ማህሌት አብዱል
የተወለዱትና ያደጉት ምስራቅ ሸዋ አካባቢ ነው:: በዝዋይ ከተማ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በማቲማቲክስ ትምህርት ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ቻይና ቤጂንግ በኢኮኖሚክስ ሰርተዋል:: ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል::በተለያዩ የትምህርት ሴክተሮችም ላይ ሰርተዋል:: የኢንቨስትመንት ኮምሽን ኮምሽነርም ነበሩ:: ካለፉት ሰባት ወራት ወዲህ ደግሞ በአዳማ ከንቲባነት ነው እያገለገሉ የሚገኙት:: አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአዳማ ከንቲባ ከአቶ ሃይሉ ጀልዴ ጋር በከተማዋ እየተከናወኑ ስላሉ የልማት ስራዎች ቃለምልልስ አድርጎላቸዋል:: እንደሚከተለው ይቀርባል::
አዲስ ዘመን፡- እንደአዳማ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩት አንኳር የልማት ስራዎች ምን አንደሚመስል ያስረዱንና ውይይታችን ብንጀምር?
አቶ ሃይሉ፡-ባለፉት ስድስት ወራ በከተማችን ከየትኛው ጊዜ በላቀ በርካታ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል:: በተለይም ደግሞ ታስታውሺ አንደሆነ እኔ ወደ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሆኜ በተመደብኩበት ወቅት ከአጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በከተማችንም ሆነ በሌሎች የኦሮምያ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች ነበሩ:: በተለይም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞትን ተከትሎ በብዙ የኦሮምያ ከተሞች የሰላም መደፍረስ ሁኔታ ነበር:: በአዳማም በተወሰኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና በግል ድርጅቶች ላይም ውድመት ደርሶ ነበር:: እኔም ያንን ሁኔታ ለማረጋጋት ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነው የመጣሁት:: ከዚሁ ጎን ለጎን ወደዚህ ስመጣ ካየኋቸው ጉዳዮች መካከል በዋናነት ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ነው:: እንደመጣሁ ‹‹አለመረጋጋቱ ለምንድን ነው የተከሰተው? ህዝቡስ ምን ይፈልጋል?›› የሚል ግምገማ ነው ያካሄድነው:: በግምገማችንም አጠቃላይ ህዝቡ ልማት፣ በሰላም አብሮ መኖርና ማደግ እንደሚፈልግ አስምረን ያዝን:: በተጨማሪም የተወሰኑ ሰዎች የግል ፍላጎታቸውንና የፖለቲካ አጀንዳዎቻቸውን ለማሳካት ሲሉ በሚፈጥሩት ጫና ጊዜያዊ ሁኔታዎች ትንሽ ክፍተት እንደነበረውም ገምግመን ነው ወደ ስራ የገባነው::
እንደ ኦሮምያ ክልል የ10 ዓመት እቅድ ወጥቷል፤ ይህ እቅድ ኦሮምያን ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚመራት ከመሆኑም ባሻገር በተጨባጭ በቤተሰብ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ እምርታ የሚያመጣ ነው:: ምክንያቱም የልማት ስራዎቻችን በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ካልገቡና የግለሰቦች ኑሮ መሻሻል ካልቻለ ምንም ዋጋ የለውም:: እንደ ሀገርም እድገት ለማስመዝገብ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው:: ግን ደግሞ እድገቱ ተካፋሎ የሚደርሰን ሳይሆን በተጨባጭ በእያንዳንዳችን ቤት ውስጥ መግባት ይገባዋል:: ለዚህ ደግሞ የአደማ ከተማ ህዝብ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ነው ለማወቅ ጥረት ያረግነው:: ህዝቡ በዋናነት ሰላም እንደሚፈልግ ግን ደግሞ ብዙ ሰላም የሚያውኩ አጀንዳዎች በማንና እንዴት እንደሚቀሰቀሱ ለማጣራት ጥረት አድርገናል::
በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ከአመራሩ ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው ራሱን እንዲፈትሽ ነው ያደረግነው:: በተለይም የከተማዋን የፀጥታ መዋቅር ማጥራት አለብን ብለን ከፖሊስ ጀምሮ እንዲፀዳ ተደርጓል:: ጊዜውን የማይመጥን፤ የከተማዋን ህዝብ ፍላጎት የማያሟላ፤ ከወቅቱ ጋር የማይራመዱ አካላት እርምት እዲወስዱ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው:: በመሆኑም የፀጥታ መዋቅሩን ፖሊስ መልሶ የማደራጀትና የሕዝቡን ሁኔታ አዳምጦ እንዲሰሩ ለማድረግ ጥረት ተደርጋል:: ከዚያም ጎን ለጎን የፖለቲካ መዋቅሩ ከከተማ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን አመራ መልሰን ወደ ማደራጀት ስራ ነው የገባነው::
አስቀድሜ እንዳልክሽ እኛ ወደ ስራ ስንገባ የለየነው ትልቁ ጉዳይ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ገቢ ለመጨመር ያለንና የሌለን ነገር መለየት ነው:: ስለዚህ በርካታ የልማት ስራዎች የመሰራታቸውን ያህል በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ለይተናል:: እነዚህን ክፍተቶች ማረምና የነበሩትን ለማስቀጠል አንዱ ስራችን ነው የነበረው:: የነበሩ ጥንካሬዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማስቀጠልና ለተሻለ ውጤት፣ ተጠቃሚነት፣ አገራዊ አንድነት፣ ልማትና የኢትዮጵያ ብልፅግና ማድረስ አንዱ አላማ ስለነበር ያንን ለማሳካት እንደሚገባን አቅጣጫ በመያዝ ሠራተኛው ከታች ጀምሮ በባለቤትነት እንዲሰራ በማድረግ ነው ወደ ተግባር የገባነው::
አዲስ ዘመን፡- አዳማ ላይ ይነሱ ከነበሩ ችግሮች መካከል በዋናነት የህገወጥ መሬት ወረራ ጉዳይ ነው:: ይህንን ችግር ከመፍታት አኳያ ስለተሰሩት ስራዎች ቢያብራራሉን?
