ክፍለዮሐንስ አንበርብር
በዚህ አምድ በአገራዊና ቀጣናው ጉዳዮች ላይ በሕግ መነፅር የተለያዩ ጉዳዮችን ዳስሰናል። የዓምዱ እንግዳ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በአግባቡ ሲወጡ ከቆዩት በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማዕረግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐፅድቅ መኮንን ናቸው። የሕግ ባለሙያው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሷቸውን ሃሳቦች እነሆ።
አዲስ ዘመን፡– መልክ እየቀያየሩ በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶች በሕግ ዓይን ሲታዩ ምክንያታቸው ምንድን ነው?
አቶ መርሐፅድቅ፡- በአገሪቱ የተተከለው ሥርዓት በቅንነት ተወስዷል ተብሎ ቢታመን እንኳ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት ሲሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው፣ ስሪታቸው፣ ባህላቸው የተለያየ ማህበረሰቦች አሉ። ይህ ግን አንድነትን የሚፈታተን መሆን የለበትም።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ የኖረ ቢሆንም ለእነዚህ ማንነቶች መሬትን ለብቻ ነጥሎ ይህ የአንተ ብቻ ነው ብሎ ለአንድ ወገን ንብረትና የሆነ አምሳል የተፈጠረ መሬት አድርጎ መወሰኑ፣ ለዓመታት ከታሰበው በላይ እንዲጦዝ መደረጉ፣ ከጋራ ጉዳይ ይልቅ በግል ጉዳይ ብቻ እንዲጨነቁ ብሎም አገራዊ ስሜት እንዲኮሰምን ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል መለያየት አይቀሬ ቢሆንም የአንድ አገር ሕዝብና የተጠቃለለ ሕዝብ ከማለት አያግድም። ይሁንና መሬትን ለብሕር የአስተዳደር ዘይቤ መከተሉ፣ ተቀብሎ ወደ ሥራ መቀየሩና ልምምድ የተደረገበት ከታሰበው በላይ እንዲጦዝ ተደርጓል። በጋራ ጉዳይ ሳይሆን ሁሉም በግል ጉዳይ ላይ ብቻ አሊያም ከአገር በላይ ስለክልላቸው ብቻ አብዝተው እንዲጨነቁ አድርጓል።
ይህም መቀበል ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግሕት በመቀበል በጣም እንዲገዝፍና እንዲራገብ ተደርጓል። ግን ወደ ኋላ ተመልሰን ስንመለከት ሁሉም ብሔረሰቦች ተባብረው ነው ኢትዮጵያን ያቆዩዋት። በአድዋ ጦርነት ወቅት የሆነውን ማስታወስ በቂ ነው። ሁሉም ብሔሮች የአገሪቱን ብሔራዊ ጥሪ ተቀብለው አገራቸውን ሲከላከሉና ሲጠብቁ ኖረዋል። ይህም ማለት እንደዛሬ አልነግራቸውም እንጂ በዚያን ጊዜ ልዩነት የለም ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት የልዩነት ሃሳብ ለምን ገዝፎ ተቀባይነት አገኘ?
