
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ” የተሰኘ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን በተለያዩ አራት ከተሞች ያካሂዳል። የዚህ ውድድር የመጀመሪያ መዳረሻ ከተማ የሆነችው ሀዋሳ ባለፈው የካቲት የግማሽ ማራቶን ፉክክር አስተናግዳለች። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ጅማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለተኛዋ የውድድሩ መዳረሻ በመሆን በተለያዩ ርቀቶች ውድድሮችን ማስተናገዷ ይታወቃል። ሦስተኛ የውድድር ከተማ “የሯጮች ምድር” የተሰኘችውና በርካታ ወርቃማ ኦሊምፒያንን ያፈራችው ቦቆጂ ሆናለች። “ታላቁ ቦቆጂ ሩጫ” የፊታችን እሁድ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ እንደሚከናወን በቱሪዝም ሚኒስቴር ሰሞኑን በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል።
የአትሌቶቹ ምድር በምታስተናግደው የጎዳና ላይ ሩጫ በአትሌቶች እና የጤና ሯጮች መካከል የ12 ኪሎ ሜትር ውድድር ፣ የ16 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር እና የሕፃናት የሩጫ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ የሚሄዱ ተሳታፊዎች ምዝገባው እስካለፈው እሁድ ግንቦት 10/2017 ዓ.ም ተከናውኗል። ከጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሩ በተጨማሪ በአርሲ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የሚደረግ የእግር ጉዞ እና የካምፒንግ ፕሮግራምን ያካተተ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በአትሌቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር በርካታ ጠንካራ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ውድድሩ ጠንካራና ተተኪ አትሌቶችንም እያፈራ ይገኛል። ዘንድሮም በርካታ ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አምና የውድድሩ አሸናፊ የነበረችውና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የ10ሺ ሜትርን ማሸነፍ የቻለችው አትሌት ትዕግስት ደጀኔ ዘንድሮም ቦቆጂ ላይ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ለማሸነፍ እንደምትሮጥ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ እንደገና አበበ ባደረጉት ንግግር፣ “ቦቆጂን በአትሌቶቿ እና በአሰልጣኞቿ እናውቃታለን፤ አትሌቶቿ ያሳወቋትን ያህል አስተዋውቀን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ግን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፣ ህልማችንም ይኸው ነው” በማለት በቆጂ ላይ ቱሪዝም ሚኒስቴር ለከተማዋ ዕድገት ያሰበውን ሥራ ይፋ አድርገዋል። በአጠቃላይ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እና ለማሳደግም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው፣ “ስፖርት ባሕል እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከስፖርት ቱሪዝም ብዙ ተጠቃሚ መሆን አለባት ፤ ለዚህም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። ከዚህም በፊት የነበሩትን ውድድሮች በተለይም በቅርቡ ጅማ ላይ የተካሄደው ውድድር ጥሩ ማሳያም ነው። ቱሪዝም ሚኒስትር እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም ለዚህ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ከዚህም በመቀጠል በጋራ ይህን ለማጠናከር የምንሠራ ይሆናል” ብለዋል፡፡
የቦቆጂ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በዙ አበበ፣ “ከተማችን በካርታ ላይ ትንሽ ግን በጣም ዝነኛ ከተማ ናት ፤ ባፈራናቸው አትሌቶች ልክ ከተማችን ባታድግም ለዚህ ዓመታዊ ውድድር ልዩ ዝግጅታችንን አጠናቀናል” በማለት በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ቦቆጂ ከተማ ምክትል ከንቲባው ልዩ ባንዲራና ቲሸርት ከሁለቱ ሚንስትር ዴኤታዎች እጅ ተረክበዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የዚህ ልወቅሽ ኢትዮጵያ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ጠቀሜታ አጠር ባለ ጥናት የጅማን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ በመውሰድ የቀረበ ሲሆን፣ በዝርዝሩም የኢኮኖሚ፣ የቱሪዝም ፍሰት እና የስፖርታዊ ግንኙነት ጥቅም ተዳሷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም