ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
የዛሬ መቶ ሃያ አምስት አመት በወርሀ የካቲት 1888 ጣሊያን ከብዙ ወታደሮችና ከብዙ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ጋር የአትንኩኝ ባዮችን ሀገር ኢትዮጵያን ልትወር ባህር አቋርጣ መጣች። በወቅቱ ነገሩ በውይይት እንዲፈታ ከኢትዮጵያ በኩል የእንነጋገር ጥያቄ ቢቀርብም በጦር መሳሪያዋና በወታደሮቿ የተማመነችው ጣሊያን ግን አሻፈረኝ አለች። በሀገራቸውና በርስታቸው ለመጣባቸው ቀልድ የማያውቁት ኢትዮጵያውያን እኛ ቆመን እማ የሀገራችን ዳር ድንበር በባዕድ ሀገር ሲወረር ዝም ብለን አናይም ሲሉ ተቆጡ። በአንድነት በህብረት ሆ ብለው ተነሱ።
ቁጣቸው..እልሃቸው ከህብረትና ከአንድነታቸው ጋር አብሮ ብዙ ነገር አስቦ የመጣውን ወራሪ ጦር ድባቅ መቱት..ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ዓለምን ያስደነቀ ጀግንነት ፈጸሙ። በዘመናዊ ወታደርና በጦር መሳሪያ ተደራጅቶ የመጣውን ወራሪ ኃይል በአንድነት በመቆም ከሀገራቸው አባረሩት። ይሄ ከሆነ እንሆ መቶ ሃያ አምስት ዓመት ተቆጠረ። ያኔ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስልጣኔን ለመጀመር ደፋ ቀና የምትልበት ሰሞን ነበር አይደለም ዘመናዊ መሳሪያ ቀርቶ ባህላዊ መሳሪያው እንኳን በሚፈለገው መልኩ የሌላት ሀገር ነበረች። ግን የህዝቡ አንድነት..ግን የህዝቡ ቁጣና የአልደፈርምነት ስሜት ታላቅ ነበርና ዘመን የማይሽረውን ከአፍሪካ አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን አድዋን ፈጠረው።
የኢጣሊያን መሸነፍ ዛሬም ድረስ ተዓምር የሚመስልና ፈጽሞ ማንም ይሆናል ብሎ ያልገመተው ነገር ነበር። ምክንያቱም ዓለም ላይ በስልጣኔና በዘመናዊነት ብዙ የተራመደች ሀገር ዘመናዊነትን ባላየች ሀገር ትሸነፋለች ብሎ የጠበቃ አልነበረምና ነው። ይሄን ሁሉ ዘመን አልፎም የአድዋ ድል ለእኛ ለጥቁሮቹ ኩራት ለነጮቹ ደግሞ ውርደት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ዛሬም ድረስ ላይ አለ። እድሜ በአንድነት ለቆሙት አባቶቻችን ባርነት የማታውቅ ለብዙዎች ምልክትና ምሳሌ የሆነችን ታላቅ ሀገር አስረክበውናል። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት የሚገርም ነበር።
ከጦርነቱ በፊት ከመኳንንቱና ከሹማምንቶቹ ጋር ያልተስማሙና ቅራኔ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች ቢኖሩም ጣሊያን ሀገራችንን ልትወር መምጣቷን ሲሰሙ ግን ሁሉም ከዳር እዳር ያለልዩነት ያለቅራኔ የንጉሱን የክተት አዋጅ ተቀብለው ወጡ። አያችሁ ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነች? በውስጣችን ብዙ ልዩነት ብዙ ቅራኔ ሊኖር ይችላል፣ ፖለቲካው ሊመቸን ላይመቸን ይችላል በሀገር ጉዳይ ላይ ግን አንድ ነን። ያኔ በቅራኔ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሀገራቸው በጣሊያን ስትወረር ዝም ብለውና አያገባኝም ብለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ይሄ ሁሉ ታሪክና ጀግንነት አይኖርም ነበር። የአድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያ ድል ነው። የመላው አፍሪካ ድል ነው። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከአድዋ የድል ብስራት በኋላ ነጻነታቸውን ያገኙ ናቸው።
ባጠቃላይ አሁን ላለችው አፍሪካ መመስረትና መቆም ትልቁን ድርሻ የወሰደችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። አድዋ የተባበሩ ክንዶች፣ በአንድ የቆሙ ልቦች የፈጠሩት የተጽእኖ ውጤት ነው። አድዋ ጽናታችን ያስገኘው ትርፍ ነው። አንድነታችን አብሮነታችን ያመጣው በረከት ነው።
በአድዋ የታየው የአባቶቻችን ህብረትና አንድነት ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያክል ተጽዕኖ እንዳሳደረ መገመት አይከብድም። ዛሬ ላይ የምንጠራባቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የትላንት የአንድነት ውጤቶቻችን ናቸው። ዛሬም ሀገራችን ኢትዮጵያ በአንድ የሚያስቡ በአንድ የተባበሩ ወንድማማች ህዝቦችን ትሻለች። ከአለፈው በባሰ በብዙ ችግርና መከራ ውስጥ ናት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መፍትሄ በሚሹ፣ የእኛን አንድነት በሚፈልጉ በብዙ ችግሮች የተያዘችበት ጊዜ ነው። የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ እየበዙ የመጡበት፣ የጀመረችውን ለውጥ ለማደናቀፍ እዛም እዚህም ነገር የሚዶልቱ የተበራከቱበት የጭንቅ ወቅት ላይ ናት። አለንልሽ ልንላት ይገባል። ልዩነታችንን ትተን በአንድነት በመቆም ይሄን አስከፊ ጊዜ እንድናሳልፋ እየጠበቀችን ነው። በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን የእኛን አንድነት በእጅጉ ትሻለች።
ህዝባችን ከኋላ ቀርነት የሚያወጣው የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል። በአንድነት በመቆም ጠላቶቻችንን ማሳፈር አለብን። በውስጥም በውጭም ውድቀታችንን የሚፈልጉ ገንዘብና ቁስ እየደገፉ መውደቃችንን የሚጠባበቁ ብዙዎች ናቸው። ሰላማዊ መስለው የክፋት መረባቸውን የዘረጉብን ሞልተዋል። ሀገራችን አንገቷን የደፋችበት ሰሞን ላይ ነን ቀና ልናደርጋት ይገባል። ከሌላት ላይ ቆርሳ በድህነት ጎኗ ቀን ያወጣችን ብዙዎች ነን ዛሬ በተራችን የጭንቀት እንባዋን ለማበስ ከጎኗ መቆም አለብን።
የሚረዳት ጠፍቶ ግራ በተጋባችበት በዚህ አስጨናቂ ሰዓት አጋርነታችንን እናሳያት። የአባቶቻችንን አንድነት ህብረት እያሰብን ከመንግሥት ጎን በመቆም የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይኖርብናል። ግፈኞች በፈጠሩት የውሸት ትርክት ተመርተን አንድነታችንን አንጣ። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሀበሻዊ ቤተሰባዊነታችንን አናፍርስ። እኛው ለእኛ እንቁም። ከተረዳዳን ከራሳችን አልፈን ለሌላው የምንተርፍ ክንደ ብርቱዎች ነን። በአንድነት ከቆምን የሚፈሩን ብዙዎች ናቸው። በአንድነት ከቆምን የሚደፍረን የለም። ሁሉም አፋቸውን የሚከፍቱብን መለያየታችንን አይተው ነው። የኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ የቀመሱ እዚህም እዛም ሞልተዋል። የሚያሸንፉን ስንለያይ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው ዛሬ በመካከላችን እሳት ፈጥረው እርስ በርስ የሚያባሉን። ብዙ ጎረቤት ሀገራት አንድነታችንን ጠልተው የራሳቸውን ሀገር እያለሙ የራሳቸውን ህዝብ እያሳደጉ የእኛ ህዝብ ግን በድህነት በኋላቀርነት እንዲኖር የተንኮል ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ የሚችላቸው የለም..ብዙ ዘመናትን አብረው ቆመው ታላቅ ነገር አድርገው አይተናቸዋል ስለዚህ እርስ በርስ እያባላን እርስ በርስ ፍቅር እንዳይኖራቸው በማድረግ እንዲጠፉ ማድረግ አለብን የሚሉ በሩቅም በቅርብም ብዙ ጠላቶች ተነስተዋል። እውነት ነው ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ከቆሙ፣ በአንድ ላይ ከተነሱ የሚያቆማቸው የለው ይሄን ደግሞ ዓለም ያውቀዋል። ጎረቤት ሀገራትም ይሄን እውነት ተረድተው ነው ለዘመናት በፍቅር በአብሮነት የሚኖረውን ህዝብ ለመለያየት እየሰሩ ያሉት። መንቃት አለብን ለሀገራችን ዘብ የምንቆምበት ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን። ሀገራችንን አለንልሽ ልንላት የሚገባን ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው። ለጠላት መጠቀሚያ መሆን የለብን።
በሀገራችን ላይ የአባቶቻችን አደራ አለብን። እንዳንለያይ አደራ ያሉን ብዙዎች ናቸው። በአንድነት ከቆምን የሚፈራን ብዙ ነው አይደለም ግብጽና ሱዳን ቀርቶ ሀያላኖቹ ሀገራትም አይችሉንም ጣሊያን ዓለም ላይ ካሉ ሀያላን ሀገራት አንዷ ነበረች..ግን በተባበረ ክንድ ተሸንፋለች። ማሸነፊያችን አንድነት ነው።
አንድ ከሆንን ዛሬም ነገም የአድዋን አይነት ብዙ ታሪኮችን መስራት እንችላለን። ይሄ የሚሆነው ግን አንድ ስንሆን ነው። ብሄርተኝነትን ገለን፣ የኔ የአንተ ሳንባባል በኢትዮጵያዊነት ተያይዘን የቆምን ጊዜ ነው። ያኔ ጊዜው የእኛ ይሆናል ያኔ ውድቀታችንን የሚጠብቅ የሚያፍሩበት፣ ሊጥሉን..ሊያባሉን የሞከሩ ሁሉ የሚሸማቀቁበት የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ይሆናል። እመኑኝ እስካሁን ከስልጣኔ የራቅነው አንድነት ስለሌለን ነው። ከሀገር ቀድመን ተፈጥረን ከሀገር ኋላ የቆምንው አንድነት ስላጣን ነው።
በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ ታላቅ ኢኮኖሚ የገነቡ ሀገራት በአብሮነት የቆሙ ናቸው። በጣም የሚገርመው ደግሞ በብዙ ነገር ተለያይተው በአንድነት የቆሙ መሆናቸው ነው። እኛ በብዙ ነገር አንድ ሆነን..ተጋብተን ተዋልደን እየኖርን እንኳን የተለያየን ህዝቦች ነን። ይሄ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። ሰዎች በብዙ ልዩነት ውስጥ ተግባብተው በሚኖሩበት ዘመን እኛ በብዙ አንድ መሆን ውስጥ ተለያይተን መኖራችን ሁሌም ያሳዝነኛል። መንቃት አለብን.. እስካሁን ባለማወቅ ጥፋት ስንሰራ ኖረናል አሁን ወደራሳችን ወደ አባቶቻችን ስርዓት የምንመለስበት ጊዜ ነው።
ጠላቶቻችንን የምናሳፍርበት፣ የሀገራችንን ውለታ የምንከፍልበት ጊዜአችን ነው። ወንድማማች ህዝቦች ነን…ልዩነታችንን ወደ ጎን ብለን ለጋራ ጥቅም የምንሰለፍበት ጊዜ ይሁን። እስካሁን በአለማወቅ ብዙ ሆነናል አሁን ግን እንንቃ ዓለም ትቶን እየሄደ ነው። ከኋላ የተነሱ አልፈውን እየሄዱ ነው። ለአንድነታችን እንልፋ..ትንሳኤአችን ከፊት ነው…እስካሁን ወድቀናል አሁን ግን ቀና የምንልበት ጊዜ ነው። ዓለምን ያንቀጠቀጠው የአድዋ ጀግንነት በእኛ የተባበረ ክንድ መደገም አለበት።
ብዙ ልማቶች ብዙ ህዳሴዎች እኛን እየጠበቁ ነው። ብዙ ነገዎች ብዙ ስልጣኔዎች የእኛን አብሮ መሆን እየናፈቁ ነው። ብዙ ተስፋዎች ብዙ ህልሞች የእኛን መመለስ የእኛን መተቃቀፍ እየጠበቁ ነው። ያላገጡብን ያሽሟጠጡን ሁሉ እንዲያፍሩ በአድዋ ማግስት በአንድነት መቆም አለብን። አድዋ የሁላችን ቀለም ነው። አድዋ የእኔና የእናንተ የአንድነት ነጸብራቅ ነው። የኔና የእናንተ አባቶች በደማቸው ያቆሙት እውነት ነው። ባልሰለጠነ ዓለም ያልሰለጠኑ አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው የገነቡልንን እውነተኛ ሀውልት ነው። እኛ በሰለጠነ ዘመን ላይ ስልጡን ነን ባይ አዋቂዎች የአባቶቻችንን አደራ መጠበቅ ሲገባን በመለያየት መቆማችን በጣም ያሳዝነኛል።