አቶ መርሐፅድቅ፡- አዎ! ያው በደርግ አገዛዝ ዘመን በአገሪቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ የመብት ጥሰት ነበር። ከዚያን በኋላ በርካታ የብሔራዊ ነፃነት ንቅናቄ አውጪዎች እንደ አሸን ተፈልፍለው ነበር። ከዚያ ቀደም ሲል አገሪቱ በፊዶ ካፒታሊስት ሥርዓት ነበር የምትተዳደረው።
ከዚያ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አዲስ ሲፈጠሩ አንዳንዶቹ በፖለቲካ አስተሳሰብ ስር ሆነው መደራጀት፣ ሌሎቹ ደግሞ በብሔራዊ ነፃነት ንቅናቄ ሥር ሆነው መደራጀት ለምሳሌ ‹‹ኦሮሞ የኦሮሞ ነፃ አውጭ፣ ትግሬ የትግራይ ነፃ አውጭ ….›› ብለው ተደራጁ።
በዚህ የአገሪቱን የመደብ ጭቆና ተብሎ በማርክሲስቶች የሚዘመረው እነርሱ ደግሞ ብሔራዊ ጭቆና ነበር ብለው በአገሪቱ የአንድ ሃይማኖት፣ ብሔር ጫና እና ጭቆና ነበር ብለው የሚያምኑ ክፍሎችንና ሕዝቡን ክፉኛ ቀሰቀሱ። ይህም ቅስቀሳ ኢህአዴግ በኋላ ህብረት የሆኑትን የተለያዩ የብሔራዊ ነፃ አውጪ ንቅናቄዎችን ፈለፈለ።
በእርግጥ ሕዝቡ ደርግን አይወደውም ነበር። ህወሓት ደግሞ ይህን በማዛባት የራሳቸውን ፍላጎት ሕዝብ ላይ ለመጫን ሰሩበት። ይህ ደግሞ በየጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ከሞላ ጎደል ሕገመንግሥት አድርጎ ያለ ሕዝብ በቂ ውይይትና የተወሰኑ በየቀበሌው ካድሬዎች የተረቀቀላቸውን የፅንሰ ሃሳብ መንፈስ ጥልቅ ክርክር እና ውይይት ሳይደረግ በአዎ እና አይደለም መንፈስ ሕዝብ እንደተወያየ ተደርጎ የፖለቲካ ፕሮግራሙ በተለይም በዚያን ጊዜ አቅም የነበረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አዘጋጅቶ የነበረውን ሕዝብ ላይ ሕገመንግሥት ብለው አፀደቁት።
ይህ ሕገመንግሥት ደግሞ የብሔር ፖለቲካን አነገሰ። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የዚህችን አገር ሉዓላዊ መሥራቾች ናቸው፤ እነርሱ ከሌሉና ካልተስማሙ ኢትዮጵያ የምትባል ነገር አትኖርም።
ዛሬም ይሁን ከመነሻው ሉዓላዊ ሥልጣን ከአገሪቱ ወርዶ ለብሔርና ለየብሔረሰቡ መሰጠት አለበት የሚያሰኝ ድምፀት ያለውና አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገመንግሥት እንዲፀድቅ መደረጉ ለአንዳንዶቹ ክፋት የበከሉን አስተዋፅኦ አድርጓል።
ስለዚህ ከሕዝቡ ይልቅ የፖለቲካ ሊሂቃንና ሹማምንቶች መቀስቀስ የጀመሩት የአገሪቱ መሬት ለየብሔር የተከፋፈከለ ነው ብለው መስበክ ነበር። ስለዚህ መሬቱን በዚያ አካባቢ ስመጥር ወይም ቁጥሩ የበዛ ማህበረሰብ ብሔር፣ ብሔረሰብ ተብሎ መሬት እየተከፈለ በመስጠት የማያዛልቅ አድራጎት ተፈፀመ።
በሂደት ደግሞ እያንዳንዱን ብሔር እንወክላለን የሚሉ ሳይወከሉ ተወካይ ነን የሚሉ የብሔር ጠበቆች እየተነሱ ኅብረተሰቡ ከሚያውቀው ማህበራዊ ሥነ ምግባርና ሥሪት ውጪ መስመር ማሳት ጀመሩ።
አዲስ ዘመን፡– በሕዝብ ሳይመረጡ ተወካይ ነን ብሎ መነሳት ይቻላል?