አቶ ሃይሉ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ እንግዲህ እነዚያ ስራዎች ተጠናክረው እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉ እንቅፋቶች መኖራቸውን አይተናል:: ከዚያ ውስጥ አንዱ ያለየነው ነገር ያለንን ውስን ሃብት በአግባቡ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይን ነው:: በዚህ ረገድ ራሳችንን ስንገመግም እንደአዳማ የመሬት አስተዳደርን ከፍተኛ ችግር እንደነበር ነው ያየነው:: ይህ ዘርፍ ከፍተኛ የመሬት ምዝበራ የሚታይበትና ብልሹ አሰራሮች የተንሰራፉበት መሆኑን ለማወቅ ችለናል:: በግምገማ ችግሮቻችን ከመለየት ባለፈ የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጠናል:: ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው አመራር መቀየር ነበር እንደአቅጫ ሲፈፀም የነበረው:: አመራሩ ብቻውን ለውጥ አያመጣም:: ስለዚህ ይህንን አቅጣጫ መከተል እንደማያወጣ እምነት ተይዟል:: በመሆኑም ከታች ያለውን ሰራተኛ መልሶ የማደራጀት፣ ከፍተኛ ክፍተት ያለባቸውን ከቦታው ዞር የማድረግና ጠንካር ያሉና የተሸለ ለህዝብ አገልጋይነት ራሳቸውን የሰጡና በግምገማ በጥንካሬ የገመገሙትን በተሸለ ስራ ከፊት በማውጣት አዲስ እቅድ እንዲያወጡ ነው ያደረግነው::
ይህም ቢሆን በቂ አይደለም:: በአሰራር መምራት አለብን ብለን ነው የተነሳነው:: በተለይም መረጃ አያያዝ፣ የሃብት አስተዳደራቻችን ላይ ችግር ስለነበረበት የመሬት አስተዳሩን በአግባቡ መምራት አለብን ብለን የካዳስተር ስራ መተግበር የጀመርነው:: በዚህ መሰረት በተየዘው በጀት አመት እስከ 80 በመቶ የሚደርሰውን የአዳማን መሬት ወደ ካዳስተር ስርዓት ለማስገባት አቅደን ነው ወደ ስራ የገባነው:: ለዚህም 32 ሚሊዮን ብር የመደብን ሲሆን አስፈላጊውን የሰው ሃይል አሰባስበንና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልተን ነው እየሰራን ያለነው:: በዚህም መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሬት ዙሪያ ለማመን የሚያዳግቱ ስራዎችን መስራት ችለናል:: ከዚህ ቀደም በዘርፍ የነበረውን የመሬት ስርቆት ሙሉ ለሙሉ አቁመናል ብለን መደምደም ባንችልም መንገዱን ማጥበብ ጀምረናል:: ያለንን የመሬት ሃብት ወደሲስተም እንዲመጣ ጅምር ላይ ነን::
ከዚህ በተጨማሪም ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ አባወራዎች የቀድሞ ይዞታ አይታወቅም ነበር:: ህጋዊ የሆነ የባለቤትነት ሰነድ የላቸውም:: እነዚህ ሰዎች ለዓመታት እንዲሁ ይኖራሉ እንጂ ሕጋዊነት ስለሌላቸው የተሸለ ቤት የመስራ እድል የላቸውም:: ቦታውንም ለመጠበቅም ሆነ ለማልማትም አይችሉም ነበር:: ህጋዊነት ስለሌላቸው ከነገ ዛሬ እንነሳለን መቼ እንነሳለን የሚል ስጋት ይዘው ነው ለዓመታት የኖሩት:: ይህንን ችግር ለመፍታ በተደረገው ጥረት አስገራሚ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መስራት ችለናል:: አስካሁን ድረስ ለስድስት ሺ ሰዎች ህጋዊ ሰነድ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል:: በሌላ በኩል አካባቢ አስቀድሞም በህገወጥ ወረራ መልክ የተየዘ ስለነበር ግለሰቦቹ ቤታቸውን የሰሩት ያለፕላን ነበር:: በዚህ የተነሳ ምንምአይነት መንገድም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን አዳጋች ሆኖየቆየው:: የሚገርምሽ መሬቱ የተያዘበት ሁኔታ ተሸከርካሪ ለማስገባት አዳጋች ከመሆኑ የተነሳ አደጋ እንኳን ቢመጣ ማምለጥ የማይቻልበት ሁኔታ ነው የነበረው:: አሁን ላይ ግን ነዋሪዎቹን በማስተባበር በተሰራው ስራ መንደሩ በፕላን እንዲደራጅ ተደርጋል:: ለዚህም በዋናነት የህበረተሰቡ ቀና ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ማስታወስ እወዳለሁ::
