አቶ ቢኒያም ኢሮ የተቋማት ቁጥጥር ኢኒስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ም/ዋና ዳይሬክተር
መግቢያ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፍረዱኝ ዓምዱ፣ የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣንን በተመለከተ፣ “አገልግሎት ለማግኘት ተቋሙን በእንባ ደጅ የሚጠኑ ቅሬታ አቅራቢዎች” በሚል ርዕስ ከኅብረተሰብ የቀረበ ቅሬታንና የጋዜጠኞች ምልከታን በማካተት ባለፈው ሳምንት (ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ.ም) እትማችን አንድ ዘገባ ማውጣታችን ይታወሳል። ዘገባችንን ለማጠናቀር በተንቀሳቀስንበት ወቅት (በአካልና በደብዳቤ) ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምላሽ ለማግኘት እንደተቸገርን ጭምር ጠቅሰን፤ በቀጣይ ዘገባዎቻችን የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ፈቃደኛ ከሆኑ የሚሰጡንን ምላሽ ይዘን እንደምንመጣ ቃል ገብተን ነበር። ዘገባውን በጋዜጣችንና በዲጅታል ሚዲያችን አማካኝነት ይዘን መውጣታችንን ተከትሎ ተቋማችን ሁለት ዓይነት ተቃራኒ የሚመስሉ ምላሾችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
የመጀመሪያው ከተገልጋዮች አቅጣጫ የተገኘ ሲሆን፤ ተመሳሳይ ዓይነት ችግር እንደገጠማቸውና በአገልግሎት ሰጪ ተቋሙ ቅር መሰኘታቸውን የገለጹ ናቸው። (የተወሰኑ አስተያየቶችን በግርጌ ማስታወሻ ስላሰፈርናቸው መመልከት ይቻላል።) በአንጻሩ ሁለተኛ ምላሽ የተቀበልነው ከአገልግሎት ሰጪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሲሆን፤ በዘገባው የቀረበው መረጃ እንደማይገልጸው፣ ይልቁንም የተቋሙን ስም ለማጠልሸት የቀረበ ተራ ክስ እንደሆነ እና በዝግጅት ክፍላችን ጭምር ቅር እንደተሰኘ ነግሮናል።
እንደ አንድ ሕዝብን ለማገልገል እንደተቋቋመ ሚዲያ በዘገባዎቻችን፣ በተለይም የመልካም አስተዳደርን የተመለከቱ ከፊል የምርመራ ዘገባዎቻችን እውነትን ሲፈትሹ ሚዛናዊነት እንዳይጎድላቸው ለማድረግ ከተገልጋይም ከአገልጋይም አንጻር ማቅረባችን ተገቢ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም በዛሬው ዘገባችን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በቀረበ ቅሬታ መሠረት ምላሻቸውን ለማስተናገድ በባለሥልጣኑ የተቋማት ቁጥጥር ኢኒስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ም/ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ቢኒያም ኢሮ ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ ይዘን መምጣታችንን እየገለጽን፤ ዘወትር እንደምንለው ፍርዱን ለአንባቢ እንተዋለን። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፦ የተቋሙ ተግባርና ኃላፊነት ቢያሳውቁን?
አቶ ቢንያም፦ የኤፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የትምህርት ጥራት የሚቆጣጠር ተቋም ነው። ጅማሬውን ኤጀንሲ አድርጎ አሁን ላይ ባለሥልጣን ደረጃ ደርሷል። ላለፉት 16 ዓመታትም አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በሀገሪቱ የሚሰጡ አጠቃላይ የትምህርት ፈቃዶችን ይሰጣል። የሰጣቸውን ፈቃዶችም ይቆጣጠራል። በቁጥጥር ሥርዓቱም የዳበሩና ተገቢውን መስፈርት ያሟሉ ተቋማት ሲፈጠሩ በፕሮግራም ዕውቅና ይሰጣል። በተጨማሪም የትምህርት ማስረጃን የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል። በመንግሥትና በግል እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለተገኙ የትምህርት ማስረጃዎች አቻ ግመታ ይሰጣል። ይህም ብቸኛው በሕግ የተቋቋመ ተቋም አድርጎታል።
በተጨማሪም እንደ ሀገር አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ደረጃን ይቆጣጠራል። ከቅድመ መደበኛ እስከ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ያለውን የትምህርት ጥራት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ ይጠይቃል ይፈትሻል። የተማሪና የመምህራን፣ የተማሪና የመጽሐፍ ጥምርታን ይቆጣጠራል። ይህን መሠረት በማድረግ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል። ማስተካከያ ካልተወሰደ ለመንግሥትና ለሕዝብ ያሳውቃል። አጠቃላይ ትምህርትን በሚመለከትም ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ይሠራል።
አዲስ ዘመን፦ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለሥልጣኑን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ያላችሁ ቅሬታ ምንድን ነው?
