እስማኤል አረቦ
‹‹ሀብታም መንግስተ ሰማያትን ከሚወርስ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል›› የሚለውን ሃይማኖታዊ ጥቅስ በሰማሁ ቁጥር የእኛ ሀገር ስግብግብ ነጋዴዎች ትዝ ይሉኛል።
መቀማትን እንጂ መስጠትን የማያውቁ፤ዋጋ መጨመርን እንጂ መቀነስን ያልተማሩ፤ መንጠቅ እንጂ መለገስ ያልፈጠረባቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ዛሬም በህዝቡ ውስጥ መከራ እየዘሩ የራሳቸውን ኪስ በማደለብ ላይ ይገኛሉ።
በእነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች አልጠግብ ባይነት የተነሳ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል።እናት ልጆቿን ሻይ አፍልታና ዳቦ ገዝታ ትምህርት ቤት መላክ ተስኗታል።ህጻናት በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት ለመሄድ ተገደዋል።አረጋዊያን ጡረታቸው ሰባራ ዕቃ አልገዛ ብሏቸው ለልመና ጎዳና ለመውጣት ተገደዋል።
ስግብግብ ነጋዴዎች አየሩን እያዩ በሚዘውሩት ገበያ ጧት የነበረው ዋጋ አመሻሽ ላይ ጨምሮ ይገኛል፤ለወር ያሉት ለሳምንት አልበቃ ብሏል።የድሃው ጓዳ ተራቁቷል፤ኑሮ ምርጊት ሆኖበታል።
እነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ከድሃው የሚወስዱት ብዙ ነው፤ ለድሀው የሚሰጡት ግን ምንም የላቸውም። መውሰድ እንጂ መስጠትን አያውቁም።መቀማትን እንጂ መቸርን አልተማሩም ፤መዝረፍን እንጂ መመጽወትን አልታደሉም።በህዝብ ችግር ላይ ማትረፍን እንጂ ለህዝብ አለሁልህ ማለትን ሲያልፍም አይነካካቸውም።
የሰሞኑም የዘይት ድብብቆሽ ድራማም ያሳየን ይህንኑ ሃቅ ነው።ህዝቡ የዘይት ያለህ በሚልበት በዚህ ወቅት ሁለት ሚሊዮን ሊትር ዘይት ደብቆ በህዝብ ሬሳ ላይ ህንጻ ለመስራት ከማሰብ የበለጠ ቁማር ከወዴት ይገኝ ይሆናል።የጉድ ሀገር ነውና ይህ ሰው መቼም ነጋዴ ነኝ ማለቱ የሚቀር አይመስለኝም።
ነጋዴ የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው።ህዝብ ገንዘብ ሲያገኝ ፤በልቶ ማደርና ለዕለት ጉርሱ መትረፍ ሲችል ነው ነጋዴ አትርፎ መግባት የሚችለው።ይህን ያልተረዱት የእኛዎቹ ስግብግብ ነጋዴዎች ዕለት በእለት በሚሰቅሉት ዋጋ ህዝቡ ጓዳው እንዲራቆት የሚለብሰው ቀርቶ የሚበላውም እንዲያጣ እያደረጉት ነው።
ይህ ደግሞ ነገ ከነገወዲያ ህዝብ በኑሮ ውድነቱ እንዲማረርና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ማድረጉ ስለማይቀር ዞሮ ዞሮ ነገ እበለዋለሁ ፤ ህንጻ እሰራበታለሁ፤ ዱባይና ለንደን ሄጄ እዝናናበታለሁ ተብሎ የተከዘነው ገንዘብ በተማረረው ህዝብ ዶጋ አመድ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ማሰቡ ብልህነት ይመስለኛል።
የእኛ ሀገር አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምንም አይነት ሰብዓዊነት የፈጠረባቸው አይመስለኝ።አብዛኛው ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ በልቶ በማያድርበት ሀገር፤ከዛሬ ተርፎ ለነገ ጥሪት በማይቋጠርበት ድሃ ህብረተሰብ ላይ ፤ተፈጥሮ የሚጠይቀውን ርሃብና ጥም ለማስታገስ ጎዳና ላይ በልመና የሚተዳደረውን ህዝብ አልፎም ኑሮ አንገሽግሾት በየበርሃውና በየውቅያኖሱ እግሬ አውጪኝ የሚል ድሃ ህዝብ ባለበት ሀገር በህንጻ ላይ ህንጻ ለመጨመር ድሃውን በኑሮ ማንገላታቱ የግፍ ግፍ ነው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በመሬትም በሰማይም ማስጠየቁ አይቀርም።