አቶ መርሐፅድቅ፡- ሕዝብ ከተቀሰቀሰ እንዲህ ነው። የምትቀሰቅሰው የተወሰነ ክፍል ምንጊዜውም ቢሆን በአንተ ሥር አድርገህ ለተወሰነ ጊዜ አይዲዮሎጂህን በስፋት የማሰራጨት ዕድል ካገኘህ መላው ሕዝብም ባይሆን የተወሰነ ደጋፊዎችን አታጣም። ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከመሆኑ በፊት በትግራይ ሕዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ ሲኩራራ ነው የኖረው።
ይህ ማለት ህወሓት ምርጫ ቀርቦለትና ህወሓት ተመርጦ አይደለም። ይህ ማለት መሰል አካባቢ በቀል ድርጅቶች መጀመሪያ የየራሳቸውን እሴት ዘርግተው የሚያምኑበትን አይዲዮሎጂ ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። በዚህ የረጅም ጊዜ ደፋ ቀና ጥረት አንዳንዴም በሰይፍ ጭምር እየተጠቀሙ ኅብረተሰቡን የራሳቸውን ያደርጉታል፤ ያስገብሩታል።
ለአብነት እንኳን ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ወዲህ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ብናይ የህወሓት ሃሳብ ተሸካሚዎች በመኖራቸው ህወሓት ተሸንፎ እንኳ ታሪክ ቢሆንም እውነት ነው ብሎ ማመንና በዚህ ልክ ፍጻሜ ይሆናል ብሎ የማመን ፍላጎት የላቸውም። ለረጅም ዓመታት አማራጭ ካልነበራቸውና መጥፎ ቅስቀሳ ከተደረገ መሰል አስተሳሰብ መኖሩ አይቀሬ ነው። ለዚህ ቡድን ኀዘኔታም ሊያሳዩ ይችላሉ። ሆኖም ‹‹ትክክለኛ ተወካይነት ሊመጣ የሚችለው በምርጫ ብቻ ነው።››
አንዳንዱ ተወካይነት ደግሞ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለተወሰኑ ጥቅሞች ተሰብስበው ደጋፊ ይሰበስባሉ። ዘመቻ ያካሂዳሉ። በዚህ በኩል የሚሰበሰብ ደጋፊ በነቂስ ወጥቶ በሕጋዊ መንገድ ባይመርጥህም ተወካዬ ነው ብለህ እንድታምን የሚያስፈልገውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል፤ የተወሰነ ተቀባዮችም አያጣም።
አሁን አንዳንዶቹ የነፃ አውጪ ተወካይ መስለው ለድጋፍ ሰልፍ የሚወጡት ሰዎች እውነተኛ ፍላጎታቸው የሚገለፅበት አይደለም። ተቀስቅሰው የወጡ ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ በኃይልና በጫና ነው። የእያንዳንዱ ብሔር ተቆርቋሪ ከሕዝብ ነው የወጣነው፤ ቋንቋህን እንናገራለን ባህሉን እናውቃለን ብለው ይቀሰቅሳሉ። በተለይም ደግሞ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን በማማለል ደጋፊ ያደርጉታል።
ቀደም ሲሉ የነበሩት መንግሥታት ወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አላደረጉትም። ተምሮ ሥራ ያጣ እና ዲግሪ ያንጠለጠለ ወጣት ችግር ላይ ስለሆነ ወዲያውኑ ለማነሳሳት ቅርብ ነው። ይህን ቶሎ ለመቀላቀል የሚያግደው ነገር የለም።
በመሆኑም ይህን የሚመክት ማዕከላዊ መንግሥት በሌለበትና ይህን የብሔር ፖለቲካ አካሄድ አደገኛ ነው አድብ ግዙ ብሎ ማስቆም በማይችልበት ሁኔታ ለመሰል አመፅ ወዲያውኑ ሊነሳሱ ይችላሉ። በዚህ አማላይ ፍልስፍና የየብሔሩ ተወካዮች በዚህ መንገድ ተወካዮች ነን ብለው የሚያስቡትን ያነሳሳሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ ችግሮች የማይከስሙትከማዕከላዊ መንግሥት መዳከም ወይስ ፍላጎት ማጣት?
