ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬን “በአፋጣኝ” የተኩስ አቁም ድርድር እንደሚጀምሩ አስታወቁ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን “በአፋጣኝ” የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩ ተናግረዋል። ትራምፕ ይህን ያሉት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሁለት ሰዓት የዘለቀ የስልክ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ነው። ትራምፕ የስልክ ልውውጡን “እጅግ መልካም” ብለው የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል ከስምምነት ሊደረስባቸው እንደሚገባ አሳውቀዋል።

ምንም እንኳ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ቢናገሩም፤ በቅርቡ ስምምነት ይፈፀማል የሚል ግምት የለም። ትራምፕ ከፑቲን በተጨማሪ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ውይይት አድርገዋል። ፑቲን ከዩክሬን ጋር ለመሥራት እና “ወደፊት የሰላም ስምምነት ለመድረስ” ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ ዜሌንስኪ በበኩላቸው “ይህ ወሳኝ ወቅት ነው” ብለው አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን እንዳታገል ጥሪ አቅርበዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ያቀረቡትን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ጉዳይ ችላ ብለውት አልፈዋል። ከትራምፕ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉት ዜሌንስኪ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሚደረስ ሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት” ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀው፤ ነገር ግን ሞስኮ ዝግጁ ካልሆነች “ቅጣት ሊጣልባት ይገባል” ብለዋል።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ካደረጉት የስልክ ልውውጥ ቀደም ብሎ ንግግር ያሰሙት ዜሌንስኪ ዩክሬንን በተመለከተ ሀገራቸው ያልተሳተፈችበት ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳይደረስ ጠይቀዋል።ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው “ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት ይጀምራሉ። ከተኩስ አቁም ስምምነት በላይ ጦርነቱን ለማስቆም ንግግር ያደርጋሉ” ብለው ይህን ጉዳይ ለዜሌንስኪ ማሳወቃቸውን ጽፈዋል።

“ይህን ለማድረግ በሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ሁለቱ ሀገራት ውይይት ያደርጋሉ። ምክንያቱም ከሌላው በላይ ስለጉዳዩ የሚያውቁት እነሱ ናቸው። ”ዜሌንስኪ የተኩስ አቁም ስምምነቱ “አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረትን ሊያካትት ይገባል” ይላሉ።ትራምፕ አሜሪካ ከሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ራሷን እንደማታገል ቢያስታውቁም “ቀይ መስመሩን ካለፉ ግን” ከጉዳይ ራሳቸውን ሊያገሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አሜሪካ ከአደራዳሪነት ራሷን እያገለለች ነው የሚለውን ሃሳብ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።ትራምፕ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ስምምነት ለመድረስ ቁርጠኝነት አለማሳየታቸውን አውስተው፤ አሜሪካ ከጠረጴዛው ገሸሽ ልትል እንደምትችል ጠቁመዋል።

ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ጦርነቱ ስለሰለቻቸው ማቆም ይፈልጋሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ፑቲን ከትራምፕ ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ “ግልፅ፣ ገንቢ እና አስፈላጊ” መሆኑን ገልጸዋል። ትራምፕ ከፑቲን ቀጥሎ ከዜሌንስኪ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ላይ የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዚዳንት እንዲሁም የፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን እና ፊንላንድ መሪዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You