ሰላማዊት ውቤ
የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት ነው ግብርና ። ከግብርናም ደግሞ በውጭ ገበያ የዶላር ምንጭ የሆነው ቡና ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። ይሁንና ቀደም ባሉት ረጅም ዓመታት የቡና ምርቱ በሚሰጠው ያህል ጥቅም ትኩረት አልተሰጠውም።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሸምሱ ይሄንኑ እውነታ ያረጋግጣሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የቡና ምርት ጉዳትና ጥቅሙን የሚያሳውቅ ባለቤት እንኳን እንዳይኖረው ተደርጓል። ቀደም ብለው በነበሩት ዓመታቶች ቡና ቦርድ፣ቡናና ሻይ ሚኒስቴር እንዲሁም ቡናና ሻይ ባለስልጣን ይባል የነበረበት አደረጃጀት ለመፍረስ ተዳርጓል ። ከዚያ በኋላም በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ በሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት የሰብል ልማት ባለሙያ ፤ወርዶም የቡና ባለሙያ እስከ መባል ደርሷል።
በእነዚህ ዓመታት ሥራ ባለመሠራቱ ብዙ ጉዳት ማጋጠሙን አቶ መሀመድ ያስታውሳሉ ።
ቡናው ባለቤት የሌለው ብሎም የቡናው ምርት ለሀገር ኢኮኖሚና ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅም ሳያስገኝ ቆይቷል። አርሶ አደሩ የምርቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ቡና ላኪዎችም ቡና ወደ ውጭ የሚልኩት በአገኙት አጋጣሚና በጥረታቸው ልክ እንጂ መንግሥት ደግፏቸው እንዳልነበር ይጠቅሳሉ ። እንዲሁም የቡና ግብይት የሚመራበት አዋጅና ደንብ አልነበረም ።የውጭ ቡና ገበያተኞችን ለመሣብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ኮንፈረንስ የለም።
ኃላፊው እንዳሉት ፤ኢትዮጵያም በትላልቅ የዓለም ኮንፈረንሶች ላይ ተሳታፊ አልነበረችም፤ኮንፈረንሶቹንም አታዘጋጅም ነበር ። ይህም በመሆኑም ቡናዋን የማስተዋወቃ እና ገበያን የማፈላለግ አቅሟ የተዳከመ ነበር ። በአጠቃላይ የነበረው የቡና ገበያ ሂደት በዘፈቀደ የሚመራና ቡናን ለኮንትሮባንድ ሰለባ እንዲሆን ያደረገ ነው።
በ2008 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከተቋቋመ በኋላ ቡናው ባለቤት አግኝቷል።አሁንም ከጥራት፣ከኮንትሮባንድና ከሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች ጋር የተያያዙ እንከኖች ቢኖሩም አብዛኞቹ ችግሮች መፈታታቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል ።
ባለስልጣኑ በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለብዙ ዓመት ያልተገኘ ውጤት መታየቱን ይናገራሉ። ወደ ውጭ የሚላከው ቡና መጠን፣ ላኪዎቹ፣ ቡናው የሚያወጣው ዋጋ፣ የሚላክባቸው ሀገራት ብዛት ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።
ኃላፊው እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ የማዘጋጀት ዕድል ማግኘቷ በራሱ የቡና ዕድገት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሄን ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ራሷን ችላ አካሂዳዋለች።ኮንፈረንሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ ለአራተኛ፣በአፍሪካ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።ኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው ባለስልጣኑ ከተቋቋመ በኋላ የኢትዮጵያ ቡና ባለቤት ተገኝቶለታል፣በዚህ ላይ የቡና መገኛ ናት፣ቡናዋም ጣዓሙ ሰናይ በመሆኑም፤ ቡናው በዓለም አቀፍ ገበያ ተመራጭና ተፈላጊ ነው ።በመሆኑም ኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄድ አለበት የሚል ዓለም አቀፍ ውሳኔ ተላልፎና አቋም ተይዞ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ።
በአጠቃላይ ባለስልጣኑ በተቋቋመ አምስት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ላይ የሚሰሩ ሦስት ታላላቅ ማህበራትና ድርጅቶች ስብሰባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አካሂደዋል።
አሁን ላይ በባለስልጣኑ በቡና አልሚው አርሶ አደርና ቡና ወደ ውጭ በሚልከው ገዢ መካከል ያለው ከ15 እስከ 20 የሚደርስ ደላላ ከመካከል እንዲወጣ ሆኗል። ቡናው የሚመራበት ደንብ ተዘጋጅቶ ወጥቷል።አርሶ አደሩ የቡና ምርቱን ቀጥታ ወደ ውጭ የሚልክበት አሰራር ተመቻችቷል። የአርሶ አደሩ የገበያ መስመር እንደ ድሮው አንድ አይደለም። ቢፈልግ በአካባቢው ካሉት ማህበራት ጋር ተሳስሮ እንዲሸጥና እንዲገበያይ ቢሻው ለአቅራቢ እንዲሸጥ የሚያስችሉና እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ አማራጮች ክፍት መደረጋቸውን ነው ኃላፊው ያብራሩት። ቡና ዘመናዊ የገበያ መረጃ መቆጣጠሪያ ስርዓትም ተበጅቶለታል ብለዋል ።
በቅርቡ የባለስልጣኑን የ2013 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገመገመው የግብርና፣ አርብቶ አደርና አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ላሉ ሥራዎችና የገበያ መረጃ መቆጣጠሪያ ስርዓት መዘርጋቱን በመገምገም አድናቆቱን ችሮታል።
ቋሚ ኮሚቴው በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር በአገራችን እንዲዘጋጅ መደረጉን አድንቋል ። የአገርን ገጽታ ከመገንባት፣ የአርሶ አደሮችን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን አመልክቷል። እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና አዘጋጅቶ ሌሎች አሸናፊ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ከማፍራት አንጻር ድርሻው የጎላ እንደሆነ ገምግሟል።
ከዚህ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የገበያ መረጃ መቆጣጠሪያ ስርዓት ተግባራዊ የሚደረግበት ሶፍት ዌር እንዲበለጽግ መደረጉ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ጠቅሷል። የአገራችንን ቡና ለመላው ዓለም ሊያስተዋውቅ የሚያስችለው ብራንድ መዘጋጀቱና በተለያዩ አገራት እንዲመዘገብ የማስደረጉ ሥራ መጀመሩ አበረታች ነው ሲልገልጿል።የግብይት መዳረሻዎቻችን ከማስፋት፣ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ የማተኮር እና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የተሄደበት ርቀት አበረታች መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበሌ፤ የባለስልጣኑን የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ የቀጣይ 10 ዓመት መሪ ዕቅድ መነሻ በማድረግ ሁለንተናዊ ተሳትፎን ባረጋገጠ ሁኔታ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት። ይሄም ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት ‹‹በተለይ ዓለም አቀፉን የቡና ገበያ መቆጣጠር እንዲቻል ጥራት ያለው ቡናን በማቅረብ ረገድ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል›› ብለዋል። የቡና ምርትና ምርታማነት ከፍ ለማድረግ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ የቡና ዛፎችን የማደስ ሥራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ አስረድተዋል።
በተጨማሪ በቂ የቡና ባለሙያ ከማፍራት አንጻር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ እየተሰጠ እንደሚገኝም ሲገልፁ ተደምጠዋል። ከሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ሁለገብ የቡና እና ቅመማ ቅመም ስልጠና ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ባለሙያዎችን ለማሰልጠንም የስምምነት ሰነድ መፈረሙን ነው የተናገሩት። ደረጃውን የጠበቀ የቡና ቅምሻ ስልጠና ማዕከል እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቡና ቅምሻ ላቦራቶሪ ተገንብቶ ለትግበራ እየተዘጋጀ ይገኛል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንደገመገሙት ባለስልጣኑ እየሰራ ያለው ሥራ አበረታች ነው።በቀጣይም አገሪቱን እና በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና ምርታማነትን ለማስፋፋት በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013