አቶ መርሐፅድቅ፡- በተለያየ መንገድ ሊገለፅ ይችላል። ማዕከላዊ መንግሥት ላይ የሚቀመጥ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱ የዜጎችን ደህንነት መጠብቅና ማስከበር ነው። ምንም እንኳን አገሪቱ በብሔር፣ ቋንቋ የተከፋፈለች ብትሆንም ዜጎች የሚባሉት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በመጨረሻ እንደ ሀገር ስንጠራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንወከለው አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። በዚህ የሚሰባሰቡ ሰዎች እንደ ልምዳቸው፣ ዕድሜያቸው፣ እንደ መንግሥቱ ተቋማት ጥንካሬ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
አሁን ያለውን መንግሥት ብንወስድ ፈሳሽ መንግሥት ነው። ፈሳሽ ነው ስልህ ገና የጠጠረ መንግሥት አይደለም። ለረጅም ጊዜ ህወሓት ይህችን አገር በመዳፍ ውስጥ አስገብቶ በአምሳሉ ደግሞ ኢህአዴግ የሚባል ራሱ ጠፍጥፎ የሰራው ዩኒዬን ፈጥሮ ከብረት በጠነከረ መንገድ አገሪቱን ከ27 ዓመታት በላይ ለማስተዳደር ሞክሯል።
ህወሓት ተገልሎ ከዚህ ወጥተው ማዕከላዊ መንግሥቱን የመሠረቱ ኃይሎች ጭቃና ጨፈቃ ለመሆን አልቻሉም። ጥንካሬ የሚለካው በዚህ ነው። የራሱ የሆነ የጠራ አይዲዮሎጂ ኖሮህ፣ አገር በምትመራበት ጊዜ አቅም ያለህ መንግሥት መሆን አለብህ።
ጥንካሬ መገለጫው አንዱ በተቋማት ጥንካሬና ሁሉንም በመወከል ችሎታ ነው። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ችግሮች ነበሩ። ሆኖም ከውስጡ የወጡ አዲስ የመንግሥት ማንነትን በመፍጠር ላይ ናቸው።
እነዚህን ገጣጥመን ስንመለከት በዓለም አቀፍ ገጽታ መጥፎ የሚባሉ ሥራዎችን በመቀየር ከዚህ በፊት አገሪቱ የምትታወቅበትን ምስል በመቀየር የሚዲያ ነፃነትን በማረጋገጥ፣ ዴሞክራቲክ በመሆን፣ የታሰሩትን በመፍታት የማይካዱ በጎ ነገሮች አሉ። ግን ደግሞ በውስጡ ያሉትን የአስተሳሰብ አንድነትን በሚገባ አረጋግጦ በሚያስመካ ደረጃ የጠነከረና ሁሉንም በመወከል ብቃት ላይ ነው ማለት አይቻልም።
ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ቅቡልና ጠንካራ አይደለም። ሁሉንም በመወከል ብቃት ላይ ነው ለዚህም የተሟላ አቅም አለው ማለት አይቻልም። ገና ምርጫ አልተካሄደም። አንዳንዶቹ በመንግሥት ውስጥ ያሉ ኃይሎች ተሸጋግረህ አጠናክረህ ትቀጥላለህ ማለት ነው እንጂ ኢህአዴግ ቢፈርስም በውስጡ የኢህአዴግ ካርቦን ኮፒ በውስጡ የያዘ መንግሥት ነው። እነዚህን ይዞ ያለ መንግሥት ነው።
ግን ፍርስርስ የሚል መንግሥት ነው ባትልም ግን የረጋ አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኩሪ ታሪክ ያለውና በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነች አገር ናት። ይህን የሚወክልና የሚመጥን ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ስለማይቻል አሁን ከእርሱ የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት በዚህ ደረጃ መወገዱ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል?