በሌላው ሀገር እኮ ያላቸው ሰዎች መታያ እና መገለጫ ሃብትን አፍስሶ ድሃዎችን መርዳት እንጂ በድሃው ሞት ላይ ማትረፍ አይደለም።ድሃው ያለበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎች ማቃለል እንጂ ለድሃው እንደገና ጫናና መከራ መሆን አይደለም።መብላት ያቃታቸውን ህጻናት በመደገፍ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ማድረግ እንጂ ከድሃው ልጆች ጉሮሮ ቀምቶ የራስን ልጅ አውሮፓና አሜሪካ ማስተማር አይደለም።እስከመቼ በባዶ ሆድ ላይ ይተረፋል።በረሀብ ላይ ይቀለዳል።
በኢትዮጵያውያን እናቶች ላይ ማትረፍ እኮ ከግፍም ግፍ ነው።አንዲት ኢትዮጵያዊ እናት ልጆቿን ትምህርት ቤት ለመላክ የማታየው መከራ የለም።ጉሊት ውላና በጸሃይ ተቃጥላ፣እንጨት ለቅማ፣ሰው ቤት ልብስ አጥባ፣የጉልበት ስራ ሰርታ፣ ባሬላ ተሸክማ እና መከራዋን በልታ ልጆቿን ትምህርት ቤት የምትልክ ናት።
ይህች መከረኛ እናት አንዱ ሞላ ስትል ሌላው እየጎደለባት ፣ አንዱን ስትጠግን ሌላው እየተሸነቆረባት ፣ አንዱን ስትጠግን ሌላው እያፈሰሰባት እሷ እየሞተች ልጆቿን ሰው ለማድረግ እንቅልፍ አጥታ የምትባዝን ፍጡር ነች።
ይህ ከደላቸው ጥቂት እናቶች በስተቀር የብዙ እናቶች የእለት ተዕለት ህይወት ነው።ሆኖም እነዚህን እናቶች ከመደገፍና መከራቸውን ከመጋራት ይልቅ ጭራሹኑ ስኳርና ዘይት በመደበቅ፣ጤፍና ስንዴን በመከዘን በዚቹ ምስኪን እናት ላይ ዋጋ ለመጨመር የሚደረገው እሩጫ ልብ የሚያሳምም ነው።ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ነው።
ለነገሩ ህሊና ያለው ሰው ነው የሰው ልጅ ችግር በተለይም የኢትዮጵያ እናቶችን ችግር ተመልክቶ ልቡ በርህራሄ ሊነካ የሚችለው።ልቡ በጥቅምና በጭካኔ የታወረ በሬሳ ላይ ሁሉ ለማትረፍ ሲዳዳው አይተናል።ለስግብግብ ነጋዴዎች አይደለም ሸቀጥ ሰው ከነብሱም ቢሆን ዋጋ ካወጣ ከመሸቀል ወደ ኋላ አይሉም።ድሃውን እርቃኑን በማስቀረት ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው እየዞሩ የማይጠረቃ ፍላጎታቸውን ለመሙላት ሲባዝኑ ይታያሉ።
የእኛ ሀገር ስግብግብ ነጋዴዎች ሌላ ሀገር ያላቸው እስኪመስል ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡት ዕቃ እንኳን ለወገን ለጠላትም የሚመረጥ አይደለም።በመናኛ ዕቃ ሀገሪቱን በማጥለቅለቅ ሀገር ውስጥ ከመድረሳቸው በሚያረጁ ቁሳቁሶች እንድንጥለቀለቅ አድርገውናል ።በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከዋጋ መናር በዕቃው መናኛነት የተማረረው ደሃው ሸማች ንግድና ነጋዴነትን ውግዝ ከመአሪዎስ ለማለት ደርሷል።
አንዳንዶቹማ በድሃው ላይ ከማትረፍ አልፈው ከድሃ ደሃው ምጽዋት ይጠይቃሉ።የኢህአዴግ ስርዓት ትቶልን ካለፋቸው ቃላት መካከል የድሃ ድሃ የሚለው አንዱ ነው።ስርዓቱ ብዙሃኑን ድሃ አድርጎ ፤በአምሳሉ የተቀረጹትም ስግብግብ ነጋዴዎች ድሃ የነበርነውን የድሃ ድሃ አድርገውናል።ገሎ እንደሚፎክር ጀግናም ድሃ አድርገውን እንደገናም የድሃ ድሃ ብለው ይጠሩናል።
