ባለብሩህ አእምሮው አካል ጉዳተኛ

ዜና ሀተታ

ከማል አብዱራማን ይባላል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሲሆን በምዕራብ አርሲ ገደብ አሳሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የብየዳ ሙያ ሰልጣኝ ነው፡፡አካል ጉዳተኛ ስለሆነ ብዙ መንገድ በእግሩ መጓዝ አይችልም፤አካል ጉዳተኞች ዊልቸር ሲጠቀሙ ቢመለከትም ለመግዛት ግን አቅሙ አልነበረውም፡፡

አካል ጉዳተኝነት የአእምሮ ጉዳተኛነት እንዳልሆነ በጽኑ የሚያመነው ከማል ላጋጠመው ችግር መፍትሔ የማፈላለግ ጥረት ቀጠለ፡፡ በአካባቢ ላይ በቀላሉ የሚያገኛቸውን ብረታ ብረቶችን በመጠቀም በአእምሮው ሲያሰላስለው የነበረው ዊልቸር ለመሥራት ወሰነ፡፡

ሥራውን ሲጀምር የሌሎች ሰዎች ድጋፍ በመጠየቅ ዲዛይኑን ራሱ ቀርጾ በሚፈልገው ልክ አካል ጉዳተኞች የሚገለገሉበት ዊልቸር ሠርቶ ህልሙን እውን አደረገ፡፡ ከእዚያም እጁን ያፍታታበትን የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው ለራሱ ይገለገልበት ጀመር፡፡

ዊልቸሩም እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ሥራዎችን ለመሥራት አስችሎታል፡፡ ሆኖም በወቅቱ እየሠራ የሚማር በመሆኑ የሚሠራበት ቦታ ድረስ እቃዎችን የሚያደርሱለት ሰዎች እየሰለቹት መምጣታቸውን ተገነዘበ፡፡በራሱ ለመሥራት እንዲችል ብዙ ጊዜ ሳይጠፋ በሚገለገልበት ዊልቸር ከኋላ በኩል እቃውን የሚጭንበት ሳጥን መሥራት ቻለ፡፡

ይህም ያለሰዎች እርዳታ ሥራውን እንዲያከናውን የበለጠ ምቹ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የፈጠራ ሥራውን እያሳደገ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን መሥራቱ ቀጠለ፡፡ የበለጠ ሥራውን ሊያቀላጥፍለት የሚችል የፈጠራ ሥራ ለመሥራት በማሰብ ሦስት ሰዎች መጫን የሚችል ባጃጅ ሠርቷል፡፡

የፈጠራ ሥራዎችን በየጊዜው እያሳደገው የመጣው ከማል የጭነት አገልግሎት የሚሰጥ ሞተር ሳይክል ሠርቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው 4ኛው የክህሎት ውድድር ማቅረብ ችሏል፡፡

አካል ጉዳተኛ ቢሆንም በፍጹም ሰዎችን ለማስቸገር አልፈልግም የሚለው ከማል፤ በራሱ መሥራትና እንደልቡ ሊንቀሳቀስበት የሚችል ፈጠራ መሥራቱ በራሱ ብዙ ነገሮች እንዲያከናውን እንዳገዘው ይገልጻል፡፡

ይህን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት አንድ ወር ጊዜ ብቻ ፈጅቶበታል፡፡ የጭነት ሞተር ሳይክሉ እንደሌሎች ሞተር ሳይክሎች ሁለት ጎማ ያለው ሳይሆን ሦስት ጎማ እንዲኖረው አድርጎ መሥራቱን የሚገልጸው ከማል፤ ማርሹም ሆነ ፍሬኑ እጅ ላይ ተደርጎ መሠራቱ አካል ጉዳተኞች እንደልባቸው ሞተር ሳይክሉን እንዲነዱ ያስችላቸዋል፡፡ ሞተር ሳይክሉን ራሱና ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ የሠራው ቢሆንም፤ ሌሎችም ሰዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

ከማል እንደሚለው፤ ሞተር ሳይክሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሞተር ሳይክሉ በቤንዚል የሚሠራ ሲሆን፤ በአንድ ሊትር ቤንዚል ሠላሳ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይችላል፡፡ የጭነት አገልግሎት በመዋል የሚቻል ሲሆን፤ አራት ኩንታል የመጫን አቅም አለው ይላል፡፡

የፈጠራ ሥራውን በተለያዩ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች ተጠቅሞ የሠራው መሆኑን ገልጾ፤ ሞተር ሳይክሉ ለጭነት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ጭነቱ በዝናብ እንዳይበሰብስ የሚያደርግ ጥላ የተሠራለት መሆኑን ይገልጻል፡፡ የጭነት ሞተር ሳይክሉ 170ሺህ ብር የፈጀ ሲሆን፤ ሥራውን ሲሠራ ኮሌጁ የገንዘብና የማሽነሪ ድጋፍ እንዳደረገለት ያስረዳል፡፡

ወደ ውድድር ከመምጣቱ በፊት ቀደም ሲል የሠራቸውን ሦስት ዊልቸሮች ከ6ሺህ እስከ 8ሺህ ድረስ መሸጡንም ያስታውሳል፡፡ ሁለተኛ የፈጠራ ሥራው የሆነውን ሦስት ሰዎች የምትጭነውን ባጃጅም እንዲሁ 80ሺህ ብር መሸጡን ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ አቅም ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ዊልቸሮችን በመሥራት ድጋፍ ማድረጉንም ይገልጻል፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹም በእዚህ መልኩ እድልና የገቢ ምንጭ እንደሆኑትም ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ይህንን ሞተር ሳይክል ያሉበትን ክፍተቶች በማየት ማሻሻል እንደሚቻል ጠቅሶ፤ ሌሎች አዳዲስ መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራ ሥራዎችንም ለመሥራት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ወደፊትም ለአካል ጉዳተኞች የሚጠቅሙ የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት አላማ አድርጎ እንደሚሠራ ገልጾ፤ ሞተር ሳይክልን ወደ ባጃጅ በመቀየር አካል ጉዳተኞች በቀላሉ ሊሠሩበት እንዲችሉ በማድረግ ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እየሠራ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ሦስት ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቻለሁ የሚለው ከማል፤ በአሁኑ ወቅት የፈጠራ ሥራዎቹን ራሱም ሆነ ሌሎች ሰዎች እንዲገለገሉበት እያደረገ ይገኛል።

ቀደም ሲል በ2015 ዓ.ም ‹‹በኢትዮ ክህሎት ውድድር›› በሰመር ካምፕ መግባቱን ገልጾ፤ ማበልጸጊያ ማዕከሉ ሆኖ የሠራው አራት ሰዎች መጫን የሚችል ባጃጅ በክህሎት ባንክ ውስጥ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You