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የተሰሩት ስራዎች ምን ያህል ውጤት እያመጡ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሃይሉ፡- አንቺ እንዳልሽው ዘንድሮ ሌላው ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን የገመገምነው የንግድ ስርዓታችን ላይ የነበረው ክፍተት ነው:: በዚህ ዘርፍም ከፍተኛ ግመገማ በማድረግ ማሻሻያዎች ተሰርተዋል:: ይህንንም ስራ የጀመርነው ከታች ካለው ሰራተኛው ነው:: በዋናነት በንግዱ ዘርፍ የነበረው አስራር ህጋዊነት የለውም:: ማን ህጋዊ ነጋዴ ነው? ማንስ አይደለም? የሚለው ነገር አይታወቅም ነበር:: በነበረው የቁጥጥር መላላት ሁሉም የፈለገበት ቦታ ላይ ሆኖ የሚሰራበት ህጋዊው ከህገወጡ የማይለይበት ሁኔታ ነበር:: ትልቅ አከፋፋይ ሆኖ ሳለ የሸቀጣሸቀጥ ፍቃድ ያወጣል:: ይህንን የሚቆጣጠር ሰው የለም:: ስለዚህ አንዱ ችግር ሕገወጥነት ነው::
ስለዚህ ህጋዊ ነጋዴ ሆነው እንዲሰሩ በአግባቡ አልመራንም ብለን ነው ራሳችንን በየደረጃው የገመገምነው:: በነገራችን ላይ የዚህ ችግር መነሻው ከውስጣችን መሆኑን ነው ያየነው:: በየደረጃው ያለው ባለሙያ የተቀመጠውን አሰራርና መመሪያ በአግባቡ አያውቀውም፤ ወደታች አውርዶም የንግድ ስርዓታችን ህጋዊነት እንዲኖረው አላደረግንም:: በዚህም ምክንያት ህገወጥ ንግድ ተስፋፍቷል ብለን ነው የገመገምነው:: በዚህም ምክንያት ተደራራቢ ተፅዕኖዎች ያደረሰ ሲሆን አንደኛ ህጋዊ ነጋዴዎቸው ነግደው አንዳያተርፉ አድርጎል:: ይህም ትክክለኛ ተወዳዳሪነትን ይቀንሳል:: በአንድ በኩል ህገወጥ ነጋዴና ግብር የማይገብረውን በህገወጥነቱ አንዲቀጥል የሚያበረታታው ሲሆን በሌላ በኩል ህጋዊና ግብር የሚገብረውን ነጋዴ ፍትሃዊ ውድድር እንዳያድርግ ጫና ፈጥሮበት ቆይቷል:: ስለዚህ ይህንን ለማሻሻል ሲባል በዘርፍ ያለውን አጠቃላይ አሰራር ህጋዊነትን የማለበስ ሥራ በስፋት ተሰርቷል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው ከፍተኛ ችግር የነበረው በመንግስት በድጎማ የሚገቡ የፍጆታ እቃዎች ላይ የነበረው ክፍተት ነው:: ከዚህም ውስጥ አንዱ የዳቦ ማሽን የሌለው ነጋዴ ማሽን እንዳለው ተደርጎ ዱቄት ይወስዳል:: ስኳርም ይወጣል ግን የት እንደሚሄድ አይታወቅም:: ዘይትም በተመሳሳይ መንገድ ነው ከህዝብ ጉሮሮ የሚነጠቀው:: በዚህ ረገድም በርካታ አሻጥሮች ነበሩ:: ይህንን ለማሻሻልና ወደ ህጋዊ ስርጫት ለማምጣት ከፍተኛ ርብርብ አድርገናል:: መንግስት በድጎማ የሚያመጣውን ፍጆታ በመሃል ላይ ያሉ ህገወጦች የሚከብሩበት ሳይሆን ለህዝብ በቀጥታ ሊደርስ ነው ሚገባው ብለን ስንገመግም ክፍተቱን ለማየት ጥረት አድርገናል:: የሚገርሙ ውጤቶች መጥተዋል::
አዲስ ዘመን ፡- ሌላው በህዝብ ላይ ከፍተኛ ምሬት ሲፈጥር የቆየው የከተማዋ የጥራንስፖርት አገልግሎት አሰራር ነው:: በዚህ ረገድ ምን አይነት ተጨባጭ ስራዎች ተሰርተዋል?
አቶ ሃይሉ፡- ልክ ነው፤ ስራችንን እንደጀመፈርን ከፈተሸናቸው አገልግሎቶች መካካል የትራንስፖርት ዘርፉን ተጠቃሽ ነው:: በቅድሚያ በዘርፍ ያለውን ችግር በጥናት ለመፈተሸ ጥረት አድርገናል:: ይህ ዘርፍ እውነቱን ለመናገር የተጣለ ሴክተር ነው:: በዚህ ዘርፍ በዋናነት አራት አይነት ችግሮች መኖራቸውን ገምግመናል:: በዚህም ዘርፍ ህገወጥነት፣ ሙስና፣ አቅም ማነስ፣ በቤተሰብና እውቅና ቅጥር የመፈፀም ሁኔታዎች መኖሩን ነው ያየነው:: በተለይም ይህ ዘርፍ የሚሰጠው አገልግሎት ቀጥታ ከህዝብ ጋር ስለሚገናኝ ብዙ የቁጥጥር ችግር ይስተዋልበታል:: የትራንስፖርት ማህበራቱ በቅጡ የሚመሩ አልነበሩም:: መኪና የሌለው ማህበር ውስጥ ገብቶ ቦርድ የሚሆንበት አጋባብ ነው ያለው:: በሁሉም ሴክተር ትልቁ ችግር ወደ ውስጥ ተመልክተን ለመፍታት ዝግጁ ያለመሆን ነው:: አመራሩም፤ ባለሙያውም ራሱን እንዲፈትሽ የማደረግ ስራ አስቀድመን የሰራነው:: በተለይም ችግሩ የሚጎለበትን ግለሰብ ከቦታው ላይ የማንሳት ስራ ተከናውኗል:: በእነዚህ ስራዎቸው ላይ የተሸሉ ጅምሮች አይተናል::
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋን ደረጃዋን የጠበቀች ከማድረግ አካያ በበጀት አመቱ በእቅድ የተያዙ ስራዎች ምን ደረሱ?
