ራስወርቅ ሙሉጌታ
ወይዘሮ ይመኙሻል (ስማቸው የተቀየረ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በተደጋጋሚ በባለቤታቸው የደረሰባቸው ድብደባ ያስከተለባቸው አካላዊ ጉዳትና ይህንንም ተከትሎ የተፈጠረባቸው የማህጸን ካንሰር ህመም ግንኙነት እንዳይፈጽሙና እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ እግር ከወርች አስሯቸው ቆይቷል። ይህም ሆኖ ባለቤታቸው በነጋ በጠባ አንዴ በስድብ አንዴ በድብደባ መቆሚያ መቀመጫ በማሳጣት አራት ልጆችን ወልደው እስኪያሳድጉ ሲያስመርራቸው ኖረዋል።
ወይዘሮዋ ‹‹እልም ብዬ ልጥፋ›› እንኳን እንዳይሉ ደግሞ ከእሳቸው ውጪ ሊንከባከብና ሊጠብቃቸው የሚችል ዘመድ አዝማድ የሌላቸው አራት የአብራካቸው ክፋይ የሆኑ ልጆቻቸው እራሳቸውን ተስፋ አድርገው ይጠብቋቸዋል። እሳቸው ደግሞ ከክፍለ ሀገር የመጡና ለከተማው ኑሮ አዲስ የሆኑ፤ በዚያ ላይ ትምህርት የሌላቸውና በቂ ጥሪትም ያልቋጠሩ በመሆኑ ነገሮች ሁላ ጨልሞባቸው ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር በስሚ ስሚ በጎረቤቶች ምክር «መፍትሄ ሊሰጡሽ ይችሉ ይሆናልና እስኪ ሄደሽ ሁሉን ነገር ነግረሽ አዋያቸው» ሲባሉ ወደ ኢትዮጵያ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር ያቀኑት።
እዚያም ሲደርሱ በወቅቱ የነበሩት የማህበሩ የህግ ባለሙያዎች ተቀብለው ካነጋገሯቸው በኋላ ችግራቸው ደብዳቤ በመጻፍ አልያም የምክር አገልግሎት ብቻ በመስጠት የሚፈታ ሆኖ ስላላገኙት አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብና ከራሱ ከተቋሙ ጠበቃ በማቆም ጉዳዩን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ያቀናሉ።
በወቅቱ ወይዘሮ ይመኙሻል አራት ልጆቻቸውን ከቤት ይዘው ወጥተው የነበረ በመሆኑ ለጉዳዩ በፍጥነት እልባት ማሰጠት አልያም እናት ከልጆቻቸው ጋር ለግዜውም ቢሆን የሚያርፉበት ቦታ አግኝተው እንዲቆዩ ማድረግ ከማህበሩ ይጠበቅ ነበር።
ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ ምንም ገቢ ያልነበራቸውና የቤት እመቤት የነበሩት ወይዘሮ ይመኙሻልም ሆኑ አራት ልጆቻቸው የጎዳና ህይወትን መቀላቀል የመጨረሻ እጣ ፈንታቸው ነበር።
ባለቤታቸው ደግሞ በወቅቱ እቤት ውስጥ ድብደባ ዛቻና ስድብ ከመፈፀም ባሻገር ለቀለብ የሚሆን ተቆራጭ እንኳን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም። በዛ ላይ ይኖሩባት የነበረችው አንዲት ክፍል የቀበሌ ቤት በመሆኗ ያለው ሁኔታ ሁለቱን ጥንዶችና አራቱን ልጆች አምስት ቤተሰብ ማለት ነው ካለ መስማማት ይዛ ለመቀጠል የምትበቃ አልነበረችም።
በመሆኑም ማህበሩ የመጀመሪያ ስራው ያደረገው ባቆማቸው ጠበቆች አማካኝነት ቤተሰቡን እያወኩ ያሉትን አባት ሙሉ ለሙሉ ቤቱን እንዲለቁ በማድረግ ወደ ጎዳና ሊወጣ የተዘጋጀውን ቤተሰብ እዚያው አንድ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ መታደግ ነበር።
ይህንን ማሳካት የተቻለ ቢሆንም ሰውየው በአካባቢው ስለሚኖር ከቤት ቢወጣም በተደጋጋሚ እየተመላለሰ ቤተሰቡን ማወኩን እናት ላይም ድብደባ መፈጸሙን ሊያቆም አልቻለም።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስቸጋሪው አባት ወደ ቤት እንዳይገባ ብቻ የሚከለክል ስለነበርና የሚኖሩበት ቤት በአንዲት መንደር ውስጥ ከዋና መንገድ በርቀት የውስጥ ለውስጥ አስቸጋገሪ መንገዶች ተጉዞ የምትገኝ በመሆኑ ሰውየው መንገድ ላይ በመጠበቅ ይረብሻቸው ጀመር።
ይህ ደግሞ ቤቱን ከተረከቡ በኋላ ከልብስ ማጠብ ጀምሮ ሌሎች የጉልበት ስራዎችን በመስራት የአራት ልጆቻቸውን ህይወት በመታደግ ለማስተማርና ለቁም ነገር ለማብቃት ለሚውተረተሩት እናት ሌላ እንቅፋት ነበር።
እናም ጠበቆቹ ምንም አይነት ችግር ከመፈጠሩ በፊት ሰላም ለማውረድ ሰውየው ወደ ቤተሰቡ እንዳይደርስ የሚያደርግ ውሳኔ በፍርድ ቤት በኩል እንዲሰጥ ያደርጋሉ።
ይህም ቢሆን ግን በርካታ ውጣ ውረዶች የነበሩበት ሲሆን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የህግ ባለሙያዎች በአንድ ቀን ሁለት ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመመላለስ የወይዘሮ ይመኙሻልን ጉዳይ ይከታተሉ ነበር።
ስለሆነም ቤት እንዳይገባ ማስከልከል ብቻ ሳይሆን ሌላ እርምጃ መወሰድ ስለነበረበት ሌሎች የመረጃ ማሰባሰብና የህግ ድጋፎች በማህበሩ በኩል ከተደረጉ በኋላ ሰውየው እየሰራ ባለው ስራ የስድስት ወር እስራት እንዲፈረድበት እስከማድረግ ይደርሳሉ። ከዚህ በኋላ ነበር ወይዘሮ ይመኙሻልና ቤተሰባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም አየር በመተንፈስ በቤታቸው በነፃነት ለመኖር የበቁት።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በመላው ሀገሪቱ በየአመቱ ከሁለት መቶ ሺ በላይ በመመደብ የወይዘሮ ይመኙሻል አይነትና ሌሎች በሴቶችና ልጆቸ ላይ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችንና የተለያዩ ህግ ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችን በመያዝ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ካለምንም ክፍያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም በርካታ ቤተሰቦችን ከመበታተን በተለይም እናትና ልጆችን ከመለያየትና የጎዳና ህይወትን ጨምሮ ለተለያዩ የጉስቁልና ኑሮ ከመዳረግ ብሎም ከአካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት እየታደገ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወንድምነህ ለማ እንደሚሉት፣ ማህበሩ የተቋቋመው በ1987 ዓ.ም የሴቶች ጉዳይ እኔንም ይመለከተኛል የሚል አቋም በነበራቸው ሴት የህግ ባለሙያ ኢትዮጵያውያን ነበር።
የተቋቋመበትም ዋነኛ አላማ የሴቶችን መብት ከወንዶች እኩል ለማስከበርና ለማስጠበቅ እንዲሁም በኢኮኖሚ፤ በማሀበራዊና በፖለቲካው መስክ ሴቶች ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በማሰብ ነው።
የህንንም ከግብ ለማድረስ ማህበሩ ሲቋቋምም ሶስት ፕሮግራሞችን ይዞ መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን ከእነዚህም አንደኛ ሴቶች መብታቸው ሲጣስ ነጻ የህግ ድጋፍ መስጠት፤ በሁለተኛ ደረጃ ህዝብን የማስተማር ስራ ሲሆን በዚህ በኩል (እንደ ፖሊስ ቃቤ ህግ ዳኛ ህብረተሰቡንና ሊሎች የሚመለከታቸውን አካላት ባለጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ በማድረግ የማንቃት ስራ)።
አንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ የጥናትና ምርምር እንዲሁም በህግና ሌሎች ጉዳዮች የሚሻሻሉ ነገሮች ሲኖሩ እንዲስተካከሉ ጥናቶችን በማከናወንና ነበራዊ ሁኔታን ከግንዛቤ በማስገባት ማስተካከያ እንዲደረግ የግፊት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
‹‹ማህበሩ ከሶሰት መቶ በላይ ሴት የህግ ባለሙያ አባላትና የህግ ባለሙያ ያልሆኑ በተለያዩ መስኮች የተመረቁት ተባባሪ አባላት አሉት›› የሚሉት አቶ ወንድምነህ፤ እስካሁን ከሁለት መቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠቱን በማስታወስ ‹‹እነዚህ ተገልጋዮች አንድ ደብዳቤ ለመፃፍ ወደ ባለሙያ ቢሄዱ በትንሹ አራት መቶ ብር ይጠየቃሉ።
ነገር ግን በማህበሩ ለአንድ ተገልጋይ ቢያንስ ከአስራ አምስት ገጽ በላይ ደብዳቤዎች ይጽፋሉ። በተጨማሪ ጉዳዩ ምንም ያህል ግዜ ቢወስድ ጠበቃ ቆሞ ሰው እስከ መጨረሻ እንዲከታተልላቸው ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ጠበቆች በሳምንት አንድ ግዜ ስለሚገቡ የሚመጡ ተገልጋዮች ሁለተኛ ቀን መመለስ ካለባቸውና የገዘብ እጥረት እንዳለባቸው ከታወቀ ምን አልባት በትራንስፖርት ምክንያት ቀርተው መብታቸው እንዳይነፈግ ሊያገኙት የሚገባ ጥቅማቸው እንዳይቀር ማህበሩ የትራንስፖረት ገንዘብ በመስጠት ድጋፍ ያደርግላቸዋል›› ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ከአዲስ አበባ ውጪ በአማራ፤ ኦሮሚያ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ ደቡብና ጋምቤላ ክልሎች እዲሁም በድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ቢሮ ከፍቶ እየሰራ ይገኛል። በቅርቡ በሱማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ቢሮ ለመክፈት በእንቀስቃሴ ላይ ሲሆን የተፈጠረው ያለመረጋጋት ሲስተካከልም በትግራይ ክልል አገልግሎቱን ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል።
