የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤የሀገሪቱ ህብረት ሥራ ማህበራት መጠን እየጨረ ነው፤ ማህበራቱ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው በሚያከናውኗቸው ተግባሮችም ስኬታማ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ከ2003 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት መጠን በ55 በመቶ ጨምሯል፡፡ የዩኒየን አባል የሆኑ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት መጠንም 15 ሺ 813 ደርሷል። ባለፉት አምስት ዓመታት የዓባላት ቁጥር ከ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ከፍ ብሏል፡፡
የማህበራቱ አባላት ህይወት እየተሻሻለ ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት የሠሩና የገዙ ፣ የገንዘብ ችግር ሲያጋጥማቸው እየተበደሩ ጉዳያቸውን የሚተኳኩሱ ፣ወዘተ አባላት መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበራት ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ በመፈጠሩ የሰው እጅ ከማየት እንዲሁም የአራጣ አባዳሪዎች ሲሳይ ከመሆን ድነዋል፡፡ በመቆጠባቸውም የገንዘብ አቅማቸውን እያሳደጉ ናቸው፡፡
የወተት እንዲሁም የመኖ ማቀነባበሪያ፤ የዱቄት፣ የዘይት እና የመሳሰሉት ፋብሪካዎች ወዘተ ባለቤት እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ለተያያዘችው ጥረትም መሰረት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
የግብርና ምርቶችና የኢንዱስትሪ ሸቀጦች ግብይት ተዋናይ እየሆኑም መጥተዋል፡፡ የአርሶ አደሩን ምርቶች ለሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ያቀርባሉ፡፡ እንደ ቡና እና የቅባት እህሎች ያሉትን የአርሶ አደሩን ምርቶች ወደ ወጪ በመላክም ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ተግባሮች አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲሁም ሸማቹ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ እንዲያገኝ ማድረግ አስችለዋል፡፡ በእዚህም የግብይት ሰንሰለት መርዘምን በማሳጠር የዋጋ መናርንም እየተካላከሉ ናቸው፡፡
ማዳበሪያና መሰል የግብርና ግብአቶችን ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ በመረከብ ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብአት ፍላጎቱን እያሟሉ ከመሆናቸው ባሻገር በሀገሪቱ እየጨመረ ለመጣው ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው፡፡ በቁጠባ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠንም እየጨመረ መጥቷል፡፡
ማህበራቱ ለእዚህ የበቁት በርካታ ተግዳሮቶች እያሉባቸው ነው፡፡ ኤጀንሲው ማህበራቱን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት አድርሳለሁ ብሎ በቀረጸው ስትራቴጂ ላይም ይህ በሚገባ ተመልክቷል፡፡ በተማረ ሰው አለመመራታቸው፣ የሀብት ብክነት መስተዋሉ እንዲሁም በህዝቡ ዘንድ ስለማህበራቱ ያለው ግንዛቤ አሁንም ጥሬ መሆኑ ወዘተ ሲታይ ገና ብዙ መሥራት ያለባቸው ተግባር እንዳለ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እድር ላሉ ማህበራዊ ተቋማት ያለው አመለካከት ከፍተኛ የመሆኑን ያህል በህብረት ሥራ ማህበራት በመታቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹን መፍታት እንደሚችል ማስገንዘብ እና አባል ማድረግ ላይ ገና አልተሠራም ማለት ይቻላል፡፡
አድገዋል ተመንድገዋል የሚባሉት እነ አሜሪካ ጃፓን እና የመሳሰሉት ሀገሮች በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እያከናወኑ የሚገኙት ተግባር ሲታይም ሀገራችን በህብረት ሥራ ማህበራት ገና ጀማሪ እንጂ የሚያኩራራ ደረጃ ላይ ደርሳለች የሚያሰኝ ሁኔታ እንደሌለ በግልጽ ያሳያል፡፡
ከእዚህ አኳያ የኢፌዴሪ የህብረት ሥራ ኤጀንሲም የማህበራቱን ተግዳሮቶች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ማህበራቱን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ለማድረስ ያስቀመጣቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ትክክለኛ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡
በስትራቴጂው ላይ እንደተመለከተው በ2025 ዓ.ም ወይም በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የኅብረት ሥራ ማህበራት የአባላት ዕድገት በገጠር አርሶ/አርብቶ አደር 85 በመቶ እና በከተማ 75 በመቶ ይደርሳል፡፡ በገጠር የሚገኙ የግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት የግብርና እና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መቶ በመቶ ለአባላት ይሰጣሉ፡፡
በአገሪቱ በአጠቃላይ ከሚሰበሰበው የቁጠባ መጠን ውስጥ የፋይናንስ ኅብረት ሥራ ማህበራት ድርሻ 25 በመቶ እንዲሁም የፋይናንስ ኅብረት ሥራ ማህበራት ለአባላት የሚያቀርቡት የብድር አገልግሎት ድርሻም 90 በመቶ ይሆናል፡፡
በኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች መቶ በመቶ እሴት የተጨመረባቸው ይሆናሉ፡፡ በኅብረት ሥራ ማህበራት የሚሰጠው የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት እና አገልግሎት ሃምሳ በመቶ ይደርሳል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራቱ አባሎቻቸውን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ከማድረጋቸው በተጓዳኝ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡
የትኩረት አቅጣጫዎቹ በእርግጥም ማህበራቱን ወደፊት ያራምዳሉ፡፡ አገሪቱን አላለውስ ያላትን ድህነት ለመቀነስም የጋራ ክንድን በማሳረፍ ሁነኛ መሳሪያ ይሆናሉ። አቅጣጫዎቹን ለማሳካት የተቀመጡት መፍትሔዎችም እንዲሁ ብዙ ለመሥራት ተገቢ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
ይሁንና ስትራቴጂ ማስቀመጥ ብቻውን ብዙ ርቀት አያደርስም፤ ዋናውና ቀጣዩ ሥራ መሬት ላይ አውርዶ መተግበሩ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ኤጀንሲው፣ ማህበራቱና አባላቱ ቁርጠኛ አቋም ሊይዙ ይገባል፡፡ ሥራዎቻቸውን በየጊዜው እየፈተሹ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን እንዲሁም ሲምፓዚየሞችን በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ይደረስባቸዋል የተባሉት የትኩረት አቅጣጫዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብትም ይፈልጋሉ፡፡ ለእዚህ ደግሞ አንዱ መፍትሔው ህብረተሰቡን አባል ማድረግ እንደመሆኑ በእዚህ ላይ በስፋትና በተጠናከረ መልኩ መሥራት ይገባል፡፡
መንግሥት የህብረት ሥራ ማህበራት በኢኮኖሚው እና በማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው በሚገባ በመረዳት መደገፍና መከታተል ይጠበቅበታል፡፡ ከእዚህ የአንበሳው ደርሻ የሚጠበቀው ከፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ይሆናል፡፡ የትኩረት አቅጣጫዎቹ ሰፊና ርብርብን የሚጠይቁ እንደመሆናቸው ባለድርሻ አካላትን በመያዝ ማህበራቱ ተገቢውን ስፍራቸውን እንዲይዙ ማድረግና ድህነትን ጋራ በጋራ መናድ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011