ሙሉቀን ታደገ
ጁንታው ሃገር አስተዳድራለሁ እያለ የህዝብ ሀብት ያለማንም ከልካይ እየመዘበረ እንደፈለገ ሲፈነጭበት ቆይቷል። የጁንታውና የጥፋት እድምተኞቹ የመዘበሩትን የህዝብ ሀብት አገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው እንደፈለጉ ይንበሸበሹበት ነበር። እነሱና አጋፋሪዎቻቸው በተሰረቀው የህዝብ ሀብት የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራሉ።
በጁንታው ላይ የተወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ የገንዘብ ምንጫቸው የነጠፈባቸው በውጭ የሚኖሩ ተላላኪዎች ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ እንዳልተፈጠሩ፣ የኢትዮጵያን ጡት እንዳልጠቡ፤ በኢትዮጵያ እንዳልተማሩ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ጥላሸት ለመቀባት እየተሯሯጡ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ የመጣው ሁለንተናዊ ለውጥ ያልተዋጠላቸውና ለጥቅማቸው ብቻ ተገዥ የሆኑ እነዚህ የጁንታው ተላላኪዎች በአሜሪካ እና በአውሮፓ በሚገኙ መንገዶች ከተጋዳላይ ወደ ተንከባላይ ተቀይረው በሀሰት የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት እየተንቀሳቀሱ ናቸው። በጡት አባታቸው የህወሓት ጁንታ ቡድን በህዝብና በአገር ላይ የፈጸመው ክህደት ገና ቁስሉ ሳይጠግ እናንተ የእሱ ተላላኪዎች አደብ መያዝ ስለምን አቃታችሁ? ስለምን የኢትዮጵያን ስም በአለም መድረክ ያለ ምግባሯ ስም እየሰጣችሁ አገራችሁን ለማንቋሸሽ ቆርጣችሁ ተነሳችሁ ? ጊዜው ይርዘም እንጂ ሴራ መጨረሻ ላይ ራስን እንደሚያጠፋ ከአባታችሁ ከህወሓት ብትማሩ አይሻላችሁም ወይ ? ስል እጠይቃለሁ ።
የእነዚህ የንዋይ ሴሰኞች ፀረ ኢትዮጵያ አካሄድ ለማውገዝና እውነቱን ለዓለም ለማስረዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በተለይም በውጭ አለም የምትኖሩ ወገኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ስለ ሃገራቸውና ስለ ወቅታዊው ሃገራዊ ጉዳይ ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመናገር የሃገራቸውን መልካም ክብርና ስም ለማጥፋት የተነሱ ሰዎችን ድል በመንሳት ሐሰትን በእውነት እንዲያሸንፉ ጥሪ አድርገዋል።
ይህ ጥሪ ተከትሎ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ከሰሞኑ በአሜሪካ በሁሉም ግዛቶች (ስቴቶች) የሚገኙ ከ800 በላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሃይማኖት አባቶች፣ የአደረጃጀት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የአድቮኬሲና ሌሎች አካላት በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ (የዙም) ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ በዋሺንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደ ነው።
በስብሰባው የተሳተፉ ዲያስፖራዎችም ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይታቸውን አጠናቀዋል። በዚህም በውጭ የሚኖሩ የጽንፈኛው የህወሐት ቡድን ደጋፊዎች በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች አማካኝነት አለም አቀፍ ማህበረሰቡን፣ የውጭ መንግስታትንና የአለም አቀፍ ተቋማትን ለማሳሳት በትግራይ ህዝብ ስም የሚያካሂዱትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እንደሚያወግዙ ገልፀዋል። ይህንን በብቃት ለመመከትም በተደራጀ መንገድ እንደሚሰሩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በትግራይ ክልል እና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች የተፈናቀሉ እና አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ ወገኖቻችችን ተመልሰው እንዲቋቋሙ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም ቃል ገብተዋል። ይህ ውሳኔ በእውነት ትልቅ ቦታ ሚሰጠው ነው። ምክንያቱም በትግራይ ስም የሚነግዱት የህወሓት ፍርፋሪ ለቃሚዎች አንድም ቀን ለትግራይ ህዝብ ችግር ለመድረስ አንድ ብር ሳያዋጡ በስመ ተወላጅ እያደረጉ ያሉትን የሀሰት የፕሮፖጋንዳ እርቃን ሚያስቀር በመሆኑ ነው። እነዚህ ሀፍረት የለሽ በትግራይ ህዝብ ስም ከመነገድ ውጭ በችግሩ ወቅት ደርሰውለት አያውቁም።
ሌላው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ካወጡት ያቋም መግለጫ አንዱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጋር የሚያያዝ ነው። በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም ወገን የሚነዛውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ አጥብቀን እናወግዛለን፤ ለግድቡ ማስጨረሻ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።
እንደሚታወቀው በውጭ ሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ በመሳተፍ ሁሌም በታሪክ ተከትቦ የሚኖር አኩሪ ገድል መፈጸማቸው ሚታወስ ነው። ይህ ልክ እንደ አደዋ እና ሌሎች የሃገር ብሄራዊ የድል ቀናቶች መጪው ትውልድ ሲያከብረው እና ሲዘክረው ሚኖር ተግባር ይሆናል። የሃገር ፍቅር ከሱሶች ሁሉ ትልቁ ሱስ መሆኑን የሚያሳየው ኢትዮያዊያን ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ ቢርቁ በመንፈስ እና በተግባር ግን ከኢትዮጵያ መለየት እንደማይቻል ነው።
በአጠቃላይ ከግድቡ ጋር ተያይዞ የአገራችን የከፍታ ተምሳሌት የሆነው እና በሚሊዮን የኢትዮጵያ ጓዳዎች ጭምር ብርሃንን ሊፈነጥቅ ጫፍ ለደረሰው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠናቀቅ ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቃል።
ሌላው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመግለጫቸው እንዳስቀመጡት ሱዳን ከወረረችው የኢትዮጵያ ግዛት በአስቸኳይ እንድትወጣ ጠይቀዋል። “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል“ እንዲሉ ጁንታው እና ጭፍሮቹ የጀመሩትን ሀገር የማተራመስ ሴራ ያየቸው ሱዳን ስንት እና ስንት ድጋፍ ከኢትዮጵያ ተችሯት እንደ ሃገር እንዳልቆመች ሁሉ፤ በአብዬ ግዛት ያለው የኢትየጵያ ሰላም አስከባሪ ለሱዳን ሰላም ዋጋ እንዳልከፈለ፤ ሰላም አስከባሪው የኢትየጵያ ጦር ከሃገራቸው ሳይወጣ እንደዚህ አይነት አሳፋሪ ድርጊት በኢትዮጵያ ላይ መፈፀም የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል አይነት ነው የሚሆነው። ይህን አሳፋሪ ድርጊት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊን በፅኑ አውግዘውታል።
አሁንም የጁንታው የነዋይ ሴሰኞች እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ እየፈፀሙት ያለውን ግፍ በውጭ የሚኖሩ ኢተዮጵያዊን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የመረጃ መረቦች እና ትይንተ ህዝቦችን ጭምር በማድረግ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013