አቶ ሃይሉ፡- እንደሚታወቀው አደማ ትልቅ በጀት ከሚያንቀሳቅሱ ከተሞች አንድ ናት:: ወደ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በአመት እንዲሰበስብ ይጠበቃል:: ከዚህ ውሥጥም 1ነጥብ 8 አካባቢ ከተማው ላይ ለተለያዩ ስራዎች ኢንቨስት ይደረጋል:: ስለዚህ ዘንድሮም ይህንን ገቢ መሰብሰብ አንዱ ትልቁ ስራ ብለን ነው የወሰድነው:: ለዚህም ማህበረሰቡን በስፋት ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሚገኘው ገቢ በሚገባው ልክ ከተማዋን ማልማት አለበት ብለን አቅጣጫ አስቀምጠናል:: ከዚህ አንፃር በርካታ የልማት ስራዎች በሁለት መልኩ ነው እየሰራን ያለነው:: አንዱ መንግስት ራሱ አቅዶ የሚሰራው ሲሆን ሁለተኛው በህዝብ ተሳትፎ የሚሰራ ነው:: እነዚህ ስራዎች በአጠቃላይ 86 የሚሆኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ:: ከዚያ ውስጥ 24ቱ ያደሩና በተፈጥሮዋቸው ተንከባለው የመጡ ናቸው:: ከእነዚያ ውስጥም ዘንድሮም የሚጠናቀቁ አሉ:: 13 የሚሆኑት ደግሞ ተጠናቀዋል:: በነገራን ላይ 66 የሚሆኑት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ናቸው:: ከዚያ ውስጥም 20 የሚደርሱትን አጠናቀናል::
አዲስ ዘመን፡- ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል ጥቂቶቹን ቢጠቅሱልን?
አቶ ሃይሉ፡- ዘንድሮ አንዱ ለውጥ ያመጣበት ጉዳይ የፕሮጀክት ስራ ነው:: በጊዜ ጨረታ አውጥተን በጊዜ ወደ ስራ ገብተናል:: በዚህም እስካሁን 15 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገድ ተሰርታል:: የከተማ አስተዳር ቅጥር ጊቢ በግርግሩ ምክንያት ተቃጥሎ የነበረ ሲሆን በ40 ቀናት ውስት ሙሉ ለሙሉ በአዲደስ መልክ ገንብተን ለከተማዋ ነዋሪ ተገቢውን ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች እየሰጠን እንገኛለን:: እንዳልኩሽ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል:: ትኝሽ ዘግይተን የጀመርነው የኢፋቦሩ ትምህርት ቤቶችን ነው:: እነሱንም ባለን ግምገማ የተሸለ ደረጃ መሆናችንን አይተናል:: በዚህ ፕሮጀክት እጥረት የተከሰተውም በፋይናስ አካሄዱ መሰረት ገቢው ዘግይቶ ስለሚመጣ ነው:: በዚህ ምክንያት ስራውን ያዝ ያደረግንበት ሁኔታ አለ::
አዲስ ዘመን፡- በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ካሉት ስራዎች መካከል ጥቂቶቹን ቢጠቅሱልን?
አቶ ሃይሉ፡- እንግዲህ አስቀድሜ የገለፅኩልሽን በጎ ጅምሮች ይዘን ነው ወደ ህዝብ የገባነው:: ወደ ህዝብ ስንገባ 15 የሚሆኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ፤ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ በህዝብ የሚሰሩ ናቸው:: እነዚህ አስቀድሜ ካነሳሁልሽ በመንግስት ከሚሰሩት ፕሮጀክቶች ውጭ ናቸው:: ለምሳሌ አንዱ አባገዳ ፓርክ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ መጥታችሁ ብታዩት የሚገርም ፓርክ ሆኖ ነው የምታገኙት:: በዚህ ፕሮጀክት እንጦጦ ፓርክን እዚህ ለማምጣት ነው እየተሞከረ ያለው:: ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንደሚሉት በትኝሽ እንጀምራለን ትልቅ እናደርጋለን ብለን በመነሳት በትንሹ ጀምረናል:: በእርግጥ አሁን ላይ በተወሰነ ሄክታር ላይ ነው የጀመርነው:: ይህ ፕሮጀክት የሚገነባበት ስፍራ ከተማዋን የምታዩበት ወደ ፊት ትልቅ የቱሪስት መስህብ ይሆናል ብለን ያሰብነው የልማት ስራ ነው:: ሥራው በህዝብ ተሳትፎ የሚሰራና ለከተማው ወጣቶች ሥራ እድል የሚፈጥር ነው:: አጠቃላይ ስራው እስከ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ይፈጃል:: ወደፊት ግን እያሳደግነው ስለምንሄድ እስከ አራት ሚሊዮን ብር ያስፈልገናል ብለን እናምናለን::
ሌላው አዳማ ደረጃውን የጠበቀ መግቢያ በር እስከዛሬ የላትም:: ዘንድሮ በያዝነው እቅድ መሰረት ሶስት መግቢያ በሮች ለመስራት አስበን እየሰራን ነው የምንገኘው:: አንደኛው ከአዲስ አበባ ሲመጣ አዲስ አበባን ባህልና እንጦጦን በሚያፀባርቅ መልኩ ዲዛይን ተሰርቶ ነው የሚገነባው:: በተመሳሳይ ከአሰላ ሲመጣ እነሶፍ ኡመርንና አትሌቶችን የሚያሳይ፣ የሃረር በር ደግሞ ሃርርን ከሚያንፀባርቁ ነገሮች አንዱ የሃረር ጅብ እንደመሆኑ ያንን የሚያሳይ ነገር ለመስራት ነው የታሰበው:: በነገራችን ላይ ለአንዱ ብቻ 1ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ነው የሚያስፈልገው:: ሶስቱም በባላሃብቶች ነው የሚሰራው::
