኝ የተገዙ አገራት ዛሬም ድረስ ጭቁን አስተሳሰብ ይዘው ነው እየተጋዙ ያሉት ።በሥልጣኔም ከእኛ አልገፉም።በነገራችን ላይ ቅኝ ገዢዎች እንዲያገለግላቸው የሚፈልጉትን ሕዝብ እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ነው የሚያስተምሩት ።ይህም ኋላቀር ሆነው እንዲኖሩ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው።
እናም እኛ ታሪክ ያለን ኩሩ ሕዝብ እንደመሆናችን ተቻችለን፤ ታሪካችን የጋራ መሆኑን አውቀን፤ በታሪካችን ኮርተን አገራችንን እየጠበቅን መኖር አለብን ።ከመናቆርና እርስ በርስ ከመገዳደልና ከመመቀኛኘት ይልቅ አገር ልማት ላይ ብናተኮር ካሰብነው የብልፅግና መስመር ለመግባት አያዳግተንም ።በተለይም በሃሳብ ልዕልና በማመን ከተራመድን ኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት ሊኖራት ይችላል ብዬ አምናለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- በድጋሚ የዘመን እንግዳ ሆነው ከእኛ ጋር ቆይታ በማድረግዎ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013