አቶ መርሐፅድቅ፡- ህወሓት ጥሩ ተወዳዳሪ እንዲሆን የተሰጠውን ዕድል አልተጠቀምበትም። ቢኖር እኛ ደስታችን ነው። ህወሓት ዱሮ የሰራው ታሪክ እንደእነ ሩዋንዳ እና ዩጎዝላቪያ አይደለም እኮ እዚህ አገር የተከናወነው። ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ በፀጥታ ኃይሎቹና በፍትህ አስተዳደር አካላት በሰብዓዊነት የሰራውን የጉዳቱ ሰለባዎች በሚዲያ ቀርበው ሲናገሩ ነበር።
በፍርድ አደባባይ ለሰራው ሥራ ይህ ነው የሚል ፍርድ ባይገኝም እንኳን የተረፉ ሰዎች ወጥተው በሚዲያ ሲናገሩ ብዙ ሰቆቃ ሲደርስባቸው ነበር። ‹‹ሳይለንት ጄኖሳይድ›› ሲፈፅሙ ነበር።
ይህን ሲፈፅሙ ከነበሩት አካላት ጋር ሙሉ ለሙሉ ሠላም እና እርቅ አልወረደም። በመሰል የተቀነባበረ እና የረቀቀ ወንጀል ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ለሕግ የሚቀርቡት። ሆኖም የሆነውን እንለፈውና ቀጣይ የበለፀገች ኢትዮጵያን እንገንባ የሚለውን ጥሪና ዕድል መጠቀም አልቻለም።
ከባለፈው ስህተት ተፀፅቶ ጥሩ ተገዳዳሪም እንዲሆን ዕድል አግኝቶ ነበር። ግን ይህን ዕድል ለመጠቀም አልፈለገም። ይህን የሚያነሱ ብዙ ናቸው። በሌላ መንገድ ደግሞ የትግራይ ተወካይ ህወሓት ብቻ ነው ማለት አይቻልም። ከውጭም ከውስጥም ተጠርተው የሽግግር ኃይል ሆነው ፖለቲካውን ቅርፅ አስይዙ ተብሏል።
ሆኖም ለሕዝቡ ለመቅረብ ያላቸው ዕድል ገና አልተሟላም። ጥርት ያለ ፕሮግራም በማቅረብም አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች በቁጥር ያንሳሉ የሚሉ እምነት የለኝም በጥራት ጉዳይ ሊነሳ ይችላል።
ህወሓት ጠንካራ ነበር የሚል እምነት የለኝም፤ እንደ ቢስማርክ በብረት ቀጥቅጦ ሲገዛ ስለነበር ነው። ህወሓት የለመደውም ዴሞክራሲ አይደለም ግን ወደፊት ተፎካካሪ ሆኖ ወደ ዴሞክራሲ ይመጣል የሚለው ደግሞ ሌላ ክርክር ነው። ግን ያው ህወሓት የመጨረሻ እቅዱ የተመለከትነው በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ አስነዋሪ ድርጊት መፈፀም ነው።
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ወንጀል እስከምን ሊያስቀጣ ይችላል?
አቶ መርሐፅድቅ፡- ይህ በጣም ከባድ ነገር ነው። በፍሬ ነገር እንኳን ቢታይ የውስጥ የራሱን ኃይሎች በመጠቀም ራሱን አደራጅቶ ከሚገባው በላይ ለራሱ ግምት ሰጥቶና የተዛባ ሥዕል ወስዶ በውስጥና በውጭ ተደራጅተው የሀገሪቱን መከላከያ ወግቷል። መከላከያ የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት ማለት ነው። ይህን ማድረግ አገሪቱን ያለጠባቂ ማስቀረትና ሉዓላዊነትን መድፈር ነው።
አሁን በሥራ ላይ ባለው እና 1997 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ከአንቀፅ 244 እስከ 248 የመከላከያ ኃይሉን በመውጋት፣ በከፍተኛ ክህደት ሉዓላዊነት ጥሶ ሀገርን ለጠላት በመስጠት ትልቅ ጥፋት አድርሷል። ይህ ቅጣቱ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ የሞት ፍርድ የሚያስፈርድ ነው።
በእርግጥ አሁን የተወሰኑት ቀርተው አብዛኞቹ አልቀዋል። በሕግ ፊት ቀርበው ለምን ለዚህ እንደተነሳሱ ማወቅ ቢቻል መልካም ነው። አሁን የፈፀሙት ወንጀል በተደራጀ መንገድ ሲሆን እጅግ የከፋ ወንጀል ነው።
