ውብሸት ሰንደቁ
በኢትዮጵያ ጥሪት የሌላቸውን ደግፎ ሥራ ላይ ለማሰማራት ብሎም ሀብት እንዲያፈሩ ለማድረግ ታልሞ አምስት የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አበዳሪ ተቋማት ወደሥራ የገቡት በጣት ከሚቆጠሩ ጊዜያት ወዲህ ነው። በሀገር ደረጃ ሲታሰብ የተቋማቱ ተደራሽነት አጠያያቂ ቢሆንም ያሉትም በልምድ የዳበሩ አለመሆናቸውና በቅንጅት ሊያሠራ የሚችል ምህዳር ባለመፈጠሩ ከፈተና አልዳኑም።
ዜጎች የሚያነሷቸውን የሠርቼ ልደግ ጥያቄዎች በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልል በሚገኙ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ማህበራት ለመሸፈን መሞከር በራሱ አንዱ የዘርፉ እጥረት ሲሆን ከዚህ ባሻገር በሥራ ውስጥ የሚገኙት አበዳሪ ተቋማት በብድር አመላለስ፣ በተበዳሪዎች አመላመልና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ችግር ውስጥ ተዘፍቀው ዜጎች ተገቢውን ጥቅምና አገልግሎት ከማግኘት እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ።
ለዘርፉ የተመደበ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ከዓለም ባንክ በረጅም ጊዜ ብድር ተገኝቶ ገንዘቡን መጠቀም ያለመቻሉ ጉዳይ አሳስቦኛል ያለው የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ባለሥልጣን ባለድርሻ አካላትን ሰብስቦ መክሯል። እኛም ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ወራት አግር ከወርች ያሰሯችሁ ችግሮች ምን ምን ነበሩ በቀጣዮቹ ስድስት ወራትስ ምን አስባችኋል ስንል ጠይቀናል።
አቶ መሳይ ኢንሴኒ የአዲስ የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ይሄ አገልግሎት በሀገራችን ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ናቸው የተቆጠሩት፤ ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በዋናነት ያለውን ችግር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ማህበረሰቡ ስለዚህ ዘርፍ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ ነው። በተለይ የመንግሥት አካላት የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት እንዲሳለጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን መወሰን ላይ በአዋጁ የተቀመጡ ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ ስለማይወጡ ዘርፉ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል።
ከእነዚህ ውስጥ ገቢዎችንና ጉሙሩክን ለአብነት አንስተው በካፒታል ዕቃ ዙሪያ በተለይ በሥም ዝውውር፤ የካፒታል ዕቃ ባለቤትነት ከመስጠት አንፃርና በመሳሰሉት አዋጁን መሰረት ባደረገ መልኩ የተጠቀሰው ተቋም ወደ ተግባር አለመግባቱን ተናግረዋል።
የአስመጪዎችና አቅራቢዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም የዘርፉ ተግዳሮት ነው ።የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች ስለ ካፒታል ዕቃ ብድር ቅድመ ዕውቀቱ ኖሯቸው ቢመጡም ስለ ማሽኑ ሁኔታ ማወቅ፤ ስለካፒታል ዕቃው ዓይነት መለየት፤ ያስመጡትን ማሽን በጥልቀት አውቆ አገልግሎቱን ለመጠቀም ያለው ሁኔታ ሌላ ተግዳሮት ሆኖ የሚወሰድ መሆኑን ይገልጻሉ። ከአቅራቢዎቹ በኩል የሚነሳው ችግር በአብዛኛው በሀገር ውስጥ የካፒታል ዕቃዎችን የሚያመርት አለመኖሩ እንዲሁም ከውጪ የሚመጡ ዕቃዎች ራሱን የቻለ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ መሆናቸው ዘርፉ ላይ ጥላውን ያጠሉ ተግዳሮት ሆነው ይጠቀሳሉ።
የካፒታል ዕቃ አቅርቦት አገልግሎት በአዋጅ ፀድቆ ወደሥራ የተገባው ከማኑፋክቸሪንግ ሥራው ሁሉ ትልቁን ችግር የሚፈታ ነው። የካፒታል ዕቃ አቅርቦት ተግባራዊ ሲደረግ የዋስትና እና የቴክኖሎጂ ችግር ፤ በማሽነሪ ምርጫ ዓይነቶች የሚከሰተውን ችግር ይፈታል፤ ከዚህም ባሻገር ኢንተርፕራይዞች ያላቸውን ገንዘብ ለሥራ ማስኬጃና ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዲያውሉት የሚያግዝ ነው። ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ በተቻለ መጠን የኢንተርፕራይዞችን ችግር የሥራ ማስኬጃ ብድር በማቅረብና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግርን የሚፈቱበት ገንዘብ በማበደር ሊተባበሩባቸው ይገባል ይላሉ አቶ መሳይ።
ማህበሩ በክልሉ ለሚገኙ በርካታ የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ እጥረት ላለባቸው ኢንተርፕራይዞች ብድርና የካፒታል ዕቃ በማቅረብ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል የሚሉት አቶ ዮናስ ገለታ ደግሞ የኦሮሚያ ካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበሩ በተቋቋመበት ሚያዚያ 2006 ዓ.ም ለሦስት ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃ ብድር ከማበደር ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ወደ 656 የሚጠጉ ማህበራት ተጠቃሚ ማድረጉንም ይናገራሉ።
ድርጅቱ ላይ የካፒታል እጥረት መኖሩን እንደችግረ የሚያነሱት አቶ ዮናስ በዘርፉ በቅንጅት መሥራት ግን ትልቁ ተግዳሮት መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ለአብነትም እንዲህ ይላሉ፡- አንዳንዶቹ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት ያስመጡትን ማሽን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሌለበት ቦታ ያስተከሉት በመሆኑ በመብራት ችግር ምክንያት ዕዳቸውን መክፈል አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የካፒታል ዕቃ አክሲዮን ማህበሩ ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥረዋል። በሌላ በኩል ምርት በማምረት ላይ የደረሱ ማህበራትም በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት በአግባቡ እየሠሩ ስላልሆነ በወቅቱ ብድራቸውን መክፈል አለመቻላቸው ያነሳሉ። ይህን መሰል ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ተቀናጅቶ በመሥራት ብቻ መሆኑን ያምናሉ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳነሱት ማሽነሪዎችን ለመግዛት ሀገሪቱ ላይ ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከማሽነሪ ፈላጊዎቹ ጋር ውል ተፈራርመን ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ድረስ ለመጠበቅ እንገደዳለን ብለዋል። በተጨማሪም ተበዳሪዎችን ከመመልመል ጀምሮ እስከማስመለስ ድረስ በሚሠሩ ሥራዎች በቅንጅት የመሥራት ክፍተቶች አሉ። ባለፈው ታህሳስ ወር በጅማ ዞንና ጅማ ከተማ እንዲሁም በምዕራብ ሐረርጌና ምሥራቅ ሐረርጌ ላይ በቅንጅት በመሥራት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ማስመለስ መቻሉን ያብራራሉ።
የደቡብ ክልል ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ እንዳሉት፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ሆኖም ግን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ የተለያዩ ማነቆዎች ተደቅነዋል ይላሉ። ከዚህም አንዱ የገንዘብ እጥረት እንደ አንድ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፤ አሁን ላይ ከልማት ባንክ ጋር በመቀናጀት የብድር አቅርቦቱን የማመቻቸት ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአጠረ ጊዜ ውስጥ ዜጎች የሚፈለግባቸውን መሥፈርቶች በማሟላት መጠቀም እንዲችሉ አቅጣጫ መቀመጡን ነው የተናገሩት።
በየቦታው አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮችን አንዱ ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር መሆኑን ገልጠው ለዚህም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሮቹን መፍታት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።እንደእርሳቸው ገለፃ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎች ብሎም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቁልፍ ፈፃሚዎች ሆነው ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው።
የመሰረተ ልማት ግብዓቶችንና የማሽነሪ አቅርቦት እጥረትን እንደ ችግር የሚያነሱ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ሁሉ በማሽነሪዎች ላይ የሚነሱት ቅሬታዎች በጊዜና በጥራት አለመቅረብና በመሳሰሉ ችግሮች ኢንተርፕራይዞች ወደሥራ የማይገቡባቸው ምክንያቶች መሆናቸውን ይናገራሉ ። ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት ከቻሉ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት እንዲቃለሉ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አቶ ታረቀኝ ጠቅሰዋል።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰፋ አበበ በተመሳሳይ በስድስት ወር ውስጥ ስለተመዘገበው አፈፃፀምና እንደሀገር የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን እንደታሰበ ጠይቀናቸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለሥራ ማስኬጃና ማሽን ሊዝ ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸውን አምነው በአጠቃላይ በሊዝ ዕቃ ፋይናንስና በሥራ ማስኬጃ ረገድ የተሰጠው ብድር ከ30 እስከ 40 ከመቶ የበለጠ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል። ይህ የሚያሳየው ባለፉት ስድስት ወራት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮች እንዳሉ ታሳቢ ቢደረግም በዜጎች በኩል ለመሥራትና ለማምረት በርካታ ጥያቄዎች ስላሉ አጣጥሞ ለመሄድ ችግሮች ነበሩ። ከልማት ባንክ ጋር ተያይዞም ብድር ያለመመለስ ምጣኔው ከፍ በማለቱ ብድር መስጠት የቆመበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ጋር በመምከር ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራት የሚቻልበትን አውድ በመፍጠር ልማት ባንክ በቅርቡ ማበደር እንዲጀምር ተደርጓል ።
