ከገብረክርስቶስ
ለትውስታ
ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ቀዳሚው የአዲስ አበባ አስተዳደር ይፋ ያደረገው የመሬት ወረራ፣ የባለቤት አልባ ሕንጻዎችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጉዳይ ነው።
እርግጥ ነው መንግሥት ይህንን መረጃ አልፎ አልፎ በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ሲያደርግ አድምጠናል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ወዲህ በተለይም ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በከተማዋ እየተንሰራፋ የመጣውን ሕገ-ወጥነት በተመለከተ በተደራጀ መልኩ የጥናት ሪፖርት ማውጣቱ አይዘነጋም።
አሁን ደግሞ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም በላይ ኃላፊነት ያለበት የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ወረራውን ብቻ ሳይሆን ከባለቤት አልባ ሕንጻዎች፣ ከመንግሥት ቤቶችና ከኮንዶሚኒየም ጋር በተያያዘ ያሉትን ሕገ-ወጥነቶች በስፋት ለመዳሰስ ሞክሯል።
በመንግሥትም ይሁን በተቃዋሚዎች እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ መደረጉ ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት ጠቃሚ በመሆኑ ሊጠናከር የሚገባው ነው።
ከሁሉም በላይ የከተማ አስተዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያካሄዱትን ጥናት እንደ ግብዓት መጠቀሙ እና በጥናታቸው ውጤት ላይም ትክክል ያልሆኑትን ነቅሶ ማውጣቱ ያስመሰግነዋል።
ጠላትና ወዳጅ በሚፈርጀው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ እየተመራን በነበርንባቸው የትላንቶቹ ዓመታት ቢሆን ኖሮ ኢዜማ እንደዚያ ዓይነት የጥናት ውጤት ይፋ ሲያደርግ በጸረ-ሰላም ድርጅትነት በተፈረጀ ነበር።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር ለመክፈት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪዎች መካከል እንዲህ ዓይነት መደጋገፎች መኖራቸው ጠቃሚ ነው፡፡
ያም ሆኖ የኢዜማን ሪፖርት ያኔ በወጣበት ወቅትም ይሁን በአሁኑ ወቅት ዋጋ የሚያሳጡ አስተያየቶች የመንግሥትን ሥልጣን ከጨበጡትም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ሲደመጡ ይሰማል፡፡
ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን ከለውጡ በኋላ የከተማዋ መሬት በሕገ-ወጦች ሲወረር ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የነበረው የከተማ አስተዳደር የኢዜማ ሪፖርት የማንቂያ ደወል ሆኖት አውቆ ከተኛበት እንደቀሰቀሰው ሊዘነጋ አይገባም።
ይህ ብቻም ሳይሆን የመሬት ወረራውም ሆነ ሌሎቹ ሕገ-ወጥነቶች እየተፈጸሙ የከረሙት እስከ ወረዳዎች ድረስ በየደረጃው በሚገኙ ሹማምንት በመሆኑ አስተዳደሩ ራሱንም እንዲፈትሽ ያስገደደው መልካም አጋጣሚ መሆኑን መናገር ይቻላል።
ያም ሆነ ይህ የተወረረው መሬትና ሌሎቹም የሕዝብና የመንግሥት ኃብቶች በምን ዓይነት የህግ ማዕቀፍ ነው እልባት ሊያገኙ የሚችሉት የሚለው ወሳኙ አጀንዳ መሆን አለበት።
በዚህ ረገድ የጥናት ግኝቱን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት በኔቶችን በተመለከተ ርምጃ በመውሰድ በችግር ላይ ላሉ ነዋሪዎች እየሰጠ ይገኛል።
በተመሳሳይም ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ወረራ ጋር የተያያዘውንም ሕገ-ወጥነት በመፍታት ቤቶቹን በዕጣ ለማስተላለፍ በመሰናዳት ላይ እንደሚገኝ መንግሥት አስታውቋል።
የመሬት ወረራው እና የባለቤት አልባ ሕንጻዎቹ ጉዳይ ግን ሕገ-ወጥነቱን በሕጋዊ መንገድ ለማስተካከል ራሱን የቻለ ከባድ የቤት ሥራ እንደሚፈጥር እሙን ነው።
ከለውጡ በፊትና በኋላ የወረራው መልክ ለየቅል ነው
የከተማ አስተዳደሩ ያካሄደው ጥናት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጸሙ የመሬት ወረራዎችን ነው።በዚሁ መሰረት በከተማዋ 88 ወረዳዎች ውስጥ ከአንድ ሺ 300 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሕገ-ወጥነት ዘዴዎች ተወሯል።
እርግጥ ነው ይህ የመንግሥት የጥናት ውጤት ኢዜማ ካጠናው በጣሙን ሰፊ ነው።የመንግሥት ጥናት አብዛኞቹን የከተማዋን አካባቢዎች ለመዳሰስ የሞከረ ሲሆን፤ የኢዜማ ጥናት ደግሞ በአምስት ክፍለ-ከተሞች ነው የተከናወነው።
ጥናቶቹ ከሚሸፍኑት ጊዜ አንጻርም የኢዜማው ከ2010ሩ ለውጥ ወዲህ ያለውን የመሬት ወረራ ሲሆን፤ የመንግሥቱ ጥናት ደግሞ የመሬት ወረራ የከተማዋ የሕልውና ሥጋት መሆን ከጀመረበት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የተከናወነ ነው።
ያም ሆኖ ከ2010 ለውጥ በፊት የነበረውን የመሬት ወረራ ከለውጡ ወዲህ ካለው ጋር በአንድ ወጥ ጥናት አካቶ ማቅረቡ አግባብነት ያለው አይመስልም።
ምክንያቱም በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ሥር-ነቀል ማሻሻያዎች ተደርገዋል በተባለባቸው የለውጥ ዓመታት የተፈጸሙትን የመሬት ወረራዎች ከዚያ ቀደም በህወሓት መራሹ መንግሥት ከተፈጸሙት ወረራዎች ጋር በአንድ ላይ ተጨፍልቀው ሊቀርቡ አይገባም፡፡
ከሁሉም በላይ ከለውጡ በፊት የነበረው የመሬት ወረራ እና ከዚያ ወዲህ እስካሁንም ድረስ ቀጥሎ ያለው የመሬት ወረራ በዓይነቱም ሆነ በአፈጻጸሙ የተለያየ ነው።በዚሁ መነሻ በጥናቱ ሊቀመጡ የሚገባቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ራሳቸውን የቻሉና ለየቅል ሊሆኑ ይገባል ማለት ነው።
በተለይም ከለውጡ ማግስት የተንሰራፋው በአሁኑ ወቅትም አሳሳቢ የሆነው የመሬት ወረራ በከተማ አስተዳደሩ ሰባራ ሰንጣራ የሆኑ መመሪያዎችና ውሳኔዎች የተፈጸመና እየተፈጸመም ያለ ነውእንዲሁም የየደረጃው የመንግሥት ሹመኞች የሕግጋቱን ክፍተት በመጠቀም በወረራው ላይ እጃቸውን ያስገቡበት አስከፊ ሕገ-ወጥነት ነው።
በዚሁ መነሻ ከለውጡ በፊት የነበረው የመሬት ወረራ መልኩ የተለየ በመሆኑ የለውጡ አመራር የጀመራቸውን የማስተካከያና የዕርምት ዕርምጃዎች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከለውጡ ወዲህ ያለው ሕገ-ወጥነት ራሱን የቻለና የተለየ መልክ ስላለው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያዎቹንና የየደረጃውን አስተዳደሮች መፈተሽ እንደሚኖርበት እሙን ነው።
ተደጋግሞ ሲገለጽ እንደምናደምጠው ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ ውስጥ ከላይ ከቁንጮዎቹ የመዲናዋ ሹማምንት ጀምሮ በየደረጃው እስከታች ድረስ በአምሳለ-ትህነግ የተቀረጹ የተደራጁ የመሬት ዘራፊዎች ተደራጅተዋል።
መንግሥት በይፋ እየገለጸው ባይሆንም በተግባር የሚታየው እነዚህ የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ አካላት በግፉዓኑ የአዲስ አበባ የኦሮሞ ተወላጅ ገበሬዎች ሥም መሬትን እንደቅርጫ እየተቧጨቁት ይገኛሉ።
ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ የወጡትን መመሪያዎች ክፍተት እና የጊዜውን ነፋስ በመጠቀም ነው።
በከተማዋ ከለውጡ ወዲህ በዚህ መልኩ የተዘረፈውን መሬት በተመለከተ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚገኘውን ዝርዝር ውጤት መጠበቅ ይገባል።
ያም ሆኖ የመመሪያዎችና የአሰራሮቹ ክፍተት አሁንም ባለመፈታታቸው የመሬት ዝርፊያው እስካሁንም መቀጠሉን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
ሰባራ ሰንጣራው መመሪያና የካቢኔው ውሳኔ
የአዲስ አበባ ማደግና መስፋት ሕይወታቸውን ካጨለመባቸው ወገኖች ግንባር ቀደሞቹ የከተማዋና የአካባቢው አርሶ አደሮች ናቸው።
የመዲናዋ እድገትና መስፋፋት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ቅሉ፤ ኃላፊነት በተሞላበትና አርሶ አደሩን ታሳቢ ባደረገ የከተማ ዕድገት ፕላን ባለመመራቱ በርካታ አርሶ አደሮችን ለችጋር እንዳጋለጣቸው መናገሩ ጉንጭ ማልፋት ይሆናል።
በዚሁ መነሻ ታዲያ ሕግ ለማውጣት የማይቸገር ሥርዓተ-መንግሥት በመገንባታችን የከተማዋ ካቢኔም የአርሶ አደሮቹን የመሬት ባለይዞታነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በመመሪያ አውጥቷል።
“አግባብ ባለው አካላት ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎችን ለማስተካከልና ለመከላከል የወጣ የአፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 16/2006” ይሰኛል ይህ መመሪያ።
የዚህ መመሪያ አንቀጽ 16 የአርሶ አደር ይዞታዎችን የውሳኔ አሰጣጥ ይመለከታል።መመሪያው የአርሶ አደር መስተንግዶ አሰጣጥን በተመለከተ ቀደም ሲል ከከተማው ክልል ውጭ እና በከተማው ማስፋፊያ አካባቢ የነበሩ የአርሶ አደር ይዞታዎች ሆነው ነገር ግን በሂደት ወደ ከተማ አስተዳደሩ የተካለሉ የመኖሪያ ይዞታዎች በባህሪያቸው ለየት ያሉ በመሆናቸው የሚስተናገዱበትን የተለየ ሥርዓት አስቀምጧል፡፡
በዚሁ መሰረት የአርሶ አደሩ ቤትና ይዞታው ወይም ቤቱ በ1997 ዓ.ም. በተነሳው የመስመር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ፤ ባለይዞታው ነባር አርሶ አደር ስለመሆኑ ከሚኖርበት ወረዳ አስተዳደር ማረጋገጫ በጽሁፍ ሲያቀርብ እንዲሁም አርሶ አደሩ በስሙ የመሬት መጠቀሚያ ግብር ከሁለት ዓመትና በላይ የገበረበት የግብር ደረሰኝ ሲያቀርብ እስከ 500 ካሬ ሜትር ድረስ በነባር ሥሪት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚሰጠው መመሪያው ደንግጓል፡፡
የአርሶ አደር ልጆችን በተመለከተ ደግሞ ቤትና ይዞታው ወይም ቤቱ በ1997 ዓ.ም. በተነሳው የመስመር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ፤ ልጆች ስለመሆናቸው የተረጋገጠ የልደት ሰርተፍኬት ወይም የነዋሪው ምስክርነትና መሬቱን ከወላጆቻቸው ስለማግኘታቸው ከወረዳው አስተዳደር ማረጋገጫ ሲቀርብ፤ እድሜያቸው 18 ዓመትና በላይ ሆኖ በወላጆቻቸው የመኖሪያ ግቢ ውስጥ ቤት ሰርተው ራሳቸውን ችለው እየኖሩ ስለመሆናቸው በወረዳው አስተዳደር ተረጋግጦ ሲቀርብ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ በስማቸው ወይም በትዳር አጋሮቻቸው ሥም ሌላ የይዞታ ማረጋገጫ ከሌላቸው እስከ 150 ካሬ ሜትር መሬት እንደሚሰጣቸው ነው በመመሪያው የተመለከተው።
ይሁንና በወቅቱ የአርሶ አደሩ ይዞታ በመሰረቱ በመስመር ካርታ ላይ የማይታይ ነበር።ይህ የመስመር ካርታ ማለት ደግሞ እስከ ሚያዚያ 1997 ዓ.ም. ድረስ የተያዙ ይዞታዎችንና የተገነቡ ቤቶችን በአየር በረራና ቤት ለቤት በተደረገ የቅየሳ ሥራ በማጣጣም የተዘጋጀ መረጃ ነበር።እናም የአርሶ አደሩ ይዞታ በዚህ መረጃ ውስጥ አይገኝም ነበር።
በመሆኑም “ቤትና ይዞታው ወይም ቤቱ በ1997 ዓ.ም. በተነሳው የመስመር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ” የሚለው የመጀመሪያው መስፈርት መመሪያው ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጠረ፡፡
በዚሁ መነሻ የወቅቱ የከተማዋ ካቢኔ ይህንን የመመሪያውን መስፈርት በማሻሻል የአርሶ አደሩ ይዞታ በመስመር ካርታው ላይ ቢታይም ባይታይም ሌሎቹን መስፈርቶች የሚያሟላ ጥያቄ እስከቀረበ ድረስ ለአርሶ አደሩ እና ለልጆቹ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህንን ተከትሎ በትክክል የተጠናቀረ መረጃ ባይገኝም እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ እፍኝ የአርሶ አደሩ ጥያቄዎች ሳይስተናገዱ አልቀረም።
ለውጡን ተከትሎ የታየውና በከተማው ውስጥ በስፋት እየታየ ያለው የመሬት ወረራ ታዲያ ከዚህ መመሪያ እና የካቢኔ ውሳኔ እንከን ጋር የተያያዘ ነው።
ከመመሪያውና ከማሻሻያ ውሳኔው በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ባለይዞታው ነባር አርሶ አደር ስለመሆኑ ከሚኖርበት ወረዳ አስተዳደር ማረጋገጫ በጽሁፍ ሲያቀርብ እንዲሁም አርሶ አደሩ በስሙ የመሬት መጠቀሚያ ግብር ከሁለት ዓመትና በላይ የገበረበት የግብር ደረሰኝ ሲያቀርብ 500 ካሬ ሜትር መሬት ይሰጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በተግባር እየተደረገ ያለውም ወረዳ አስተዳደሮቹ የጽሁፍ ማረጋገጫ ይሰጣሉ፤ በዚሁ የወረዳው የጽሁፍ ማረጋገጫ መሰረትም የወሳኝ ምዝገባ ኩነት ተቋማት መታወቂያ ይሰጣሉ።
በጣም የሚያስገርመው ደግሞ አንድ ሰው ከወረዳው የአርሶ አደርነት ማረጋገጫ ከያዘ ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤትም ወደ ኋላ ካሉ ዓመታትም ጭምር (ባክ ዴት በማድረግ) የመሬት ግብር በመቀበል ደረሰኝ ይሰጣል።
ይህንን መስፈርት በማሟላትም እዚህ ከተማ ውስጥ አንድ ብቻ ሳይሆን በቻሉት ልክ 500 ካሬ ሜትር መሬት ማግኘት ይቻላል ማለት ነው።
ለአርሶ አደር ልጆችም ተመሳሳይ ነው – ልጆች ስለመሆናቸው የነዋሪው ምስክርነት ይቀርባል፤ መሬቱን ከወላጆቻቸው ስለማግኘታቸው እና በወላጆቻቸው የመኖሪያ ግቢ ውስጥ ቤት ሰርተው ራሳቸውን ችለው እየኖሩ ስለመሆናቸው ከወረዳው አስተዳደር ማረጋገጫ ይሰጣል።
እርግጥ ነው በዚህ መመሪያና በካቢኔው ውሳኔ በእውነት ተጠቃሚ የተደረጉ የከተማዋ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ይኖራሉ።
ይሁንና የመመሪያውን የአፈጻጸም ክፍተት በመጠቀም በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጅ ሥም የከተማውን መሬት እየተቀራመቱ ያሉት የመንግሥት ሹማምንትና ተባባሪ ደላሎቻቸው እጅግ በርካቶች ናቸው።
በመሆኑም መንግሥት በዚህ ዙሪያ በአንድ በኩል የጀመረውን የወንጀል ምርመራ አጠናክሮ በመቀጠል በአርሶ አደሩ ሥም መሬት የዘረፉትን ለሕግ ማቅረብ አለበት።
ከሁሉም በላይ በአፈጻጸሙ ለመሬት ቀበኞች በሚመች መልኩ የተቀረጸውን መመሪያና የካቢኔውን ውሳኔ በአግባቡ በመመርመር የከተማውን መሬት ከዝርፊያ ሊታደገው ይገባል።
በደህና እሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013