በእርግጥ ጉዳዩ ሆዳችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳችንም የሞራል ውድቀት ደርሶበት ሃብታሞችን ቀና ብለን እንዳናይ የተዘየደ መላ መሆኑን አሁን ነው የገባኝ።መቼም እኛ ባናያቸው የላይኛው አምላክ ተመልክቶ ስግብግብ ጁንታዎችን የስራቸውን ሰጥቷቸዋል።የስግብግ ነጋዴዎች ቀን ደግሞ መቼ ይሆን ብሎ ለሚጠይቅ ቅርብ ነው። ይሰበስቡታል እንጂ አይበሉትም። ያከማቹታል እንጂ አይደሰቱበትም። ምክንያቱም ደስታ ከደሀ ጉሮሮ በተነጠቀ ገንዘብ አይገኝም።
የእኛዎቹ ስግብግብ ነጋዴዎች አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ባህርያቸው ለየት ይልብኛል።በአይነቱም እንደዚህ አይነት ንግድና ነጋዴም በሌላው ዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም።ንግድ በገበያ ስርዓት ይመራል ሲባል ብንሰማም በእኛ ሀገር በነጋዴዎች መልካም ፍቃድ ይመራል የሚለው የበለጠ ጉዳዩን የሚገልጸው ይመስለኛል።
ሀገሪቱን እየዘወረ ያለው ደላላና ነጋዴውም አይደል ? በእኛ ሀገር ለዋጋ መውጣትም ሆነ ለሸቀጦች መናር በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው አለመጣጣም የሚለው ሳይንሳዊ ቀመር ተረት ተረት ነው።ስግብግብ ነጋዴዎች ተኝተው በተነሱ ቁጥር ዋጋ ከመጨመር የሚያግዳቸው ነገር የለምና።
ነጋዴዎቻችን ዋጋ ለመጨመር ምክንያት አያስፈልጋቸውም።የአሜሪካ ምርጫ ስለደረሰ ዋጋ ይጨምራሉ።ቻይና መንኮራኩር ማምጠቋ ዋጋ ለመጨመር በቂ ምክንያታቸው ነው።ወይንም ደግሞ ህንድ በጎርፍ መጥለቅለቋ ዋጋ ለመጨመር ከበቂ በላይ ነው።እነሱ ከፈለጉ ሸማቹ አመነም አላመነም ለሁሉም ጭማሪ በቂ ምክንያት አላቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ሲቸገርና ሲንከራተት ካዩ ዋጋ ለመጨመር መልካም አጋጣሚ ነው የሚሆንላቸው።‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚለው ዝነኛ አባባልን ‹‹ሰው ላይ ለማትረፍ ሰው ሲቸገር ማየት በቂ ነው›› በሚለው ብሂል በመቀየር ከመከራ ለማትረፍ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም።የወደቀን ማንሳት፣በባስ ለመሄድ አቅም ያጠረውን ሳንቲሞችን መቸር፣ዳቦ ሳይበሉ ትምህርት ቤት የሚሄዱና በርሃብ ምክንያት የሚወድቁ ህጻናትን ከመርዳት ይልቅ በችግሮች ላይ ማትረፍ ቀላሉ መንገዳቸው ነው።ሌላው ቢቀር ታክሲዎች እንኳን ዋጋ የሚጨምሩት ሰው በጸሃይ እየተንቃቃና በዝናብ እየተደበደበ ትራንስፖርት አጥቶ ሲቸገር ሲያዩ ነው።ከመከራ ማትረፍ ከዚህ የበለጠ ምን ማሳያ አለ።
ሌላኛው የእኛዎቹ ነጋዴዎች መገለጫ ደግሞ የሰው ደስታ የሚያማቸው መሆኑ ነው።ህዝቡ የሚደሰትባቸውን በዓላት በመጠበቅ አድብቶ ዋጋ መጨመር የለመደ ነው።የሁዳዴ ጾም ሲፈታ፣የኢድ በዓል ሲደርስ ፣ጋብቻና ልደት ሲኖር ዋጋ እየጨመሩ የህዝቡን ደስታ የሚቀሙ ስግብግብ ነጋዴዎችን ቤት ይቁጠራቸው።በትምህርት ስም በየቦታው እንደአሸን የፈሉትም የግል ትምህርት ቤቶች ከሙያ ይልቅ ንግዱ አዘንብሎባቸው በአመት አመት ዋጋ እየጨመሩ ወላጅን ‹‹ምነው ባልወለድኩ ›› እያስባሉት ይገኛሉ።
ጉደኛ ነጋዴዎቻችን ታሪካቸው ብዙ ነው።አንዱ ሲነካ ሌላኛው ጉዳቸው ይመዘዛል።ይህን ያስባለኝ ደግሞ የዋጋ ንረቱና ጡዘቱ አልበቃችሁ ብሎን ባለችን ሽራፊ ሳንቲም የገዛናትም እንጀራና ዳቦ ወይም ደግሞ ከአመት ቀለባችን ተሟሙተን የገዛናት ማርና ቅቤ ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት ሆኖ መገኘቱ ነው።
ድሃው በዋጋም ተጎድቶ በጥራትም ተማሮ እንዴት ይኮናል።ሰው እንዴት አንዱንም ያጣል።ሆድ ይሉት ባላጋራ ባይኖር ኖሮ መቼ እንደዚህ ስቃይ ውስጥ እንገባ ነበር።አንድ ጊዜ ሰጋቱራ የተቀላቀለ እንጀራ እሱን ስንለምደው ጀሶ የተቀላቀለ እንጀራ፣ እሱም አልበቃ ብሎ አመድና አፈር እየተመገብን ሁሉን በል እንስሳ ከሆንን ሰነባብተናል።ማር ነው በሚል የተፈጨ ብርጭቆ የሚሸጡም ዘመናዊና በፈጠራ የተካኑ ነጋዴዎች የዚህ ዘመን ጉዶች ናቸው።
የድሮዎቹ ነጋዴዎች የዋሆች ናቸው ቢያንስ ሲቀላቅሉ እንኳን ለሰው ጤና የማይጎዳውን በመምረጥ ነው።ሙዝ የተቀላቀለበት ቅቤ ፤ሩዝ የተቀላቀለበት እንጀራ፤ ዱቄት የተቀላቀለበት ማር ወዘተ በማድረግ ሲያታልሉን ኖረዋል።ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ እንዳለው ሰው እኛም የድሮዎቹ በስንት ጣእማቸው እያልን ነው።
ከምግብ ጋር ባዕድ ነገርን ቀላቅሎ መስጠት ካነሳን አንድ ጉዳይ በዚሁ ባነሳና ባልፍ ደስ ይለኛል።በአንድ ወቅት ከእንጀራ ጋር ባእድ ነገር እየቀላቀሉ የሚሸጡ ‹ነጋዴዎችን ›በተመለከተ ለኢትዮጵያ ስነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት (በተለምዶ አጠራር ፓስተር )አንድ ጥያቄ አቅርቤ ነበር።
በተደጋጋሚ ጊዜ ከእንጀራ ጋር ባእድ ነገር እየቀላቀሉ የሚሸጡ ነጋዴዎች ተያዙ ይባላል ነገር ግን አስተማሪ ቅጣት አይወሰድባቸውም፤ ችግሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መጥቷል የሚል ጥያቄ ጉዳዩ ለሚመለከተው ሃላፊ አንስቼ ነበር።ኃላፊውም በእርግጥ በተደጋጋሚ ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን እንይዛለን ሆኖም የጨመሩት ባዕድ ነገር ምን እንደሆነ የሚለይ መሳሪያ የለም።
በአለም ላይ ከኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በስተቀር እንደዚህ አይነት መጥፎ ተግባር የሚፈጽም ነጋዴ ያለው አንድም ሀገር ስለሌ መሳሪያው ትኩረት ተሰጥቶት አልተፈበረከም።
የኢትዮጵያን ሁኔታ ካዩ በኋላ ግን መሳሪያውን ወደ ማምረት ሄደዋል።በቅርቡም በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ መሳሪያ ተመርቶ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል።ችግሩንም በቀላሉ መለየት ይቻላል የሚል ምላሽ ሲሰጡኝ ‹‹አይ ኢትዮጵያ !›› ብዬ እራሴን ከመነቅነቅ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም።
የሆኖ ሆኖ የነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ታሪክ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም።ስለነሱ እያወሩ ዝም ብሎ መመልከቱም የራስን ስጋ በእራስ እየበሉ ወደ መቃብር ማምራት ነውና መንግስት አልፎ አልፎ ከሚወስዳቸው እና ብልጭ ድርግም ከሚሉ ጥረቶች ባሻገር ቢቻል የሸማቹን መብት የሚጠብቅ የሲቪል ማህበር ማቋቋም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013