አቶ ቢንያም፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከባለሥልጣኑ ጋር ሰፊ የሆነ የሥራ ግንኙነት ያለው አንጋፋ ድርጅት ነው። ነገር ግን ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ባለሥልጣኑን ፍጹም የማይገልጽ፣ በምንም መልኩ የተቋሙ መገለጫ ያልሆነ፣ ሚዛኑን ያልጠበቀ፣ የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር የጎደለው፣ የባለሥልጣኑን ክብርና ዝና የሚነካ፣ በሕዝብና በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነትና ታማኝነት የማይገልጽ ዘገባ ይዞ ወጥቷል። በእኛ ግምገማና ክትትል ምንም እንኳን ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም አጠቃላይ ዘገባው ተቋሙን የሚያጠለሽ ነው። ከእዚህም ባለፈ በሪፎርሙ እየመጣ ባለው ለውጥ ጥቅሙ የተነካበት ኃይል ተደራጅቶ የተቋሙን ስም ለማጥፋት የተሠራ ሥራ ነው ብለን እናምናለን።
ይህን ስንል ዘገባው ፍረዱኝ በሚል አምድ የምርመራ ዘገባ ሆኖ ተገልጋዮችን አገኘን ይላል። ተገልጋዮች ላነሱት ጥያቄም ከተቋሙ ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለ ተደርጎ ቀርቧል። ይሁንና ተቋሙ ኅዳር ወር ላይ የተጠየቀው መረጃ አሁን ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከወጣው ዘገባ ጋር የሚናበብ አይደለም። በወቅቱ የተጠየቀው አጠቃላይ የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ማለትም በተቋማት ፈቃድና በቁጥጥር ሥራ ላይ መረጃ ይሰጠን የሚል እንጂ የምርመራ ዘገባ ስለመሥራት አይገልጽም። የምርመራ ዘገባ ከሆነ ጋዜጠኛው መርምሮ የደረሰበትን ጉዳይ በመጥቀስ በእዚህ በእዚህ ጉዳይ ምላሽ ይሰጠን በሚል መጠየቅ ነበረበት። ያም ሆኖ ባለሥልጣኑ በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ለሚዲያ ተቋማት የተጠየቀውን መረጃው ለሕዝብ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
በተመሳሳይ የባለሥልጣኑ ቅጥር ግቢ ለተገልጋዮች ምቹ እንዳልሆነ ተጠቅሷል። እርግጥ ነው ተቋሙ ያለበት ሕንጻ በትውስት የተገኘና የትምህርት ሚኒስቴር ለላብራቶሪ አገልግሎት የሚጠቀምበት ሕንጻ ነው። ተቋሙ በመንግሥት ድጋፍ አዲስ ሕንጻ እየገነባ ሲሆን፤ እስከ ሰኔ መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ስለሆነም ለጊዜው በምንሠራበት መሥሪያ ቦታ የተጠናቀቀ ምድረ ግቢ ለመሥራት አንችልም። ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን በተባለው ልክ ምቾት የጎደለው አይደለም። ባለን አቅም ሁሉ ለሥራ ምቹ የሆነ ከባቢን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል። (አዲስ ዘመን ያቀረበው የተቋሙን ተገልጋዮች ቅሬታ ጠቅሶ መሆኑ ይታወሳል)
አዲስ ዘመን፦በዘገባው ተቋማችሁ አስለቀሰን ስለተባሉ ተገልጋዮች ምን ይላሉ?
አቶ ቢንያም፦ዘገባው አገልግሎት ፈላጊዎች በባለሥልጣኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ መመላለሳቸውን፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መምጣታቸውን እንጂ መሠረታዊ ምክንያታቸውን አልመረመረም።(መሠረታዊ ምክንያታቸው የትምህርት መረጃን ለማረጋገጥ ኦተንቲኬት ለማስደረግ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ለጋዜጣዋ ገልጸው ነበር) ተገልጋዮች ለምን ምልልስ በዛባቸው፤ ለምን አለቀሱ፤ የሚለውን ጉዳዩ ከሚመለከተውና ዘርፉን ከሚመራው ኃላፊ መረዳት እየተቻለ ይህ ሳይሆን ቀርቷል። በወቅቱ አብሮ ተንቀሳቅሷል ከተባለው የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ክፍሉ ይህን የማስረዳት ኃላፊነት ነበረበት። ጋዜጠኞቹም ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል ለይቶ የማወቅና ጉዳዩን የመረዳት ኃላፊነት እያለባቸው ይህን አላደረጉም።
በወቅቱ ዋና ዳይሬክተሩን ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ዋና ዳይሬክተሩ በጉዳዩ ላይ በቅርብ ጊዜ መግለጫ መስጠታቸውን ገልጸዋል። ባለሥልጣኑ የተጠየቀው ጥያቄ ወቅታዊ መረጃ እንዲሰጥ የሚል ሆኖ ጋዜጣው ላይ የወጣው ግን የተቋሙን ስም ማጥፋትና ማጠልሸት ነው። ለስም ማጥፋቱ ማጣፈጫም የተወሰኑ ግለሰቦችን ለቅሶ አግንኖ አሳይቷል። ከአራቱም ማዕዘናት የሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚያለቅሱበት ቤት እንደሆነም ስዕል ፈጥሯል። ይህም ባለሥልጣኑን ለማጠልሸት የተሄደበትን ርቀት ያሳያል።
