ለምለም መንግሥቱ
ጥቅም ላይ ውለው በተጣሉ እንደ ድስት፣ የመኪና ጎማ ባሉ እና ሌሎች የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የውሃ መያዣ የፕላስቲክ ዕቃዎች የተተከሉ የተለያዩ ዕጽዋቶችና አትክልቶች በመኖሪያ ቤቶች ደጃፎች ማየት እየተለመደ መጥቷል።
አትክልት መትከሉ በበጎ የሚወሰድ ቢሆንም ዕቃዎቹን ላለመጣል ጥቅም ላይ ለማዋል ወይንስ የአረንጓዴ ልማት አካል ለመሆን ብዙዎቹ ምክንያቱን ግልጽ አድርገው አይነግሯችሁም። ብቻ በዘልማድ በደጃፎቻቸው ላይ ተክሎች እንዲኖር ከመፈለግ የመነጨ መሆኑን ይታዘባሉ።
ለዚህም ማሳያው አብዛኞቹ አትክልቶቹን አንዴ ከተተከሉ በኋላ ተንከባክበው ልምላሜያቸው እንዲጎላ ሲያደርጉ አይስተዋልም።ተከታትለው አፈር ስለማይቀይሩና ውሃም ስለማያጠጡ አትክልቶቹ በእንክብካቤ ጉድለት ውበት ከመስጠት ይልቅ የአካባቢውን ውበት ሲያጎድሉ ይስተዋላል። ከአትክልት መትከያው ዕቃ ጀምሮ ለአይን የሚታየው ተያይዞም ጤና ላይ የሚስከትለው ችግር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱን የጎላ ያደርገዋል።
በደጃፋቸው ትንሽ መሬትም ሆነ በግቢያቸው ውስጥ ሰፊ ቦታ ያላቸው ለውበት፣እንዲሁም ለምግብ እንደ ጎመን፣ቆስጣ፣ጤናአዳም፣የሥጋ መጥበሻ(ሮዝመሪ)… የመሳሰሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ተክሎች የሚያለሙ ቢኖሩም አትክልት ለመትከል ተነሳሽነቱ ያላቸውን ያህል የተከሏቸውን አትክልቶች መንከባከቡ ላይ የበረቱ አለመሆናቸው በተመሳሳይ ይታያል።
በግቢያቸው፣በአካባቢያቸውና በቤታቸው ደጃፍ ላይ በዕቃ የተለያዩ ዕጽዋቶችን የሚተክሉ ሰዎች ዕጽዋቶቹ ሊኖራቸው ስለሚችለው ውበት፣ስለሚሰጡት ጥቅምና ስለሚያስከትሉት ጉዳት በዕውቀት ዝርያዎቹን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋልም ያለው ጥረት አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል አይደለም።
በአሁኑ ጊዜ በከተሞች በተለይም በመሀል ከተማ የመኖሪያ ቤቶችም ሆኑ የተለያየ አገልግሎት መስጫዎች ግንባታቸው ወደ ላይ እየሆነ በመምጣቱ የዕጽዋት ተከላውም አብሮ መታሰብ አለበት።ህንፃዎቻቸውን በአረንጓዴ ልማት ለመሸፈን ጥረት ማድረግ የጀመሩም አሉ።
በመንግሥት በተከናወነው የቤት ልማት በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖረው ማህበረሰብ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ ግምት ውስጥ በማስገባት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ የሚከናወነው የዕጽዋት ልማት ከህንፃውና ከአካባቢው ጋር ምን ያህል እንደሚጣጣምና የልማት እንቅስቃሴውን እንዲሁም በክፍለ ከተሞች ስለሚደረግ ድጋፍ ለአብነት የአንድ ሁለቱን ዳስሰናል።
በቅጥር ግቢ ውስጥ የሚከናወነው የዕጽዋት ተከላ እንደ ሀገር በተያዘው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ውስጥ ስላለው አስተዋጽኦ ፣ ስለሚስተዋሉ ክፍተቶችና ወደፊት መሰራት ስላለበት ሥራም ቀድሞ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና አሁን የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ ደገፋ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
በግቢያቸው ውስጥ ስለሚከናወነው አረንጓዴ ልማት ሥራ ሀሳባቸውን ያካፈሉን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወረዳ አንድ ውስጥ ጀሞ አንድ ተብሎ በሚጠራው ‹‹ሰፈረሰላም›› በሚል ስያሜ የተመሰረተው የጋራ መኖሪያ ቤት ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ ታደሰ፤ እንደገለጹልኝ ማህበራቸው የሚያስተዳድረው ከህንፃ ቁጥር 243 እስከ 254 ድረስ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ህንፃ ላይ 30 አባወራ ይኖራል።
ማህበሩም ህጋዊ ሰውነት አለው። ግቢ ማስዋብን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል ከአባላቱ ወርሃዊ መዋጮ ይሰበሰባል።በተገኘው ገንዘብም ግቢው ውስጥ የተለያዩ ዕጽዋቶችን በመትከል ግቢውን አሳምሯል።አትክልቶቹን የሚንከባከብ ሰራተኛ በመቅጠርም እንዲጠበቅ አድርጓል።
ነዋሪውም ለዕጽዋቱ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግና ለሚደረገው የጥበቃ ሥራም እንዲተባበር የማህበሩ አመራር በማስታወቂያ በማሳወቅ ጭምር ዕጽዋቶቹን እንዲጠብቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል።ዕጽዋቶቹን ከሚንከባከበው ሰራተኛ በተጨማሪ በጽዳት ሰራተኞችና ነዋሪውን በየወሩ በማሳተፍ የግቢውን ጽዳት በመጠበቅ ለተክሎቹ እንክብካቤ ያደርጋል።
ወይዘሮ አልማዝ እንዳሉት፤ ማህበራቸው በዕጽዋት ልማት ሥራ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴና የልማት ጥበቃው በአንዳንድ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚያዩት የተሻለ እንደሆነ እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።ለዚህም ከእርሳቸው በፊት ከማህበሩ ምሥረታ ጀምሮ ለስድስት አመታት በሰብሳቢነት የመሩትን አቶ ስዩም ወልደሰንበትን ያመሰግናሉ።የሚኖሩበት ወረዳም ማህበራቸውን ሞዴል አድርጎ በመሸለም ለሌሎች በአርአያነት እንዲጠቀስ በማድረግ የቀድሞ መሪውን ሚና አንስተዋል።
እርሳቸውም በ2012ዓ.ም ወደ አመራርነት ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቀድሞ መሪውን ጠንካራ የአረንጓዴ ልማት ሥራ አስቀጥለው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። የአረንጓዴ ልማት ሥራ ተቆርቋሪነትንና ጥንካሬን እንደሚጠይቅ በሥራ ቆይታቸው ለመገንዘብ መቻላቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ፤ በየጊዜው ክትትል በማድረግ ግቢው ክረምት ከበጋ አረንጓዴ ሆኖ ለነዋሪው ተስማሚ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በግቢው ውስጥ የተከናወነው የአረንጓዴ ልማት በመኖሪያ ሕንፃው ላይ ጉዳት እንዳያስከትልና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑም ወይዘሮ አልማዝ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አባላቱ እዚህ ጋር ቢተከል ወይንም እዚያ ጋር ቢሆን የሚል ሀሳብ በሰጡትና በተከላውም ባደረጉት የተሳትፎ አስተዋጽኦ የተከናወነ እንጂ በውጭ ባለሙያ ድጋፍ የታገዘ አይደለም።የወረዳቸው እገዛ በየአመቱ በክረምት እንደ ሀገር የችግኝ ተከላ መርሃግብር ሲከናወን ማህበሩ ችግኝ ወስዶ እንዲተክል ከመተባበር ያለፈ ድጋፍ ያለው አይደለም።
ዕጽዋቶቹ መኖራቸው ነዋሪው በግቢው በጥላው ሥር ሆኖ ጊዜውን እንዲያሳልፍና ልጆቹንም እንዲያዝናና ጥቅም ከመሥጠቱ በተጨማሪ ንጹህ አየር እንዲያገኝ አግዞታል።ውበቱም እይታን የሚስብ መሆኑን ሌሎች ከሚሰጧቸው አስተያየት ተረድተዋል።
‹‹አትክልትና ሕፃን ልጅ ለእኔ አንድ ነው።ልጅን ተከታትሎ በማብላትና ንጽህናውን በመጠበቅ ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገለት አያድግም።በህይወትም ላይኖር ይችላል።አትክልትም እንዲሁ ነው››በማለት ያልተቋረጠ እንክብካቤ እንደሚያስፈልግና ማህበራቸውም ይህንኑ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
በአራዳ ክፍለከተማ የሚገኘው ባሻወልዴ ችሎት የጋራ መኖሪያ ቤት ማህበር በተገኘንበት ወቅት ያገኘናቸው የማህበሩ ፀሐፊና የሂሳብ ሰራተኛ ወይዘሪት አስቴር በዜ፤ በግቢው ውስጥ እስካሁን ባለው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ጠንካራ የሚባል እንዳልሆነ፣ መውጫቸውን ለማሳመር ጥረት ከሚያደርጉ አንዳንድ ነዋሪዎች በስተቀር አብዛኞቹ ትኩረት እንደማይሰጡ፣ወረዳዎችም ወቅታዊ እንቅስቃሴ ሲኖር እንጂ አጥጋቢ የሆነ ድጋፍና ክትትል እንደማያደርጉ ያስረዳሉ።ማህበሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራውን ለማጠናከር ዕቅድ መያዙን ነው ወይዘሪት አስቴር የተናገሩት።
በጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ልማት ሥራ እንደ ማህበሩ አመራሮች ጥንካሬ የሚወሰን መሆኑን ከተመለከትኩት ለመረዳት ችያለሁ።ጠበቅ አድርጎና ትኩረት ሰጥቶ በተንቀሳቀሰበት ማህበር እይታን የሚስብ አረንጓዴ ልማት ጎልቶ ይታያል። እንቅስቃሴው ደካማ በሆነበት ደግሞ ምቹ ግቢ እያላቸው እንኳን አለመጠቀማቸውን ይታዘባሉ።ከነክፍተቱም ሆኖ በብዙዎቹ አጥር ግቢ ውስጥ የተወሰነም ቢሆን የተለያዩ ዕጽዋቶች ተተክለዋል።
የክፍለ ከተሞችን እገዛ በተመለከተም በአራዳ ክፍለከተማ የተፋሰስ ልማት ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ዓለሙ ክፍለከተማው የአረንጓዴ ልማት ሥራን አጥረ ግቢን ጨምሮ በመንገድ አካፋይ፣በፓርኮች ጭምር እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።ስለ አረንጓዴ ልማት ሥራው የማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠርም ተጨማሪ ተግባር በመሆኑ በዚህ ላይ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻሉ ።
ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ በአጥረ ግቢ ውስጥ ትምህርታዊ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ተስማሚ የሆነ ዕጽዋት እንዲተክሉ በማድረግ ላይ እንደ ትምህርት ቤት በመሳሰሉ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ የሚከናወነውን ያህል እንዳልሆነ፣ክፍተት መኖሩንና ወደታች ወርደው መሥራት እንደሚቀራቸው ተናግረዋል።የዕጽዋት ዝርያ መርጠው ባያሰራጩም፤ክፍለከተማው ተስማሚ ዝርያዎችን እንደሚያስመጣ አመልክተዋል።
አቶ ዳንኤል በወረዳው በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገናል ቢሉም ማረጋገጥ ያለበት ነዋሪው ነውና ከአስተያየት ሰጭዎች የሰማነው ግን ወቅታዊ፣ ለዚያውም ችግኝ በማደል ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው።ክፍተቶችን አይቶ መሙላት ከሁሉም ስለሚጠበቅ ይታረማል ብለን እንገምታለን።በአካባቢያቸው በግል ቤት አልሚዎች ተገንብተው ማህበረሰብ በሚኖርባቸውም ቢሆን በተመሳሳይ ድጋፉ መደረግ አለበት።ጥቅሙ ለሀገር በመሆኑ ተናብቦ መሥራት ያስፈልጋል።
በአጥር ግቢ የሚከናወን የአረንጓዴ ልማት ሀገራዊ ሥራዎች ላይ ስለሚኖረው ፋይዳ የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ ደገፋ፤አሁን ባለው የከተሞች ሁኔታ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ሰፊ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መሆኑን ያወሳሉ።እርሳቸው እንዳሉት ያሉትን ውስን ቦታዎችም ቢሆን ተስማሚ የሆኑ የዕጽዋት ዝርያዎችን መትከል ያስፈልጋል።ሁሉም በአግባቡ መተግበር ከቻለ እንደሀገር ለተያዘው የአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ ልማት መርሃግብር ከፍተኛ አተዋጽኦ አለው።
ከተሞች ለፓርክና ለጫካ ሊውል የሚችል ክፍት ቦታ የላቸውም። በመሆኑም አካፋይ መንገዶችን፣አደባባዮችን፣በየተቋማቱ ያሉትን ቁርጥራጭ መሬቶች ሳይቀር በአግባቡ በመጠቀም ወደ አረንጓዴነት በመቀየር እያጋጠመ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ማስተካከል፣ እንዲሁም ብዝሀ ህይወትን ለማሻሻል፣ጎርፍምን ለመከላከል ያግዛል።የአረንጓዴ ልማቱን ከተለያየ አቅጣጫ ማየትና መጠቀም ይቻላል።ለአብነትም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱና ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታ ያላቸውን ዕጽዋትንም በመትከል ተጠቃሚነትን ማሳደግ አንዱ ጥቅም ነው።
በአጥር ግቢና በአካባቢ የሚከናወነው የዕጽዋት ተከላ በግንዛቤ የዳበረ ስለመሆኑ ዶክተር ስለሺ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣በቂ ግንዛቤ ተይዞ እየተከናወነ ነው የሚል እምነት የላቸውም። በአዲስ አበባ ከተማ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ መገናኛ በሚወስደው የመንገድ አካፋይ ላይ የተተከለው ‹‹አሮካሪያ››የተባለው የችግኝ ዘርያ ወደጎን የሚበቅልና ግዙፍ የሚሆን በመሆኑ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ከሜክሲኮ ወደ አፍሪካ ህብረት የሚወስደውም በቀላሉ በንፋስ ኃይል የሚወድቅ ዝርያ ነው። ዝርያዎቹም ሀገር በቀል አይደሉም።በመሆኑም ከኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ጋር ተስማሚ አይደሉም።
በመኖሪያ ቤቶችም ሆነ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚተከሉ ዕጽዋቶች መመረጥ አለባቸው።በተለይ ዛፍ ከሆነ ሥሩና ቅርንጫፉ ምን ያህል ሊያድግ እንደሚችልና ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።የሚተከለው ዕጽዋትም ለውበት፣ለጥላ ብቻ የሚያገለግል መሆኑ ሁሉ ተለይቶ መከናወን ይኖርበታል።
በህንፃዎች ላይና በቅጥር ግቢ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ቦታ የሚተከለው ዕጽዋት ካልተመረጠ መጤና ወራሪ ሆኖ በዘመቻ ለማጥፋት የመረባረብ ሥራ ሊጠይቅ ይችላል።በአጠቃላይ በዘርፉ ባለሙያዎች በዕውቅት የታገዘ ሥራ ካልተሰራ የአረንጓዴ ልማት ሥራው ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።አሁን ባለው የአረንጓዴ የልማት ሥራ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር ተችሏል።ተገቢነት ያላቸው ዕጽዋት በመትከል ላይ ግን ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ሰፊ ሥራ መሰራት ይኖርበታል።
እስካሁን ባለው ተሞክሮም ዕጽዋቶቹ ስለተገኙ ብቻ እንደሚተከሉ የጠቀሱት ዶክተር ስለሺ፤ የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ውስጥ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ሀገር በቀል ዕጽዋቶች ችግኞች በማባዛት ላይ መሆኑንና 114 ችግኝ ጣቢያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።ችግኞቹ መአዛማ የሆኑ፣ለመድኃኒትነትና ኦኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚቀበላቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ፣በደጃፉ፣በበረዳው፣በቤቱ ጣሪያ ላይ፣ባገኘው ክፍት ቦታ ሁሉ ዕጽዋቶችን በመትከልና ተንከባክቦ በማጽደቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።ዶክተር ስለሽ በዘርፉ የሚደረጉ ጥናቶች ከመደርደሪያ ወርደው ጥቅም ላይ ይዋሉ ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን አካፈለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013