ለምለም መንግሥቱ
ላይ ታች ብሎ በሥራ የሰነበተ ሰውነትን አረፍ ለማድረግ ሰንበት ይናፈቃል። እንደው ማልዶ ተነስቶ የታክሲውን ሰልፍ መጠበቅ፣ ለሥራ ረፈደ፣ አልረፈደ ብሎ መሯሯጡ ይቀር እንደሆን እንጂ ለቅሶው መድረሱ፣ የታመመ መጠየቁ፣ ሰርግና ሌሎች ደስታዎች መካፈሉ፣ የዕድር ስብሰባውና ሌላውም ማህበራዊ ኃላፊነት መች ፋታ ሰጥቶ ጎን ያርፋል። ሌላው ቢቀር ሰው ማልዶ ከቤቱ ወጥቶ አምሽቶ በመመለሱ ጓዳውን ለማየት እንኳን ጊዜ እያጣ ነው። ይህን ውድ ቀን በአንዱ እሁድ ጊዜ ሰጥቶ ሰዎች በየአካባቢያቸው በቀማኞች እየደረሰባቸው ስላለው ዝርፊያና ተያይዞ እየደረሰ ስላለ አካላዊ ጥቃት ከአካባቢ ፖሊስና ከከተማ አስተዳደር ተወካይ ጋር ሲመካከር ከነበረው ማህበረሰብ አንዷ ነበርኩ።
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የአካባቢ ማህበረሰብ ፖሊስ(ኮሚኒቲ ፖሊስ) ከወረዳ አንድ አስተዳደር ከተወከለ አካል ጋር በመሆን ማህበረሰቡን ባወያየበት ወቅት ለዝርፊያ የወንጀል ድርጊት ስለሚውሉ የስለት መሳሪያዎችና በየጊዜው ከወንጀል ፈጻሚው ጋር እየያዙ ለህግ ስለሚያቀርቡት፣ ተዘርፈውና አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ቢሮአቸው ስለሚሄዱ ሰዎች አንስቶ የችግሩን አሳሳቢነት የህግ አካል ከወዴት ነህ ብሎ መፍትሄ አጥቶ በየቀኑ ከቤተሰቡ አባል አንዱ የሆነ ሰው እየተጎዳበት ለተቸገረ ማህበረሰብ ይነግረዋል። በዕለቱ የተገኘው በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖረው ማህበረሰብ በማህበሩ አማካኝነት ካልተገኘህ ትቀጣለህ ስለተባለ እንጂ ተሰላችቶ የዝርፊያን ጉዳይ አቤት ብሎ ከተወው ቆይቷል። ፖሊስና ማህበረሰቡ ሲወያይ ወንጀል ይፈጽማሉ ተብለው የሚጠረጠሩና ወንጀል ለመፈጸም ምቹ ነው የተባለበት ቦታ ማዶ ለማዶ እየተያዩ ነበር።
ከማህበረሰቡ ውስጥም ሀሳብ ሲሰጥ የነበረው ሥፍራውን በጣት በማመልከት ነበር። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጀሞ ተብሎ በሚጠራው በተለምዶ መስታወት ፋብሪካ አካባቢ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ የጤና ተቋም ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ጥሎ ለግንባታውም ድንጋይና አሸዋ አፍስሶ፣ ግንባታው የሚከናወንበትንም ቦታ ቆፍሮ ከተወው በትንሹ አምስት ዓመት ይሆነዋል። ይህ ሥፍራ ነው የቀማኞች መደበቂያ ሆኖ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡና እንዳይገቡ ያስቸገረው። በአካባቢው የበቀለው ሙጃ ደግሞ የበለጠ ከለላ ሆኖላቸው ሰው ወደ እነርሱ አይደርስም።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ሥም በሸራና በላስቲክ ወጥረው የኃይላንድ ጠርሙስ ክምር በዙሪያቸው አድርገው መግቢያና መውጫ የሚያሳጡን ተጨምረው ሥጋት እየፈጠሩ መበራከታቸው እንኳን ለወረዳው አስተዳደርና ለአካባቢ ፖሊስ ለከተማ አስተዳደሩም የተሰወረ አይደለም። ጤና ጣቢያ ይገነባል ተብሎ የግንባታ ግብአት አካባቢው ላይ ተዘርግፎ ዓመታትን ሲያስቆጥር የወረዳው ጤና ጣቢያ ምን ይሰራል? በወረዳው ውስጥ የተቋቋመው የፀጥታ ዘርፉ ለወንጀል ድርጊት ምቹ የሆነን ማጽዳት ኃላፊነቱ አይደለም ወይ? የአካባቢው ማህበረሰብ ይጠቀምበት የነበረ መውጫና መግቢያ መንገድ በጉልበተኛ ታጥሮ ህዝቡ መንገዱ መዘጋቱና አማራጭ መንገድ ለመፈለግ ሲል ለዘራፊ እየተጋለጠ እንደሆነ አቤት ሲል ጆሮ ያልሰጠው ወረዳ እንደሆነ ነበር በወቅቱ ሲናገር የነበረው።
