አስናቀ ፀጋዬ
በተፈጥሮ የማእድን ሃብቶች ከታደሉ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ አንዱ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንዱ መሆኑ ይነገራል። በክልሉ ወርቅን ጨምሮ የከበሩ፣የጌጣጌጥና ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ማእድናት በስፋት እንደሚገኙም ከክልሉ ማእድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ሁሉ የማእድን ሃብት እያለ ታዲያ ሃብቱን በስፋት ጠቅም ላይ በማዋል በየደረጃው ያለ አካል እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ አሁንም በርካታ ማነቆዎች እንዳሉ ይጠቀሳል።
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀዳለ አይዛ በክልሉ በስፋት ከሚገኙ የማእድን ሃብቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ወርቅ መሆኑን ይናገራሉ። ማእድኑ በምእራብ ኦሞ ዞን በቤይሮ፣ ሱርማ፣ ማጂና ሚሊዲሻሻ ወረዳዎች ላይ ይገኛል። በሱርማና ማጂ ወረዳዎች ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወርቅ እየተመረተ ባለመሆኑም ማእድኑ ከቤይሮ ወረዳ ብቻ ለብሄራዊ ባንክ እየቀረበ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በስፋት ወደሥራ ያልተገባበት ቢሆንም በክልሉ ምእራባዊ አካባቢዎች ባሉ በቤንች ሸኮና በከፋ ዞኖች የብረትና የድንጋይ ከሰል ማእድናት እንዳሉም ጥናቶች አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ በዳውሮ ኮንታ ከፊል ወላይታና ከፊል ጋሞና ጎፋ ላይም የድንጋይ ከሰል ማእድን በስፋት ይገኛል። አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎችና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም በተወሰነ መልኩ ገብተው ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ።
ከዚህ ውጭ ቤይሮ ወረዳ ላይ ለህንፃ ግንባታ የሚሆኑ የኮንስትራክሽን ማእድናት ለአብነትም የእምነበረድ ማእድናት በጥናት ተለይተው ወደ ሥራ እየተገባባቸው ሲሆን ባለሃብቶችም ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰው አንዳንድ ሥራዎችን ጀምረዋል።
በማእከላዊ የክልሉ ዞኖች በተለይም በጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሃድያና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ደግሞ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ማእድናት በስፋት ያሉ ሲሆን ለአብነትም ካኦሊን፣ ኢንዲስፓርና ላይምስቶን የመሳሰሉ ማእድናት ይገኙበታል። በጋሞጎፋ ዞንና ደቡብ ኦሞ ቡርጂ አካባቢ በጥናት ተለይተው ለውጭ ምንዛሪ ሊቀርቡ የሚችሉ የጌጣጌጥ ማእድናት በተለይም በአሁኑ ወቅት በውጭ ገበያ ላይ ጥሩ ገበያ እያስገኙ ያሉ አኳማሪንና አጌት ማእድናት ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በስፋት ገበያ ያላገኘና በስፋት የሚመረት አማንዞናይት የተሰኘ ማእድን እንዲሁም ፍሎራይድ፣ጋርኔትና የመሳሰሉ ማእድናትም በክልሉ ይመረታሉ። በኮንሶና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ላይም ለግንባት ግብአት የሚውልና ሰፊ ገበያ ያለው ግራናይት የተባለ የኮንስትራክሽን ማእድንም በስፋት ይመረታል።
በደቡብ ኦሞ ዞን በአርብቶ አደር ሰላማጎ በተሰኘ አካባቢ ሰፋ ያለ የብረት ማእድንም እንደሚገኝ በጥናት የተለየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግሥት አንድ ኩባንያ ልኮበት ወደ ሥራ ለመግባት ሂደት ላይ ይገኛል። ታንታለም የተሰኘ ማእድንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ መኖሩንም ጥናቶች ጠቁመዋል። ነገር ግን ጥናት በስፋት የሚፈልጉ ሌሎች ማእድናት እንዳሉም ታውቋል።
እንደዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ በክልሉ ያሉ ልዩ ልዩ ማእድናት በጥናት እንዲለዩ ከተደረገ በኋላ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው መእድናትን እያመረቱ ለባለሃብቶች በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ባለሃብቶች ደግሞ ወጣቶቹ ያመረቷቸውን የማእድን ምርቶች በመረከብና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ።
