ዳግም ከበደ
ፀጉሩን በጠቋሚ ጣቱ እያከከ አስተናጋጁን የሎሚ ሻይና የላስቲክ ውሃ አዘዘው። በቅፅበት ወደቀድሞው ትካዜው ተመልሶ ማውጠንጠኑን ተያያዘ። ነገር አለሙ ታክቶታል። ጠረጴዛውን በእጁ እየተመተመ በመስኮት ወደ ውጪ አሻግሮ ይመለከታል። ላስተዋለው አላፊ አግዳሚውን የሚቃኝ እንጂ በራሱ ሀሳብ ተጠልፎ የሚዳክር አይመስልም።
ጮክ ብሎ ማሰብ ጀመረ፤“ሆሆ” አለ በለሆሳስ፤የሚናገረውን ድምፁን መልሶ ሲያዳምጥ እንደ መደንገጥ እያለ። ዙሪያ ገባውንም ቃኘ፤ “ብቻውን ያወራል” እንዳይባልም ሰጋ። በአገሩ ውስጥ የሚከናወነው ሁሉ ግራ ግብቶታል።
መሽቶ በነጋ ቁጥር አዲስ ነገር ይሰማል ፤ይመለከታል። ነገሮች የሚቀያየሩበት ቅፅበት ያስደንቀዋል። ለዚያ ነው ትንሽ እያሰበ እየደጋገመ “ሆሆ” የምትለዋን ቃል አስር ጊዜ የሚወረውራት።
ደንበኛ በሆነባት በዚህች ካፍቴሪያ መስኮት ዳር መቀመጥ ለምዷል፡፡ በሃሳብ ሲወጠር ይህችን ቦታ ይመርጣታል፡፡ ላለፈው አንድ ወር ራሱን በነገሮች ወጥሯል። ከእስከ ዛሬው ጉዞው ይልቅ አገሩ ችግር ውስጥ መውደቋን ያስተዋለው በእዚህ ወር ውስጥ ነው ቢባል ግነት አይሆንም።
ለዓመታት በቢሮ ውስጥ ተደፍቶ የእርሱ ባልሆኑ ችግሮች ውስጥ መክረሙን አሰበ፡፡ ስራውን ለመከወን ያህል የተለያዩ ጉዳዮችን የመቃኘት ግዴታ ስላለበት እንጂ ነገሮች ብዙም ስሜት አይሰጡትም ነበር። አሁን ግን በራሱ ጉዳይ ያጋጠመው ነገር ከማስደንገጥ አልፎ ትካዜ ውስጥ ከትቶታል።
ወዲያ ወዲህ ብሎ የሰበሰባትን ጥሪት ይዞ ኑሮውን ለማሻሻል ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ሰነባበቷል። ጥሪቶቹን ሰብስቦ አንድ መስመር ለማስያዝ የቢሮውን ስራ ለጊዜው
ገታ አድርጎ ወደ መንግስት ቢሮዎች መመላለስን ተያያዘው። ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው አልጠበቁትም፤ይልቁኑ ተደብቆ የከረመበት ዋሻ ውስጥ መልሰው ሊወሽቁት ይታገሉት ጀመር።
በቢሮው ውስጥ ነገሮችን ዉስብስብ የሚያደርግ ቢሮክራሲያዊ አሰራር ቢያስተውልም፣ በአገሪቱ ይህን ያህል እንደ ዳንቴልና የሸረሪት ድር የተጠላለፈ ሁኔታ ያጋጥመኛል ብሎ አስቦ አያውቅም። በሚገባበት ቦታ ሁሉ የሚገጥመው ሰልፍ፣ ግልምጫ፣ አላዋቂነት፣ ማልመጥ፣ ምቀኝነት፣ ስንፍና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ትንፋሹን አሳጠሩት፡፡
በሃሳቡ ብዛት ረስቶት የቀዘቀዘውን የሎሚ ሻይ ሳያጣጥም እየማገው ያጉረመርማል። “ታክሲ ሰልፍ፣ ክፍለከተማ ሰልፍ፣ ባንክ ሰልፍ፣ ለመብላት ሰልፍ፣ ሰልፉን ለማሳጠር ሙስና ለመስጠት በራሱ ሰልፍ አለ” እያለ ያጉረመርማል። ሻይ ተብዬውን ይጠጣና አፍታም ሳይቆይ ውሃውን ይጎነጫል፤በራሱም ላይ ይነጫነጫል።