በዘገባው ከተገልጋዮች ለቅሶና ሮሮ በተጨማሪ ባለሥልጣኑ ዲጅታላይዜሽን የማያውቀው ነው ተብሏል። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ተቋሙ የሚሰጣቸው 14 የሚደርሱ አገልግሎቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል በቀጥታ ከደንበኞች ጋር የሚገናኘው የአውተንቲኬሽን አገልግሎት ነው። ይህን አገልግሎት ለመስጠት እርግጥ ነው የሲስተም መቆራረጥ ይገጥም ነበር። የሲስተም መቆራረጡ የመጣውም ሀገሪቷ በለውጥ መንገድ ላይ በመሆኗ እና በዋናነት አካባቢው በኮሪዶር ልማት ሥራ ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ይህንንም በማስተካከል ሂደት ላይ እንገኛለን። ይሁንና ዘገባው በእዚህ ምክንያት የታዩ ክፍተቶችን ጭምር መነሻ በማድረግ ተቋሙ ምንም ዓይነት የዲጅታላይዜሽን ሥራ አይሠራም በሚል ፈርጇል። (ለትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ የዲጂታል አገልግሎቱን የተመለከትነው ቢሆንም አጠቃቀሙን በተመለከተ ለተጠቃሚዎች በማስተዋወቅ ረገድ የኮሙኒኬሽን ክፍተት በተቋሙ እንደነበርም ተግባብተናል)
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ሥራዎችን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊና ከሰዎች ንክኪ የጸዳ ለማድረግ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል የተገኙ ውጤቶችስ…
አቶ ቢንያም፦ የአመራር ለውጡን ተከትሎ ባለሥልጣኑ ጉዞውን ወደ ዲጅታል አድርጓል። መቶ በመቶ ባንደርስም ሥራው ከሁለት ዓመት ወዲህ ተጀምሯል። ሲስተሙ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየለማ ያለ ነው። ዲጅታል ፖሊሲን በማዘጋጀት ከደብዳቤ ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ዲጅታላይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ባለሥልጣኑ ከ300 በላይ ኮሌጆች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የደብዳቤ ፍሰት አለበት። በርካታ የግለሰብ ተገልጋይም ያለው ነው። ስለሆነም የደብዳቤ ፍሰቱን ሳይቀር ዲጅታል ለማድረግ ጨረታ ወጥቶ እየተሠራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሰነዶች ማረጋገጫ ወይም አውተንቲኬሽን የተባለው ዘርፍ ነው። ይሁንና ባለሥልጣኑ ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ምንም አይነት የዲጅታላይዜሽን እንቅስቃሴ አልነበረውም።
አሁን ላይ ሲስተሙ ምን መሟላት እንዳለበት ያረጋግጣል። ሰነዶቹን ያስገባል። መረጃው ከተሟላ ቀጠሮ ይሰጣል። ካልተሟላ ቀጠሮ አይሰጥም ወደ ባለሥልጣኑም አይመጣም። ባለሥልጣኑ በዋናነት ግለሰቦች ማስረጃዎችን ለማረጋገጥ ወደ ባለሥልጣኑ ቅጥር ጊቢ እንዳይመጡና ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገም ይገኛል። ለእዚህም ዲጅታላይዜሽንን ማፋጠን ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ ወስዶ ብዙ ርቀት ተጉዟል።
አሁን ላይ ጥቂት መረጃዎች ወደ መረጃ ቋት ባለመግባታቸው በማንዋል አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም፤ በማንዋል የተገኘውም ዳታ ስካን ተደርጎ ወደ ሲስተሙ ይገባል። ቀጥታ ቅብብሎሹን ዲጅታላይዝድ በማድረግ ግለሰቦች የተሟላ መረጃ ካላቸው በተለያዩ አማራጮች ባሉበት ቦታ መረጃ ይደርሳቸዋል። ሙሉ ለሙሉ ዳታ የማጥራት ሥራውም ቢበዛ ሁለት ወራትን የሚጠይቅ በመሆኑ ባለሥልጣኑ በቀጣይ ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ከጫፍ ተደርሷል። በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ የዲጅታላይዜሽን ሥራው 80 በመቶ ደርሷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራዎቹን ዲጅታላይዝ በማድረግ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለአብነትም ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ዲግሪ፣ ከ87 ሺ በላይ የማስተርስ የተማሪዎች መረጃ ሲስተም ላይ ገብቷል። ይህም ማለት ከግለሰቦች ንክኪ ጸድቶ አገልግሎት ፈላጊዎች በተቀላጠፈ እና ከማጭበርበር ነጻ የሆነ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። በአሁኑ ወቅትም ሲስተሙ ተግባራዊ ሆኖ አገልግሎት ፈላጊውን በሥርዓቱ እያገለገለ ይገኛል። ተገልጋዮች መረጃቸውን በአግባቡ በመሙላት ባለሥልጣኑ በሚሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ወደ ባለሥልጣኑ ይመጣሉ። ይህም ባለሥልጣኑ ሥራውን እየሠራ ያለው ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መንገድ ስለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው።
መቶ በመቶ እንከን አልባ ነን፤ ችግር የለብንም አንልም።ይሁንና ወደ ባለሥልጣኑ የሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች እያለቀሱና እየተንከራተቱ ነው ተብሎ የተዘገበው በባለሥልጣኑ ችግር አይደለም። ለአብነትም አንድ ኮሌጅ ተማሪዎቹን ባስመረቀ በ45 ቀናት ውስጥ መረጃዎችን ወደ ዳታ ማስገባት አለበት። ተቋሙ ይህን ባላደረገ ጊዜ ምልልሶች ይበዛሉ። ከእዚህ ቀደም በነበረው የማንዋል አሠራር መረጃ በቀጥታ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ገብቶ እዛው ተረጋግጦ ያልፍ ነበር። ለብዙ ችግሮች መንስዔ በመሆኑ አሁን ይህ አሠራር ቀርቷል። በአሁኑ ወቅት ተቋም ቀመስና ተቋምን ሽፋን ያደረጉ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች የተበራከቱ በመሆናቸው ባለሥልጣኑ ይህን ለማጣራት ጥንቃቄ እና ጊዜ ይፈልጋል። ይህም ባለሥልጣኑ እጅግ ከደከመበት እንዲበረታና ሕይወት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ነው። በአሁኑ ወቅትም ኢንሳ ያረጋገጠውን ሲስተም በመጠቀም ከሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መሶብ ሊገባ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህም ሲስተም ዘርግቶ ዲጅታል አሠራርን ተግባራዊ በማድረጉ ያገኘው ዕድል ነው።
በዋናነት መረጃው ወደ ዳታ ከመግባቱ እስከ ሲስተም አጫጫኑ ያለውን ሂደት የሚያሳይ ማኑዋል ተዘጋጅቷል። ይህም የብዙ አካላትን ያለአግባብ የሚገኝ ጥቅም ይነካል። በተቋሙ ውስጥ ተሸሽጎ በየደረጃው ሲጠቀም የነበረን ኃይል ያልተገባ ጥቅም እንዳያገኝ ማድረግ ተችሏል። አሁን ላይ አንድ ሲዲና አንድ ወረቀት እየላከ ‹‹የዲግሪ ምሩቄ ነበር፤ ማስተርስ ተማሪዬ ነበር ረሳሁት።›› በሚል ሲስተም ላይ ይጫንልኝ ብሎ የሚልክ ተቋምን አንቀበልም። ይህ ዓይነቱ አሠራር አሁን ላይ ፈጽሞ የለም። ባለሥልጣኑ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ የሚያስተናግድበት ጊዜ አክትሟል።
ባለሥልጣኑ የሚያስተናግደው ተማሪው የተማረበትን ዓ.ም መነሻ በማድረግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ ነው። ለእዚህም ባለሙያዎችን ተቋሙ ድረስ በመላክ በትክክል ተምሯል ወይ የሚለውን ጥያቄ ይፈትሻል። በተግባር ተቋማቱ ጋር ሲኬድ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ። ለአብነትም ምሩቅ ነው ተብሎ የተላከው ተማሪ ውጤት አይገኝም። እንኳን ውጤቱ የመመረቂያ ጽሑፍ ጭምር የማይገኝበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ስለዚህ ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች ናቸው ብሎ መረጃ ላከ ማለት አውተንቲኬት ይደረግለታል ማለት አይደለም። በግዢ የመጣ ከሆነ ተጣርቶ ይመለሳል። ይህም ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል። ይሁን እንጂ የእዚህ አሠራር አጋፋሪ የነበሩ በሮች መዘጋት ጀምረዋል። ስለሆነም በእኛ ችግር ሳይሆን በተማሩባቸው ተቋማት ችግር ምክንያት መመሪያ ሲከለክላቸው የሚያለቅሱ እና ቆይተው ደጅ የሚጠኑ ይኖራሉ። ሁሉን ነገር አሟልቶ እና ሕጋዊ ሆኖ አገልግሎት የሚነፈግ እና የሚጉላላ ባለጉዳይ ካገኘን ግን ይህን ባደረገው አካል ላይ የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን።
አዲስ ዘመን፦ አገልግሎት ፈልገው የባለሥልጣኑን ደጅ ጠኑ የተባሉት ባለጉዳዮች ምን ያህል ናቸው? በምን መልኩስ እየተስተናገዱ ነው?