ከዚህም ባሻገር እንግዲህ በአዳማ ከተማ ትልቁ የምታዩት መንገድ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም:: ዘንድሮ አስቀድሜ አንዳልኩሽ በግምገማችን በህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኘው ዋናው የአስፋልት መንገድ ነው:: ይህንን ከተማ ተወዳደሪ ለማድረግ ከተፈለገ የግዴታ የዚህን መንገድ ሳታንዳርድ ማስተካል ያስፈልጋል:: በዚህ መሰረትም በአሁኑ ወቅት አስፋልቱን የማስፋትና የእግረኛ መንገድ ስራ ጀምረናል:: ከኮብልስቶን ወደቴራዞ እንቀይር ብለንም መንገዱን እያሰፋን ነው:: በመሆኑም እስካሁን ከአባገዳ ጀምሮ እስከ ደራርቱ ጎዳና የሚባውን መንገድ ማስፋት ችለናል:: ይህም ሶስት መኪና በአንድ ጊዜ ማስኬድ የሚያስችል ሲሆን ግራና ቀኝ የእግረኛ መንገድ እንዲኖረው ተደርጋል:: ስታንዳርድ ያለው ዲዛይን የተጠቀምን ሲሆን አረንጓዴ ስፍራንም ያካተተ ነው:: ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ በሚባል ወጥበራ ተነሳሽነት ነው እየተሰራ ያለው::
በህዝብ ሌላ የሚሰራው የቀድሞው ባቡር ሃዲድ ዙሪያ የፓርክ ስራ ጀምረናል:: ሃዲዱ ዙሪያ የነበረውን ቆሻሻ የማፅዳትና ታሪካዊ ይዘቱን ሳይቀይር ዙሪያውን ያማሳመር ስራ ነው የተሳበው:: ለዚህም ሶስት ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሎ ነው የተገመተው::፡ ይህንንም በግል ባለሃባቶችና በህዝብ ትብብር ነው እየተሰራ ያለው:: ይህ ፕሮጀክት ሶስት ሎት ያለው ሲሆን እስካሁን ሁለቱ ባለቤት አግኝተዋል:: ይህም አካባቢውን ከማስዋብ በተጨማሪ የከተማው ነዋሪ መዛኛኛ ስፍራ የሆናል ብለን ነው የምንጠብቀው:: አሮጌውን ባቡር የምናሳይበት የአርትቴክት ስራዎች አሉ::
ከዚህም ባሻገር የከተማዋን የታሪክ ፍሰት ለማሳለጥና መጨናነቁን ለመቀነስ በአደባባች ላይ ሁለት መሸጋገሪያ ድልድችን ለመስራት አቅደናል:: ከዚያ ውስጥ አንዱ ባለቤት አግኝቷል:: እንዳአጠቃላይ በጥቂቱ እየጀመርን የከተማው ህዝብና ባለሃብት ድጋፍ ከተማዋን ደረጃዋን የጠበቀች የቱሪስት መዳረሻ ለማደረግ ነው እየሰራን ያለነው:: በየቦታው ከተማዋን የሚያሳዩ ስክሪኖችን
የሚሰቀሉ ይሆናሉ:: በተጨማሪም ወደ ስድስት የሚሆኑ ወጣት ማዕከላትም የሚገነቡ ሲሆን እያዳንዳቸው 25 ሱቆች የሚኖራቸው ይሆናል:: ከዚህም ባሻገር ዘንድሮ ብቻ 68 መማሪያ ክፍሎች በህዝቡ ትብብር ተሰርተዋል::
ከዚህ ተነስተን ህዝቡ እስከ ስድስት ወር ባለው እንቅስቃሴ የጀመራቸው ሥራዎች በጣም የሚያበረታቱ ናቸው:: ከዚህም በላይ ከተማዋን እድገት ወደላቀ ደረጃ ያደርሳታል ተብሎ ይገመታል:: አጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪ ሁሉ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥና ከተማውን ወደ ተሻለ እድገት የሚያደርሳት ሲሆን ሁሉም በሰራው መጠን የሚያገኝበት ስርዓት ለመፍጠር ነው ጥረት እያደረግን ያለነው:: 15 ኪሎ ሜትር ኮብልስቶን መንገድ አስፍተን ሰርተናል:: ይህም ነዋሪው በቀላሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆንለት ከማስቻል ባሸገር ቡና ለሚያፈሉ ወጣቶች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል::
ሌላው ሳልጠቅስ ያለፍኩት ብዞዎቹ ደብዛቸው እየጠፋ የመጣበት ሁኔታ አለ:: በግምገማችን ብዙዎቹ የመንግስት ቤቶች ካርታ እንደሌላቸው ነው የተረዳነው:: እስካሁን ባለው ግምገማ ወደ 11ሺ የሚደርሱ የመኖርያና የንግድ ቤቶች መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል:: ከዚያ ውስጥ ዘንድሮ ብቻ ስድስት ሺ ለሚሆኑት ካርታ ተሰርቶላቸዋል:: ለቀሪዎቹም መቶ በመቶ በቅርቡ ሰጥተን እንጨርሳለን ብለን እንገምታለን:: በአጠቃላይ በምንሰራቸው ስራዎች ህገወጥነትን መቀነስ፣ ህጋዊ አሰራሮችን ማጎልበት የሚሉትን ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ያለነው:: እነዚህ ስራዎችንም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ህዝቡን ማሳተፍ፣ ህዝቡን ከህገወጦች ራሱን እንዲጠብቅና ከተማዋን እንዲያሳድግ እየተረባረብን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- አስተዳደሩ ለህዝቡ የሚሰጣቸው አግልግሎቶች ምን ያህል እርካታን ፈጥረዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ሃይሉ፡- ከዚህ ተነስተን በአጠቃላይ ያለንበት ሁኔታ በሁሉም ዘርፍ ማለትም በትምህርት፣ በጤና፤ በማዘጋጃቤት አገልግሎት እንዲሁም ‹‹ስማርት ሲቲ›› ብለን የጀመርናቸው ስራዎች ሁሉ ውጤት እያመጣን ነው:: በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ህዝቡ የሚያለቅስባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት አንዳንድ አሰራሮችን ዘርግተናል:: ሃሙስ ሃሙስ እኔ ሌላ ስራ የለኝም:: የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ያለበት ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ በአዳራሽ ውስጥ ችግሩን የምናዳምጥበትና የመፍትሄ አቅጣጫ የምንሰጥበትን አሰራር ዘርግተናል:: በቀን እስከ 70 ሰዎችን እናስተናግዳለን:: ሃሙስ ላይ እኔ ባለሁበት ማክሰኞ ደግሞ በየክፍለከተማው እንዲሁም ሰኞ ቀበሌ ላይ ይኸው የህብረተሰቡን ችግር የምናደምጥበትና የምንፈታበት ስርዓት ተበጅቷል:: ባለፉት ስድስት ወራት በዚህ አሰራር ብቻ ሴክተሮች ከሚመልሱት ውጪ ከ1ሺ 198 በላይ ችግሮች ተለይቷል:: ከዚህ ውስጥም 803ቱ መልስ አግኝተዋል:: በዚህ አጋጣሚ ይህንን ስርዓት መዘርጋት በመቻላችን ህዝቡ የሚያነሳው ቅሬታዎች በአብዛኛው ትክክል መሆናቸውን ለማየት ችለናል:: እውነተኛ ሕዝብ ቅሬታ መኖሩን ራሳችንን የመገምንበት ሁኔታ ነው ያለው:: እኛም የተማርንበት መድረክ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሳምንታዊ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍቻ መድረክ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ከማስፋ አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ሃይሉ፡- ትልቁ ነገር ብዬ የማስበው እኛ የመንግስት ሰራተኞችና ሓላፊዎች እዚህ ቦታ ላይ የምንቀመጠው ህዝብን ለማገልገል መሆኑን በአግባቡ መረዳቱ ላይ ነው:: ማደግና ይህችንን አገር ማበልፀግ የምንፈልግ ከሆነ የህዝብ ውግንናችንን በተጨባጭ ማሳየት ይገባናል:: የአገልጋይነት ስነልቦና ተላብሶ ከመስራት አኳያ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰፊ ክፍተት አለ:: እያንዳንዱ ሰው ሃላፊዎችን ለማግኘት ብቻ የሚያባክነው ጊዜ የሚደርስበት እንግልት በጣም የሚያሳዝን ነው:: በነገራችን ላይ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ በግሌ አንድ ወር ጥናት አድርጌ ነው ወደ ስራ የገባሁት:: ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሰረት ሰዎችን ቢሮ ውስጥ አንድ በአንድ ሳነጋግር ችግር እየፈታሁ አለመሆኑን ተገነዘብኩኝ:: በተለይም ደግሞ ሁሉም ነገር በእኔ ብቻ የማይፈታ በመሆኑ የግድ ሴክተሮችንም የሚያሳትፍ መድረክ ማመቻቸት እንደሚገባኝ አመንኩኝና ነው ወደ ስራ የገባነው:: እንደከተማው ከንቲባ የእኔ ድርሻ ማስተባበር ነው:: ቀን ተለይቶለት የህዝቡን ችግር የምናደምጥበትን መድረክ ነው የፈጠርነው::
ይህ መድረክ እንደተፈጠረ የሚገርሙና ለዘመናት የታፈኑ ድምጾችን ነው የሰማነው:: ውይይት የምናደርግበት ስፍራ በአንድ ጊዜ 25 ሰዎችን የሚያስተናግድ አዳራሽ ሲሆን ሁሉም የሚመለከተው ሃላፊ ባለበት ችግሩ ይደመጣል:: የችግሩን ምንጭ ለመለየት ጥረት እናደርጋለን:: ሁሉም የሚመለከተውን ችግር እየለየ በባለቤትነት ይወስዳል:: በሚቀጥለው መድረክ ስንገናኝ ማን? ምን? እንደሰራ ፈት ለፊት እንነጋገራለን:: ይህም ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሻጥሮችን በቀጥታ እንዲፈቱ ከማድረጉም ባሻገር የግልፀኝነት ባህል እንዲዳብር ያደርገዋል:: ከዚህም በተጨማሪ ልክ እንደህዝባዊ ችሎት ፊት ለፊት በመወያየታችን አንዱ ለሌላው ምስክር የሚሆንበትን እድል ያገኛል:: ከዚህም ባላፈ ቃል ገብቼ ያልፈፀምኩትም ነገር ካለ እነዚያን ሰዎች በምስክርነት ይዘው በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊከሱኝ ይችላሉ:: ለእኔ ከቁጥሩም በላይ ለህዝቡ ተደራሽ መሆኑ ብቻውን ለህዝብ አንድ እፎይታ ነው:: ከዚህም ባሻገር በህዝብና በመንግስት መካከል የነበሩ ብዙ ደላሎች ከውስጡ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታን ፈጥራል:: መንግስትንና ህዝብን የሚያጋጩ እንዲጋለጡ ያደርጋል:: ማንኛው ሰው እዚህ ሲመጣ ስሙም ሆነ መታወቂያው ተመዝግቦ በመሆኑ ማን መቼ መጣ? ምን ይዞ መጣ ? የሚለው ነገር ስለሚመዘገብ ውሸት የሆነው ይጋለጣል:: ይህ በመሆኑ ህዝቡ በቀጥታ ፊት ለፊት ከመንግስት ጋር እንዲገናኝ እድል ከፍቷል::
በሁለተኛ ደረጃ ሁሉም ሴክተር እዚህ በመገኘቱ ያለውን ነገር ሁሉ ህዝቡ እዚህ አራግፎ ይሄዳል:: ይህም እኛም እንድናስብ እድል ሰጥቶናል:: መመሪያ ማንበብ፤ አዋጆችን ማወቅ አለብኝ :: ካልሆነ መልስ መስጠት አልችልም:: ባለሙያውም የሚሰራውን ነገር በጥንቃቅ እንዲሰራ ያደርገዋል:: በፊት ህዝቡ የሚገናኝበት መድረክ የሌለ በመሆኑ በገንዘባቸው ነበር አገልግሎት ለማግኘት የሚሞክሩት:: አሁን ግን የሚናገሩበት እድል ስላገኙ በሙሉ እምነት ነው መብታቸውን እየጠየቁ የሚገለገሉት::
በተጨማሪም ባለጉዳዮችን ለማናገር የሚባክነው ጊዜ እንዲቀርና በአግባቡ ስራ እንዲሰራ ያደርጋል:: በመሆኑም ምንም እንኳን ችግሮቹ ብዙ ቢሆኑም ጥቂት የማይባሉትን መፍታት ችለናል:: እኛ ደብቀን የምንሰራው ነገር የለም፤ ያለነው ህዝብን ለማገልገል ነው:: ይህ መድረክ ህዝብና መንግስትን ለማቀራረብ ፍቱን መድሃኒት መሆኑን በተግባር ስላረጋገጥን ነው ወደ ክፍለከተማና ወረዳ ደረጃ አሰራሩ እንዲወርድ ያደረግነው:: አስቀድሜ አንዳልኩሽ ከቁጥርም በላይ ትርጉሙ ትልቅ ነው:: ይህንን አሰራር በመዘርጋታችን ብቻ ችግር ከመፍታት ባለፈ ጊዜንና ጉልበትን በመቀነስ ረገድ የጎላ ድርሻ እየተጫወተ ነው:: ይህ ተሞክሮ ልሎች አካበቢዎች ወስደው ቢሰሩት ጥሩ ነው የሚል ምክር አለኝ::እኛ ለውጥ አምጥተንበታል::
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ከማስጠበቅ አኳያ ምን አይነት ስራዎች ተሰርተዋል?
