ፍቅሬ አለምነህ
ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከጀርባ በዓለም አቀፍ ተዋናዮች ተደግፈው እናፈርሳታለን፤ እንበታትናታለን ይህም ካልሆነ ብሔር ከብሔር ጎሳን ከጎሳ እያባላን፤ እያፋጀን፤ ሰላም ያጣች፤ ስትታመስ የምትኖር መረጋጋት የሌላት ሀገር እናደርጋታለን ብለው እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም እየሰሩ ነው። ወግድ ሱዳን !! ወግድ ግብጽ !! ብለናል።
የዚህ ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ዋነኛዋ ባለቤትና ተዋናይ የሴራው ጠንሳሽ መሪና አቀናባሪ የካሊፋይቶቹ ሀገር ግብጽ ነች። ግብጽ ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ጠላት የጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መቀፍቀፊያ አደራጅ በፋይናንስ የምታግዝ በካይሮና በአሌክሳንደሪያ ቢሮ ለእያንዳንዳቸው ሰጥታ የሬድዮ ጣቢያ ከፍታ ኢትዮጵያን ለዘመናት ስትወጋ ስታደማ የኖረች ሀገር ነች። የእጇ ን የምታገኝበት ቀን ሩቅ አይሆ ንም።
የግብጽ ወታደራዊ መሪዎች እብሪተኛና አምባገነን የሆኑ የራሳቸውን ሕዝብ የዳቦና የስራ አጥነት ጥያቄ መመለስ ያልቻሉ በስልጣን ጥም የሰከሩ ከአቅማቸው በላይ የሚንጠራሩ ግን ደግሞ ወደዱም ጠሉም በሕዝቡ ትግል እንደተለመደው ከስልጣን የሚወገዱ ወደ መቃብር የሚወርዱ ናቸው።
አልሲሲም እንደሌሎቹ አምባገነኖች ሁሉ የሚጠብቀው እጣ ፈንታ ይኸው ነው። ግብጽ የምትባል ሀገር ከበረሀነት በዓባይ ውሀ አማካኝነት ነው ወደ ገነትነት የተለወጠችው። ግብጽ የዓባይ ውሀ 85 በመቶ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሰላም ለማሳጣት ለዘመናት የሄደችበት የሴራ፤ የተንኮል፤ የምቀኝነት መንገድ ላስተዋለ ምን ያህል በኢትዮጵያ ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ እንዳላቸው በገሀድ ያሳያል።
ግብጽ የበረሀ ገነት የሆነችው በእኛው የአባይ ውሀ ነው። ኢትዮጵያ ግድብ እንዳትሰራ ግብጾች ከጀርባ በሚያደርጉት የሴራ ፖለቲካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖና ጫና እየተደረገብን በተፈጥሮ ሀብታም የሆነችው ሀገር ኢትዮጵያ በድህነት በተረጂነት እየማቀቀች እንድትኖር አስገድደዋት ኖራለች። ዛሬ ያ ጨዋታ አብቅቶአል። የግብጽንና የሱዳንን መሰሪ መሪዎች ሴራ ወግድ ብለናል። ወግድ ሱዳን። ወግድ ግብጽ። የሀገራችንን እጣ ፈንታ ልማትና እድገት የምንወስነው እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም።
በእኛ ውሀ ሱዳንም ሆነ ግብጽ የማዘዝ የመጫን አንድም ምንም መብት የላቸውም። ለዚህ የሚንበረከክ ትወልድ የለንም።
የሰላሙን በር ረግጠው ድንፋታና ዛቻ ውስጥ ከገቡ ሰነበቱ። እብሪታቸው ተንፍሶ በዓለም ፊት የሚዋረዱበት ግዜ ሩቅ አይደለም።
