
ኢትዮጵያ የብዙ ስመ ጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ታሪክ ይነግረናል።
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው፡፡
በሀገር ውስጥም ደምቀው የሚታዩ እና ሥራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም በየዘርፉ ይገኛሉ። ዛሬም ባለውለታነታቸውን ለመዘከር የተነሳነው ዕውቁ የባንክ እና የፋይናንሰ ሰው አቶ ለይኩን ብርሃኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ናቸው።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ ገምታ ከአባታቸው ከአቶ ብርሃኑ ገምታ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጉደቱ አንበቻ ሰኔ 4 ቀን 1937 ዓ.ም በቀድሞ ወለጋ ክፍለ ሀገር በጊምቢ አውራጃ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በጊምቢ ደጃዝማች ገ/እግዚአብሔር አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞ አጠራር ነቀምቴ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
ከዚያም በመቀጠል የከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀድሞ አጠራር ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሐምሌ ወር 1961 ዓ.ም. በከፍተኛ ውጤት አጠናቀው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። አቶ ለይኩን ብርሃኑ በሕይወት ዘመናቸው በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ለ47 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን አገልግለዋል።
ከጥር 1968 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1971 ዓ.ም. የቀድሞ የአዲስ ባንክ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከጥቅምት 1971 ዓ.ም. እስከ 1972 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው እድገት ላደረጉት በጐ ተጽእኖ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማኔጅመንት ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በስማቸው “ለይኩን ብርሃኑ” ቅርንጫፍ ከፍቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ ከጥቅምት 1972 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1975 ዓ.ም. የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመጋቢት 1978 ዓ.ም. እስከ መስከረም 1981 ዓ.ም. የትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ዋና ኃላፊ እንዲሁም ከጥቅምት 1982 እስከ ጥቅምት 1984 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በ1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተከተለችውን የኢኮኖሚክ ሪፎርም ፕሮግራም በማስተግበር ከኅዳር 1984 ዓ.ም. እስከ መስከረም 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን በአስተባባሪነትና በአስፈጻሚነት ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል።
በተለይም በደርግ ዘመነ መንግሥት ለ17 ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ዝግ አድርጎት የቆየውን የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ክፍት ለማድረግ አዳዲስ ባንኮችና ኢንሹራንሶች እንዲቋቋሙ የባንክና ኢንሹራንስ ሥራ ፈቃድ አዋጆችን በማውጣት በአሁኑ ጊዜ 30 የግል ባንኮች እና 17 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ መንገድ የከፈቱና የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ባለራዕይና አስተዋይ መሪ ነበሩ።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በነበሩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ተቆልሎ የነበረው የውጭ ዕዳ ጫና በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ፣ እንዲሁም አብዛኛው ደግሞ እንዲሰረዝ ከአበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመደራደር አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ ጠንካራ መሪ ነበሩ፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በመጨረሻው የሥራ ዘመናቸው ከመጋቢት 1988 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 2003 ዓ.ም. የአዋሽ ባንክ አክሲዮን ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ባንኩን ከ14 ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ባንኩን እንደ ልጃቸው በመመልከት ሙሉ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይቆጥቡ ባንኩ ዛሬ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ ጠንካራ መሠረት የጣሉና የራሳቸውን ዐሻራ ያኖሩ የባንኩ ባለውለታና ታላቅ ሰው ናቸው። በአሁኑ ጊዜ አዋሽ ባንክ እና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በጋራ ያስገነቡትን የዋና መ/ቤት ሕንፃ በማስጨረስና ለአገልግሎት በማብቃት በግል ባንኮችና ኢንሹራንሶች ዘንድ ፈር ቀዳጅ እና ታሪካዊ የሆነ ሥራ ሠርተዋል፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በሙያቸው እና በእውቀታቸው ሙያዊ ምክርና አመራር በመስጠት የተለያዩ ድርጅቶችንና ማህበራትን አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር መሥራችና ሊቀ መንበር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ብሔራዊ ኮሚቴ አባል፣ የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል፣ የ“PSS” መሥራች አባል በመሆን በተለያዩ ጊዜያቶች አገልግለዋል፡፡