ማህበሩ በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ እንደ መሆኑ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ በቀጥታ የሚቀርብለትን የገንዘብ ድጋፍ እየተቀበለ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በወቅቱ ተስተካክሎ የነበረውና የግል እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችን የሚመለከተው አዋጅ ገቢውም እንዲቀንስ ስራውንም በተገቢው መንገድ እንዳይከውን አድርጎት ቆይቷል።
በዚህም የተነሳ በቅርቡ በሀገሪቱ ለውጥ እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ አብዛኛው እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው በበጎ ፈቃደኛ የህግ ባለሙያዎች ትብብር ነበር። በአሁኑ ወቅት የአዋጁን መሻሻል ተከትሎ በርካታ ስራዎችን መስራትና ገቢውንም ማሳደግ የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ከመንግሥታቱ ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) እና የስርዓተ ፆታ ተቋም (UN Women) እንዲሁም ከፕላን ኢትዮጵያ (Plan Ethiopia) እና ከኢንዴንጀር ሄልዝ (Engender Health) ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል።
በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በኩልም ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ካሉ የፖሊስ፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግና ሌሎች የሴቶች ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላትም ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ይገኛል።
የአዋጁ መነሳት የገቢ ማስገኛ መንገዶች እንዲስፋፉ እድል የሰጠ በመሆኑ ማህበሩ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ለመቅጠር፤ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ለመስራትና ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም አዳዲስ የአገልግሎት አይነቶች ለመዘርጋት አስችሏል፡፡
በቀጣይም ማህበሩ በራሱ ገቢ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል በቋሚነት የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለመስራት እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ ወንድምነህ ይናገራሉ። «ማህበሩ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ሴቶችን ብቻ ሳይሆን በርካታ ቤተሰብን በመታደግ ላይ ይገኛል» የሚሉት ደግሞ ከሶስት አመታት በፊት ማህበሩን በቅጥር ሰራተኝነት ከመቀላቀላቸው በፊት ረዘም ላለ ግዜ የህግ ተማሪ እያሉ በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግሉ የቆዩና በአሁኑ ወቅት በማህበሩ የህግ አገልግሎት ባለሙያ የሆኑት ወይዘሪት ሰላማዊት ደሳለኝ ናቸው።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ በአብዛኛው ወደ ማህበሩ ችግር ደርሶባቸው የህግ ድጋፍ አገልግሎት ፍለጋ የሚመጡት ልጆች ያላቸው ሴቶች ሲሆኑ አብዛኛዉን ጊዜ የማይሰጥ የመጠለያና የእለት ጉርስ የማግኘት ችግር ያለባቸው ናቸው።
በተጨማሪ የራሳቸው የገቢ ምንጭ የሌላቸው ብዙ ያልተማሩና የስራ ልምድም የሌላቸው ሲሆኑ ስራ መስራት የሚችሉ ቢኖሩም ልጆችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት ስላለባቸው ስራ ሰርተው ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚበቁ አይደሉም። በመሆኑም በቀጥታ ለእናቶችም ሆነ ለልጆቹ የሚደረገው ድጋፍ ቤተሰቡን ከመበተንና ከተለያዩ ቸግሮች የሚታደግ ነው።
በዚህ አካሄድም በማህበሩ የህግ አገልግሎት ክፍል የሚሰጠው ድጋፍ ከማማከር ባለፈ ይግባኝን ጨምሮ የክስ ማመልከቻዎችን መጻፍ፣ ጥብቅና መቆም እንዲሁም በህግ አካሄድ የማያዋጡ ጅምሮችንና አማራጭ ሀሳቦችን ለተገልጋዮች ማመላከትን ያካትታል። በተጨማሪም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለተለያዩ የመግስትም ሆነ የግል ተቋማት ተገልጋዮች ያሉባቸውን ችግሮች በመግለጽ ችግሮቻቸውን እንዲቀርፉላቸው ወይንም ትብብር እንዲያደርጉላቸው የትብብር ደብዳቤም ይጻፋል።
አንዳንድ ጊዜም የህግ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማኅበሩ የሚመጡ ተገልጋዮች የሚያርፉበት ቤትም ሆነ የሚበሉት ምግብ የማያገኙ፣ ልጆች የያዙና እርጉዝ ስለሚሆኑ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ከማህበሩ ጋር በትብብር ወደሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በመላክና ማቆያ እንዲገቡ በማድረግ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ ይደረጋል።
የተለያዩ የስነ ልቦናም ሆነ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተገልጋዮች የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በመንግስት ስር ወዳሉና ይህንን አገልግሎት በነጻ ወደሚሰጡ ተቋማት እንዲላኩም ይደረጋል።
ወይዘሪት ሰላማዊት እንደሚያስረዱት፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ባለው ቅርንጫፍ፣ በህግ አገልግሎት ክፍል ውስጥ ሁለት የህግ ባለሙያዎችና ሁለት ጸሀፊዎች በቋሚነት እየሰሩ ሲሆን ሌሎች ስምንት ደግሞ በበጎ ፈቃደኝነት በየሳምንቱ አንድ አንድ ቀን በመገኘት አገለግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ባሉበት ሆነው አስፈላጊ ሲሆን የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ የማህበሩ አባል የሆኑ የበጎ ፈቃድ ሰራተኞችም አሉ።
በእነዚህ ባለሙያዎች በቀን ከ10 እስከ 25፤ በየአመቱ ደግሞ ከ18 ሺህ በላይ አለሁ ባይ ያጡ የጉዳት ሰለባ የሆኑን ከውልደት እስከሞት እንዲሁም ከ18 አመት በታች የሆናቸው ልጆች (ወላጅ መሆናቸውን ማረጋገጫ ባቀረቡ ግለሰቦች በኩል) አየተስተናገዱ ይገኛሉ።
በዚህም የማህበሩ ሰራተኞች እጅግ በተጣበበ ሰአት ከመስራታቸው ባሻገር ብዙ ግዜ የምሳ ሰአታቻውን የሚያሳልፉት ተገልጋዮችን በማወያያት ነው። በልዩ አስተያየት የማህበሩ አባላት የሆኑና ለባልና ሚስት ጉዳይ ከዚህም ወስጥ ለእርቅ ሲሆን ብቻ ማህበሩ ለወንዶችም ድጋፍ የሚያደርግበት አሰራር አለ።
ማህበሩ ሁሉንም አይነት የህግ አገልግሎት ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን አብዛኛዎቹ ወደ ማህበሩ የሚመጡ ጉዳዮች ከፍትሀ ብሄር ጋር የተያያዙ ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ የወንጀል ጉዳዮችም ይቀርባሉ።
ተደጋፊዎች ፍትሀ ብሄርም ሆኖ የተለያየ አይነት ጉዳይ ይዘው የሚመጡ ቢሆንም በጣም ከጥቂቶች በቀር ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የሚያቀርቡት የፍቺ፤ የንብረት ክርክር፤ የልጆች ቀለብና የመሳሰሉትን የባልና ሚስት ጉዳዮች ነው።
በተደራሽነት ረገድም በተለያዩ ምክንያቶች መንቀሳቀስ የማይችሉ ሲኖሩ ደግሞ ህጋዊ ውከልና ባላቸው በተወካዮቻቸው በኩል፤ እንዲሁም በከባድ ችግር ማህበሩ ድረስ መምጣትም ሆነ ውክልና ለመስጠት የማይችሉና ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ መሆኑ የተረጋገጠላቸው ሲኖሩ ደግሞ እዚያው ድረስ በመሄድ አገልግሎቱን እየተሰጠ መሆኑንም ወይዘሪት ሰላማዊት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013