አቶ በፍቃዱ፡- እንደአጠቃላይ አገር ማለት እያንዳንዱ ሰው ስብስብ ድምር ውጤት ነው:: በመሆኑም በየሴክተሩ ያለን ሃላፊዎች ሀገራዊ ሁኔታውን ተረድተን ከሰራን ሀገራዊ ተልዕኮን የማናሳካበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም:: ስለዚህ በየአካበቢው በተለይም እንደአዳማ በርካታ ብህር ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸው ከተሞች በህዝብ መካከል በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኑኝነት እንዲኖርና እንዲያብብ መትጋት አለብን ብዬ አምናለሁ:: ከዚህ ተፃራሪ የሆኑ ጉዳዮችን በማራቅ በህዝቡ በጋራ ወደ ልማት አንዲንቀሳቀስ ማድረግ ይጠበቅብናል:: በተጨማሪም እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ፍትሃዊ አሰራሮች መዘርጋት ይገባናል:: በመሆኑም አዳማ ባለፉት ስድስት ወራት አንፃራዊ ሁኔታ ሰላም የሰፈነባትና ህብረተሰቡ በሰላም ውሎ የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥራል:: በዚህ ውስጥ ህዝቡ በነቂስ የተሳተፈበትና አስተዋፅኦ ያበረከተበት ሁኔታ ነው ያለው:: እንደምታውቂው አደማ ላይ አሁን በርከት ያለ የህዝብ ፍሰት ይሰተዋላል:: ሁሉም ሆቴል በሚባል ደረጃ በየቀኑ በስብሰባዎች የተያዘ ነው:: ይህም የሰላም ውጤት ነው:: ህዝቡ ከፀጥታ መዋቀሩ ጋር ሆኖ በመስራቱ ነው::
በሌላ በኩል አገራዊ ሁኔታውን በመረዳት በአገር ደረጃ የተቀረፁ የልማት መርሃ ግብሮችን በከተማችን ልክ ቀርፀን ስራ ላይ ማዋልንም ያትታል :: ከዚህ አንጻር አንደክልልም ሆነ በአገር ደረጃ አሳፋሪ ሆኖ የቆየንበት ጉዳይ በምግብ እህል ራሳችንን ያለመቻላችን ነው:: በተለይም ለምና ምቹ የአየር ሁኔታ እያለን ስንዴ ዛሬም ድረስ ከውጭ የማስመጣችን ጉዳይ እኔ በግሌ በአስነዋሪ መልኩ ነው የማየው:: ከዚህ አንፃር ክልሉ ያቀደው እንዳለ ሆኖ በከተማችን ብቻ ዘንድሮ 155 ሄክታር ስንዴ በመስኖ ዘርተና:: ይህም እኛም የድርሻችንን መወጣት አለብን በሚል የገባንበት ነው:: ከከተማው በጀት ቀንሰን አስፈላጊውን ግብዓት አሟልተን ነው ወደ ስራ የገባነው::
አዲስ ዘመን፡- ችግሮችን በፊትለፊት እንዲፈቱ ከማድረጉ ስራ ባሻገር ያጠፉ አካላት የሚጠየቁበት አሰራር ተዘርጋቷል? ከሆነስ ምን ያህሉን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል?
አቶ ሃይሉ፡- በነገራችን ላይ አሁን በዘረጋነው አሰራር መሰረት ተጠያቂነት በየቀኑ አለ:: ለምሳሌ አንድ አመራር ዛሬ የወሰደውን ስራ ነገ የት እንደደረሰው ይጠየቃል:: አሰራርና መመሪያ ጥሶ የሚሰራውም የሚጠየቅበት አግባብ አለ:: እስካሁንም ህግ ጥሰው የተገኙ የታሰሩ አሉ:: አሁን ላይ ግን አጠቃላይ አሃዝ ምንያህል እንደሆኑ ልነግርሽ አልችልም:: ግን ደግሞ ለአብነት ያህል ብጠቅስልሽ በመሬት አስተዳደር ቢሮ አካባቢ አሰራርና መመሪያን ጥሰው የተገኙ ከ10 በላይ የሚሆኑ አካላት ተጠያቂ እንደሆኑ አውቃለሁ:: ለእኛ ግን ትልቁ ጉዳይ በየቀኑ ሁሉም ተጠቂነትን ማዕከል አድርጎ ስራውን በጥንቃቄ እንዲሰራ ማድረጉ ነው:: ራሳችንን በዚህ ደረጃ ስንገመግም በየቀኑ መማር እንደሚገባን አይተናል:: ከዚሁ ጎን ለጎን ከአንድ ሺ በላይ ህገወጥ ግንባታዎች እንዲፈርሱ አድርገናል:: እንዳልኩሽ ግን በዋናነት ለህዝብ የቆምን መሆናችን በተግባር በሃላፊነት መስራታችን ላይ ነው:: ይሕንን ካደረግን እየቀነስን እንሄዳለን የሚል እምነት አለን:: እያስተማርን ካልሆነ ደግሞ ሶስተኛ የመንግስት አካል አንዲመረምር የሚደረግ ነው የሚሆነው:: በተጨማሪም በብልሹ አሰራርም የሚታዩና የታሰሩ አሉ::
አዲስ ዘመን፡- እንደአገር ተቃጥቶ በነበረው የመፈራረስ አደጋን ከመቀልበስ አኳያ በመንግስት የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ለእርሶ ምን ትርጉም አለው? እየተሸረሸረ የመጣውን የአገር ፍቅር ስሜት ለማጎልበት የከተሞች ሚና ምንድን ነውስ ይላሉ?
