ይበል ካሳ
በአስተማማኝ ሰላሟና ለኢንቨስተሮቿ በምትሰጠው ምቹ መስተንግዶዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ ባለሃብቶች ተመራጭ እየሆነች የመጣችውና ከኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ፈጣን ዕድገት እያሳየች በምትገኘዋ በውቧ የደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻዎች የተውጣጣን እንግዶች አንድ ላይ ታድመዋል።ታዳሚውን የጠራው የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ የጥሪው ዓላማ ደግሞ አገራችን እየተከተለችው ባለችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ትግበራ ሂደት የላቀ አፈጻጸም ያላቸው አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና የእርስ በእርስ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያደርጉ መድረክ መፍጠር ነው።
ከጥር 24 እስከ 26 ለሦስት ተከታታይ ቀናት በዚያ ታድሞ በቆየነው የልምድ ልውውጥና የምክክር መድረክ ላይ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋር በመተባበር በሃምሳ የልማት ተቋማት ላይ በሃገር ደረጃ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናትን መሰረት በማድረግ በተተገበሩ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ላይ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይትና ምክክር ተካሂዷል።በዚሁ ወቅት የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ፤ ስትራቴጂውን መነሻ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የማጣጣሚያና የማስተሳሰሪያ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ በየዘርፉ እየተሰሩ በመሆናቸው በትግበራ ሂደቱም ስኬታማ የሆኑ ውጤቶች መመዝገባቸውን ይናገራሉ፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ ከተለዩ አብይ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን የሚጠቁሙት ኮሚሽነሩ፤ በመሆኑም የዘርፍ መስሪያ ቤቶች በዕቅዳቸው አካትተው እየተገበሩት መሆናቸውን ያመላክታሉ።የምክክር መድረኩ ዓላማም የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያግዙ በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች እየተሰራባቸው የሚገኙ የተለያዩ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን ለአስፈጻሚና ፈጻሚ አካላት ለማስተዋወቅና ለአተገባበራቸውም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ታስቦ የተካሄደ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
በቀጣይም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ያላቸው አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች በየዘርፉ ተለይተው የሚተገበሩበትን መንገድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራ በምክክር መድረኩ ለተገኙት ባለድርሻ አካላት እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ አሸጋጋሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ ባለ ድርሻ አካል ከሆኑት መካከል አንደኛው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው።የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምክክር መድረኩ ተባባሪ አዘጋጅ ሲሆን ሚኒስቴሩን ወክለው የተገኙት የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ልማት ቁጥጥርና አስተዳደር ዳይሬክተሯ ወይዘሮ አዳነች አሰጋው በጉዳዩ ላይ የጥናታዊ ወረቀት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካላቸው መንስኤዎች መካከል ኢንዱስትሪዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ሆኖም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ አብዛኞቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚለቁትን በካይ ቆሻሻ የሚያክሙበትና ተረፈ ምርታችውን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚችሉበት አሠራር የሌላቸው መሆኑን በጥናታቸው ያመላክታሉ።በዚህም በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ብክለት እያስከተሉ በመሆናቸው በብዝሃ ህይወት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።በመሆኑም መንግስት ፋብሪካዎችና አምራች ኢንዱስትሪዎች በካይ ቆሻሻቸውን የሚያከሙበትን፣ ተረፈ ምርታቸውን መልሰው ጥቅም ላይ የሚያውሉበትንና አካባቢን ሳይጎዱ ማምረት የሚችሉባቸውን አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማበረታታትና አለፍ ሲልም ማስገደድ ይኖርበታል።ሆኖም በጨርቃ ጨርቅና በቢራ ፋብሪካዎች አካባቢ አረንጓዴ ቴክኖሎጂን የመጠቀም መልካም ጅምር መኖሩን የሚጠቁሙት ዳይሬክተሯ፤ በዚህ ረገድ ሁሉም አምራቾችና ፋብሪካዎች ከብክለት የነጻ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙና በመጠቀም ላይ የሚገኙትም ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን እንዲያጋሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከመንግስት ይጠበቃል ይላሉ።ለዚህም መንግስት እንዲህ ዓይነት አረንጓዴ ቴክኖሎጂ አሸጋጋሪዎችን የሚያበረታታበት የአሠራር ማዕቀፍ ማዘጋጀትና መተግበር ይገባዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በቆየው የአረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቂያና የልምድ መለዋወጫ መድረክ ጥቂት የማይባሉ ቴክኖሎጂዎች ተዋውቀዋል።ከእነዚህ መካከል ከፋብሪካዎችና ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ጭሶች የሚያደርሱትን ብክለት የሚቆጣጠር “የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂና ከሆስፒታሎችና ከሌሎች የህክምና ተቋማት የሚወጡ አደገኛ የኬሚካል ውጋጆችንና ከማዘጋጃ ቤቶችና ከሌሎችም ተቋማት የሚለቀቁ አደገኛ ደረቅ ቆሻሻዎች ተቃጥለው በሚወገዱበት ወቅት ጭሳቸው የአካባቢን አየር ሳይበክል የሚያቃጥል ጭስ አልባ አደገኛ ቆሻሻ ማቃጠያ ማሽን ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል።
ለአካባቢን አየር ንብረት ብክለት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በሚታወቁት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ከእንስሳት ቆዳ የሚዘጋጅ ማጣበቂያ፣ “ምስር ኮላ” የሚባል አረንጓዴ ቴክኖሎጂም በመድረኩ ላይ ቀርቦ ተዋውቋል።
በምክክር መድረኩ ላይ አገሪቱ በምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ትውውቅ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ በሚገኙት በተለይም በሁሉም የቴክኖሎጂ ባለቤቶችና አሸጋጋሪዎች ዘንድ ተደጋግመው ከተነሱት ችግሮች መካከል የመንግስት ድጋፍ ውስንነትና የፋይናንስ እጥረት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።ሁሉም ቴክኖሎጂ አሸጋጋሪዎች በተቻለ መጠን መንግስት ከጎናቸው ሆኖ እንዲያግዛቸውና በተለይም ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና ብድር አኳያ ያለውን ችግር እየተከታተለ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ጭስ አልባ አደገኛ ቆሻሻ ማቃጠያ ማሽን ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ የፈጠራ ባለቤትነት መብትን ያገኙትና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጀምሮ ከተለያዩ አካላት የዕውቅና እና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ኢንጂነር ሚካኤል ገብረመድህን የፋይናንስ ጉዳይ ትልቅ ማነቆ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።ሥራውን ከጀመሩ ሦስት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም በገጠማቸው የፋይናንስ እጥረት የተነሳ ብዙም ቴክኖሎጂውን መሬት ላይ አውርዶ መጠቀም አልተቻለም።ሆኖም በራሳቸው ጥረት ሦስት ለሚሆኑ ድርጅቶች ማሽኑን መግጠማቸውን የሚገልጹት ኢንጅነር ሚካኤል፤ “ በእኛ ጥረት ብቻ የትም ልንደርስ አንችልም፤ ቴክኖሎጂውን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል በቂ ፋይናንስ ያስፈልጋል፤ በዚህ በኩል መንግስት የሚያግዘን ካልሆነ ጥረታችን አጉል ልፋት ነው የሚሆነው” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሃገር ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ መሆኑን የሚያመለክቱት ቴክኖሎጂስቱ የፈጠራ ባለሙያዎችን የፈጠራ ውጤት ደግፎ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያለበት መንግስት ነው።ምክንያቱም ቴክኖሎጂስቶችና የፈጠራ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው አዳዲስ ፈጠራዎችን ማበርከትና ማስተዋወቅ ቢችሉም የፋይናንስ አቅም ውስንነት ስላለባቸው ለመተግበር ስለሚቸገሩ ነው።
በዚህ ረገድ ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት ችግር ለመቅረፍ መንግስትን ጠይቀው ያውቁ እንደሆነና ምንስ ምላሽ እንዳገኙ የተጠየቁት ኢንጅነር ሚካኤል፤ “የደብረ ብርሃኑን መድረክ ጨምሮ የሚመለከተው አካል ችግሩን እንዲፈታልን መንግስትን ደጋግመን ጠይቀናል የሚሰጠን ምላሽ ግን ፈንድ እያፈላለግን ነው” የሚል ነው ይላሉ።ሆኖም አሁንም ድረስ ችግሩ አልተፈታም።በመሆኑም አንዳንዶቹ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ አመንጭዎችና ባለቤቶች በተስፋ መቁረጥ ከሥራው እንደሚወጡ የሚጠቁሙት ኢንጂነር ሚካኤል፤ “እኛ ግን ችግሩ ይፈታል ብለን አሁንም በተስፋ እየጠበቅን ነው” ይላሉ፡፡
ከፋብሪካዎችና ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ጭሶች የሚያደርሱትን ብክለት የሚቆጣጠር “የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂን ይዘው የቀረቡት ዶክተር ፋንታሁን አበበ በበኩላቸው፤ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን ተቀብሎ ጥቅም ላይ በማዋልና በማስፋፋት ረገድ የፋይናንስ አቅም ወሳኝ መሆኑን ያመላክታሉ።
የእርሳቸውን ፈጠራ እንደማሳያ በማንሳት ቴክኖሎጂው የአየር ብክለትን ከማስቀረት ባሻገር ከፋብሪካዎች የሚወጣ በካይ ጭስን(ጋዝን) ወደ አመድ በመቀየር ከአመዱ ብሎኬትና ጭስ አልባ ከሰል ለማምረት እንደሚያስችል ይናገራሉ።ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በቀላሉ በሃገር ውስጥ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ከአካባቢያዊ ጥበቃ ባሻገር ለሃገር ዕድገት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑንም የሚያመላክቱት ዶክተር ፋንታሁን በቅድሚያ ግን ቴክኖሎጂው በአግባቡና በሚፈለገው ደረጃ ወርዶ እንዲተገበር የመንግስትን ድጋፍና ትኩረት ያሻል።በተለይም ቴክኖሎጂውን ወደ ህያው መሣሪያነት ቀይሮ በተግባር ጥቅም ላይ ለማዋልና መስጠት የሚገባውን ጥቅምና አገልግሎት ለታለመለት ዓላማ እንዲሰጥ ለማድረግ አስፈላጊውን የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ።
በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ የአምላክሥራ ታመነ እንደ ችግር ለተነሱትና ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።በዚህም በመድረኩ ቀርበው የተዋወቁትና ልምድ ልውውጥ የተደረገባቸው ሁሉም አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች እጅግ ችግር ፈችና የጎላ ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን አድንቀው፤ በዚህ ረገድ እያጋጠሙ ያሉ ማናቸውም ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።ከዚህ አኳያ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና በቴክኖሎጂው አሸጋጋሪዎች፣ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መንግስት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት ፡፡
በአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ የሃብት ማፈላለግ፣ ፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ትርሐስ መብራቱ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችንና በማሸጋገርና ጥቅም ላይ በማዋል ሂደት በተለይም ከፋይናንስ አቅርቦት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ይገልጻሉ።ስለሆነም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር ሥራ ላይ የተሰማሩ ግሉ ዘርፍ ባለ ድርሻዎች ሥራቸውን ሳይቸገሩ እንዲሠሩና የሚፈልጉትን የፋይናንስ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እንዲቻል ኮሚሽኑ ኃላፊነት ወስዶ ከሚያከናውናቸው ተግባራትና ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ሌሎች አማራጮችንም ጥቅም ላይ ለማዋል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ የግሉ ዘርፍ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ አሸጋጋሪዎችና አስተዋዋቂዎች በመደበኛነት ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባሻገር ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ትውውቅ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማገዝ ከተቋቋመ “Green Climate fund” ከተባለ ተቋም ጋር በቀጥታ የሚገናኑበትንና ድጋፍ የሚያገኙበትን ዕድል አመቻችቷል።በቀጣይም በሃገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን የቅንጅት ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።በሂደት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሚቀረፉበትንና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ በመፍጠር ሃገሪቱ በትኩረት እየተገበረችው ከምትገኘው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መጠቀም የሚገባትን ያህል እንድትጠቀም ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እንደሚሰራ ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013