ለአብነትም በጋሞ ዞን ገረሴና ማርታገርዳ በሚባሉ ወረዳዎች ላይ ወጣቶች ተደራጅተው አኳማሪን የተሰኘውን ማእድን በማምረት ለላኪ ባለሃብቶች ያቀርባሉ። ባለሃብቶቹ ደግሞ ምርቱን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል። በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች ላይም የድንጋይ ከሰል የሚያመርቱ ወጣቶችን በማደራጀትና ከትላልቅ ኩባንያዎች ጋር በማገናኘት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል።
ለዚህም በማእድን አጠቃቀም ዙሪያ ለወጣቶቹና ባለሃብቶቹ የሚያገለግል የመግባቢያ ሰነድ በክልሉ የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ በኩል ተዘጋጅቷል። ይሁንና የማህበረሰቡ ግንዛቤ አሁንም ባለመቀየሩና አንዳንድ ኩባንያዎች ሲመጡ ሃብታችንን ይወስዱታል የሚል የተዛባ አመለካከት በመኖሩ ከማእድን ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ጠቅም ማግኘት አልተቻለም። ይህም እስካሁን ድረስ የክልሉን የማእድን ሃብት ለመጠቀም ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ማነቆ አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ ቢሆንም ወጣቶችን በተወሰነ ደረጃ በማደራጀት ከዘርፉ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ማዕድን በሚገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ የጥናት ተደራሽነት አለመኖር ለዚህም ከመንግሥት በኩል ከፍተኛ የበጀት እጥረት መኖር፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የላብራቶሪ ተደራሽ አለመሆንና አለመሟላት፣ በየደረጃው ያለው አካል በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ በማእድን ዘርፍ ሥራ ለመሳተፍ አቅም ያላቸው የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ያለመኖርና ህገወጥ የማእድን ንግዶችም የክልሉን የመእድን ሃብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል ተጨማሪ ማነቆዎች ሆነዋል።
የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችም የክልሉ መእድን ዘርፍ ሌሎች ማነቆዎች ሲሆኑ በተለይ ደግሞ ወርቅ በስፋት በሚመረትበት የአርብቶ አደር አካባቢ ቤይሮ ወረዳ የባንክ ተዳራሽ አለመሆን የዘርፉ ትልቁ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። ከወርቅ በተጨማሪ አካባቢው የገበያ ሰብል አምራችና ሌሎችም የማእድን ሀብቶች በስፋት የሚመረቱበት ከመሆኑ አኳያ የብሄራዊ ባንክ በአካባቢው ላይ ባንክ እንዲከፈት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ድረስ ግን ለጥያቄው መልስ አልተገኘም። የማምረቻ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ውስንነት፣ በማሽን የታገዘ የአመራረት ሥርዓት ያለመኖርና በምርት ላይ እሴት የሚጨምሩ መሳሪያዎችን ለወጣቶች አለማቅረብም ሌሎች የዘርፉ ማነቆዎች ናቸው።
ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ለውጡ ከመጣ ወዲህ የክልሉ ማእድን ዘርፍ በተወሰነ ደረጃ ትኩረት እያገኘ መጥቷል። እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት በተለይ ደግሞ የባንክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ብዙ ጥረቶችን ቢያደርግም እስካሁን ግን ምላሽ አላገኘም። ሆኖም በቴክኖሎጂ የታገዙ መሳሪያዎችን ለማቅረብ የፌዴራል ማእድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል።
የማእድን ጥራት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ኤጀንሲው በክልሉ ከሚገኙ አርባ ምንጭ፣ ዲላ፣ ወላይታና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ጥናቶችን እያስጠና ይገኛል። ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬዬ ጋርም በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013