ካጋጠሙት ሰንካላ ቀናት መካከል ጨጓራውን የላጠው በግቢው ውስጥ ሊወድቅ ያለውን የመብራት ምሰሶ ለማስነሳት ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሄደበት ጊዜ አንዱ ነው።ይህን እያስታወሰ ነገር ማመንዠጉን ተያያዘው።
ዶሴውን ሸካክፎ ከሚኖርበት አቅራቢያ ወደሚገኝ ዲስትሪክት ማልዶ ይሄዳል።የቢሮው ሰአት ደረሰ፡፡ ጉዳዩን ለማስፈጸም ሲሞክር ፊታቸው ዳመና የመሰለ እንኳን ሊያናግሯቸው ሊያዩአቸው የሚያስፈሩ ሰራተኞች ገጠሙት።
ፈራ ተባ እያለ “በግቢዬ ወድቆ አደጋ ሊያስከትል የደረሰ የኤሌክትሪክ ምሰሶ አለ፤እንዲነሳልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፤ለሚደረግልኝ ትብብርም በቅድሚያ አመሰግናለሁ” በሚል አጭር ማመልከቻ አስገባ።
መልሳቸው ግን “መብራት የለም፤ሲስተም አይሰራም ፤ነገ ተመልሰህ ና” የሚል አጭርና ተስፋን ከአፈር የሚቀላቅል ነበር። ነገ ዛሬ ሲሉት ደጅ አስጠኑት። ሊወድቅ ቋፍ ላይ ስለደረሰው ምሰሶሲያስብ አገሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለች እየመሰለው አስር ጊዜ መባነን ከጀመረ ሰነባብቷል።
ከወር በፊት ከቤቱ የሚወጣው ጠዋት የሚገባውም ምሽት ስለሆነ የሚኖርበትን አካባቢ በሚገባ አይቶት አያውቅም። ባለው ጊዜ ሰፈር ውስጥ ዞር ዞር እያለ ሲመለከት እጅግ ብዙ አስደንጋጭ ነገሮችን አስተዋለ።
በቆሻሻ የተሞላ ቱቦ፣ ከነዋሪው ገንዘብ ቢሰበሰብም ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣አስተዋሽ የሚፈልጉ በየጎዳናው የተኮለኮሉ ታዳጊዎች፣ በየመንገዱ ተበታትኖ የተቀመጠ የኮንስትራክሽን እቃ የሚያየው ሁሉ ልብን የሚያደክም ሆነበት። በሰፈሩ አገሩን አየበት።
ከመብሰልሰል ወጥቶ የላስቲክ ውሃውን ጎንጨት ካደረገ በኋላ ሞባይሉን መነካካት ጀመረ። አንድ ጉዳይ ትኩረቱን ሳበው። ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች አንገቱን አቀርቅሮ ስማርት ስልኩ ላይ ሲያፈጥ ቆየና ፈገግ ብሎ ቀና አለ።
ጥርሱን ያስገለጠው ጉዳይ አንድ የማህበራዊ ገፅ ተሟጋች ክፍለ ከተማ ሄዶ ያጋጠመውን ጉዳይ የሚተርክ ነበር። በመደነቅ ስሜት “ውጥንቅጡ ለወጣው የኛ አገር ችግር ይህን መሰል ሰው ነው የሚያስፈልገን” በማለት በረጅሙ ተነፈሰ። ፅሁፉ እንደሚከተለው ይነበባል።
ጽሁፉ ከሰሞኑ ከታዘብኩትና ጆሮዬ ጥልቅ ያለ አንድ አስቂኝ (መቼም አላለቅስ ነገር) ወግ ላካፍላችሁ ብሎ ይጀምራል። ሰውየው አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ክፍለ ከተማ ይመላለሳል።
ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል ባልደረባ ምክንያት እየደረደረ ብዙ አመላለሰው። “ቀጠሮ አለ፣ ወረፋ አለ፣ የሚስተካከል አለ” ምናምን… ይልና – “በቃ ላንተ ‘በአስቸኳይ’ ይሰራልህ ‘የአስቸኳይ’ ክፈል” ይለዋል። ባለጉዳዩ ገባው።
ብዙ አመነታ – አሰላሰለ። ከዛ ወጥቶ ሊሄድ አለና ጀርባውን ሰጥቶት ለደቂቃ ከቆመ በኋላ – ተመልሶ ወንበሩ ላይ ይቀመጣል። “እሺ ስንት ልክፈል?” ሲል ጠየቀ፡፡
ድርድሩ ተጀመረ። በስንት ንዝንዝ – አገልግሎት ሰጪው የክፍለ ከተማ ሰራተኛ ለባለጉዳዩ “በቃ 30,000 ብር አምጣ” ይለዋል። ተስማሙ።
ይሄን ጊዜ ባለጉዳዩ ስልኩን ጎንበስ ብሎ ነካካና፤ ለአገልግሎት ሰጪው ሲያወሩ የቆዩትን አስደመጠው። ሲቀዳው የቆየው መረጃ ነበር። ‘አገልጋይ’ – አይኑ ፈጠጠ – ድንዝዝ አለ።
ከደቂቃዎች ዝምታ በኋላ “አሁኑኑ እጨርስልሃለሁ። ዲሊት አድርግና ከዚህ ውጣልኝ” ሲል ባለጉዳዩን ይጠይቀዋል፡፡
ባለጉዳይ ፈርጠም ብሎ “አላጠፋውም – ጉዳዬን ብትጨርስልኝም አልወጣም”ሲል ይመልስለታል፡፡
አገልግሎ ሰጪው ላብ በላብ ሆነ። “ለምን? የፈለግከው ይሰራልሃል…” መንተባተብ መለማመጥ መለመን ጀመረ።
ባለጉዳይ ኮስተር ብሎ – “ጉዳዬን ጨርሰህ ዶክመንቶቼን ከ30 ሺ ብር ጋር አሁኑኑ አስረክበኝ።” ሲል አሳሰበው፡፡
“ያምሃል እንዴ ሰውዬ? 30ሺ ብር ከየት አመጣለሁ? የመንግስት ሰራተኛ እኮ ነኝ?” የግንባሩና የአፍንጫው መገናኛ ላይ ጤዛ ሰርቶ ቸፈፍ ማለት ይጀምራል። “ከየት አምጥቼ እንድሰጥህ ነበር እኔን የጠየክኝ?” ሲል ባለጉዳይ መልሶ ይጠይቀዋል፡፡
ከረዥም አደንቋሪ ፀጥታ በኋላ የክፍለ ከተማው ሰራተኛ የሰውየውን አዝማሚያ አይቶ የማይላቀቀው መሆኑን ሲረዳ፤ ጉዳዩን ሊፈፅምለት ተፍ ተፍ ማለት ይጀመራል። በ25 ደቂቃ ውስጥም ይጨርስለታል። የባለጉዳዩን ዶክመንቶች እፍቱ አስቀመጠና እጁን ዶክመንቱ ላይ እንደጫነ “ይኼው” አለና ቀና ብሎ ባለጉዳዩን ይመለከተው ጀመር።
ባለጉዳዩ ሊናገር ገና አፉን ሲያላቅቅ ሰራተኛው ስልኩን አንስቶ በጣቶቹ እየነካካ “የባንክ አካውንትህን” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
እኔም በሙሰኞች የተቸገረው ባለጉዳይ በአንድ መስሪያ ቤት በደረሰበት በደል የተነሳ ወንበር ላይ ቆሞ እጮሃለሁ ያለውና ይህን የሰማው ሃላፊ ጉዳይህን እጨርስልሃለሁ፤ዝም በል ሲል የተመጻነበት እና በቴሌቪዥን መስኮት የተላለፈ እንድ የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማስታወቂያ ትዝ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013