በእኛው የዓባይ ውሀ የግብጽም ሆነ የሱዳን ካሊፋይቶች ሊነግዱበት ጭራሹንም ሊያዙበት አይችሉም። እኛ የእነሱን ነዳጅ አልጠየቅንም።አካፍሉን አጋሩን ኑና እንደራደር አላልንም። በውሀችን የማዘዝ መብታችን የተጠበቀ ነው። ካልመሰለን ለእኛ ካልተመቸ የሀገሩን ብሔራዊ ጥቅም ለባእድ አሳልፎ የሚሰጥ ተፍረክርኮ ተብረክርኮ የሚጎናበስ ልጅ በኢትዮጵያ ምድር አልተወለደም። በኩራት ለሀገራችን ለመዋጋት ለመሞት ዝግጁዎች ነን። ለሱዳንና ለግብጽ ሴራ አንንበረከክም። መጣችሁብን ዛዲያማ ገጠምነ ነው ነገሩ።
በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ብዙ ርቀት ሄዳ በተለያዩ መንግሥታት ዘመን በሰላም ተፈጥሮ የለገሰንን ውሀ ተካፍለን መኖር እንችላለን የሚል ሀሳብ ለግብጾችም ሆነ ለሱዳኖች ስታካፍል ኖራለች። ጉዳዩ ከመቸውም ግዜ በላይ በዚህ ዘመን ግልጽ ነው።
የእነሱ ፍላጎት ኢትዮጵያ በድህነት በርሀብ በተፈጥሮ ድርቅ በአየር ንብረት ለውጥ እየተመታች እያላት ሳትጠቀምብት ድሀ ሆና ስትኖር ግብጽ ደግሞ በእኛው የዓባይ ውሀ ታላላቅ ግድቦችን ሰርታ መስኖ እያለማች፤ የአትክልት እርሻ እያረሰች በዓለመም ገበያ እየሸጠች፤ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ሰርታም እየተጠቀመች ጭራሹንም ድሆች ችጋራሞች ረሀብተኞች ተረጂዎች እያሉ አንዳንድ የግብጽ መሪዎችና ምሁራን ሲሳለቁብን ኖረዋል። አሁን ያ ዘመን ያበቃል። ወግድ ሱዳን ወግድ ግብጽ!!
የዓባይን ወንዝ ውሀ ከፈለግንም ገባር ወንዞቹን በሙሉ አቅጣጫቸውን በመቀየር ወደ መስኖ ልማት እናውለዋለን። ከልካይ የለንም። ደግሞም ይህ የሱዳንና የግብጽ እብሪት ካልተነፈሰና ልክ ካልገባ እናደርገዋለን። ዘለአለም ግብጽ ኢትዮጵያን ከዘመን ዘመን ከትውልድ ትውልድ ስትወጋን ስታደማን አትኖርም። ወይ አብረን ተከባብረን እንኖራለን፤ አሊያም ተያይዘን አብረን እንጠፋለን። ኢትዮጵያ ጠፍታ ግብጽ የምትባል የስግብግቦች ጠገብን የማያውቁ መሪዎች ያሉባት ሀገር አትኖርም። የሚሆነውም ይኸው ነው።
ዲፕሎማሲም መጠንና ደረጃ አለው። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንም ከሁለቱም ሀገራት ጋር ልናቋርጠው እንችላለን። በ24 ሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የሱዳንንም ሆነ የግብጽ ሰላይ ዲፕሎማቶችን የተለያዩ ድርጅቶቻቸውንና ዜጎቻቸውን ሀገራችንን ለቀው እንዲወጡ ማድረግ እንችላለን። እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደረገ፤ ብዙ የታገሰ፤ ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ የሰጠ ሀገር የለም። ኢትዮጵያ የእኛ እንጂ የእነሱ አይደለችም።
ሀገሩ የእኛ ግዛት እንጂ የግብጽ ወይንም የሱዳን አይደለም።ግብጽ የቀድሞውን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን እስከ አፍንጫው ታንክ መድፍ ቢኤም ተዋጊ ሚግ ጀቶች አስታጥቃ የኢትዮጵያን ግዛት 700 ኪሎሜትር ጥሳ እንዲገባ ያደረገች ሀገርሡ ከስልጣን ስለወረዱ የኢትዮጵያ ጀነራሎችም ብዙዎቹ ስለተቀነሱ ወደ አመራር የመጡት መኮንኖች ስለማይችሉ ኢትዮጵያ መወረር ያለባት ሰዓቱና ወቅቱ አሁን ነው የሚለውን ውሳኔ ያሳለፉት የግብጽና ሶማሌ መሪዎች በአንድነት ሆነው ነው። ግብጽ አሁን ደግሞ በሱዳን በኩል መጣች። ወዳጄ ዘለአለም ስንወጋ ስንደማ ስንሞት ስንገደል አንኖርም። ወግድ ሱዳን። ወግድ ግብጽ።
