አስናቀ ፀጋዬ
አቶ ካላቃ ገነሞ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የማልቃ ወረዳ ማዲቾ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እርሳቸው በሚኖሩባት ከተማ አቋርጦ የሚያልፈው አቧራማ መንገድ በእግርም ሆነ በተሽከርካሪ ለመጓዝ አስቸጋሪ ሆኖ እንደቆየ ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ነብሰ ጡር ሴቶችና የታመሙ ሰዎች ወደ ጤና ተቋም ለመድረስ ረጅም ሰዓታት እንደሚፈጅባቸውና አንዳንዴም ጤና ተቋም ሳይደርሱ ሰዎች የሚሞቱበት ሁኔታ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
የአካባቢው አርሶ አደሮችና ነጋዴዎችም ምርቶቻቸውን ወደ መሃል ከተማ አውጥተው ለገበያ ለማቅረብ ሲቸገሩ እንደነበርም ያስረዳሉ። በመንገዱ መበላሸት ምክንያት ተደጋጋሚ የመኪና አደጋ ደርሶ እንደነበርና የሰዎች ህይወት ማለፉንም ይገልፃሉ።
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሃዌላ- ወተራሬሳ-የዩ-ወራንቻ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በይፋ ማስጀመሩን ተከትሎ እርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ነዋሪዎች ተስፋን የፈነጠቀ ዜና መስማታቸው አስደስቷቸዋል። የመንገዱ መገንባት እስካሁን ድረስ በጉጉት ሲጠባበቁት የነበረ መሆኑና በአሁኑ ወቅት ሥራው በመጀመሩ ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ይገልፃሉ።
የመንገዱ ግንባታ መጀመር እስካሁን ድረስ በህብረተሰቡ ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮችን በተለያየ መንገድ እንደሚቀርፍ፤ ለዚሁ የመንገድ ግንባታ በተለይ ከወሰን ማስከበር ሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት ለማቃለል ጎረቤቶቻውን በማስተባበር ለወሰን ማስከበሩ ሥራ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት ።
በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የመልጋ ወረዳ ትራስፖርትና መንገድ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አረጋ ኢታበብ የሃዌላ- ወተራሬሳ-የዩ-ወራንቻ መንገድ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰራ ቃል የተገባ ቢሆንም በአካባቢው ነዋሪ ላይ የተለያዩ ችግሮችን በመፍጠር ሳይሰራ ከአሥራ ሶስት ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ይገልፃሉ። ህዝቡም ከነገ ዛሬ ይሰራል እያለ በጉጉት ሲጠብቅ እንደቆየና ብዙዎችም ይህን እንደናፈቁ ሳያዩ ህይወታቸው ያለፈ እንዳሉም ይናገራሉ።
በተለይ ደግሞ በ2010 እና 2011 ዓ.ም አካባቢ የመንገድ ግንባታው እንደሚጀመር ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ሳይጀመር በመቅረቱ የአካባቢው ህብረተሰብ ተስፋ ቆርጦ እንደቆየ ኃላፊው ያስረዳሉ። ይሁንና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ፕሮጀክቱን በይፋ በማስጀመሩ የአካባቢው ህብረተሰብ ተስፋ ዳግም እንደለመለመ ይገልፃሉ።
መንገዱ አሰልቺ፣ እልህ አስጨራሽ፣ ህብረተሰቡም ያመረተውን ምርት ገበያ በማውጣት ለመሸጥ የሚቸገርበት፣ እናትም ከጤና ተቋም ይልቅ በቤት እንድትወልድ ያስገደደ ነበር። ዛሬ ላይ የመንገድ ሥራው በይፋ መጀመሩ መላው የአካባቢውን ህዝብ ያስደሰተ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በመጀመሩም መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለወሰን ማስከበር ሥራው ቀና ትብብር በማድረግ የመንገድ ሥራው እንዲፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸውም ይጠይቃሉ።
የመንገዱ ግንባታ የሚከናወንበትን አብዛኛውን አካባቢ የሚሸፍነው የመልጋ ወረዳ ሰሞኑነ በወረዳው የሚገኙ 12 ቀበሌዎችን አቋርጦ የሚያልፍ ከመሆኑ አኳያም እንደ ፅህፈት ቤት አመራርም ነባር ይዞታ ከሆኑት ውጪ አዲስ ቤት እንዳይሰሩ በማድረግና በመጠበቅ የወሰን ማስከበር ችግር እንዳያገጥም አስቀድመው መስራታቸውን ያብራራሉ።
ፕሮጀክቱ ነባር ይዞታዎችን የሚነካ ከሆነም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመነጋገርና ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው በማድረግ ከይዞታቸው እንዲለቁ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል ። ለዚህም ከህብረተሰቡ ጋር አስቀድመው ውይይት ማድረጋቸውንም ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ እንደሚገልፁት፤ በይፋ ግንባታው የተጀመረው የሃዌላ- ወተራሬሳ-የዩ-ወራንቻ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የሲዳማ ክልልን ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ጋር ያስተሳስራል። ፕሮጀክቱንም ጨረታ በማሸነፍ በ1 ቢሊዮን 879 ሚሊዮን 883 ሺ 516 ብር አገር በቀሉ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ያከናውነዋል።
የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኢ ሲ ኢ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስና ዩኒኮን ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ በጥምረት እንደሚያከናውኑት አስታውቀዋል። ለመንገድ ግንባታው የሚውለውን ሙሉ ወጪም የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ይሸፍናል። ከአዲስ አበባ 285 ኪሎ ሜትር ርቀት ቱላ ከተማ የሚጀምረው ፕሮጀክቱ በሶስት ዓመት ከስድስት ወር ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል።
እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ አሁናዊ ገፅታው በጠጠር ደረጃና ከተገነባ ረጅም ዓመታትን ያቆጠረው ይኸው መንገድ በአገልግሎት መደራረብ ሳቢያ በመጎዳቱ በህብረተሰቡና መንገዱን በሚጠቀሙ አሸከርካሪዎች ላይ ተፅእኖ ሲያሳድር ቆይቷል። በቀጣይ መንገዱ ሊያበረክት ከሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃርም ደረጃውን ከፍ በማድረግ በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ይገነባል።
መንገዱ በዞን 21 ነጥብ 5 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር 7 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎም ይሰራል። የመንገዱ መስፋትና ደረጃ ማደግ በመስመሩ የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎችን በአስፓልት መንገድ በቅርበት በማስተሳሰርና የትራንስፖርት ጊዜን ከሶስት ሰዓት ተኩል ወደ አንድ ሰዓት ተኩል በማሳጠር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል።
ከዚህ ባለፈም መንገዱ በሚገነባበት ስፍራ ላሉ ትንንሽ ቀበሌዎች የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጥራል። ለአካባቢው ህብረተሰብም ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር የሙያ ባለቤትም ጭምር እንደሚያደርግ ይጠበቃል። መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙትን የጤና፣ የትምህርትና የሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተደራሽነትን እንደሚያቀላጥፍም ይታመናል።
ይህ መንገድ የሚገነባበት ስፍራ ብዙ ከተሞችን አቋርጦ የሚያልፍ እንደመሆኑና ስፋቱም አሁን ካለበት የሚጨምር በመሆኑ የመንገዱ ግንባታ በሚካሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የመስተዳድር አካላት፣ የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲሁም የመንገዱ ተጠቃሚዎች የመንገዱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት እየሆነ የመጣውን የወሰን ማስከበር ችግር እንዳይከሰት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013