የግብርና ግብዓቶችን በቴክኖሎጂ የማሰራጨቱ ጅማሮ ተጠናክሮ ይቀጥል!

ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 130 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ የሚመግብ ዘርፍ ነው። በሌላ በኩል 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው ቀጥታ ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ከውጭ ምንዛሪ አንጻርም ብንመለከተው አብዛኛው ድርሻ የሚገኘው ከእዚሁ ዘርፍ ነው።

ይህንኑ ሃቅ በመገንዘብ በተለይ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። የሀገሪቱን መልክዓ ምድርና የአየር ጸባይን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች በመሠራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በአቅሟ ልክ አምርታቸው የማታውቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በዋነኝነት መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ከሰጠው ትኩረት የመነጨ ውጤት ነው፡፡ በተለይም ግብርናውና ለዘመናት ሲሠራበት ከነበረበት ተለምዷዊ አሠራር በማላቀቅ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሎታል፡፡

በተለይም በሀገሪቱ የ2025 የዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ተግባር መገባቱ ለግብርናው ዘርፍ አዲስ ብስራት ይዞ ብቅ ብሏል። ለግብርናው ወደ ኋላ መቅረት አንዱ ምክንያትም ግብርናው ከባሕላዊ አስተራረስ እና ከግብዓት ስርጭት አለመላቀቁ ነው፡፡

በተመሳሳይም የቴክኖሎጂ መጓደል አርሶ አደሩ እና አምራቹን በማራራቅ አላስፈላጊ የዋጋ ጫና እንዲፈጠር ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች አርሶ አደሩ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ወቅታዊ የምርቶችን ዋጋ እንዲያወቅ እና እንዲገበያይ በማድረግ አላስፈላጊ የደላላ ጣልቃ ገብነትን የሚያስቀሩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚታዩ ለምርታማነት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ከስር ከስሩ ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ግብርናው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንዲያስመዘግብ መንገድ ጠርጎለታል። ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት፤ የሕዝቡ አሰፋፈር ከሜዳማ እስከ ተራራማ ድረስ የተለያየ መሆኑ እና ወደ አርሶ አደሩ የሚቃረቡ መንገዶች ለትራንስፖርት ምቹ ባለመሆናቸው የተነሳ ግብአቶችን በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለማዳረስ ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ለእዚሁ አንዱ ማሳያ በ2014 እና በ2104 በነበሩ የምርት ወቅቶች ማዳበሪያን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ ከፍተኛ የሆኑ ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በተመሳሳይም ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ ጋር በአግባቡ የማይደርስበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡

ይህንኑ በመረዳትም መንግሥት በሕገወጥ ተግባራት ውስጥ የተሠማሩትን ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን ዘላቂ በሆነ የግብአቶች ስርጭት እንዲኖር አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡

የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦቶች ፍትሐዊ እና ከሕገወጥ አሠራር የጸዳ እንዲሆን አሠራሩ ዲጂታላይዝድ እንዲሆን ተደርጓል። የምርጥ ዘርም ሆነ የማዳበሪያ ፍላጎት፤ አቅርቦትና ስርጭት የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋቱ እያንዳንዱ ክልል ምን እንደሚፈልግ እና መቼ ሊቀርብለት እንደሚገባም በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ይህም የግብአት አቅርቦቱ ለብክነትም ሆነ ለብልሹ አሠራር እንዳይጋለጥ ያደርገዋል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ግብርና ነው። ይህንን ዘርፍ በሚፈለገው ልክ በቴክኖሎጂ መደገፍ ካልተቻለ ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ስለማይቻል የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ የመደገፉ አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። የበርካታ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየውም የሀገር እድገት እና ብልፅግና ሊረጋገጥ የሚችለውም ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ልክ ነው። ግብርናው በቂ ፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ እገዛ ካገኘ የሚሰጠውም ውጤት በዛው ልክ የተትረፈረፈ ይሆናል፡፡

ስለዚህ አሁን በጅምር ላይ ያለውና ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባበት ግብዓቶችን በቴክኖሎጂ የማሰራጨት ጅማሮ ተጠናክሮ መቀጠል ከቻለ ራስን በምግብ ከመቻል አልፎ በቀላሉ ለውጭ ገበያም የግብርና ምርቶች አቅርቦ ሀገርን ማሳደግ ይቻላል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You