አቶ ለይኩን ዕድሜያቸው ለጡረታ ደርሶ በጡረታ ከተገለሉ በኋላም ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ልምዳቸውን እና የሕይወት ተሞክሯቸውን ለሌሎች በማጋራት ሀገራቸውን በታማኝነት በማገልገል ለሌሎች መልካም አርአያ የሆኑ የሀገር ባለውለታ ነበሩ። አቶ ለይኩን ብርሃኑ በተፈጥሯቸው ሩቅ አሳቢ፣ በአቋም ጽናታቸው የሚታወቁ፣ ሥራ ወዳድ እና ጉምቱ የባንክ ባለሙያ ነበሩ፡፡
አቶ ለይኩን በሥራ ዘመናቸው ባንኮች ዘመናዊ አሠራርን የተላበሱ እንዲሆኑ በብዙ ለፍተዋል። ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፤ ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና የማይተካ ሚና ይጫወታል። በተለይም በአሁኑ ጊዜ የባንኮች የአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የኢኮኖሚ ዝውውሩ በቀጥታ የተያዘው ቴክኖሎጂው ጋር በመሆኑ እድገታቸውም ሆነ ውድቀታቸው ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ልክ የሚለካ ነው። ከዚህ አንጻር የእኛም ሀገር ባንኮች በጊዜ እንዲነቁ የአቶ ለይኩን አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከቴክኖሎጂ በሻገር የፋይናንስ ተደራሽነቱም በታላላቅ ከተሞች ላይ ብቻ ታጥሮ የቆየውን አገልግሎት ወደ ገጠር ከተሞችም በማዳረስ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ በባንክ ዘርፍ ውስጥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡት አቶ ለይኩን ከአንድ እንግሊዛዊ እና ከአምስት አሜሪካውያን ቀጥሎ ከመጡት ኢትዮጵያውያን የባንክ ገዢዎች ስድስተኛ ሆነው የሠሩ ጉምቱ ባለሙያ ናቸው። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደ ባንክ ሥራ ከገቡ እና በሰለጠኑበት ሙያም ሀገራቸውን ከአገለገሉ ጥቂት ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡
የባንክ ዘርፍ ሁልጊዜ በአዳዲስ አሠራሮች እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መታገዝ አለበት። ይህንን የሚረዳ እና ራሱንም ከወቅቱ አስማምቶ የሚመራ መሪ ደግሞ ሁልጊዜም አሸናፊ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህንን ማድረግ ከቻሉ ጥቂት አመራሮች መካከል ደግሞ አቶ ለይኩን ብርሃኑ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
አቶ ለይኩን ዘመናዊ አሠራር እና ቴክኖሎጂ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ዋና ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረጋቸውም ባሻገር በደርግ ወቅት ለውድድር ዝግ ሆኖ የቆየውን ዘርፍ ለግል ሴክተሩ ክፍት እንዲሆን ሙያዊ አስተዋጽኦቸውን ያበረከቱ ሰው ናቸው። የባንክ ኢንዱስትሪውም ሆነ ሌሎች ዘርፎች ለግል ባለሀብቱ ክፍት እንዲሆኑ እና የግል ሴክተሩም የራሱን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለሀገር እንዲያበረክት በመንግሥት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ከዳር በማድረስ አንድ ለእናቱ የነበረውን ንግድ ባንክ ዛሬ 31 የተለያዩ ባንኮች አገልግሎት እንዲሰጡ ፈር ቀዳጁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን በመቆጣጠር እና በመደገፍ ሚናውን እንዲወጣ እና ባንኮች ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በመደገፍ ጭምር አቶ ለይኩን ያልነጠፈ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርንጫፍ ብዛት፤ በሚሰጠው አገልግሎት ዓይነት እና የደንበኞችን ርካታ በማረጋገጥ ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲገኝ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዘመናት ያዳበረውን ልምድም አዲስ ለሚቋቋሙ ባንኮች በማካፈል ስሙ የሚነሳ ሲሆን ከዚሁ ጋር የአቶ ለይኩን አስተዋጽኦም የሚዘነጋ አይደለም። በግል ባንክ ዘርፍም የአዋሽ ባንክን ተወዳዳሪ እና ተደራሽ በማድረግ ረገድም ዐሻራቸውን ያሳረፉ ባለሙያ ናቸው፡፡
ሆኖም ለሀገራቸውን ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ሲያደርጉ የኖሩት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። አቶ ለይኩን ብርሃኑ ከወ/ሮ ስሉስ አስፋው ኃይሌ ጋር ሚያዝያ 1960 ዓ.ም. የተጋቡ ሲሆን ሦስት ወንድ ልጆች እና ስድስት ሴት ልጆች ወልደዋል። እንዲሁም የአስራ ሰባት የልጅ ልጆች አያት መሆን የቻሉ ሲሆን፣ የአንድ የልጅ ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሠማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የባንክ እና የፋይናንስ የሀገር ባለውለታ አቶ ለይኩን ብርሃኑ ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም!
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም