ኢያሱ መሰለ
የፍልስፍና አባት የሆነው አርስቶትል የሰው ልጅ ፖለቲካዊ እንሰሳ ‹‹political animal›› እንደሆነ ይናገራል። ሰው ማህበራዊ መስተጋብሩን ለማቀላጠፍ የተለያዩ ጉዳዮችን በጋራ ያከናውናል።
ሀገር መስርቶ መንግስት ያቋቁማል፤ ህግና መተዳደሪያ ደንቦችን አጽድቆ ስራ ላይ ያውላል፤ በአጠቃላይ አንድ ሀገር፤ ሀገር ሆኖ ከተመሰረተ በኋላ በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እልባት ለመስጠት የሚያስቸሉ መዋቅሮችን ይዘረጋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን በመከተል ህዝቦቻቸውን ያስተዳድራሉ። አንዳንድ ሀገሮች ከዓለም ስልጣኔ እና እድገት ጋር በመራመድ አንዳንዴም ቀድሞ በመሄድ የአስተዳደር ስርዓታቸውን እያዘመኑ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው እድገት የሚበጀውን ቀና መንገድ ያሳያሉ፤ ሎሎች ደግሞ ከሚያስተዳድሩት ህዝብ እጅግ ወደ ኋላ ርቀው፤ ከዘመናዊ አስተሳሰብና አሰራር ተጣልተው፤ ስለ ሀገራቸው እና ህዝባቸው እድገት ሳይሆን ስለ ግል ስልጣን እና ጥቅማቸው ብቻ በማሰብ ወደ ፊት መራመድ የሚፈልገውን ህዝብ ቀይደው ይይዙታል።
በእነርሱ የግል ፍላጎትና ጥቅም ምክንያት የሀገር እድገት ይቀጭጫል፤ የህዝቦች ተስፋ ይጨልማል። ዘመኑን ባልዋጀ የፖለቲካ ፍልስፍ ላይ ተቸንክረው የሚቀሩ መሪዎች ግጭታቸው ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘመንም ጋር ይሆናል። በድሮ በሬ ማረስ የሚቻለው ያኔ ነው፤ እነዚያ በሬዎች ዛሬ በህይወት የሉም። አርደን በልተናቸዋል ካልሆነም አርጅተው ሞተዋል።
ዛሬ ባሉት በሬዎች ማረሳችንን ትተን የጥንቶቹን እየጠበቅን ቁጭ የምንል ከሆነ ሳናጣ እንራባለን። ሁል ጊዜ እልፍ ብለን ማሰብ ይኖርብናል። እልፍ ብለን ስናስብ የዛሬዎቹን በሬዎች የሚተኩ ትራክተሮች መኖራቸውንም እናስተውላለን።
ዘመን ያኮርፋል፤ ዘመን ይጣላል፤ ዘመን አንቅሮ ይተፋል። መጨረሻ ላይ ‹‹ዘመን ቢጥላት፣ ቀን ቢያዋርዳት፣ ድመታችንን አይጥ ወሰዳት›› የሚለውን ምሳሌያዊ ንግግር እየተረቱ መቀመጥ ብቻ ይመጣል።
የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው ሊዮ ስትራውስ “የፖለቲካ ፍልስፍና ምንድን ነው / What is political philosophy›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሁፉ የሚያስረዳን የፖለቲካ እውቀት በነበረው እሳቤ ላይ ተወስኖ የማይቆምና በየጊዜው ፈጣን ለውጥ የሚታይበት መሆኑን ነው።
ከዚህ አንጻር ፖለቲከኞች በተለይም አፍሪካውያን መሪዎች ራሳቸውን ከዓለም ግስጋሴና ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር እያጣጣሙ ከመሄድ እንጻር ያሉበትን ደረጃ ስንመለከት ያሳፍራል።
በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወንበራቸውን የያዙ ወይም የለቀቁ የአፍሪካ መሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ባልተገባ መንገድ ስልጣን ይዘው በመጡበት አኳኋን ከስልጣን የሚወገዱ ናቸው።
አሁን አሁን የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ሲሉ እራሳቸው ያጸደቁትን ህገ መንግስት እራሳቸው ሲጥሱ ወይም በሚመቻቸው መንገድ ሲያሻሽሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ለአብነት የአይቬሪኮስት፣ የኮንጎ፣ የኡጋንዳ፣ የቡርንዲን መሪዎች ውሳኔ ማስታወስ በቂ ነው።
ኢትዮጵያን ከልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግስት እሰከ ኢህአዴግ አስተዳደር ድረስ ጤናማ የስልጣን ሽግግር አላደረገችም። ልጅ ኢያሱን አጼ ሃይለ ስላሴ፤ አጼ ሃይለስላሴን ደርግ፤ ደርግን ኢህአዴግ ከስልጣን ያስወገዷቸው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን በደባ እና በጡንቻ ነበር።
ሀገሪቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩት መሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦና ያሳደሩት ተጽእኖ መኖሩ ባይካድም እርባና ቢስ በሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና እየተመሩ የሀገሪቱን ዝብርቅርቅ ሁኔታ ውስጥ መክተታቸው የሚካድ አይደለም። ያለፉትን ስርዓተ መንግስቶች ለታሪክ እንተዋቸውና ባለንበት በዚህ ዘመን ስላየነው እናውራ።
የኢህአዴግን ካባ ተጎናጽፎ ህዝቦችን ለማለያየት እና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲተጋ የነበረው ጁንታ ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት እና ከስልጣልን ላይ ከተወገደ ጥቂት ዓመታት ወዲህ የነበሩትን ተለዋዋጭ መልኮቹን ከማካቬሊ የፖለቲካ ፍልስፍና አንጻር እንመልከት።
ስለማካቬሌ ብዙ ተብሏል። ለጊዜው ዋለልኝ እምሩ፤ (2009 ዓ.ም) ‹‹የፍልስፍና መንገድ›› በሚለው መጽሐፉ ስለማካቬሌ ፖለቲካዊ እይታ የዘረዘራቸውን አራት መሰረታዊ መለያዎች መነሻ አድርጌያለሁ። ማካቬሌ የፖለቲካ ፍልስፍናውን ከመጀመሩ በፊት ለፍልስፍናው መሰረት የሆኑት የህይወት ተሞክሮዎቹ ነበሩት።
የመጀመሪያው መልካምና ተመስጋኝ መሪ በሰው እጅ ሲጠፋ መመልከቱ፤ ሁለተኛው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሪ ጭካኔ በተመላበት ዘግናኝ ሁኔታ ተቃዋሚን በአደባባይ ገድሎ ሲጥልና ከዚያ በኋላ ያ መሪ ሲፈራ መመልከቱ፤ ሶስተኛ ማካቬሊ ለህዝብ ብሎ ባደረገው ትግል የታገለለት ህዝብ በሀሰት መስከሮ ሲያሳስረው ማየቱና፤ በመጨረሻም ህዝብ ስርዓተ አልበኛ እንደሆነና መሻሻል እንደማያሳይም መገንዘቡ የራሱን የፖለቲካ መስመር እንዲከተል ምክንያት ሆነውታል።
የማካቬሌ ዓላማ በግዜው በክልል መንግስታት ተከፋፍላ የነበረችውን ጣሊያንን ወደ አንድነት ማምጣትና እንደፈረንሳይ ያሉ ሀገራት የሚከተሉትን የአስተዳደር ስርዓት እውን ማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን የተቀደሰ ዓላማ መልካም በሆኑ ህጋዊ ዘዴዎች ማሳካት እንደማይቻል ተረደ።
በሃይማኖት አባቶች፣ በአካባቢ መሪዎች እና በህዝቡም ዘንድ ያለው ችግር በርካታ መሆኑን የተረዳው ፈላስፋው እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በሰፈኑበት ሁኔታ የኢጣሊያንን አንድነት ማምጣትም ሆነ የሰለጠነ የመንግስት ስርዓት መገንባት አይቻልም ብሎ አሰበ። ከዚህ በኋላ እንዴት መምራት እንዳለበት ገጠመኞቹንና ልምዶቹን ቀምሮ ተከታዩቹን አራት የፍልስፍና መርሆዎቹን ስራ ላይ ማዋል ጀመረ።
1. መሪ ሥነምግባርን አሽቀንጥሮ መጣል አለበት
ማካቬሌ ህዝብ ሲከፋ መሪ የበለጠ ክፉ መሆን እንዳለበት አመነ። ይህ ሰው ይህን ሀሳብ ሊከተል የተገደደው ክፉ ሆኖ አይደለም፤ ቀደም ሲል የህዝቡን ክፋት ስለተመለከተ መጥፎ ህዝብ መጥፎ መሪ ያስፈልገዋል በሚል ፍልስፍና ፖለቲካና መልካም ስነምግባር አብረው አይሄዱም የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ነው።
እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ማካቬሌ ስነምግባርን አሸቀንጥሮ መጣል ያስፈልጋል ብሎ የተነሳው የሰለጠነችና አንድነቷ የተጠበቀ ጣሊያንን ለመፍጠር ካለው ጉጉት የተነሳ ነው። እንዲህ ዓይነት የፍልስፍና ድምዳሜ ላይ የደረሰው ያለምንም ይሉኝታ ዓላማውን ለማሳካትና ጣልያንን ለማሻገር በማሰብ ነው።
የእኛ ሀገር መሪዎች ስነምግባርን አሽቀንጥረው የሚጥሉት ግን እንደማካቬሌ ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር አይደለም። ጁንታው ስልጣን ከመልቀቁ በፊትም ይሁን ከለቀቀ በኋላ ስነምግባርን አሽቀንጥሮ የጣለው የሰለጠነችና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሳይሆን በተቃራኒው ለማፈራረስ፣ ህዝቦቿን ለመበታተን፣ ለመዝረፍ፤ ለመዋሸት እና የግል ጥቅሙን ለማሳደድ በማሰብ ነው።
ባለፉት ዓመታት ሀገርን ከሚያስተዳድሩ መሪዎች የማይጠበቁ አስገራሚ የስነ ምግባር ችግሮች እዚህ ሀገር ላይ ተስተውለዋል። በሜቴክ ስም የተመዘበረውን የሀገር ሀብት፣ ያለቀረጥ የሚገቡ እቃዎች፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ዶላርን ማሸሽ፣ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታዎች፣ በህዳሴው ግድብና በትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የተፈጸሙ ዘረፋዎች ወዘተ ለስነምግባር የተሰጠውን ዋጋ ከሚያሳዩ ብልሹ አሰራሮች ጥቂቶቹ ናቸው። ማካቬሌ ሀገሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር ሲል አሽቀንጥሮ የጣለውን የመሪነት ስነምግባር የእኛ ሀገር መሪዎች ሀገራቸውን ለመግደል ተጠቅመውበታል።
2. መሪ የሃይማኖትና የቅድስና ህይወት ሊኖረው አይገባም
የማካቬሌ ፍልስፍና የሚያሳየው ሃይማኖትን ህዝብ ይከተለው እንጂ መሪ ሊከተለውና ሊኖርበት አይገባም ይላል። ማካቬሌ “መሪ ሃይማኖተኛ ከሆነ ትሁት ይሆናል፤ ትህትና ደግሞ ደካማ ያደርጋል” የሚል ፍልስፍናን ይከተላል።
ጁንታው ለሃይማኖት ቦታ አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶችንም በማሳደድና በማሰር ሃይማኖት ቦታ እንዳይኖረው አድርጓል። ኢትዮጵያ መንግስት መስርታ መተዳደር ከጀመረች ወዲህ እንደ ኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጣልቃ የገባ ወይም ጥቃት ያደረሰ የለም። የህብረተሰቡን ስነልቦና ለማዳከምና እርስ በእርስ ለማጋጨት ሃይማኖትን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል።
ግለሰቦችን ለማሰር ሲል መስጊዶች ላይ ቦንብ አፈንድቶባቸዋል፤ አብያተ ክርስቲያኖች ተቃጥለዋል። በገዳም የሚኖሩ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ያለበደላቸው ታስረዋል አንዳንዶቹም ተገድለዋል። በምዕመናን የሚወደዱና ተሰሚነት ያላቸው የየእምነቱ ታወቂ ሰዎች ጽንፈኛና አሸበሪ እየተባሉ ወህኒ ተወርውረዋል። እኛ እናውቅላችኋለን ብለው ያለ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ የማይፈልጉትን አውርደው የሚፈልጉትን ሾመዋል።
በዚህም አንዱን ሃይማኖት ሁለትና ሶስት ቦታ ከፋፍለዋል። መንግስት ህግ የማስከበር ርምጃ በወሰደበት ወቅት ባለቀ ሰዓታቸው ሳይቀር የሃይማኖት ተቋማትን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ሞክረዋል። ታሪካዊውን የአልነጃሺ መስጊድን እንደምሽግ ተጠቅመው ጉዳት እንዲደርስበት አድርገዋል፤ የአብያተ ክርስቲያናት ግቢና ቤተመቅደሶች መዋጊያ ሆነዋል።
ታዲያ እነዚህን ድርጊቶች ስናይ ጁንታው የማካቬሌን ፖለቲካዊ ፍልስፍና የተከተለ መሆኑን ነው። ልዩነታቸው ግን ማካቬሌ ሀገሩን ወደ አንድነት ለማምጣት ሲል ያደረገው መሆኑና ጁንታው ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያደረገው መሆኑ ላይ ነው።
3. መሪ ለስልጣኑ ህጋዊነት መጨነቅ የለበትም
በማካቬሌ ፍልስፍና ህጋዊ መንግስት የሚያስፈልገው መረጋጋት ባለበት ሀገር ውስጥ ነው። መረጋጋት ከሌለ ህግ ቢኖርም ተግባራዊ አይሆንም፤ ህግ አልባነትን በህግ ማስተካከል አይቻልም። ህግ በጠፋበት ዘመን ህጋዊ ስርዓት መፍጠር የሚቻለው ጸጥ ለጥ አድርጎ በጉልበት መግዛት ሲቻል ነው የሚል ፍልስፍና ይከተላል።
ደግሜ ላስታውሳችሁ የምፈልገው ነገር ማካቬሌ እንዲህ አይነት አቋም የያዘው የሰለጠነችና አንድነቷ የተጠበቀ ጣሊያንን ለመፍጠር መሆኑን እዳንዘነጋ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት ባለስልጣናት ታዲያ እራሳቸው ያጸደቁትን ህግ የሚያፈርሱት የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘምና የግል ጥቅማቸውን አስጠብቀው ለመጓዝ ሲሉ ነበር።
በጁንታው ሀገሪቱን በበላይነት ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ በርካታ ህገወጥ ስራዎች ተሰርተዋል። አምስት ጊዜ የይስሙላ ምርጫ አካሂዶ አሸንፌያለሁ እያለ በማጭበርበር ስልጣን ይይዛል። በ1997 ዓ.ም የተደረገውን የምርጫ ማጭበርበር ተከትሎ ለተቃውሞ የወጡ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተገድለዋል። ከሰብዓዊ መብት ረጋጣ አንጻር ለማመን የሚያስቸግሩ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ስለ ፍትህ፣ ስለመብት፣ ስለ እኩልነት ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች እስር ቤት ተወርውረዋል፣ ወንዶች ብልታቸው ተኮላሽቷል፤ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ጥፍራቸው በጉጠት ተነቅሏል፣ እግራቸው ተቆርጧል፤ በርካቶች ታፍነው ደብዛቸው ጠፍቷል፤ ጁንታው ስልጣን ከለቀቀ በኋላም በየአካባቢው ግጭቶችን በመፍጠር ለሰዎች ሞትና መፈናቀል፣ ለንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። ህግ በማስከበሩ ሂደት በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ አካሂዷል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ቡድኑ በሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና ህግ የማያከብር መሆኑን ነው።
4. መሪ አስመሳይና አታላይ መሆን አለበት
ማካቬሌ በዚህ የፍልስፍና ሀሳቡ ያልተረጋጋን የፖለቲካ ሁኔታ ማለፍ የሚችሉት ተንኮለኛ ሰዎች ናቸው ብሎ ያምናል። ስለዚህ መሪ ጥሩ ሰው ሳይሆን ጥሩ ሰው ሆኖ ሰውን መቅረብ አለበት። ነገር ግን አስመሳይነቱን ህዝቡ እንዳያውቅበት መጠንቀቅ አለበት ይላል።
በኢትዮጵያ ታሪክ አስመሳይና አታላይ መሪዎች የታዩት በኢህአዴግ ዘመን ነው። ትግራይን ነጻ ለማውጣት ከጅምሩ በረሃ የገባው ህወሓት ነጻ አወጣችኋለሁ የሚላቸውን ህዝቦች ጭምር እያታለለ እዚህ የደረሰ ነው።
በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ምክንያት እርሱ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች ለረሃብ የተጋለጡ የትግራይ ህዝቦችን ከሚረዱ ድርጅቶች ላይ ድጋፍ ተቀብሎ አከፋፍላለሁ እያለ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር መዝብሯል። ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ከህዝብና ከሀገር የመዘበረውን ሃብት በራሱ ስም አድርጎ እንደ ኢፈርት ባሉ ድርጅቶቹ አማካኝነት በጨረታና በተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎቹ እየተጠቀመ የሀገርን ሀብት ዘርፏል።
ታላቂቷን ትግራይ ለመመስረት ካለው ህልም በመነጨ የብሄር ፌደራሊዝምን እውን አድርጌያለሁ በሚል በራሱ ፍላጎት ከዚህ ወዲህ የእከሌ፤ ከዚህ ወዲያ የእከሌ እያለ ኢትዮጵያን ሸንሽኖ የወሰን ጉዳይ የግጭት መንስኤ እንዲሆን አድርጓል። ክልሎችን በእጅ አዙር እራሱ እየመራቸው እራሳቸውን በራሳቸው እንደሚያስተዳድሩ አድሮጎ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሲነዛና ሲያስመስል የኖረ ድርጅት ነው።
ጁንታው ሳያስበው ስልጣኑ ከእጁ ከወጣ በኋላ ከእርሱ ውጭ ሀገር መምራት እንደማትችል ህዝብን ለማሳመን የተለያዩ የማታለያ ሙከራዎች አድርጓል። ዶላር በማሸሽና የውጭ ንግድን በማስተጓጎል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማዳከም ሞክሯል፤ ግጭቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። እራሱ ህግ እያፈረሰ ህግ መንግስቱ አልተከበረም በማለት ፌደራል መንግስትን እንደ ህገወጥ በመቁጠር እንደ ተበዳይ ሆኖ የትግራይ ህዝብን በማታለል ለጥፋት ከጎኑ እንዲቆም ሲሰብክ ሰንብቷል።
“የትግራይ ህዝብ ሆይ ወራሪ ሃይል እየመጣብህ ስለሆነ እራስህን ተከላከል” በማለት ያሰለጠናቸውን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ በማዝመት ክህደት ፈጽሟል። ሲፈልገው የሰሜን እዝ መከላካያ ሰራዊት በራሱ ጊዜ ከትግራይ ህዝብ ጎን እንደቆመ አድርጎ ያወራል፤ ሲፈልገውም መብረቃዊ ጥቃት በመሰንዘር ሰራዊቱንና ትጥቁን እንደተቆጣጠረ ይናገራል። መንግስት ህግ የማስከበር ርምጃ መውሰድ በጀመረበት ወቅት ደግሞ የወራሪውን ሃይል ደምስሰናል በማለት የተለመደ ዲስኩሩን ይነዛል፤ ተስፋ ሲቆርጥ ደግሞ የድረሱልኝ ጥሪ ያሰማል።
ይህ አስመሳይና ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው ቡድን የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን እየነዛና የትግራይ ህዝብን እያደናገረ የደሃ ልጆችን በጦርነት ውስጥ ማግዷል። በጦርነት ወደ ስልጣን ለመመለስ ሲል በርካታ ታዳጊዎችን አስቀጥፏል።
እነ ስብሐት ነጋ ከፊት ለፊታቸው ያሰለፏቸውን ህጻናት እሳት ውስጥ ከማገዱ በኋላ እነርሱ በዘጠና ዓመታቸው በህይወት መኖር አጓጉቷቸው እጃቸውን ሲሰጡ ስናይ የቡድኑን መሰሪነት የበለጠ እንረዳለን። እነርሱ ልጆቻቸውን ውጭ ሀገር እያስተማሩ ለመሰሪ ዓላማቸው የድሃ ልጆችን ነብስ አስገብረዋል።
ዛሬም የጁንታው ደጋፊዎች ስለ ድል አድራጊነታቸው ሲነግሩን ይህ ቡድን አታላይነትን እና አስመሳይነትን ከማካቬሌ የተማረ ሳይሆን ማካቬሌን ያስተማረ ያስመስለዋል። “ዋሽቶ ከማጣላት ዋሽቶ ማስታረቅ” እንዲሉ ማካቬሌ የአስመሳይና አታላይነትን ባህሪ የመረጠው ሀገሩን ከውድቀት ለመታደግ ካለው ጉጉት ነው። የእኛዎቹ ግን የግል ጥቅማቸውን ለማካበትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013