(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
“ከሠፈር ባሻገር”
“ኮተቤ” የሚለው ስም ከአዲስ አበባ ሠፈሮች መካከል የአንዱ ስያሜ ብቻም አይደለም። ስሙ ሲጠራ ወደ አእምሯችን ከተፍ የሚሉ በርካታ ጉዳዮችን ማስታወስ ይቻላል። ከብዙዎቹ መካከል አንዱና ምናልባትም ቀዳሚው ከኮተቤ ጋር በቅርብ የተቆራኘውና የብዙ ታሪኮች ባለቤት የሆነ የትምህርት ተቋም መገኛ መሆኑም ጭምር በአክብሮት ይዘከራል። ያ ጥንታዊ አስኳላ የኮተቤው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን በተከታታይ እያደገ በመሄድም እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከፍታ የጨመረ ተቋም ለመሆን በቅቷል።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ስም የያዙት ቀዳሚዎቹ “የኤለመንተሪና የሁለተኛ” ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዜና መዋዕል ከዘፍጥረት እስከ ዛሬ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸው የታሪክ ትስስር ጥርት ተደርጎና በትክክል ተመዝግቦ ስለመገኘቱ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም መሠረቱ የተጣለው የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ድል ተመትቶ በሽንፈት በተባረረበት ማግስት በ1935 ዓ.ም እንደነበር ተባራሪ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከመምህር እስከ ወታደር፣ ከታላላቅ ደራሲዎች እስከ ዓለማችን ግዙፍ ሳይንቲስቶች፣ ከዱክትርና እስከ ፕሮፌስርነት፣ ከሕክምና እስከ የእርሻ ጠበብት ወዘተ. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ታላላቅ ምሁራንን አላፈራም ብሎ ለመወራረድ ያዳግታል። ከምድራችን ጫፍ እስከ ጫፍ በዚህ ት/ቤት ውስጥ ተምረው ያለፉ ባለ ምጡቅ አእምሮ ዜጎች ቁጥር በአግባቡ ቢጠና የሚገኘው ውጤት የትየለሌ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። “ኮተቤ ተማሪ ነበርኩ” ማለትን ጥንት በፍቅር፣ ዛሬ በኩራት በቃልና በግለ ታሪክ መጻሕፍቶቻቸው ሳይቀር የሚመሰክሩ ብዙዎች ናቸው።
ከላይ ስለጠቀስነው ክብሩና ትሩፋቱ ስለ ኮተቤው የትምህርት ተቋም “እነማን ምን አሉ? ምንስ ብለው መሰከሩለት?” እያልን የዋቢዎችን ቃል ብንዘረዝር የመጽሐፍ ታሪክ እንጂ የጋዜጣ ጽሑፍ ሊሆን ስለማይችል ብዙዎችን ሊወክል የሚችል የአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ምስክርነት ብቻ ለማሳያነት ጠቅሼ አልፋለሁ። እኚህ አንጋፋ ምሁር “ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ – የሕይወት ጉዞዬ” መጽሐፍ ደራሲና በሥነ ሕይወት የዕውቀት ዘርፍ (Biology) አንቱታን ያተረፉት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ናቸው። ፕሮፌሰር ሽብሩ በእጅጉ ስላሞገስነው ስለዚህ የትምህርት ተቋም በመጽሐፋቸው ውስጥ የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር።
“እኔን ወደ መደበኛ የሕይወት መንገድ የመራኝ የኮተቤ ትምህርት ቤት ነበር። ከገጠር ከነበረኝ እኔ “እንደማን ልሁን” ብሎ ምኞት ጨርሶ ያላቀቀኝ የኮተቤ [ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ] 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ነው። ምክንያቱም ያደኩበት አካባቢ የሚደነቅ “ሽፍትነት” ብቻ ሆኖ ሳለ ኮተቤ ስገባ የተቀየረው የመኖሪያዬ አካባቢ ብቻ አልነበረም። ሁሉም ነገር ነበር የተቀየረው። የእኔ ዓለም ተቀየረች ማለቱ የበለጠ ሁኔታውን ያብራራል።
ኮተቤ መጥፎ እና ደጉን፤ ጠቃሚ እና ጎጂውን የለየሁበት የትምህርት መድረክ ሲሆን፣ ሸፍታ ለመሆን ከመመኘት፣ ሽፍቶችን በጣም ከማምለክ፣ የተላቀቅሁበት፣ በተለያየ ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን ለመምሰል የተመኘሁበት ቦታ ነበር። በአጠቃላይ ኮተቤ ዓይኔን የገለጥኩበት ቦታ፣ የዕይታ አድማሴን ያሰፋሁበት አምባ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። አስተሳሰቤን፣ አስተያየቴን፣ የምኞት አድማሴን፣ ፍላጎቴን፣ በአጭሩ እኔነቴን (የጎጃሙን ሽብሩን) የቀየረ ኮተቤ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ ነበር ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ።”
የትምህርት ቤቱ ታሪክ እንደሚያወሳው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ወደ ኮሌጅነት ከፍ ብሎ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንንና የስፖርትና የሰውነት ማጎልመሻ ባለሙያዎችን ማፍራት የተጀመረው በ1951 ዓ.ም ነበር። ከዓመታት በኋላም አዲስ አበባ መምህራን ኮሌጅ በሚል ስያሜ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የተግባረ ዕድ ግቢ ውስጥ እንዲያርፍ ተደረገ። በ1967 ዓ.ም አሁን ወደሚገኝበት የኮተቤ ግቢ ውስጥ ተዘዋውሮ በተለያዩ ደረጃዎችና ስያሜ አንዴ ማዕከላዊ መንግሥት ሌላ ጊዜ የከተማው አስተዳደር “በባለንብረትነት” በመቀባበል እያስተዳደሩት ቆይቶ ከጳጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉያ ውስጥ በመውጣት “የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ” የሚለውን ስያሜ እንደያዘ ተጠሪነቱ ለፌዴራል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን ተወስኖ ዘመነ ልደቱን “ከሰባ ዓመት በላይ” የማሰኘት ፀጋ ሊጎናጸፍ ችሏል። የዚህ አንጋፋ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ታሪክ በሚገባ ጥርትና ፍንትው ተደርጎ መጻፍ እንደሚገባው የአደራ ጠጠሬን አጥብቄ በመወርወር ላነሳው ወደፈለግሁት ዋና ጉዳይ እንደረደራለሁ።
አበጀህ! ያሰኘው የተቋሙ የሰሞኑ በጎ ጅምር፤
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስትር ጋር በመተባበር ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ የሆነ የምሁራን ውይይት በሸራተን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር። “ብሔራዊ ጥቅሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ ሀገር በመገንባት ሂደት የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ የውይይት መድረክ የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝር የዳሰሰና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት ከአንጋፋ የትምህርት ተቋም የሚጠበቅ “አንጋፋ” ጅምር ነበር።
“ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነቷን እና ጥቅሟን ለማስከበር በታሪክ ያደረገቻቸው ተጋድሎዎችና በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የዜጎች ብሔራዊ ኃላፊነት” (በዶ/ር አልማው ክፍሌ)፣ “በሀገር በቀል ዕውቀቶችና ልምዶች ውስጣዊ ችግሮቻችንን ከመፍታት አንጻር የባህል ተቋማት ሚና” (በዶ/ር ከይረዲን ተዘራ)፣ “ህዳሴ ግድባችን አንድነታችንንና ሉዓላዊነታችንን ከማስጠበቅ አንጻር የዜጎች የአርበኝነት ተሳትፎ አስፈላጊነት” (በዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ) የሚሉ ርዕሶች የተዳሰሱበት ያ መድረክ ጊዜውን የጠበቀና ለወቅቱ ምላሽ ጥሩ ማሳያ ነበር ብሎ በጥቅሉ መደምደሙ ይበጅ ይመስለኛል።
ከጥናት ጽሑፎች አቅርቦትና በተነቃቃ ሁኔታ ተሳታፊያኑ በግልጽነት ካደረጉት ውይይቶች በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ወቅቱን የጠበቁና ሀገራዊ ችግሮቻችንን በስፋት የዳሰሱ ነበሩ። ከፕሮቶኮል ሽፍንፍን የጸዳው ንግግራቸውና መልዕክታቸው የአቋማቸውን ጥንካሬና ቁርጠኝነታቸውን የሚያሳይ ጭምር መሆኑም በራሱ የሚያስመሰግናቸው ነው። ቃል በሥራ እየተተረጎመ ፍሬው ሲንዠረገግ ለማየት ከታደልን በዳግም ቅኝት ለመመለስ አናመነታም።
ነባር ተብዬዎቹም ሆኑ ገና እያሸቱ ያሉት በርካታ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎችና እነርሱን አስተባብራለሁ ከሚል ዜና ውጭ ዓይን አፋር የሆነው ኮንሰርትዬም በወቅታዊና አንገብጋቢ ሀገራዊ ችግሮቻችን ዙሪያ ጮክ ብሎ ለመናገር ድምጻቸው በሰለለበትና ዝምታ መርጠው ባሸለቡበት ወቅት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ “ከሠፈሩ” ወጣ ብሎ ባለድርሻ አካላትንና ግለሰቦችን ጋብዞ የአደባባይ ውሎ ማድረጉ በጣሙን ሊያስመሰግነው ይገባል። በተለይም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የተቋሙ ፍሬዎች ተሰባስበው በሀገራቸው ጉዳይ እንዲመክሩና የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ “በጉልህ ድምጻቸው” ያስተላለፉት ጉልህ መልዕክት ከአንድ መሪ የሚጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ነው።
እርግጥ ነው ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቻችን “ዩኒቨርሱ የሚያካልለውን ሰፊውን የተልዕኮ ግዳጃቸውን” ቸል ብለው “እንደ ዓይን አፋር ልጃገረድ” በየተቋማቶቻቸው ቅጥረ ግቢ ውስጥ እየተሽኮረመሙ የሹክሹክታ “ምክክር፣ ጉባዔ፣ ውይይት” አደርግን ሲሉ ማድመጣችንን አንክድም። ከተግባር የተኳረፈ ጩኸት በማሰማትም “አለን እኮ! ቀዳሚዎቹ እኛ ነን!” በሚሉ ሙግቶች ተጠምደው መዋላቸውም አይጠፋንም። ደፈርና ጠንከር ብለው በመሰባሰብና ራሳቸውን ይፋ በመግለጥ የሀገሪቱን እውናዊ ታሪክ፣ የፖለቲካውን አካሄድና ውሎ አዳር፣ የነጋችንን ተስፋና ሥጋት በአርቆ ገማች ድምፀት (Profetice Voice) ጥብቅና ለመቆም እግራቸው ሲብረከረክ ስናስተውል ግን በሀዘን ትካዜ በተቃኘ ትዝብት መቅጣታችን አልቀረም።
የሀገሪቱ ተማሪዎች የታሪክ መጻሕፍት ርሃብተኛ ሆነው ሲናቆሩ እያስተዋሉ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ራሳቸው የችግሩ አካል ሆነው የተገኙ ብዙ “ምሁራንን” ታዝበናል። “ከዩኒቨርሱ የትዬለሌ አስተሳሰብ” (Universal thinking) ዝቅ ብለው ራሳቸውን በጎጥ ፖለቲካ ውስጥ ዘፍቀው ለዓመታት ሲንቦጫረቁ የምናስተውላቸው “ምሁር ተብዬዎችም” ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እነዚህን መሰል “የጓዳ ምሁራን” ታላላቅ ጉባዔተኞች ስለ ዓለም ገመና በሚወያዩባቸው የተከበሩ መድረኮች ላይ “ተጋብዥ እንግዳ ሆኜ ልገኝ ነው” በማለት የአውሮፕላን ቲኬት ለመቁረጥ ሲጋፉ በተደጋጋሚ አስተውለናል።
አንዳንድ ምሁራንም አሉ “ዝም አይነቅዝም፣ ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም፣ ክፉ ቀንንና ቅዝምዝምን ማሳለፍ ጎንበስ ብሎ ነው” የሚሉ ሀገራዊ ብሂሎችን የወቅታዊ የሕይወት መርሃቸው በማድረግ በየጓዳቸው የተሸሸጉትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እውነቱን መመስከር ካስፈለገም መንግሥታዊ ተቋማት በራሳቸው ተነሳሽነት በሚጠሯቸው ስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች ላይ የከበሬታ ወንበር ተለይቶ የተሰጣቸው ለጥቂት “ምሁራንና” ለጎምቱ ሹማምንት ቤትኞች ለሆኑት ብቻ መሆኑን ለዘመናት ተኳርፈን የከረቸምነው መከረኛው የቴሌቪዥናችን መስኮት ሳንወድ በግድ ምስላቸውን ሳሎናችን ድረስ እያመጣልን ለጨጓራ ህመም እንድንዳረግ ምክንያት ሆኗል።
ለመሆኑ አንድ ሰው ምን ቢበቃ አንድ ራሱን የፖለቲካ ጠቢብ፣ የባህል ተመራማሪ፣ የኢኮኖሚ ሊቅ፣ የሕግ በሳል፣ የሃይማኖት ተንታኝ፣ የሕጻናት መብት ተቆርቋሪ፣ የሕክምናና የግብርና ምሥጢር ፈልቃቂ እያደረገ እንዴት አደባባይ ለመዋል ይደፍራል? እንደምንስ ሚዲያው ላይ ለመጣድ አቅም ይኖረዋል። ይብላኝ “ምሁራን ለሚባል ካባ ለተደረቡት ምስኪኖች” እንጂ እኛስ በየቤታችን የልባችንን እየተናገርን እፎይ ከማለት አንከለከልም። እንዲህ ዓይነቱ “ንግሥና” ባህልና ቅቡል በሆነበት ሀገር “ምሁራኖቻችን” ተሰባስበው ከመገሳሰጽ ይልቅ ዝምታ መርጠው እያጮለቁ ሲመለከቱ እኛም ተሸሽገን እንደምንታዘባቸው አልገባቸው ከሆነ ይግባቸው።
የሀገር ታሪክ ሲውሸለሸል፣ የፖለቲካ ትርምስምሱ መረን ሲለቅ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮቻችን መንታ መንገድ ላይ ቆመው አቅጣጫ ሲያማትሩ፣ “ዘውጌ አንበሶች” በድፍረትና በትዕቢት መድረኩን ተቆጣጥረው በኢትዮጵያዊነት ላይ ሲፈነጩ “ሃይ!” ማለት ካቃታቸውና ደፍረው ማረም ከተሳናቸው “ባለማስትሬቶቹ፣ ዶክተሮቹና ፕሮፌሰሮቹ” የሀገሬ ምሁራን ማዕረጋቸውን በፍርድ ቤት አስለውጠው እንደ እኛ ተራ ዜጎች “አቶ እና ወይዘሮ” ብለን እንድንጠራቸው ሊፈቅዱልን ይገባል። ጉዳዩ በዚሁ ይቀጥል ከተባለም እኛ ብዙኃን ዜጎችና “ጥቁር ካባ” ለብሰው የተመረቁበት የዕውቀት ዘርፋቸው” በጋራ ቆመን ፊታችንን እንዳጠቆርንባቸው መዝለቃችን አይቀሬ መሆኑን ከወዲሁ ሊያውቁት ይገባል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የትምህርት ተቋማት ውስጥ አልፈው በዓለም መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ፊት ያፈካሉ ተብለው የሚታመንባቸው እነዚህ ምሁራን ግዙፏን ሀገራቸውን ተሸክመው በመተባበር ወደ ታላቅነቷ ህልም ከማሻገር ይልቅ “የእከሌ ክልል ምሁራን” እየተባሉ በየጎጣቸው መሰባሰባቸውን በድፍረትና አይበጀንም ብለው በውይይቱ ላይ የሞገቱት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስተያየታቸው በዕለቱ በአድናቆት የታጀበው በደማቅ ጭብጨባ ጭምር ነበር። ለነገሩ ያ እርጉም ሥርዓት ተክሎብን ያለፈውን “የእከሌ ክልል ምሁራን፣ የእከሌ ክልል የፋይናንስ ተቋም” የሚሉ ዓይነት ከፋፋይ አስተሳሰቦችን ነቅሎ የማስወገዱ ድርሻ ከፖለቲከኞችና ከአክቲቪስት ነን ባዮች ይልቅ “እረፉ!” ሊሉና የተጣመመውን ሊያቃኑ የሚችሉት ምሁራን አልነበሩም? ዳሩ ምን ያደርጋል፤ “ለአጥንት የሰነዘርኩት ሰይፍ በጉበት ታጠፈ” እንዲሉ በርካታ የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራኑ ሀገር በፈለገቻቸው ጊዜና ወቅት ቦታቸው ላይ ተገኝተው የአለኝታነት ወግ ለማሳየት የሞራል ብቃቱን ሊታደሉ አልቻሉም።
“በአስተሳሰብ አርጠውና በጎጥ ፖለቲካ መክነው” ከምናስተውላቸው ከእነዚህ መሰል በርካታ “ምሁራን” መካከል ለህሊናቸው የቆሙና የሕዝብን ትዝብት የሚፈሩ ተምሳሌት ምስክሮችም ለእውነት ሲከራከሩ፣ ለብዙኃኑ ሲጮኹ መመልከታችንን አንክድም። ችግሩ እንደ ርሃብ ቀን ሰብል ቁጥራቸው መሳሳት ብቻም ሳይሆን ውድ መሆናቸው ጭምር ነው። ለእንደነዚህ ዓይነቱ የሀገር ምሁራን ኮፍያችንን አውልቀንና ከጉልበታችን ሸብረክ ብለን ባናመስግናቸው “ለብዕራችንም ሆነ ለነፍሳችን ጭቡ” ማትረፍ ይሆንብናል።
አንጋፋውን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በአርአያነት ጠቅሰን “አበጀህ!” ለማለት የተበረታታነው ለዚህን መሰሉ “የነፍሳችን ወቅታዊ ጩኸት” ምላሽ የመስጠት ሙከራ ማድረጉ ደስታ ስለፈጠረብን ነው። የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴርም በተጠናከረ ሁኔታ ያንን መሰል የምክክር ጉባዔ በተከታታይ የሚያዘጋጅ አንድ ግብረ ኃይል ለማቋቋም ቃል የገባውን ወደ ተግባር እንደሚለውጥ ተስፋ እናደርጋለን። ካልሆነ ግን ሁኔታውን እየተከታተልን መታዘብ ብቻም ሳይሆን እንቅልፍ ነስተን ለመቅስቀስም አንሰንፍም። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013