ኢትዮጵያ ዘመናዊ ተግዳሮቶች የሚሻገር የሰው ኃይል ለማፍራት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ የትምህርትና ስልጠና ሥርዓት በመዘርጋት ዘመናዊ ተግዳሮቶች የሚሻገርና ለሁለተናዊ ልማት የሚተጋ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራች ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል “ኢራስመስ ፕላስ 2025” ፕሮግራም የተሰኘ በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር መድረክ ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒስቨርሲቲ ሲካሄድ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲዋን በማዘመን ወደፊት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እየፈታና እየተሻገረ የሚሄድ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሠራች ነው፡፡ በእዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲዋን በማዘመን ዘመናዊ ተግዳሮቶችን የሚሻገር የሰው ኃይሏ እያዘጋጀች ትገኛለች ብለዋል።

ለሀገር እድገት ዘመኑን የዋጀ የትምህርት ሥርዓት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዘመኑን የዋጀ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ዘመን አመጣሽ ለውጦችን ለመቋቋም፣ ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና የአየር ንብረት ችግርን ለመከላከል የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል ቁርጠኝነቷን ማሳየቷን ጠቁመው፤ የሕዳሴ ግድብ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፣ ምርቶችን መልሶ የመጠቀም እንቅስቃሴ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነው የተናገሩት፡፡

የክህሎት መርሃ ግብሮችን በመንደፍና በመተግበር ረገድ ልምድ ካላቸው የአውሮፓ ተቋማት መማር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት የሚያመጣውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ፈተናዎቹን ለመቋቋም የትምህርትና ሥልጠና አሰጣጥ ጥራትን፣ ተደራሽነትን እና ቅልጥፍናን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ መሥራት ዘላቂ፣ የሰለጠነ እና ሁሉን ያካተተ የሰው ኃይል ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓለም ከእዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ህይወት መጥፋት እና የሀብት መመናመን የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል ብለዋል።

ሆኖም እነዚህን ተግዳሮቶች በትምህርት መከላከል ይቻላል። ትምህርት ለግል እድገት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብ አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ያሉት ኤባ (ዶ/ር)፤ መምህራን ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከትምህርት ጋር በማዋሃድ አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ለተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

በእዚህም “ከኢራስመስ ፕላስ” ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለመምህራን ሥልጠና ለተማሪዎች ደግሞ ነፃ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል መመቻቸቱን ገልጸው፤ በእዚህም እ.እ.አ ከ2021 ጀምሮ 600 ኢትዮጵያውያን የእዚህ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You