
አዲስ አበባ፡– ከውጭ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ። የንቦች ቀን እየተከበረ ሲሆን፤ በእዚህም በጅማ ዞን ማና ወረዳ የዘመናዊ ቀፎ የማር ክላስተር ተጎብኝቷል።
አቶ አደም በጉብኝቱ ወቅት እንዳመለከቱት፤ ግብርናውን አጠናክረን ከውጭ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ ነው።በግብርናው ዘርፍ ብዛት እና ጥራት ያለውን ምርት ይበልጥ በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ መልክዓ ምድሯ እና የአየር ጸባይዋ ለማር ምርት የተመቸ በመሆኑ ማርን በብዛትና በጥራት በማምረት ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሥራ መጠናከር ያለበት ነው ያሉት አቶ አደም፤የማር ምርትን በጥራት አዘጋጅቶ ወደ ውጭ የመላክና የገበያ ትስስር መፍጠር ለሀገር ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆኑ በእዚህ በኩል ጥሩ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሌማት ትሩፋት አንዱና ዋነኛው ዓላማ የተሟላ የአመጋገብ ሥርዓት ማምጣት ሲሆን፤ በቀላሉ በጓሮ በሚለሙ የምግብ ዓይነቶች በመተግበር በማር፣ በወተት፣ በዶሮ ማርባት እና በእንቁላል እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
ከማር ምርት በተጨማሪ በመስኖ ስንዴ ምርት፣ በሩዝ እና በፍራፍሬ ልማት የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ የግብርና ልማትን የሚያበረታታ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ አካላት ለግብርናው ምርታማነት በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ዳይሬክተር ጀነራል አበበ ኃይለገብርኤል በበኩላቸው፤ የንቦች ቀን መከበሩ ለንቦች እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ያደርጋል ነው ያሉት።
ንቦች የማር ምርት ከመስጠት ያለፈ ሚና ያላቸው በመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለደን እንክብካቤና ለአረንጓዴ ልማት መነቃቃት ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጅማ ዞን ማና ወረዳ በተደረገው ጉብኝትም የተመለከቱት የዘመናዊ ቀፎ የማር ልማት የሚበረታታ እና መስፋት ያለበት ተሞክሮ ሆኖ እንዳገኙት ጠቅሰዋል።
በጉብኝቱ ከዘመናዊ ቀፎ የማር ምርት በተጨማሪ የአቮካዶና የሙዝ ተክሎች ልማትም የተጎበኙ ሲሆን፤ የአካባቢው አስተዳደርና የዘርፉ ባለሙያዎችም ተገኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም