ሰላማዊት ውቤ
በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ግንባታዎች እየተካሄዱ የሚገኙ ሲሆን ግንባታዎቹ ቁጥራቸው 40 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። የግንባታዎችን መካሄድ ማንኛውም ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው የሚደግፈውና የሚያበረታታው ቢሆንም በሌላ ጎን ደግሞ ሕዝብን ሲያማርሩና ቅሬታ ሲነሳባቸው ይደመጣል።
ለሚነሳባቸው ቅሬታ ዋና ዋና መንስኤዎች የሆኑት በግንባታ ሂደታቸው ወቅት በአብዛኛው ከጥንቃቄ ጉድለት የሚወጣ አቧራና የሲሚንቶ ብናኝና የእንጨት ስብርባሪ ፣ የሚረብሽ ድምፅና የሚወድቅ ዕቃ ናቸው። የነዚህ መዘዝ ደግሞ የሰው ሕይወት ያለ ዕድሜው ሲቀጥፍና አካል ሲያጎድል ይስተዋላል።
ንብረትም ያበላሽና ያወድማል፤ ተረጋግቶ ለመኖርም ምቹ ሁኔታን ይነፍጋል። እንደሚባለው የልብስ፣ የጫማና የአካል ንጽህና ጠርም ነው። ያነጋገርናቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የግንባታ ቁጥጥርና ክትትል በተጨማሪም የአየር ብክለት ባለሙያዎች እንደገለፁልን በአጠቃላይ ሳንካው ብዙ ነው።
ወይዘሮ ፋናዬ ተገኑ የሳንካው ሰለባ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች አንዷ ናቸው። የሚኖሩት ኡራኤል አካባቢ ነው። እርሳቸው እንዳጫወቱን ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ባለ ሀብት አጠገባቸው ግንባታ ይገነባል። ግንባታውን የጀመረው ድንገት እሳቸው ዕውቅናው ሳይኖራቸው ነበር። በግንባታ ሂደቱ ሊደርስ ከሚችል ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅትም አላደረጉ።
በመሆኑም ግንባታው ቦታው ላይ ያሉትን ቤቶች በግሬደር በሚያፈርስበት ጊዜ በቂ ጥንቃቄ ባለማድረጉ ቤታቸው በአንድ ጎን ይደረመሳል። ደግነቱ እሳቸው በቤት ውስጥ ባለመኖራቸው ቢተርፉም ብዙ ንብረት ወድሞባቸዋል። የወደመውን ንብረት ለማግኘት ብሎም የፈረሰውን ቤት ወደ ነበረበት ለማስመለስ ከወረዳ ክፍለ ከተማ በማለት ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል። ሳይወዱ በግድ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ጊዜ ገንዘብና ጉልበትም አባክነዋል። ሆኖም በዚህ ሁሉ መከራ መካከል በሕይወት በመቆየታቸው ይፅናናሉ።
ሌላዋ ከዚሁ ከግንባታ ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው እናት ወይዘሮ ወሰኔ በላቸው ናቸው። እርሳቸውም አሁን ድረስ ባለ 12 ወለል ህንፃ ግንባታ በአጠገባቸው እየተካሄደ ይገኛል። የሚሰራው ቀንና ሌሊት ነው። በተለይ ግንባታውን የሚያካሂደው አካል አሸዋ፣ ጠጠር፣ ሲሚንቶና ድንጋይ የሚያስመጣው እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው አእምራቸው እፎይ ብሎ ሰውነታቸውን አሳርፈው እንቅልፍ በሚጥላቸው የምሽቱ ሰዓት ነው። የግንባታውም ሆነ የዚህ ሂደት ሌሊቱን በሙሉ ይዘልቃል።
በዚያ ላይ እንደ ሲኖትራክ ያሉት ትላልቅ መኪኖች ናቸው የግንባታ ግብዓቱን የሚያመላልሱት። በዚህ ወቅት በጠባብ ቦታ ሊደርስ የሚችል የመኪና አደጋም የቀንና ሌሊት ስጋታቸው ነው። በተለይ በፊት በፊት የግንባታው መሰረት ከመውጣቱ ጀምሮ የ12ቱ ወለል ግንባታ እስኪያልቅ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በግንባታው ወቅት ከሚደርስ አደጋ ለማሸሽ አብዛኛውን ሌሊት ከቤት ውጭ ለማሳለፍ ተገድደው ቆይተዋል።
ስሚንቶና አሸዋ የሚቀላቀለው፣ የሚነፋውና የሚፈጨው መስኮታቸው ስር የነበረ በመሆኑ ድምፁ ብናኙ ብዙ ጉዳት አድርሶባቸዋል። ልብሳቸው፣ መኝታቸው፣ የቤት ቁሳቁሳቸውና ምግባቸው ሳይቀር በአቧራ ሲበከል ቆይቷል። ከሳንባ ጋር በተያያዘ የአተነፋፈስ፣ የጉሮሮ ችግር፣ በአስም፣ በቆዳና በአፍንጫ አላርጅክ ተይዘውም ሰርክ ጤና ጣቢያ ለመመላለስና ወጪዎች ለማውጣት ተገድደዋል።
ጣሪያቸው በልስንና በግንባታ ሂደት በፍንጥርጣሪ ጠጠሮች ተበሳስቷል፤ በአቧራም ጠግቧል። በአጠቃላይ ይሄ የእሳቸው መስዋዕትነት ምን የሚሉት ድርሻ እንደሆነ ባያውቁም በአጠገባቸው በሚካሄድ ግንባታ ደርሶባቸው ተሰቃይተዋል።
ገንቢዎች በሕብረተሰቡ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ጭራሹንም ካሣ አለመክፈላቸውና ችግሩን አለመረዳታቸው ያበሳጫቸዋል። ከጥቅም ውጭ ያደረጉትን ቤት በነበረበት ገንብቶ አለማስረከባቸው ሕጉ በዚህ ላይ ጫና አለማድረጉ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። በከተማችን ይሄን የመሰለውን ፍትህ አጥተው የሚሰቃዩ እንዳሉም አጫውተውናል። አንዳንዶቹ ግንባታዎች ህጋዊ እንደማይመስሏቸውም አልሸሸጉንም።
ቦታው አራት ኪሎ ከቱሪስት ሆቴል ወደ አምባሳደር ቲያትር የሚወስድ ታክሲ የሚያዝበት ነው። ከዚህ ጀምሮ ባሻ ወልዴ ችሎት ላይ በአስፋልቱ ግራና ቀኝ በርካታ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከግንባታዎቹ መካከል ሁለቱ ግንባታዎች የመንግሥት ሌሎቹ የግለሰቦች ናቸው።
በነዚህ ግንባታዎች መካከል የፓርኪንግ ሥራ የሚሰራው ወጣት አሸናፊ ፍቅሬ እንደሚለው እኛም እንደታዘብነው ግንባታዎቹ የሚከናወኑት ምንም ዓይነት ለጥንቃቄ የሚረዳ አጥር ወይም ሽፋን ሳያደርጉ ነው።
በመሆኑም ብዙ ጊዜ በመካከላቸው ባለ ጠባብ አስፓልት ላይ የሚተላለፉ መኪኖች በግንባታ ሂደት በሚወድቁ ዕቃዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል። ዳር ላይ የቆሙትም እንዲሁ የተለያየ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ሀገር ሰላም ብሎ የሚያልፈው መንገደኛም የዚሁ ጉዳት ሰለባ ከመሆን የሚድንበት የለም።
በዚሁ አካባቢ በጽሕፈት ሥራ የተሰማራው ወጣት ትንሳኤ አሊ እንደነገረን ደግሞ አካባቢው ከግንባታዎቹ በሚወጣ በአሸዋ፣ በሲሚንቶ ብናኝና በአቧራ ተበክሏል። በነዚህም ምክንያት ፕሪንተር፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን በተደጋጋሚ ተበላሽቶበታል። እነዚህን ለማሰራት ከገቢው በላይ ወጪ አውጥቷል። በአቧራና በብናኙ ልብስና ጫማው እንዲሁም ሰውነቱ ከመቆሸሽ አልፎ የቆዳ አለርጅክና የዓይን ህመም አትርፏል።
እዚሁ መደዳ በጫማ ዕድሳት የተሰማራው መህዲ ካሚል አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄዱና ጥንቃቄ በማይደረግባቸው ግንባታዎች መማረሩን ነው ያጫወተን። የሚኖርበት ኦሮሚያ ሎጂም ሥራ ቦታውም ግንባታ የሚካሄድበት ነው።
ሥራ ቦታው ከአቧራ ጀምሮ በተለያዩ ከግንባታው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሲረበሽ ይውላል። ማታ ወደ ቤቱ ሄዶ በማረፊያው ደግሞ በሌሊት ግንባታ ምክንያት በመኪናና በግንባታ መሣሪያዎች ጩኽት ሲታወክ ያድራል። ይሄ በኑሮው ላይ ጭንቀት ፈጥሮበታል።
በቂ እንቅልፍ ስለማያገኝም ድካም እንዲሰማውና ሥራውንም በአግባቡ እንዳያከናውን አድርጎታል። መህዲ እንደሚናገረው እንዲህ ዓይነቱ ችግር በከተማው ነዋሪ ላይ የሚፈጠረው ገንቢዎች ያለ በቂ ጥንቃቄ በዘፈቀደ ግንባታ ስለሚያካሂዱ ነው። የልማት ተነሽን እንኳን አስቀድሞ በማመቻቸት የማስነሳት ልምድ የላቸውም።
ሆኖም የከተማዋ ነዋሪ እንዲህ እየተሰቃየ እየሞተም ጭምር መቀጠል የለበትም ባይ ነው። ጥንቃቄ የታከለበት አሠራር መዘርጋት እንዳለበትም መክሯል።
በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሰረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ቁጥጥርና ክትትል ባለሥልጣን የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኢንጅነር ሙሉጌታ ሊግዲ ሕብረተሰቡ የሚያነሳው ቅሬታም ሆነ ጥንቃቄ ያልታከለበት አሠራር በከተማ አስተዳደሩ መኖሩን ይናገራሉ። አቶ ሙሉጌታ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 40 ቅሬታዎች ከሕብረተሰቡ መቅረባቸውንም ገልፀውልናል። 39ኙ ምላሽ ማግኘታቸውንና አንዱ በሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ ቀደም ሲል በአርባ ስድሳና በሌሎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ የሚቀርቡ ቅሬታዎች እንደሚበዙ ጠቅሰዋል። አሁን ላይ ያለው አሠራር ከበፊቱ እጅግ የተሻለ ነው። ቅሬታዎችም ቀንሰዋል። ቅሬታዎቹ የገቡት የሞት፣ የአካል፣ የንብረት መውደም እንዲሁም የአሠራር ጥሰትና የአፈፃፀም ችግሮች ተከስተው እንደሆነም አልሸሸጉንም። የተከሰቱበት ምክንያት ግንባታዎቹ ሳይታጠሩና ሳይሸፈኑ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በመገንባታቸው እንደሆነም አስምረውበታል።
አሁን ሥራ ላይ ያለው የ2010 መመሪያ ማንኛውም አካል የህንፃዎች ግንባታ በሚያከናውንበት ወቅት ከማንኛውም የአደጋ ስጋት ነፃ መሆንና መሸፈን፣ መንገደኛ እንዳይገባ አካባቢውን ማጠር እንዳለበት እንደሚጠቅስም አጫውተውናል። እንዳከሉት የግንባታ ሠራተኞች ራሳቸው ከከፍታ ቦታ ላይ እንዳይወድቁና የአካል ወይም የሞት ጉዳት እንዳይደርስባቸው አንፀባራቂ አልባስና ሌሎች የደህንነት መጠበቂያ መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አሠራርም አለ።
የህንፃ ግንባታ አዋጅ ማንኛውም ህንፃ ሲገነባ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት እንዳለበት ያስቀምጣል። ግንባታውን ሲያጠናቅቅም ቀድሞ ወደ ነበረው ይዞታ የመመለስ ግዴታ አለበት ይላል። አስተዳደሩም ገንቢዎች ይሄን ግዴታቸውን እንዲፈፅሙ ያስገድዳቸዋል። አሁን ላይ በከተማዋ የሚካሄድ ህገ ወጥ ግንባታ የለም። መኖሩ ከታወቀም ተቋማቸው በአስቸኳይ ያስቆመዋል።
በአጠቃላይ በግንባታ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ነው። የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቁጥጥርና ክትትሉ ማዕቀፍ እንዲገቡ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ግንባታ ከመጀመራቸው በፊት ለገንቢዎች የሚሰጠውን ጨምሮ ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ይሰጣልም።
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአየር ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ እንደሚሉት አንድ ከተማ በተለያየ መንገድ ሊበከል ይችላል። የመኪና ጭስ፣ የሚቃጠል ቆሻሻ፣ ግንባታ በራሱ የአየር፣ የድምፅና የውሃ ብክለትን ያስከትላል። የአቧራ ወይም የሌሎች ነገሮች ብናኝ የብክለት ደረጃ ልኬት 65 ነው።
ይሁንና እነሱ በመስክ ምልከታ እንዳስተዋሉት 999 ደርሶ በመሣሪያው የተነበበት አለ። ሕዝቡ በዚህ ለጤናው አደገኛ በሆነ ሁኔታ ነው የሚተላለፈው። መንገዶች በሚሠሩበት ጊዜ የሚነሳ አቧራ ከዚህ በላይ የሚሆንበት አጋጣሚም እንዳለ ነው አቶ መሰረት የገለፁልን ።
‹‹አዲስ አበባ ውስጥ የቤት ብቻ ሳይሆን የመንገድ ግንባታ ይከናወናል›› ሲሉ የሚያክሉት ባለሙያው በመስክ ምልከታ እንዳስተዋሉት ከነዚህ መንገዶች የሚነሳው አቧራ ብናኝ ከፍተኛ እንደሆነም ይገልፃሉ። በአንድ አካባቢ የሚገኝ ብናኝ መደበኛ የብክለት ልኬት ደረጃ 65 ነው።
ሆኖም በመንገድ ሥራ ወቅት 999 የሚገባበትና ከዚህም በላይ የሚሄድበት አጋጣሚ መኖሩን ታዝበዋል። ይሄ ብናኝ ከጤና አንፃር በሳንባ ውስጥ ገብቶ ካንሰርን ያመጣል። አስም፣ አፍንጫ፣ ጉሮሮ፣ የቆዳ አለርጅኮች ያስከትላል። ሆኖም አያሌ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ለጤና አደጋ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይመላለሳሉ።
ወደ ሰው ቤት በመግባት በንብረት ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳል። ብናኙ መንገድ ዳር ያለ ቤት ቆርቆሮ ላይ በማረፍ የሰውን ጣራ ዕድሜ ያሳጥራል። በዚህ ምክንያት መንገድ ዳር ያሉ ቤቶች ቆርቆሮ ቀለም በየጊዜው ለመቀየር ይገደዳል። የግንባታ ኮንትራት ስምምነት ሲያያዝ አቧራ እንዲህ ዓይነት ጉዳት እንዳያደርስ ተብሎ በመኪና ውሃ ለመርጨት በሚል የሚያዝ በጀት አለ።
ሆኖም በምልከታው እንደታዘቡት በበጀቱ የሚጠቀም አካል የለም። አሁን ላይ ይሄ ሁሉ ተደምሮ በሀገራችን ከ10 ገዳይ በሽታዎች የአካባቢ ብክለት ሁለተኛውን ደረጃ ሊይዝ መብቃቱ የሚያሳዝን ነው። ይሄን ለመቀየር ኮሚሽኑ ከጤና ሚስቴርና በየደረጃው ካሉ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል ብለውናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013