ኢትዮጵያ የብዙ አባቶች እውነት ናት። የብዙ ልቦች የብዙ ክንዶች ውጤት ናት። የብዙ ሞቶች የብዙ ስቃዮች ፍሬ ናት። በአንድነት በወንድማማችነት በመቆም ለአባቶቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት መግለጽ አለብን። በጥላቻና በመለያየት ውስጥ ምንም የለም። አባቶቻችን ተለያይተው ቢሆን ምናልባት ዛሬ ላይ እኔና እናንተ በዚህ ልክ ላንገኝ ሁሉ እንችል ነበር። ስልጡን ዘመን ላይ ነው ያለነው እንደዘመኑ ማሰብና እንደዘመኑ መራመድ ያሻናል።
ትላንት ምንም ቢሆን እንኳን መርሳት ነው ያለብን። ለበደሉን ይቅርታ የምናደርግበት አዲስ ጊዜ ላይ ነን። ብዙዎች ሊጥሉን ሊያደናቅፉን እግራችን ስር እንቅፋት እያስቀመጡ ነው። ሊለያዩን ሊያባሉን ቀን ከሌት እየሰሩ ነው ለእኛም ለሀገራችንም ቀጣይነት ስንል በማስተዋል መኖር አለብን። ለኔ ከአንተ ወዲያ ለአንተ ከኔ ወዲያ የሚጠቅምና የሚበጅ ማንም የለም። ዳር ቆመው በለው የሚሉ እነሱ በተደላደለ ህይወት ውስጥ ናቸው ምንም የሌለህን አንተን ለሞትና ለስደት ለእንግልትም ከመዳረግ ባለፈ የሚጠቅሙህ ነገር የለም። ለክፋት ሲመርጡህ ለሞት እያዘጋጁህ እንደሆነ አስብ። አንተ ለዚች ሀገር ታስፈልጋለህ። የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በአንተና በአንቺ በኔም እጅ ውስጥ ነው ያለው። ክብራችን ሀገራችን ናት። መመኪያችን መታፈሪያችን እርሷ ናት። በአንድ እንቁም እንጂ..አንድነት ይኑረን እንጂ ወደፊት የምንሰራቸው በርካት ህልሞች አሉን።
ብዙዎች የኢትዮጵያ ከፍታ አስፈርቷቸው ነው እኔና አንተን በማባላት እድገቷን ለማደናቀፍ የሚሞክሩት። እስካሁን ተጣልተንና ተጋድለን ተለያይተን ያተረፍነው ምንም የለም። መጪው ዘመን የእርቅ እንዲሆንልን ሁላችንም መልካም ፍቃድ እናሳይ። እኔ ፍቅርህን ይቅርታህን ሽቼ ፊትህ አጎንብሻለው አንተም ይቅር በለኝ። በዚህ አይነቱ የአባቶቻችን ስርዓት ታላቋን ኢትዮጵያ እንድንገነባ በአንድነት እናብር እላለሁ። እንደ ህዳሴ ግድባችን ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እኛን እየጠበቁ ነው። አንድነታችንን አብሮነታችንን የሚፈልጉ በርካታ ሀገራዊ ልማቶች ከፊታችን አሉ። እኔ ለአንተ አንተም ለኔ ካሰብን ህመሜን ከታመምክ ህመምክን ከታመምኩ በኔ ጉዳይ ካገባክ በአንተ ጉዳይ ካገባኝ ያኔ እኛን አያድርገን..በሁሉ ነገሯ የምትደነቅ ታላቂቷን ኢትዮጵያ ካልፈጠርን ምናለ በለኝ። ብቻ ግን እኔና አንተ እንፋቀር..እንከባበር..አንድ እንሁን። ብቻ ግን ወንድሜ..ወንድሜ እንባባል።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ስትፈርስ ለማየት ጓጉተው የሚጠብቁ ብዙዎች ናቸው እርሷ አትፈርስም ጠላቶቿ ይፈርሳሉ እንጂ፣ የጠሏት ይወድቃሉ እንጂ፣ ክፉን የሚያደርጉባት ያፍራሉ እንጂ እሷ ምንም አትሆንም። የአድዋ ድል የተባበሩ ክንዶች ውጤት ነው። ተለያይተን አንተም እኔም ካሰብነው አንደርስም። ህልማችን እውን የሚሆነው ስንተጋገዝ አብረን ስንቆም ብቻ ነው። እኔ ላንተ አንተም ለእኔ እናስፈልጋለን ተለያይተን ለየብቻ የምንፈጥረው ተዓምር የለም። ተዓምራችን ያለው በአብሮነታችን ውስጥ ነው..አንድ እንሁን። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013