በማይካድራ የሆነም ጅምላ ጭፍጨፋ ነው። ወታደርን አስፋልት ላይ አስተኝተው በመኪና መደፍጠጥ እጅግ ከባድ ወንጀል ነው። በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ምርኮኛ ቢኖር እንኳን ሰብዓዊነቱ በአግባቡ መያዝ አለበት ይላል። ህወሓት ያደረገው ግን በተቃራኒ ነው። እነዚህ ድርጊቶች በወንጀል ሕጉ 269 እስከ 280 ድረስ የተደነገገውን ጥሰዋል፤ በከፍተኛ ወንጀልም ያስጠይቃል።
ይህን ያደረጉት ሳይገነዘቡት ቀርተው ሳይሆን ሆን ተብሎ ነው። ይህን ትዕዛዝ ሲሰጡ የነበሩ የህወሓት አመራሮች ናቸው። ይህ ወንጀል እንዲፈጸምም ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ትዕዛዝ ሰጪ ናቸው። አንዳንዶቹም ቀጥታ በሚዲያ ወጥተው የፈፀሙትን ተናግረዋል። አስገራሚና አሳፋሪ ቢሆንም አንዳንዶቹ ወጥተው በ45 ደቂቃ የፈፀሙትን እንደ ጀብድ ሲተነትኑ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ በሚዲያ ወጥተው መናገራቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ራሳቸው ውለታ አልዋሉም ብለው ያስባሉ?
አቶ መርሐፅድቅ፡– እኔ በበኩሌ ደስተኛ ነኝ። እነርሱ ቀደም ሲል መሰል መረጃ ለማግኘት በድብደባ እና ተጠርጣሪዎችን በማሰቃየት ነበር። አሁን ግን በራሳቸው ጊዜ ነው ምስክር የሆኑት። አሁን ከማስረጃው ከግማሽ በላይ ራሳቸው ምስክር ሆነዋል። ይህ አንዳንዶቹ ከመሞታቸው በፊት የዋሉት ችሮታ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከህወሓት መንኮታኮት ማግስት የሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባትና የኢትዮጵያን መንግሥት አካሄድ እንዴት ይመለከቱታል።
አቶ መርሐፅድቅ፡- የውስጥ አለመረጋጋቱ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ሰዓት የውጭ ጠላቶች ሊወሩን ይሞክራሉ። ያው ‹‹አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው ነው›› የሚባለው። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ያውቃሉ። ኢትዮጵያ በጠላት የተከበበች አገር ናት። እኔ የማልስማማበት እና በመለስ ዜናዊ ብሔራዊ ደህንት እና ፖሊሲ ስትራቴጂ ውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቷ ድህነት ብቻ ነው ይላል።
ጠላቷም ከውስጥ እንጂ ከውጭ አይደለም የሚል ነው። ይህን በመሰረታዊነት ይዘነው እስካሁን ለመቀየር አልቻልንም። ኢትዮጵያ ቀድሞውንም የቅርብ ብቻ ሳይሆን የሩቅ ጠላቶቿ ብዙ ናቸው። ለዚህ የራሷ ታሪክ ነው ጠላትነት መነሻ የሆነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካ ነፃነቷ አስከብራ የቆየች አገር ናት።
የቆዳ ስፋቱ በተለያየ መንገድ ሊጠብም ሊሰፋም ይችላል። የራሷ እንጂ የሌሎች የማትመኝ ስትነካ ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ሆ! ብሎ የሚወጣ ነው። ነፃነቷን ከማስጠበቅም በላይ ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ትልቅ ሚና አላት። ይህ ለአውሮጳውያኑ ጭምር የማይዋጥ ነገር ነው።