አቶ ሃይሉ፡- መጨረሻ ላይ ከጠየቅሽኝ ጥያቅ ልነሳና በእኔ እምነት ትውልዱ ውስጥ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረውና ከወገኖቹ ጋር በፍቅርና በሰላም ለመኖር በመጀመሪያ እያንዳንዱ ሰው ራሱን መውደድ አለበት ብዬ አምናለሁ:: ራሱን የሚወድ በእርግጠኝነት አገሩን ይወዳል:: ራስ መውደድ ማለት ለራስ ዋጋ መስጠት ማለት ነው:: እኔ አየር ላይ ስለማልኖር ወይም ሌላ ፕላኔት ላይ ስለማልኖር ለምኖርባት ምድር ደግሞ መጨነቅ አለብኝ:: ሁሉም ራሱን መውደድ አለበት:: ቤተሰቡን አካባቢውን መውደድ አለበት:: ይህች አገር ለማንም የምንተዋት አይደለችም:: አባቶቻችን ኢትዮጵያን ዋጋ ከፍለው እዚህ አድርሰዋል:: ክፍተት ይኑረው፤ አይኑረውም በሰላም ይህችን አገር አቆይተውልናል:: ሃላፊነት አለብን:: አገራችን ደሃ ነች:: ግን ደግሞ በርካታ አማራጮች አሏት:: አገርን ወደን እየሰራን ህዝብን ማስተማር አለብን:: ምክንያቱም ሌላ አገርም በትምህርትና በስራ አጋጣሚ ያየኋቸው አገራት መበልፀግ የቻሉት ራሳቸዉን ብሎም አገራቸውን የሚወዱ ዜጎችን ማፍራት በመቻላቸው ነው:: አገራችንን እንደአይናችን ብሌን አይተን ለእድገቷና ብልፅግናዋ መስራት መቻል አለብን:: ስለዚህ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቤተሰቡን ተንከባክቦ ሃላፊነት አይቶ የሚሰራ ከሆነ አገር ትበለፅጋለች:: ግን ደግሞ ብልፅግና በፉከራ አይመጣም:: መስዋትነትን ይጠይቃል:: ምንአልባት ከሚገፉን ነገሮች ራሳችንን መቆጠብ ይገባናል:: ይህች አገር ለሁሉም ትበቃለች፤ ዋናው በፍቅርና በመቻቻል ተባብረን መስራትና መለወጥ ይገባናል::
በነገራችን ላይ ሁላችንም አገርንና ፖለቲካን ነጥለን ማየት መቻል አለብን:: በአለም ላይ ያሉ ርዕዮተአለሞች እንደየሁኔታዎቻቸው የጠቀሙዋቸውን ያህል ጉዳት ያመጡ አሉ:: ፖለቲከኞች መገንዘብ አለብን ብዬ የማስበው አገር ከፓርቲም ሆነ ከግለሰብ ፍላጎት ትበልጣለች:: መንግስታት ይቀያየራሉ፣ አገር ትቀጥላለች:: ሰዎች ያልፋሉ፤ አገር ትኖራለች:: ስለዚህ አሁን ያለው ትውልድ አገሪቱን እንደፈለግነው እንድናደርግ አልተፈቀደልንም::ለሚቀጥለው ትውልድ በአግባቡ ጠብቀን የሚገባንን ያህል ብቻ ተጠቅመን የማስገባት ሃላፊነት አለብን:: የተፈጥሮ ሃብቱን በሚገባ ካልተጠቀምን ምንአልባት ለሚቀጥለው ትውልድ ተወቃሽ እንሆናለን:: እኛ በእድገት ወደ ኋላ ብንቀርም ካደጉት አገራት ስህተት መማር መቻል አለብን::
ሌላው የህግ ማስከበር ሂደቱ ብዙ ተብሏል:: ምንምአልባትም በእኔ ግምገማ በጣም አስተማሪና ብዙ ሰዎች ሲገምቱት ከነበረው ፈጥኖ የተጠናቀቀ የህግ ማስከበር ስራ ነው ማለት ይቻላል:: በዚህ ውስጥ መሪዎቻችን ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል:: በሌሎች ስራዎችም መማር መቻል አለብን:: ብዙ አስተማሪ ነገሮች የታዩበት፤ ሰራዊታችን ለህዝብ ሲል ዋጋ የከፈለበት ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ የተጠናቀቀ መሆኑ አስተማሪ ያደርገዋል:: ለዚህ ደግሞ መሳካት የህዝቡ ተሳትፎ አይነተኛ ሚና ነበረው ማለት ይቻላል:: በመካላከያ ሰራዊታችን ላይ በደረሰው ጉዳት ህዝቡን በጣም አስቆጥቷል:: ስለዚህ የዚህ ውጤት የሚመስለኝ ሕዝቡ በቅን ልቦና በመሳተፉ የመጣ ነው የሚመስለኝ:: አጠቃላይ ሂደቱ በጥበብ የተመራ ነው:: እርግጥነው ብዙዎቻችን ባይሆን የምንወደው፤ ግን ደግሞ ከመጣ በኋላ በጥበብ የተመራበት አግባብ በእርግጥም አስተማሪ ነው:: በህግ ማስከበሩ ያየነውን ጥበብና ትብብር ድህነትን ለማሸነፍም መድገም ይገባናል ብዩ አምናለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ሃይሉ፡- እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ በከተማችን የልማት ስራ ዙሪያ ማብራሪያ እንድሰጥ እድል ስለሰጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ::