በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ብስክሌት ዋንጫ ውድድር በዛሬው እለት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በአፍሪካ ብስክሌት ዋንጫ ውድድር ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድንም ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል።
በዛሬው እለት ሶስት የፍፃሜው ውድድሮች ተካሂደው ነው የአፍሪካ ብስክሌት ዋንጫ ውድድር ፍፃሜውን ያገኘው።
ውድድሮቹም በአዋቂ ወንዶች ኤርትራውያኑ አትሌቶች ሲራክ ተስፎም፣ ዳዊት የማነ፣ ዳኒኤል ሀብተሚካኤል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ፤ ኢትዮጵያዊው ሬድዋን ሳሊህ 8ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል።
ከ23 ዓመት በታች ወንዶች ውደድርም ኤርትራውያን ብስክሌተኞች ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመግባት ውደድሩን ማሸነፋቸው ነው የተነገረው።
በአዋቂ ሴቶች በተደረገ ውድድር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የወርቅ፣ ናይጄሪያ የብር እንዲሁም ኢትዮጵያ የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።
ከ23 ዓመት በታች ሴቶች ውድድርም ናይጄሪያ የወርቅ፣ ኢትዮጵያ የብር እንዲሁም ኤርትራ የነሃስ ሜዳሊያዎችን ማግኘታቸው ነው የተነገረው።
በዚሁ መሰረት የደረጃ ሰንጠረዡን የውድድሩ አስተናጋጅ ኤርትራ በ10 ወርቅ፣ በ6 ብር እና በ 5 የነሃስ ሜዳሊያዎች ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቅ ችላለች።
ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በ2 ወርቅ እና በ 3 የነሃስ ሜዳሊያዎች 2ኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1 ወርቅ፣ በ5 ብር እና 4 የነሃስ ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው ናይጄሪያ በ1 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያ 4ኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ሩዋንዳ በ2 የብር እና 2 የነሃስ ሜዳሊያ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።