ተገኝ ብሩ
ጎበዝ ተቀድመሀል፤ በዚሁ ከቀጠለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አለመግባባት ውስጥ ሊገባ ይችላል።አለመግባባት የሩቅ ሰው ሳይሆን ከወለድነው ልጅ ከታናሽ ወንድማችን ከቤተሰብ መሐል ዘግይቶ ወደዚህ ዓለም ከተቀላቀለ ታዳጊ ጋር ነው ያልኩት።እኛ እዚያው የነበርንበት ቦታ ሆነን ስንጠብቀው፤ ልጁ ከእኛ ብዙ ርቆ በንቃት ቀድሞ እኛኑ ያስገምተን ይሆናል።
“እሱ ገና ልጅ ነው፤ ኧረ በልክ እንዲገባው አድርገህ ንገረው አይረዳም እኮ!!” የሚለው አባባል ፉርሽ የሚያደርጉ እሳት ትውልዶች ተፈጥረዋል።አንድ ጉዳይ ለመግለጽ ስንጀምር ከአፋችን ነጥቀው አሳምረው የሚጨርሱልን፣ መግለፅ የከበደን ጉዳይ ገና አፉን ከፈታ ጥቂት ዓመታት ያለፈው ታዳጊ ህፃን አብራርቶ ሲተነትልልን መገረማችን ግድ ነው።
ጉድ ነው! ዘንድሮ፤ ልጁ ወደ አዋቂነት አዋቂውን ወደ ልጅነት የሚመልስ ተግባርና ሁናቴ መታዘባችን በርክቷል።ወገን እኛ አንድ ቦታ ላይ ሳንቀሰቀስ መቆማችን የሚያሳውቁን መጪውን ስንመለከት ነው።በተለምዶ ህፃናት ጉዳዮችን በፍጥነት አይረዱም አልያም ስለተለያዩ ጉዳዮች ያላቸው መረዳት አነስተኛ ነው ይባላል።
ዛሬ ይህን ሀሳብ ፉርሽ የሚያደርጉ በየመንደሩ አጋጥመውን አፋችንን ከፍተን የምንሰማቸው በንግግራቸው የሚያስደንቁን በተግባራቸው አጀብ የሚያስብሉን ብላቴናዎች ተበራክተዋል።እኛ ለእሱ አልያም ለእርሷ ይከብዳል ብለን ሸፋፍነን ልናልፈው የምንፈልገው ጉዳይ ግልጥልጥ አድርገው ከኛ በተሻለ መልኩ ሊያስረዱን ይችላሉ፡፡
ጎበዝ ! የፈጀውን ፍጅቶ ከትውልዱ ጋር አብሮ መሮጥ ነው የሚያዋጣው።አለበለዚያ እኛ ወደ ኋላ ስንሸመጥጥ እነሱ ወደፊት አራባናቆቦ ሆነን እንዳንተላለፍ።በእድሜው ማነስና በተለምዷዊ እሳቤና አተያያችን በአንድ ጉዳይ ላይ እውቀት የለውምና ባስረዳውም አይገባውም ብለን የገመትነው ታዳጊ ልጅ፤ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳዩ ከአንድ እድሜ ጠገብና በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት ካለው ግለሰብ በተሻለ ሁኔታ ማብራሪያ ቢሰጥበት አለመገረም አይቻልም አይደል።ለዚህ እኮ! ወዳጆቼ! ተበልጠናል የምለው።በንቃት ከኛ የተሻሉ ነገሮች በመረዳት ከኛ የላቁ ትንታጎች በየመንደሩ ተፈጥረዋል፡፡
እኛ የቀደምነው የገዘፉ ጉዳዮችን ዘንግተን ባነሱ ጉዳዮች እርስ በርስ በምንታረክበት፤ በምንጨቃጨቅበት መንገድ ባጠበብንበት በዚህ ጊዜ ትንንሾቹ ልጆቻችን ከኛ ቀድመው ዓለም በሰፊ መነፅር መመልከት ጉዳዮችን መተንተን ተሽለው ተገኝተዋል።በነገሮች አረዳድ አልያም ምልከታ ላይ እኛ የሆነ ቦታ ላይ ቆመን( እስታክ አድርገን) ልጆች ፈጥነው ከእኛ ደርሰው ብሎም አልፈውን የሄዱ ይመስላል። የእረፍት ቀኔ ቤተሰብ ጥየቃ ስሄድ የማገኛ የእህቴ ልጅ የስልክህን ስጠኝ ጌም ልጫወትበት ጥያቄዋ ቋሚ ምላሽ ያገኝ ዘንድ አሰብኩና ከጥናት ሰዓትዋ ውጪ የምትጠቀምበትና ለትምህርትዋ የሚረዱ መረጃዎችን የያዘ የተማሪዎች ታብሌት ልገዛላት ከስራ ወጥቼ የመርካቶን ታክሲ ያዝኩ።ከጎኔ የተቀመጡ ሁለት በእድሜ በግምት 5 ወይም 6 ዓመት የሚሆናቸው ተማሪዎች ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ቦርሳቸውን አንግበው በአንድ ወንበር ላይ ለሁለት ተቀምጠዋል።
ከሁለቱ ህፃናት በቀር በሚኒባስ ታክሲው ውስጥ ያለ ተሳፋሪ ድምፅ አይሰማም።ሁለቱ ህፃናት ያወራሉ።የሚያወሩት ወሬ ግን ከእነሱ የሚጠበቅ ስላልነበር የአንደበታቸው ስል መሆን ጆሮዬ አቅንቼ እንዳደምጣቸው አደረገኝ።ሁለቱ የተለያየ ጉዳይ ላይ ተራ በተራ ሀሳብ ይሰጣጣሉ።በጉዳዩ ልዩነት ቢኖራቸውም መደማመጥና ተራ በተራ መናገርና መስማት መቻላቸው አስገረመኝ የሚነጋገሩት ክርክር መልክ ሳይሆን ስርዓት ያለው ውይይት በሚመስል መልስ ነበር።
ልጆቹ የሚነጋገሩበት ጉዳይ እኛንም ያስቆመን ወደምንፈልግበት ቶሎ አላደርስ ብሎ የሚያንፋቅቀን የትራፊክ መጨናነቅ ነው።አንደኛው ልጅ በንግግሩ መሀል እንዲህ አለ “ ከትምህርት ቤት ከወጣን ስንት ደቂቃ አለፈ፤ መንገድ ላይ ሊመሽብን እኮ ነው። “እኔ ትልቅ ብሆን በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ተወዳድሬ በማሸነፍ ሰፊ ሰፊ መንገዶችን አሰራ ነበር፡፡” ሲል በመገረም አትኩሬ ተመለከትኩት።ይሄ ልጅ አሁን የችግሩ ጥልቀት ተገንዝቦ አድጎ ቢሆንና እድሉ ቢያገኝ የሚሰራው ማሰቡ ገረመኝ።በዚህ እድሜው እንዴት ከእሱ እድሜ ላቅ ያለ ሀሳብ ውስጥ ሰጥሞ ችግርን ከመፍትሄ ጋር ሊያስብ ቻለ? እራሴን በጥያቄ ውስጥ አስምጬ ሳለሁ ሌላኛው ልጅ የሚሰጠው ሀሳብ መለሰኝ፡፡
“አይ አንተ ደግሞ ስንት ችግር እያለ መንገድ ጠበበ ምናምን ትላለህ እንዴ… ደሞ በዚህ ብትወዳደር የሚመርጥህ መኪና ያለው ብቻ ነው።መኪና የሌለው እንደሚበልጥ አታውቅም እንዴ?” ሲለው በዚህኛ ልጅ የሀሳብ ጥልቀት ይበልጥ ተገረምኩ።እኛ የት ነን ያለንው ጎበዝ? እነዚህ ችግር ነው ብለው በቅርብ የገጠማቸው ወይም የተመለከቱትን እንዲህ እፈታው ነበር ብለው ምኞትና ፍላጎታቸው የገለፁበት ታላቅ ጉዳይ በትንንሾቹ ሰምቼ የትልልቆቹ የኛ ሁኔታ አሳሰበኝ፡፡
የታክሲው ጉዞ ቀጥሏል፤ የልጆቹን ወግ ሰምቼ እኔም መደመሜን እንዲሁ።ታክሲው አንድ አደባባይ ተሻግሮ እግረኞች ከሚሸጋገሩበት ማቋረጫ መስመር አለፍ ብሎ ሲቆም ረዳቱ የታክሲው በር ከፍቶ ወርዶ ከአንድ እድሜው 7 ከሚገመት ልጅ ጋር ክርክር ገጠመ።ጉዳዩ ምን እንደሆነ ለማወቅ በአይኔ መከታል ጀመርኩ።ልጁ ጋቢና እገባለሁ ይላል ረዳቱ ደግሞ ከኋላ ካልገባህ ብሎ ይከለክለዋል።ይሄኔ የረዳቱና የብላቴናው ሁኔታ ይመለከት የነበረው የታክሲው ሹፌር ረዳቱን ተጣራና “በቃ አስገባው፤ ይሄ አስቸጋሪ ልጅ እንደው ምን ይሻለኛል፡፡” ብሎ ሲያማርር ሰማሁ፡፡
ትንሽ እንደተጓዝን ልጁ የሹፌሩ ልጅ መሆኑ ከሚለዋወጡት ቃላት መገንዘብ ቻልኩ።ልጁ “አባ ጓደኛህ አየለ የት ጠፍቶ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ አባት “ማን በላይ ነው” ብሎ መልሶ ጠየቀው። “አዎ እወደዋለሁ፤ እባክህ እቤት ጥራው ይምጣ” በማለት ሲናገር አባት መልሶ ስራ በዝቶበት ነው፤ ይመጣል የሚል መልስ ሲሰጠው ልጁ “ለዚያ ነው የከሳው አይደል ለልጆቹ ብሎ ለስራ ሲሯሯጥ፤ ደግ ልጁ እኮ ድርዬ ነው አባቱ እንዲህ እየለፋ” ሲል ባለማመን አንገቴን አስግጌ አየሁት።ልጁ የተናገረው ከእድሜው በላይ ሆኖብኝ ድጋሚ ሌላ መገረምን በውስጤ አጫረብኝ፡፡
ጎበዝ በኋለኞቹ ላለመቀደም እንትጋ።ቢያንስ ከእነሱ እኩል ሆነን ካለፈው እንደተለመደው የተሻልን ሆነን እንገኝ።እነዚህ ትንታጎት ነገ ላይ ከፍ ባለ ሀሳብ ከፍ ሊያደርጉዋት የሚችሉት አገራቸውን እነሱን በሚመጥኑና ነገአቸውንም የሚያሳምሩ ታላቅ ተግባራት ላይ እናዘውትር።አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013