በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 102 ቁጥር አንድ መሰረት፣ በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይቋቋማል ይላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ተቋም ለበርካታ ዓመታት ገለልተኛ አይደለም፤ በገለልተኛ አካላትም እየተመራ አይደለም፤ የህዝብን ድምጽም ማስከበር አልቻለም፣ የሚሉ ወቀሳዎች ሲሰነዘሩበት ቆይተዋል፡፡ መንግስትም ይሄን ወቀሳ ለመቀየርና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን እውን ለማድረግ የሚያስችል ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ የሚያስችለውን እርምጃ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በመሾም ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድም፣ የተቋሙን ሰብሳቢ ሹመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ መንግስት መስርተው ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ ከቆዩ ቀደምት አገራት አንዷ ብትሆንም፤ የህዝቦቿን ፍላጎት የሚመጥንና የሚመልስ የዴሞክራሲ ተቋም መገንባት አልተቻለም፡፡ በተለይም የህዝብና መንግስትን የሚያስተሳስረው ማህበራዊ ውል በህዝቦች ነጻ ፈቃድና ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡
ምክንያቱም ይህ የነጻ ፈቃድ ውል የሚመሰረተው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በመሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም መንግስት ሌሎች ባለድርሻዎችን ሳያወያይና ሳያማክር ለራሱ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በምርጫ ቦርድነት ያስመርጣል፣ በዚህም ምርጫ ይጭበረበራል የሚሉ ክሶች በስፋት ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ አሁን እየተወሰዱ ያሉ የእርምት እርምጃዎችም ምርጫ 2012 እውነተኛ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሚታይበት እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡
ሆኖም ከዚህ ሁሉ ክርክርና ውዝግብ በኋላ፤ ከሰሞኑ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደመጠው የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ የመመረጥ ዜና ሁሉንም በሚያስብል ደረጃ አስደስቷል፤ አስማምቷልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግለሰቧ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና የትኛውም አካል ከህግ በታች እንደመሆኑ ለህግ መገዛት አለበት የሚል ጽኑ አቋም ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይሄው እውነትም የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች እየተመራ አይደለም በሚል ለዓመታት ሲሞግቱ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ጭምር ምስክርነትን ያገኘ ክስተት ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ “አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም፤ አንድ እጅም ብቻውን አያጨበጭብም” እንዲሉ፤ የወይዘሪት ብርቱካን ጠንካራ ሰብዕናና የስራ ትጋት ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም፤ ስለዚህ ሌሎች መከናወን ያለባቸው ቀሪ የቤት ስራዎች አሉ፤ ሲሉ እነዚህ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች አካላት ተደምጠዋል፡፡ ይህ ሀሳብ እውነትነት ያለው ብቻም ሳይሆን ገዢና ተቀባይነት ያለውም ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ይህ ተቋም ቀደም ሲል በበርካቶች ሲተች የቆየ ነው፡፡
አሰራሩም ሆነ አደረጃጀቱ ችግር ያለበት ስለመሆኑ፤ የሰው ሃይሉም ቢሆን ከአናት ጀምሮ እስከ አስመራጮች ገለልተኛ ያልሆኑ ይልቁንም ለገዢው ፓርቲ የቆሙ ስለመሆናቸው በስፋት ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡ እናም ይሄን ተቋም ፈትሾ ግለሰቧን በሚያግዝ መልኩ ማደራጀቱ ቀጣይ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ የቤት ስራ ደግሞ አንድም ከተመራጯ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ሁለተኛም ህገ መንግስቱን የማስከበርና በዛው አግባብ እንዲከናወኑ እድል ከመስጠት አኳያ በመንግስት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ተመራጯ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ በርካቶች የለውጥን ተስፋ የጣሉባቸው እንደመሆኑ፤ ተቋሙን የመምራት ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ገለልተኝነት ሲባል ለፓርቲ ታማኝ ከመሆን አለመሆን ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ለሕግና ሕጋዊ ስርዓት መቆምን፣ ለህዝብ ፍላጎት መስራትን፣ ብሎም የህዝብ ድምጽ ባልተገባ መንገድ እንዳይባክን በቁርጠኝነት መስራትን የሚመለከት ነው፡፡
እርሳቸው ደግሞ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ድረ ምርጫ ሂደቶች በስኬት እንዲጓዙ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ውሳኔ መሰረት እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሃላፊነት ተሸክመዋል፡፡ እናም የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን የሚችለው ተቋሙ ስራቸውን በሚያግዝ መልኩ እንዲደራጅ በማድረግ፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፤ የቦርድ አባላትን ከመምረጥ ጀምሮ ተቋሙ ከሁሉም አካላት ነጻ እንዲሆን ማስቻል፤ ህግ አውቆና አክብሮ በህግ አግባብ የሚሰራ አድርጎም በማደራጀት ተቋሙ ህዝብ የሚያምንበት ሆኖ የሚሰራበትን ቁመና ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በመንግስት በኩልም በእስካሁኑ የምርጫ ሂደቶች ሲነሱበት የነበሩ ወቀሳዎችን ለመሻር የቦርዱን ሰብሳቢ በመሾም አንድ ብሎ የተጀመረውን ቁርጠኛ እርምጃ እስከታችኛው የተቋሙ መዋቅር የሚመደቡ ሰራተኞች ለህግና ህገ መንግስት መከበር የሚሰሩ እንጂ ለፓርቲ የሚወግኑ ሆነው ከሚቀረጹበት አሰራር እንዲወጣ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የገዢው ፖለቲካዊ ፍላጎት ብቻ እንዲፈጸም ከሚደረግ ጣልቃ ገብነትም መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
በመሆኑም በተቋሙ የሚከናወን እያንዳንዱ ተግባር በግልጽ የሚከናወንበት፤ የምርጫ ሂደትም ሃቀኛና ትክክለኛነቱ የሚረጋገጥበት አሰራርና መዋቅርን መዘርጋትና ለዚሁም የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ከባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከእስካሁኑ የምርጫ ሂደት በመማር የተሻለ አሰራር ለመፍጠር ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
ይህ ሲሆን ነው የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ የሚፈልገውን መርጦ የመብቱ ተጠቃሚ መሆኑን የሚያረጋግጠው፤ የመንግስት ተጠያቂነትም የሚሰፍነው፤ የተመራጯም አመራርነት ፍሬ አፍርቶ ተቋሙም በህዝብ ዘንድ እምነት ኖሮት ድምጼ ዋጋ አለው በማለት መብቱን በተግባር ወደማዋል የሚመጣው፡፡