የአድዋ ታሪክ፤ የፋሺስት ወረራ ወቅትም ያደረግነው ራስን የመከላከል ታሪክ አለን። ‹‹ከጣት ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ ኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አስተያየት በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ እንጂ ለኢትዮጵያ ፍቅር አላቸው ማለት አይቻልም። ይህን ታሪካችንን አይወዱትም ዛሬም ድረስ የሚከሰት ጉዳይ ሲሆን ጠላቶቿን የሚያበዛ መሆኑ አያከራክርም።
አገሪቱ ከኢህአዴግ አገዛዝ ጀምሮ ኃይሏ የተቀዛቀዘው የባህር ወደብ ያጣች ቀን ነው። ቢቸግረን እርጥብ የባህር ወደብ በሙሉ አስረክበን ደረቅ ወደብ እንገነባለን። ይህ የባህር በር ሆኖ አያገለግልም። በአንድ ወቅት ሦስት የባህር ወደብ ያላት አሁን ምንም የላትም። በዚህ መንገድ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረግ ትክክል መሆኑ በበርካታ አረብ አገራት ይታመናል።
እነዚህ የአረብ አገራት ደግሞ በግብጽ የበላይነት እንዲመራ የተሰራ ነው። ከግብጽ ጋር መጣላት ማለት ደግሞ ከመላው አረብ ጋር እንደመጣላት ይታሰባል። ብቻ በሱዳንም ሆነ በሱማሊያ በኩል ያለውን የድንበር ሁኔታ እንግሊዝ ጥላ ያለፈችው ጠባሳ አለ። እንግዲህ አሁን በሱዳኖች በኩል የሚደረገው የወረራ ሙከራም እንግሊዞች ጥለውት በሄዱት ጠባሳ ነው።
እንዲሁም በባንዳነት የሚሰሩ የራሳችን ሰዎች አሉ። በተጨማሪም ለ100 ዓመታት የነበረውን ስምምነት በሱዳን በኩል ባለማክበር የተፈጸመ ነው። ከሱዳን በስተጀርባ ግብፅ መኖሯንም ማወቅ ይጠቅማል። የሆነው ሆኖ መንግሥት ከሁሉም ነገሮች በፊት ዲፕማሲውን ማጠናከር አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ሱዳን ከበስተጀርባዋ ግብጽ ዋንኛ ተዋናይ ከሆነችና በርካታ አረቦች አሉ ካልን ኢትዮጵያስ ምን አላት?
አቶ መርሐፅድቅ፡-የግብጾችን ያክል አይብዛ እንጂ ከዓረቡ ዓለምም ቢሆን ኢትዮጵያም ወዳጅ አላት። የግዴታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ባይኖርም ለዓለም መረጋጋት ሲባል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ይከታተሉታል።
ከዚህ በዘለለ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር የገነባችው ስም ብዙ እየጠቀማት ነው፤ በቀጣይም ብዙ ፋይዳ አለው ብዬ አምናለሁ። ምዕራባውያንም የሚገነዘቡት ጉዳይ አለ። በተቻለ መጠን ግን የዲፕሎማሲውን መንገድ መቀጠል ይገባል።
የሆነው ሆኖ ግን ኢትዮጵያ በሉዓላዊነት እንደማትደራደር የቅርብ ሳምንታት ታሪክ ማየት በቂ ነው። ልዩነቶች ቢኖሩንም የውጭ ጠላት በወረረን ጊዜ ከታሪካችን መረዳት የሚቻለው የአገር ብተና እና አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ዝምታን የማይመርጡ ናቸው።
ሆኖም የሱዳን ኃይሎች የተጠቃን መስሎ ሲታያቸው የሚያደርጉት የረከሰ ፕሮፓጋንዳ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን። አሁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ለመሙላት ተቃርበናል።
ይህ ደግሞ ግብጽ ሌላ አማራጭ ለመጠቀም ይዳዳታል። ሱዳንም በዚህ እቅድ ውስጥ ትካተታለች። በመሆኑም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ባገናዘበ መንገድና ኃላፊነት ልንንቀሳቀስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ መርሐፅድቅ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013