አቶ ቢንያም፦ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው። በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ደረጃ የትምህርት ማስረጃዎችን አጣሩ ተብሏል። ስናጣራ የግለሰቡ ስም ዳታ ላይ ከሌለ ሀሰተኛ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ተገልጋዮቹ ወደ ባለሥልጣኑ የሚመጡት በአብዛኛው ባለሥልጣኑ አጣርቶ መረጃዎችን ወደ ኮሌጆች ሲልክ ነው። በእዚህ ጊዜ ታድያ ተቋሙ አስተምሬያቸዋለሁ፤ ነገር ግን ረስቼያቸው ነው በሚል ዳታ ይዞ ይመጣል። ይህ ማለት (ሚስድ) የተባለ ዳታ ማለት ነው።
አሁን ላይ በብዛት ወደ ባለሥልጣኑ የሚመጡትና ተንገላቱ የተባሉት ተገልጋዮች ከ10 እና ከእዛም በላይ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። እነዚህ ተገልጋዮች መረጃቸው ሙሉ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በራሳቸው ጊዜ በባለሥልጣኑ ቅጥር ግቢና በአካባቢው ይታያሉ። ይዘው ለመጡት ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ መልስ ይፈልጋሉ። ስለሆነም ለእነዚህ ሰዎች እንግልት ተጠያቂው ባለሥልጣኑ ሳይሆን የተማሩበት የትምህርት ተቋም ነው። ተቋማችን ሕጋዊ ሆኖ ለመጣ አካል ጥቅሙን ይሰጠዋል። ሕገወጥ ሆኖ ማስረጃ ይዞ ለመሄድ የሚጣደፈውን ደግሞ ባለሥልጣኑ ተረጋግቶ እና አጣርቶ የሚሰጠው ይሆናል። እያንዳንዱ ተገልጋይም በመመሪያው መሠረት ብቻ ይስተናገዳል።
መመሪያውን ያሟላ ተገልጋይ ሳይቆይ ይስተናገዳል። ሲስተሙ ላይም በእዚሁ መመሪያ መሠረት በሥርዓት ከሞላ በፍጥነት ተስተናግዶ የሚሸኝ ይሆናል። አሁን የሚመጣው ተገልጋይ ሲኦሲ ሳይኖረው አልያም ዘግይቶ የሚመጣ፣ አውተንቲኬት ለማድረግ የሚያስችሉ መስፈርቶችን የማያሟላና ጊዜ ወስዶ ወደኋላ ሄዶ ማጣራት የሚፈልግ ነው። በእዚህ መሀል መረጃውን በጥድፊያ ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ አለ። ባለሥልጣኑ ይህን የመቆጣጠር ኋላፊነት ያለበት በመሆኑ መረጃዎችን ጊዜ ወስዶ ያጣራል። በየቢሮው ሲዞሩ የሚታዩትና አለቀሱ የተባሉት ተገልጋዮች መመሪያው ሊያስተናግዳቸው ያልቻሉ ተገልጋዮች ናቸው። ስለዚህ በባለሥልጣኑ ምክንያት አላለቀሱም።
አዲስ ዘመን፦ርምጃ የተወሰደባቸውና የተቀጡ ተቋማትን ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ አንጻር የተሠሩ ሥራዎች ካሉ ቢጠቀሱ
አቶ ቢንያም፦ርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት ሲባል አንደኛውኑ ከሥርዓቱ የወጣን ተቋም ርምጃ ተወስዶበታል ብለን ለማኅበረሰቡ ይፋ እናደርጋለን። ይህም ከሚዲያ አዘጋገብ አንጻር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው። ለአብነትም ባለሥልጣኑ ሁለት ክሶች ገጥመውታል። ሥራ ላይ ያሉና ያልተዘጉ ተቋማት የዲሲፕሊን ግድፈት ተገኘባቸው። ግኝቱንም ይፋ አደረግን። ጉድለቱ ጥቂት ጉድለት ነው። ይህን ክትትል በማድረግ ማረም ያስፈልጋል። ይሁንና ይህን በሚዲያ ማውጣት የተቋማቱን ሕልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው። ምክንያቱም ሥርዓት ውስጥ አሉ፤ ከሥርዓቱ አልወጡም። ስለሆነም ጥንቃቄ እናደርጋለን። ለእዚህም ነው ከሥርዓቱ ያልወጣ እና መታረም ያለበትን በሚዲያ መግለጽ ያቆምነው። ከእዚያ ባለፈ በዓመቱ መጀመሪያ ፈቃድ ያላቸውና የሌላቸውን ተቋማት ለማኅበረሰቡ ግልጽ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረግን ነው።
በአሁኑ ወቅት ለተቋማት አዲስ ፈቃድ እየተሰጠ አይደለም። ቀድሞ በነበረው አመራር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ160 በላይ ኮሌጆች ወደ ገበያው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህም የትምህርት ጥራቱ ላይ ተጽዕኖ አምጥቷል። ዲግሪና ማስተርስ በስፋት እንዲመረት ተደርጓል። አሁን ላይ ይህን በመታገል ውጤት ማምጣት ተችሏል። በመሆኑም ባለሥልጣኑ አዲስ ፈቃድ ከመስጠት ይልቅ እድሳት በማድረግ ዳግም ምዝገባ እያደረገ ይገኛል። በዳግም ምዝገባው ኮሌጁ አልያም ዩኒቨርሲቲው መስፈርቶቹን አሟልቷል ወይ የሚለውን በመፈተሽ ዳግም ምዝገባ እየተደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅትም አዲስ መስፈርት የወጣ ሲሆን፤ ትንሹን መስፈርት ማሟላት የቻለ ተቋም ይቀጥላል። ያላሟላውና ከመስፈርቱ የሚወጣው ደግሞ ከሥርዓቱ ይወጣል። ይህን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ እስካሁን 85 የሚደርሱ ተቋማት ከሥርዓቱ ወጥተዋል። ይህም ማለት ከኮሌጅነት የተሰረዙ ሲሆን፤ ተማሪዎችም በእነዚህ ኮሌጆች እንዳይማሩ ይፋ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ከትምህርት ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ ቢንያም፦ ትምህርት ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት የሚሠራ ሥራ እንጂ ትርፍ ለማጋበስ ታስቦ የሚሠራ አይደለም። ስለሆነም ተቋማቱ ይህን መለየት ይጠበቅባቸዋል። ተቋማቱ መመሪያን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ባለሥልጣኑ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል። ከመመሪያ ውጪ የሚሠሩትን ደግሞ ከሥርዓቱ እንዲወጡ ያደርጋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ባለሥልጣኑ በሠራው የቁጥጥር ሥራ 85 ተቋማትን ከሥርዓቱ ውጪ አድርጓል።
እርግጥ ነው የትምህርት ሥራ ውጤቱ በአንድ ጊዜ የሚታይ አይደለም በጊዜ ሂደት የሚመጣ ነው። እስካሁን የመጣንበት መንገድም ሀገር በትምህርት ጥራት ወድቆ አይተናል። ከእዚህ በኋላ ያለውን ለማሻሻል ደግሞ ባለሥልጣኑ ኃላፊነት አለበት። ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለው ጥረትም ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ነው።
ምክንያም ከእዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የሀሰት የትምህርት ማስረጃ ሕጋዊ ሆኖ ሲበረታታ ቆይቷል። አሁን ላይ ግን ይህን ማስቀረት በመቻሉ ይህ ለምን ቀረ የሚሉ ጥቅማቸው የተነካ አካላት ከውስጥም ከውጭም ይፈታተኑናል። ያም ቢሆን ታድያ ባለሥልጣኑ በተቻለው አቅም ሲስተሙን መሠረት በማድረግ በትክክል የለፋና የተማረ ሰው መረጃ እና የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ከተቋማት በሚመጡ ብልሹ አሠራሮች በርካቶች ሳይማሩ ማስተርስ ተሸክመው ይመጣሉ። ባለሥልጣኑ እንዲህ ዓይነቱን ሕመም በመረዳት ሀገርን ለመለወጥ ብሎም ዜጎችን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እየለፋ ባለበት በእዚህ ወቅት ተገልጋዮችን እያንገላታ እንደሆነ ተዘግቧል። ይህ ፍጹም ስህተት ነው።
ይህ የሚደረገው ከእዚህ ቀደም ባለሥልጣኑ ይታወቅበት የነበረው ብልሹ አሠራር ለምን አልቀጠለም ከሚል መነሻ ነው። ጥቅሙ የተነካበት አካል አዲስ ዘመን ጋዜጣን ተገን አድርጎ የመጣ ሲሆን፤ ለምን ቁጥጥር ጠበቀ እና ማጭበርበር ለምን ተከለከለ በሚል መነሻ ነው። አሁንም እያጭበረበሩ ሲነግዱ የነበሩ ተቋማት ከባለሥልጣኑ ጋር ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም ከሥርዓቱ ውጪ ይሆናሉ። ለእዚህም ከሥርዓቱ ውጪ የሆኑት 85 ተቋማት ምስክር ናቸው። በትክክል መመሪያውን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ተቋማትም በተመሳሳይ ሥርዓት ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል።
ባለሥልጣኑ ይህን እያደረገ ባለበት ሁኔታ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣው ዘገባ ተገልጋዮች አሰሙ የተባለው ሮሮ ትክክለኛ ያልሆነና ባለሥልጣኑን የማይመለከት ነው። ተገልጋዮች ከትምህርት ተቋማታቸው ጋር ባላቸው የተበላሸ ግንኙነት ምክንያት ባለሥልጣኑ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ባለሥልጣኑ በየጊዜው ከመመሪያ ውጪ የሚሠሩ የትምህርት ተቋማትን ይፋ ያደርጋል። ስለሆነም ተማሪዎችም ፈቃድ ያለውና ትክክለኛ የሆነ ተቋም መርጠው የመማር ኃላፊነት አለባቸው። ባለሥልጣኑ በዋናነት የትውልድና የሀገር ጉዳይ በሆነው የትምህርት ጥራት ላይ እየሠራ ባለው ሥራ አሻራውን ጥሎ የማለፍ ዓላማን ያነገበ እንጂ የትምህርት ተቋማትንና ተገልጋዮችን የማጉላላት ዓላማ የሌለው መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ባለሥልጣኑ ትምህርትን ለሸቀጥ ሳይሆን ትውልድን መገንቢያ ለማድረግ በሚል እያከናወነ ያለው ጥረት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቢንያም፦ ከእዚህ ቀደም በነበረው አመራር የትምህርት ጥራት ላይ እየሠራሁ ነው ፎርጂድን እያጋለጥኩ ነው ብሎ እየተናገረም ከ165 በላይ አዳዲስ ኮሌጆችን ፈጥሯል። ኮሌጆቹም መሠረታዊ የተባሉ መስፈርቶችን ሳያሟሉ የኮሌጅነት ዕውቅናን አግኝተዋል። የትምህርት ሥራ የተረጋጋ ከባቢን የሚፈልግ ሰፊ የማንበብና የማሰላሰያ ጊዜን የሚጠይቅ ሥራ ነው። ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ፈቃድ ሲታደል ኖሯል። ስለሆነም አሁን ላይ ግን ባለሥልጣኑ የተበተነውን ፈቃድ እየሰበሰበ ይገኛል። የትምህርት ተቋማት ላይ በሚያደርገው ጥብቅ ቁጥጥርም ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጥራት ላይ መሠረት አድርገው እንዲሠሩ እያደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም አዲስ መስፈርት በማውጣት ትንሹን መስፈርት ማሟላት የቻሉ ተቋማት ብቻ እንዲቀጥሉ ተደርጓል። ዳግም ምዝገባ ተብሎ እየተሠራ ያለውም በእዚሁ ምክንያት ነው። በዳግም ምዝገባ አንዳንድ ሁኔታዎችን ታሳቢ ማድረግ ባይቻል ኖሮ በርካታ ተቋማት ከሥራ ውጪ ይሆኑ ነበር።
ሀገር የሚሠራው ለትውልድ እንደመሆኑ ባለሥልጣኑ ለመጪው ትውልድ አስቦ እየሠራ ነው። ምክንያቱም ዛሬ እኛ እየከፈልን ያለነውን ዋጋ የነገው ትውልድ እንዳይገጥመው ታሳቢ ይደረጋል። ለእዚህም የግል ትምህርት ዘርፍን የሚቀላቀል ሰው ውስጣዊ በሆነ ፍላጎት እንዲገባ፤ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በዘፈቀደ የሚከፈት ፕሮግራም እንዳይኖር፤ አዋጭና አስፈላጊነቱ በተረጋገጠበት ፕሮግራም ብቻ ተቋማት እንዲከፈቱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ለእዚህም ነው ከ375 ተቋማት 85 ተቋማት መስፈርቱን ማለፍ ሳይችሉ የቀሩት። በቀጣይም ከቀሩት 290 ያህል ተቋማት ውስጥ አብዛኞቹ ይቀነሳሉ።
ባለሥልጣኑ ትምህርት ‹‹እንደማንኛውም ንግድ ሠርቼ አተርፍበታለሁ›› የሚል አካልን ሳይሆን ለትውልድ አስቦ ውስጣዊ በሆነ ፍላጎት የሚሠራና መጠነኛ ትርፍ ለማትረፍ የሚሠሩ ዜጎችና ባለሀብቶች እንዲሠማሩበት ይፈልጋል። ትምህርት እንደሌላው የንግድ ሥርዓት ትርፍ ማጋበስ የሚቻልበት ዘርፍ ነው ብሎ የገባ ካለ ተሳስቷል። አሁን ላይ ይህ አሠራር የለም። ለእዚህም ለትውልድ ግንባታ ባለሥልጣኑ ከፍተኛ ትግል እያደረገ ነው። ነገር ግን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሲጠቀም የነበረና ጥቅሙ የተነካበት አካል ቢኖርም፤ ባለሥልጣኑ ግን ለሀገርና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ እየሠራ እየታገለ እንደሆነ አረጋግጣለሁ።
አዲስ ዘመን፦ መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተሠሩ ሥራዎች፤
አቶ ቢንያም፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ ፈቃድና እድሳትን በተመለከተ በ74 ተቋምና በ83 ካምፓሶች ላይ የክትትል ሥራ ተሠርቷል። ከእነዚህ መካከልም የሥነ-ሥርዓት ጥሰት የተገኘባቸው ተቋማት ተለይተዋል። እነሱም 47 ተቋማትና 58 ካምፓሶች ከማስጠንቀቂያ ፕሮግራም እስከ መዝጋት የሚደርስ ርምጃ ተወስዶባቸዋል። እነዚህም በባለሥልጣኑ ክትትል የተሠሩ ጥቅል ሥራዎች ናቸው።
ሌላው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የተመረቁ ተማሪዎች ቁጥር ከየካምፓሱ ይመጣል። ይህም ቁጥጥር ክፍል ይገባል። የ2015፣ 2016 እና 2017 ዓ.ም ተመራቂዎችን አዘግይተው ያስገቡና አውተንቲኬት ይደረግላቸው የእኔ ምሩቆች ናቸው የሚሉና አጠቃላይ ክትትል የተደረገባቸው 40 ተቋማት 54 ካምፓሶችና 139 ፕሮግራሞች ናቸው። በእነዚህ ላይ በተደረገው የማጣራት ሥራም አብዛኞቹ ችግር ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል። ችግር በተገኘባቸው 57 ተቋማትና 89 ካምፓሶች ላይም ባለሥልጣኑ የቅጣት በትሩን አሳርፏል።
ባለሥልጣኑ የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መንገድ እየሠራ ሲሆን፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 97 ሺ 565 አዳዲስ የመጡ የተማሪዎችን ዳታ አጣርቶ ወደ ዳታ ቤዝ አስገብቷል። እነዚህ ተማሪዎችም አውተንቲኬት ለማድረግ አንድ ደረጃ ያለፉ ሲሆን፤ በቀጣይም ከዲፕሎማ ጀምሮ ሲኦሲና ሌሎችን መረጃዎችን ጭምር የማጣራት እጅግ ፈታኝ የሆነ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ሕጋዊ መሰል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተቋም ቀመስ ሆኖ መምጣቱ ትልቁ ፈተና ነው።
አዲስ ዘመን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ሥራው እንዴት እየተከናወነ ነው?
አቶ ቢንያም፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከለውጡ ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው። እርግጥ ነው የመጣንበት መንገድ የተበላሸ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። አሁን ላይ ግን መጪው ትውልድ ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሠራ ነው። ለእዚህም ከተቋሙ ከራሱ ጀምሮ እውነትም የጥራት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ነው ወይ የሚለውን ለመመለስ የሪፎርም ሥራ እየተሠራ ነው። ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ወደ ሪፎርም ከገቡ ስምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንዱ በመሆኑ ለሪፎርሙ የሚመጥን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በዋናነት ባለሥልጣኑ የጥራት ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ ራሱ ተመዝኖ ዕውቅና ማግኘት ይኖርበታል። ሌላው ከታች ጀምሮ ባሉ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ የአጠቃላይ ኢንስፔክሽን መመሪያዎች፣ ደንቦችን መስፈርትና ደረጃዎች እያዘጋጁ ናቸው።
በመሆኑም ከእዚህ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴርና ከየክልሉ ትምህርት ቢሮ የሚመጡ ሪፖርቶች በትክክል መስፈርቱን ያሟሉ መሆን አለመሆናቸው ይጣራል። እንዲሁም ዜጎቹ ምን ደረጃ ላይ ናቸው የሚለውን በተግባር አጣርቶ ክፍተቶችን የሚሞላ ተቋም እንዲሆን በከፍተኛ ጥረት ይሠራል። ከግልና ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንጻር ደረጃ ተዘጋጅቷል። በቀጣይም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር በመስፈርቱ እንዲያልፉ ይደረጋል። በመሆኑም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ዝቅተኛውን መስፈርት ማለፍ ካልቻሉ ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነን በማለት መቀጠል አይችሉም። በአጠቃላይ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ዕውቅና እስከ መስጠት ባለው የአሠራር ሂደቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ የበቃና የነቃ ዜጋ ለመፍጠር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ባለሥልጣኑ ከሚፈተንበት አንዱ አጣብቂኝ ብዙ ፍላጎቶች ያሉበት እንደሆነ ተጠቅሷል፤ ይህን ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ቢንያም፦ ባለሥልጣኑ ኤጀንሲ በነበረበት ጊዜ ብዙ ጥቅሞች ይሯሯጥበት የነበረ በመሆኑ በርካታ ያደሩ ሥራዎች አሉበት። ከእዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶችን ጨምሮ ማኅበራቶቹ የቦርድ አባላት በመሆናቸው የሚቆጣጠራቸውን ተቋም እንደፈለጉ ይመሩት ነበር። ይህም ማለት ‹‹ማማሰያው በእጃቸው ነበር›› በመሆኑም የሚቆጣጠራቸውን ተቋም ያምሱት ነበር። አሁን ላይ ግን ያን ማማሰያ ተነጥቀዋል። ማማሰያው በእጃቸው በነበረበት ወቅት ፈቃድ እንደፈለጉ ወስደዋል፤ አድሰዋል፤ የትምህርት ማስረጃዎችን አውተንቲኬት አስደርገዋል።
አሁን ግን ሥራው ከእነዚህ ባለሀብቶች እጅ ወጥቶ መንግሥት እጅ ገብቷል። ተቋምና የግል ባለሀብቶቹ ያላቸው ግንኙነት በልክ እንዲሆን አሠራር ተበጅቶለታል። ይህ ሲሆን ታድያ ጥቅሙ የተነካ ኃይል አለ። ይህ ኃይልም ማስተርስና ዲግሪን እንደ ዘይትና ሽንኩርት እየቸበቸበ ከፍተኛ ገቢ ሲያገኝ የነበረ ኃይል ነው። ይህ ኃይል ባለው አቅም ሁሉ ባለሥልጣኑን ለማጠልሸትና በዘርፉ እየመጣ ያለውን ለውጥ በማደናቀፍ የተነጠቀውን ማማሰያ ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል። አሁን ላይ ግን ይህ ሊሆን አይችልም። ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረገው ጥረትም ‹‹ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ለመላላጥ›› እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር ወደ ኋላ የሚመለስ ነገር የለም።
ምንጊዜም ቢሆን ለውጥ ሲመጣ ጥቅሙ የሚነካ አካል አለ። ይህን ደግሞ ዘመናዊ፣ ግልጽና ቀልጣፋ በሆነ አሠራር አከርካሪውን መስበር ያስፈልጋል። ይህን ስንል ታድያ ባለሥልጣኑ ፍጹም ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የጸዳ እጹብ ድንቅ ነው እያልን አይደለም። ምክንያቱም ለዓመታት የተከማቹ ሥራዎች ያሉበትና የገነገነ ኔትዎርክ የተዘረጋበት ተቋም ነውና። ይሁንና ባለሥልጣኑ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አሠራሩን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ ለመሆኑ መቶ በመቶ እምነት አለኝ። እንደ ከእዚህ ቀደሙ ሁሉ ማንም ሰው በፍጥነት መጥቶ የተጭበረበረ መረጃ ይዞ አይሄድም። አጭበርባሪ ከሆነ ይንገላታል። የሚንገላታውም በራሱ ችግር እንጂ በባለሥልጣኑ አሠራር አይደለም። ባለሥልጣኑ ሕገወጥ ማስረጃን ሕጋዊ ለማድረግ ከሚደረግ ግብግብ ጋር ተናንቆ ዘርፉን ከተዘፈቀበት ብልሹ አሠራር ለማውጣት ትግል እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ባለሥልጣኑ ከተሸከመው ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ አንጻር እያጋጠሙት ያሉ ችግሮች እንደምን ያሉ ናቸው?
አቶ ቢንያም፦ ባለሥልጣኑ ምንም እንኳን በቦርድ የሚተዳደር ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በራሱ በጀት የሚንቀሳቀስ አይደለም። በመሆኑም ባለሥልጣኑ ከሚሰጠው አገልግሎትና ለጥቅም ተጋላጭ ከመሆኑ አንጻር ባለሙያው በቂ የሆነ ደመወዝ የለውም። ሠራተኛው ለጥቅም ተጋላጭ እንዳይሆን በበቂ ደመወዝ ምቾቱ ተጠብቆ መሥራት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ የለም። የሠራተኛው ቁጥርም ባለሥልጣኑ ከሚፈልገው የሰው ኃይል በታች ነው። ተደጋጋሚ ዝውውር ቢወጣም ፈልጎ የሚመጣ ሠራተኛ የለም። ሌላው የሚሰጠው በጀት ባለሥልጣኑን የሚመጥን በጀት አይደለም። ብቃት ያለውን ባለሙያም በዘርፉ ማግኘት አለመቻልም ሌላኛው የዘርፉ ማነቆ ነው። በአጠቃላይ ከሰው ኃይል፣ ከብቃት፣ ከበጀትና ከቴክኖሎጂ አንጻር ባለሥልጣኑ ከፍተኛ ችግር አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ቢንያም፦ እኔም አመሰግናለሁ!
በፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም