ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ
አዲስ አበባ ውሃ በፈረቃ ለነዋሪው እያዳረሰች ነው። ይቅርታ እያዳረሰች ነው ማለት እንኳ ከበደኝ፤ እያቃመሰች ነው። አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለን ከትምህርት ቤት ስንመለስ ግር ብለን ሻይ ቤት ገብተን በብርጭቆ ተቀድቶ የተዘጋጀ ውሃ እንጠጣ ነበር፤ ወደ መንደር ውስጥም ከሆነ በር አንኳኩተን ውሃ ስጡን ብለን እንጠጣለን፤ ዛሬ የዘመነ ጊዜ መጣና እንኳን የሰው ቤት ሻይና ምግብ ቤት የሚበላ አልያም የሚጠጣ አዛችሁ ውሃ ብትጠይቁ ውሃው የደፈረሰ ነው የበርሜል ነው አልያም ውሃ የለም ትባላላችሁ።
አንዳንዶቹ ደግሞ ስንት ሌትር? ብለው ይጠይቋቹሃል። የታሸገ ውሃ ያመጣብን ጣጣ ይመስለኛል። እንደኔ ዓይነቱ የታሸገ ውሃ ገዝቶ የመጠጣት አቅም ባይኖረውም ብዙዎቹ ውሃ የለም ሲባሉም ሳይባሉም የታሸገ ውሃ የሚጠቀሙ ሆኑ።
አዲስ አበባ ውሃ የገባላት በ1886ዓ.ም ሲሆን፤ ከእንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ የተጠለፈውን ውሃ በቧንቧ እንዲዘረጋ ያመቻቸው ስዊዘርላንዳዊው የንጉሡ አማካሪ አልፍሬድ ኤልግ ነበር። በወቅቱ በእምዬ ምኒሊክ ቤት ውሃው ሲገባ ውሃ ቁልቁለት ይሄዳል እንጂ እንዴት አቀበት ይወጣል ተብሎ ተተቸ።
ውሃው ሲገባ ሰዎች ከእልልታ ይልቅ ኡኡታ ያበዙ ይመስለኛል፤ እንደውም ውሃ አቀበት ከወጣ የሰይጣን ሥራ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያጣጣሉትና ያብጠለጠሉት ነበሩበት። በወቅቱ መቼም ውሃ ከቧንቧ ተቀድቶ የሚሰጣቸው ሰዎች ምንጭና ወንዝ እያለልንማ ትቦ (ትንባሆ አላልኩም) አንጠጣም የሚሉ ይመስለኛል።
ቤተ መንግሥት የቧንቧ ውሃ አገልግሎት በገባ ሰባት ዓመት በ1893 ዓ.ም. የከተማው ኗሪ የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነ። ለንጉሡ የተዘረጋው ውሃ ቀስ በቀስ ለነዋሪውም ተረፈ፣ መቶ ዓመትም አለፈ ፤ ከከተማው ጋር ማደግ የነበረበት ውሃ አቅርቦት በፈረቃ መሆኑ ከፋ እንጂ አሁንም በቧንቧ እያለፈ ነው።
በአንዳንድ ቦታዎች ውሃ በፈረቃ መሆኑ ሲገርማችሁ የሚመጣው በጨረቃ (በምሽት) መሆኑን ሰምቻለሁ፤ በአዲስ ከተማ አካባቢ ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች፤ በፊት ምሽት ላይ ውሃ መጣ የሚለውን ለማየት ቧንቧ ስንከፍት እንቅልፍ እንዳይጥለን ስንዋትት ነበር። በኋላ ጎረቤት ተራ በተራ በሳምንት ሦስት ቀን ሌሊት ለሚመጣው ውሃ እየጠበቅን ጎረቤት ቀስቅሰንና ነግረን እንቀዳለን ብለውኛል።
በማዘጋጃ ቤቱ የወጣ ማስተር ፕላን ከተማዋን ለማሻሻል ትኩረት ቢደረግም ከተማዋ ወደጎን እንድትለጠጥ ከማድረግ ውጪ የመጣ ለውጥ የለም።
ለውጡ ከመጣም ወዲህ በውሃው ላይ የመጣ ለውጥ አላየሁም። ነዋሪው ታጋሽ ስለሆነ ውሃ አጠረን ብሎ ነውጥም አያስብም። ዝም ሲልም ውሃና ፍሳሽ ተመችቶት ነው ብሎ በደስታ ፍስስ እንዳይልና እንዳይዘናጋ አደራ እላለሁ፤ ለነገሩ ውሃ ፍሳሽ አልተዘጋም እንጂ ከተዘናጋ እኮ ዘመናት አለፉ። ያው”ነዋሪው ተው ቻለው ሆዴ!” ብሎ ነው እንጂ የውሃው ጉዳይ ከባድ ነው።
የውሃና ፍሳሽን ገበና የሸሸጉት የታሸጉት ውሃዎች ናቸው፤ የታሸጉ ውሃዎች ብዛታቸውን ቤት ይቁጠረው፤ግን የውሃና ፍሳሽ ገበና በመሸሸግ የታሸጉት ውሃዎች ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል። የመጠጥ ውሃ ሲያጡ የታሸገ ውሃ እየጠጡ ችግራቸውን ያስታገሱ ብዙ ናቸው። ችግሩ ግን የታሸገ ውሃ ገዝቶ ልብስ ለማጠብ መሞከር ቀርቶ ማሰብ የማይቻል መሆኑ ነው።
የታሸጉ ውሃዎች ስማቸው ራሱ በየጊዜው ይቀያየራል። ስማቸው ደግሞ የጉድ ነው። አላጣራሁም እንጂ እኮ ፍርፍር ውሃ ብሎም የመጣ ሊኖር ይችላል። አቢሲንያ፣ ቶፕ አንዳንዶቹ ስማቸው ላልተማሩት ቀርቶ እንደኔ ትንሽ ፊደል ለቆጠሩትም ለመጥራት ያስቸግራሉ፤ ስያሜቸውንም በእንግሊዝኛ የጻፉ አሉ። ስማቸውን መቀያየር አገልግሎት የመለወጥ አካል ነው እንዴ ብዬ? እጠይቃለሁ ለራሴ። የታሸጉ ውሃዎችን ስማቸው ስለበዛብንና ስለሰለቸን በጅምላ ስያሜ ሃይላንድ ብለን እንጠራቸዋለን ያሉኝን ሰውዬ አስታውሳለሁ።
የታሸገ ውሃ ፋብሪካ ባለሀብቶች በማዳረስ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር መልካም ሥራ ሠርተዋል። ግን ጅቡቲና ሶማሊያ ወደ መሳሰሉ ሀገሮች ውሃ እየላኩ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አይቻልም እንዴ? ወይስ ሀገሬ ወይም ሞት? ብለው ነው ሀገር ውስጥ የቀሩት? ወይስ ለነዋሪም ማዳረስ ተስኗቸው ነው? የሚለው ጥያቄ ነው።
ምንም እንኳን የውሃ ፕላስቲኮች በጆንያ እየተሰበሰቡ አካባቢ ከመበከል እንዲታቀቡ ጥረቶች ቢታዩም በፋብሪካ ድጋሚ የሚመረቱበት ዕድል ቢኖርም በተለያዩ ክልሎች የሚጣሉትን የውሃ ፕላስቲኮች የሚሰበሰቡበትን መንገድ ግን አላየሁም።
ህንፃውም ለነዋሪዎች የሚሆነው አነሰ እንጂ እየጨመረ ነው። በገጠር አካባቢ በዛፎች ተከልሎ ደጅ የሚወጣና በከተሞች በጉድጓድ መጸዳጃ ቤት የሚፈልግ ዜጋ ወደ ህንፃ ኗሪነት ሲቀየር ዘመናዊ መፀዳጃ ቤት መጠቀም ይጀምራል። ይህ ውሃ በብዛት የሚሻ ሲሆን፤ ውሃ የሌለው ቀን ደግሞ ጠረኑ እቤት የሚያስቀምጥ አይሆንም። የት ነው የመጣሁት ከቤት ውጣ ውጣ የሚያሰኝ ነው።
አዲስ አበባ እየተጨነቀች ያለችውና አፍጥጦ በሚጠብቃት በመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ነው። እንደ ቀድሞው ዘመን ከወንዞች በመቅዳት ልብስ ለማጠብ እንኳ በመጸዳጃ ቤት፣ በፋብሪካ ፍሳሾችና ቆሻሾች ስለተበከሉ አይታሰብም።
ከተማዋ በቀን እያመረተች ያለው የውሃ መጠን 500ሺ ኪዩብ ነው። በቀን የሚያስፈልጋት የውሃ መጠን ግን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በላይ ነው። በሁለተኛው የከተማዋ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ አቅርቦት ቢያስፈልግም አልተሳካም።
ለነገሩ ያለውን በስርዓት መጠቀሙ አቅቶናል። የውሃ አጠቃቀማችንም ልክና መልክ የለውም፤ ሥርዓት አልባ ነው፤ በመጠጥ ወይም በቧንቧ ውሃ መጸዳጃ ቤቶች እናፀዳበታለን፤ መኪናም ይታጠብበታል፤ ግድግዳቸው የአፈር የሆኑ ቤቶች ለመለሰን ጭቃውን ለማቡካት የመጠጥ ውሃ እንጠቀማለን፤ ሲሚንቶና አሸዋም ለማቡካት ቤትና ህንፃ ለመለሰን እንጠቀምበታለን።
መንገድና በረንዳ ለመጥረግና ለማጽዳት ስንፈልግም በክሎሪን የፀዳውን ውሃ እንጠቀማለን። ይህን ሳስበው ግን ውሃ አጠቃቀማችንን መልሶ ግልጋሎት ላይ በማዋል (በሪሳይክል) መጠቀም አንችልም እንዴ ? ውሃ ፍሳሽስ ምን እየሠራ ነው የሚለውም ጥያቄዬ ነው ማንሳት የምፈልገው። ስራዎቹ እስካሁን ጎልተው ስላልታዩኝ።
እኛም ውሃ ስነጠቀም በአጠቃቀም ላይ መተዛዘንን ባህል ማድረግ አለብን ፤ውሃ እደልብ የማግኘት እድል ስላገኘን ውሃውን አልቅጥ መጠቀምና ማፍሰስ የለብንም። ልብሳችንን አጥበን ፍሳሹን እንደገና ለመጸዳጃ ቤት (በተለይ ለህንጻ ነዋሪዎች)፣ ቤት ለመለሰን አፈር ለማቡካት መጠቀም እንችላለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013