በቀጣይ ስድስት ወራትም በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል። አንዳንድ ክልሎች በርካታ የቢዝነስ ዕቅዶችን አስገብተው ጨርሰዋል፤ አንዳንዶቹም የነሱን ፈለግ ተከትለው በመነቃቃት ላይ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።
ብድር ማግኘት የሚገባቸውን ዜጎች በአግባቡ ከመመልመል ጀምሮ በዘርፉ የታዩ በርካታ ችግሮች ነበሩ ያሉት ዳይሬክተሩ አነስተኛና መካከለኛ ላይ የተደራጁትን ለይቶ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ችግሮች ታይተዋል። በተጨማሪም አምራች ዘርፉን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው በአንድ አካል ባለመሆኑና የተለያዩ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ የነበረው የቅንጅት ክፍተት ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት መካከል የሚጠቀስ ነው።
ማሽን አቅራቢው በቂ ማሽን ከአቀረብኩ ብሎ የሚያስብ በመሆኑ፤ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የሚያበድረውም ገንዘቡን አቅርቦ ተበዳሪውን ዞር ብሎ እንደማያይ፤ የኃይል አቅርቦት የሚያቀርበውም በዚያው ልክ ብቻ ለማገልገል እሳቤ ውስጥ ካለ በሚፈለገው ልክና ፍጥነት የተፈለገውን ግብ መምታት አይቻልም። ለዚህ ነው በአንድ ላይ እና በአንድ ወቅት እንዲሁም በተከታታይ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ አካላት በቅንጅት መሥራት የሚጠበቅባቸው። ከዚህ በኋላ የግል ድርሻዬን ተወጥቻለሁ ብሎ የሚቆም አንድም ተቋም ሳይኖር በቅንጅት በመሥራት ያለውን ፍላጎት ለማርካት ይሞከራል። ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ማብዛት የሚቻለው የነዚህ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ሲኖር ነው በማለት በመጪዎቹ ስድስት ወራት በቅንጅት ለመሥራት ያለውን ፍላጎት አብራርተዋል።
በባንኮች በኩልም ጊዜን የሚወስዱና የሚያሰላቹ አሠራሮች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተስተውለዋል ያሉት አቶ አሰፋ ይህን ችግር በሪፎርም መልክ ወደለውጥ በመግባት እንዲስተካከል እና በአጭር ጊዜያት ውስጥ ብድር እንዲያገኙ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።
በመጪዎቹ ስድስት ወራት 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ለማዋል እየተሠራ ነው። በዚህ ገንዘብ በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞችና ወረዳዎች ቢያንስ አንድ ኢንዱስትሪ መገንባት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ራዕይ አስቀምጠው እየተንቀሳቀሱ ነው። በተለያዩ ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ማሽነሪ እና የስራ ማስኬጃ ለሚያስፈልጋቸው ይህንኑ ለማሟላት ነው እየታሰበ ያለው።
በአቅርቦት ሂደቱ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች እንዳሉ ሆነው ሌሎች የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡ አካላት ጭምር እንዲሳተፉ ይደረጋል። በዚህም ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብሩን ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል የሚል እምነት ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው ። በእርግጥ ገንዘቡን ሥራ ላይ ለማዋል የዝግጅት ምዕራፎች ተጠናቀው ሌሎች በተግባር የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው የሚቀሩት። ቀሪ ሥራዎችም በመጪዎቹ ስድስት ወራት የሚጠናቀቁ ናቸው። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም ይህን ገንዘብ በአጭር ጊዜና በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን ሊያገኙ እንደሚችሉ ታሳቢ አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ከተለቀቀ ለካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ መጠቀም ከሚገባን በጀት ውስጥ 40 በመቶውን ብቻ መጠቀም መቻል በኢንዱስትሪዎች ዙሪያ ያለው ችግር የፋይናንስ ችግር አለመሆኑን አመላካች ነው። በሀገር ደረጃ ከተመደበ በጀት በስድስት ወራት ውስጥ ከግማሽ ያነሰውን መጠቀም ችግሩ የፋይናንስ እጥረት ሳይሆን የአጠቃቀም ክፍተት መሆኑን የሚያሳይ መሆኑም ተገልጧል። በመሆኑም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያለፈው ያልተጠቀምንብት በጀት መኖሩን፤ የስደስት ወሩ የራሱ በጀት እንዳለና በአግባቡ መሥራት ከተቻለ ደግሞ ተጨማሪ በጀት ሊኖር እንደሚችል በማሰብ በትጋት መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ነው ያሳሰቡት። ያለውን ሀብት ከመጠቀም አንጻር የነበሩ ጉድለቶችን ማረም የሁሉም አካል ኃላፊነት መሆን አለበት የሚል መልዕክት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።
ተቀናጅቶ ባለመሥራት ምክንያት በረጅም ጊዜ ብድር ከዓለም ባንክ የተገኘው ብድር እንዳይመክን ካለፉት ስድስት ወራት ስህተቶች ተምሮ በአዲስ መንፈስ ተባብሮ መሥራት ያሻል።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013