ማህበረሰቡ ተናገሩ፣ ችግሩን በጋራ እንፈታለን ብሎ ቃል ከገባ በኋላ ተመልሶ የማያያቸውን የአዲስ ሹመኛ ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ለምዶታል። ይኽው የማይሰለቸው ማህበረሰብ በአካባቢው ያለውን ችግር ከመንገር ባለፈ በአስተዳደሩ በኩል መስተካከል ያለበት እንዲስተካከል ከእርሱ የሚጠበቀውንም ለመወጣት ሀሳቡን ከመስጠትና ቃል ከመግባት አልተቆጠበም።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የማስተዳደሩን ኃላፊነት የተረከቡ ሰሞን በነበረው እንቅስቃሴ ‹‹ልናገለግላችሁ ዝግጁ ነን›› ፣‹‹እኔ ለከተማዬ አምባሳደር ነኝ›› የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ በጉልህ ተጽፈው በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ተሰቅለው እንደነበር አስታውሳለሁ። እውነት የየክፍለ ከተማው አስተዳዳሪዎች ህዝቡ ጋር ወርደው የህዝብ ችግርን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ነው? ለቀማኞች ምቹ የሆነውን ቦታ አጽድቶ ከሥጋት ነፃ ለማድረግ እንኳን የህዝብ ጎሮሮ ጮሆ ከነቃ በኋላ እንደአዲስ ምክክር መጀመሩ አንዱ ማሳያ ነው። መንግሥት ያመቻቸውን የመንግሥት ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት(ሰርቪስ) እንኳን በጠዋት ለመጠቀም እየተቸገረ ነው።
አብዛኛው ሰርቪስ ንጋት 12ሰዓት ከ30 ነው ከመነሻው የሚወጣው። ተጠቃሚው ደግሞ ከ11 ከ30 ጀምሮ ከቤቱ ይወጣል። በዚህ ጊዜ ለዝርፊያና ለአካል ጥቃት እየተጋለጠ ይገኛል። የታክሲና የከተማ አውቶብስ የሚጠብቀውም ቀድሞ ከቤቱ ካልወጣ በጊዜ ወደ ጉዳዩ ስለማይደርስ እንቅልፉን ትቶ ሲወጣ በቀማኞች መንገድ ላይ እየቀረ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ሰሞኑን በስድስት ወር ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል። አፈጻጸሙም ከሞላ ጎደል የተሻለ መሆኑን አስቀምጧል። ይህን የህዝብ ችግር የሆነውን የዘረፋ ጉዳይ አንስተው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን አልሰማሁም። የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማጎልበትና የህዝብንም ተሳታፊነት ለማሳደግ ከወንጀል የፀዳ ከተማ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ሰው ደህንነቱ ተጠብቆ ወጥቶ ሲገባ ነው ሌላው ሁሉ የሚታሰበውና የሚሰራው። ቢረፍድም ህዝብን በማወያየት የተጀመረው የዝርፊያና የደህንነት ሥጋትን የመቅረፍ እንቅስቃሴ ከተለመደው አዲስ ሹመኛ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ይላቀቅ። በተለይም በየአካባቢው በህዝብ ገንዘብ ተገንብተው የተቋቋሙት የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት መስጫዎች ከሥም ያለፈ ሥራ በመሥራት ማህበረሰቡን ከዝርፊያ ወንጀል ይታደጉ። የየክፍለ ከተሞቹ አስተዳደሮችም ደካማው ከጠንካራው ትምህርት በመውሰድ ለአንዲት አዲስ አበባ ከተማ የሚሰሩበት ሁኔታ ይመቻች። በመዲናዋ በአካባቢ ልማት፣ በፀጥታና በሌሎችም አንዱ ክፍለ ከተማ ከሌላው የሚለያይበት ዥንጉጉር የሆነ እንቅስቃሴ መቅረት አለበት።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013