ልክ ዛሬ ግብጽ ከጀርባ ሆና ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወራ እንድትይዝ ጀነራል አልቡርህን የሚባል የምታግለበውን ፈረስ አሰማርታ መሬታችንን እንዲያዝ እንዳደረገችው አይነት ማለት ነው። የሱዳን መሪዎች ከሰውነት የወረዱ ለመሆኑ ማሳያው በግብጽ ለረዥም ግዜ የተያዘባቸውን መሬት ማስመለስ ያልቻሉ ነጻነታቸውን አሳልፈው የሰጡ መሆናቸውን ስታይ ነው።
ኢትዮጵያ ለሱዳን ብዙ ውለታ የዋለች ሀገር ነች። አሁንም ቢሆን ከሱዳንና ከግብጽ ሕዝብ ጋር ያለን ወንድማማችነት አይሻርም። የሱዳን መሪዎች ለግብጽ በባርነት ያደሩ ሎሌዎችና አሽከሮች ናቸው። ታሪክና ክብር ያለውን ለኢትዮጵያም ሕዝብ ወንድም የሆነውን የሱዳንን ታላቅ ሕዝብ የመምራት ብቃትና ችሎታ የሌላቸው ናቸው እነ ጀነራል አልቡርሀን።
ከግብጽ ባርነት ያልወጡት የሱዳን መሪዎች ታላቅ የሆነውን የሱዳንን ሕዝብ መብትና ነጻነቱን ያስከብሩለታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ጀነራል አልቡርሀን ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደተገመተው አስር ግዜ ካይሮ ሲንጦለጦል ስለነበር የማርሻል አልሲሲ አሽከር አገልጋይና ተላላኪ እንደሚሆን ሰፊ ግምት ነበር። ጀነራሉ በራሱ መቆም የማይችል ፤በራሱ እምነት የሌለው ሰው መሆኑ ስለሚታወቅ ። የሆነውም የተገመተው ነው።
የሱዳንን ሉአላዊ ሀገርነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፤ ሱዳን የግብጽ ቅኝ ግዛት ነች እንድትባል ያስደረገ ግን ደግሞ በሱዳን ሕዝብ መሪነት የተቀመጠ ሰው ነው ጀነራል አልቡርሀን።
የሱዳንም ሆነ የግብጽ የውስጥ ፖለቲካቸው ሲታመስና የሕዝብ ከስልጣን ውረዱ ግፊት ሲበዛ እንደ ማስታገሻ የሚወስዱት በዓባይ ውሀ ጉዳይ ንትርክ ውስጥ መግባትና ከኢትዮጵያ ጋር መፋጠጥን ነው። ኢትዮጵያ የእነሱ ችግር ማስተንፈሻ ወይንም ማስታገሻ አይደለችም። አንሆንምም።
የኢትዮጵያ መንግሥት የላቀ ትእግስትና የጠለቀ ዲፕሎማሲያዊ ብቃቱን ለእነሱም ለዓለምም አሳይቶአል። በዚህ ረገድ የሀሰት ትርክት እየፈጠሩ ግብጽና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ቢዘምቱም የተሳካላቸው ነገር የለም። ጭራሹንም ከሰሞኑ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ቀጣዩን የውሀ ሙሌት ብቻዋን ልትሞላ አትችልም ችግር ይፈጠራል እያሉ ነው። በገዛ ቤቴ ማን አባቱ አግብቶት ምን ቁርጥስ አድርጎት ነው እኔ ነኝ የምወስነው የሚለው አሉ አባት አርበኛው በመደመም። ሱዳንንም ግብጽንም ወግዱ አትጃጃሉብን ብለናል። በማን ሀገር በማን ቤት ማን ያዛል ?
እኛ በባርነት አልኖርንም። በእንግሊዝም ሆነ በኢጣሊያን ቅኝ ግዛት አልተገዛንም። ለነጻነታችን ፍጹም ቀናኢ የሆንን ሕዝብ ነን። ቀጣዩን የዓባይ ውሀ ሙሌት አሳምረን እንሞላለን። ካሊፋይቶቹ ማዘዝ የሚችሉት በገዛ ሀገራቸው ጉዳይ ወንዝ ካላቸው በራሳቸው ወንዝ ብቻ ነው።
በተለይ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ለመበታተን ለብዙ ዘመናት ስታሴር፤ ጠላት ስታበጅልን፤ ገንጣይ ቡድኖችን ስታሰለጥን፤ ስታደራጅ ኖራለች። ውጊያ ስታስከፍት ስትወጋን፤ የራሳችንን ዜጎች እየደለለችና እየገዛች በኢትዮጵያ ላይ ቁማር ስትጫወት ስታሰማራ የኖረች ሴረኛ ሀገር ነች።
የምንግዜም ታሪክ ይቅር የማይለው በደልና ግፍ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመች ዛሬም ከዚህ ቆሻሻ ተግባሯ ያልታቀበችው ብቸኛ ሀገር ግብጽ ነች።
ጥንት ኢትዮጵያን ለመውጋት ጦር አዝምታ ከአንዴም ሁለቴ ተገርፋ ተደምስሳ የተባረረች ሀገር ነች ግብጽ። ዛሬም ከሞከረች መጥፊያዋ ይሆናል። የትኛውም የኢትዮጵያ ትወልድ የግብጽ መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን የከፋ ግፍና በደል አይረሳም። ግብጽ ከጀርባ በምትሰጠው ድጋፍ በየጦር ሜዳው የወደቁትን ያለቁትን ኢትዮጵያውያን ሰማእቶች መቼም አንረሳም። ዛሬም በመተከል የጉምዝ ታጣቂዎችን በማሰልጠንና በመርዳት ከጁንታው ርዝራዦች ጋር በማበር የምትወጋን ግብጽ ነች። ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ከፍታ የጁንታውን ወታደራዊ መኮንኖች በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ጠልቀው እየገቡ ጥቃት እንዲፈጽሙ ሰው የሚያርዱት የሚያሳርዱት ፤ ቤትና ንብረት የሚያቃጥሉት እነሱው ናቸው።
እኛም እነዚህን ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የገቡበት ገብተን እንፋለማቸዋለን። የሱዳን መሪዎች አሁን የግድ የኢትዮጵያን መንግሥት ስበው ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ነው እየታገሉ ያሉት። አልፈው መሬታችንንም የያዙት በግብጽና በጁንታው መሪዎች ግፊት ነው።ትእግስታችን ሰፊና ጥልቅ ነው። ወስነን ስንነሳ ደግሞ ምንና እንዴት ማድረግ እንዳለብን የመጫወቻ ሜዳው ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያውቀው አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው።
ያንን መላው ዓለም ያውቀዋል። ወግድ ሱዳን፤ ወግድ ግብጽ የምንለውም ለዚህ ነው።
ይሄንን ከልካይና ሀይ ባይ ያጣ እየተግተለተለ ሰው ማሳ ውስጥ ገብቶ መሬቴ ነው የሚለውን መንጋ የተወለደበትን ቀን እስኪረግም ድረስ መግረፉን ጀግኖቹ ያውቁበታል። ኢትዮጵያን መንካት መድፈር ታላቅ ዋጋ ያስከፍላል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገርም እንደ መንግሥትም እድሜ ዘመኗን በጦርነት ውስጥ የኖረች ሀገር ነች። አንነካም። አንደርስም። ከነኩን ከደፈሩን ደግሞ እንደ እሳተ ገሞራዊ እቶን እሳት ጋይተው አንድም ለወሬ ነጋሪ ሳይወጡ አመድ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። ጀግናና ተዋጊ ለሀገሩ ሲባል ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የማይሳሳ ወደኋላ የማይሉ አምበሶች ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ወግድ ሱዳን!!ወግድ ግብጽ !! ብለናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013