ጌትነት ምህረቴ
አቶ ኡመር ሰይድ ይባላሉ። ይሠሩበት የነበረው መስሪያቤት የህዳሴ ቴሌኮም ሰሜን ምሥራቅ ዲስትሪክት ደሴ ከተማ ነው። በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙንኬሽን መስሪያ ቤት ለ20 ዓመታት ሠርተዋል። ድርጅቱ በሪፎርም ሰበብ ስድስት ሺህ ሠራተኞች ከሥራ ሲቀንስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ከዚህ በኋላ በተቀነሱ ሠራተኞች የህዳሴ ቴሌ ኮም ተብሎ የአክሲዮን ድርጅት ሲቋቋም የአክሲዮን አባል ሆኑ። ከሥራ እስከተሰናበቱበት ድረስ በህዳሴ ቴሌኮም ለሰባት ዓመታት ስሠራ ነበር ይላሉ።
“ምን ያርጋል ለ27 ዓመታት ስሠራ ቆይቼ ከነቤተሰቦቼ ሜዳ ላይ ወደኩ። ባደረብኝ የጤና ችግርና ድንገተኛ የጤና እክል ከድርጅቱ የአንድ መቶ ሺህ 652 ከሃምሳ ሳንቲም የሞባይል ካርድ አውጥቼ ወደ ቤቴ ስሄድ ታክሲ ላይ ራሴን ስቼ ስወድቅ የዤው የነበረ የሞባይል ካርድ የት እንደወደቀ አላውቅም። እኔንም ሰው አንስቶ ነው ወደ ቤቴ የወሰደኝ። የዚህ መሰል የጤና እክል ሲያጋጥመኝ ይህ የመጀመሪያ አይደለም። በተደጋጋሚ ቢሮ ውስጥ እየወደኩኝ ድርጅቱ መኪና እያዘዘልኝ ወደ ቤት እንድሄድ ይደረግ ነበር። ይህ የሞባይል ካርድ ጠፋ ተብዬ ከሥራ ተሰናበትኩ“ ሲሉ ምሬታቸውን ነግረውናል።
ፍትህ ለማግኘት እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ብሄድም ፍትህ ጎሎብኛ፣ የፍርድ ውሳኔው ተገቢ አይደለም፤ይህን ጉዳይ ህዝብ ይፍረደኝ ሲሉ ወደ እኛ መጥተው ቅሬታቸውና በዝርዝር ነግረውናል።
‹‹እኔም በወቅቱ የጤና ህምም ላይ ስለሆንኩ አቤት ለማለት ወደ ፍርድ ቤት መሄድ አልቻልኩም። በዚህ ጊዜ ነው የህዳሴ ቴሌኮም ሰሜን ምሥራቅ ዲስትሪክ አቶ ዑመር ድርጅቱን ብር ስላጎደለ የድርጅቱን ገንዘብ ይክፈል ብለው ደቡብ ወሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሰሰኝ። እኔም መልስ ይዤ ስቀርብ ገንዘቡን ማጥፋቴን አልክድም፤ግን ገንዘቡ የጠፋብኝ በከባድ ህመም ምክንያት ራሴን ስቼ ታክሲ ላይ በመውደቄ ነው። ስለዚህ ሠርቼ ልክፈል እያልኩ እያለ በህምም ላይ እያለሁ ያለአግባብ ከሥራዬ ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰናብቻለሁ ብዬ ለፍርድ ቤቱ ምላሸን ሰጥቻላሁ›› ሲሉ ያብራራሉ።
በወቅቱ ፍርድ ቤቱ የድርጅቱን ተወካይ አቶ ዑመር ለምን ከሥራ ተባረረ ብሎ ሲጠይቀው ከሥራ ያባረርነው ገንዘብ ስላጎደለ ነው የሚል ምለሽ ሰጥቶ ነበር። ይህንን እንደገና ክዶ አምስት ቀን ከሥራ ቀርቶ ነው ከሥራ ያባረርነው የሚል ምክንያት አቀረበ ይላሉ።
‹‹ፍርድ ቤቱም እኔን ምላሽ ጠየቀኝ አምስት ቀን ከሥራ እንዳልቀረሁ ተናገርኩ። ግን ከሥራዬ የተባረርኩት ገንዘብ አጉድለሀል በሚል ነው›› ስል ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጠሁ ይላሉ አቶ ዑመር። ‹‹ሆኖም ፍርድ ቤቱ የእኔን ምላሽ ውድቅ አድርጎ ብዙ ጊዜ የፈጀ ክርክር ስናደርግ ቆይተናል። በመጨረሻም ብዙ ጊዜ ስለቆየህ ወደ ሥራ የመመለስህን ጉዳይ ይርጋ ያግደዋል ተባልኩ።
እኔም በህመም ላይ ስለነበርኩ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቤ መብቴን ለማስከበር አልቻልኩም። ለመታመሜና በህምም ብዙ ጊዜ ስለመቆየቴ በሰው ማስረጃ መረጋገጥ እችላለሁ ብያለሁ። የሀኪም መረጃ አለህ ወይ ብለው ሲጠይቁኝ ሀኪም ቤት ሄጄ የምታከምበት ገንዘብ የለኝም። ከህመሜ የተፈወስኩት በባህላዊ ህክምና ነው። እናም በሰው ማስረጃ አረጋግጣለሁ አልኩኝ። የሰው ማስረጃ አቀረብኩ። የድርጅቱም ሆነ የእኔ ምስክሮች መታመሜን ምስክርነት ሰጡ›› ሲሉ የፍርድ ክርክሩን ሁኔታ ያስረዳሉ።
‹‹የሰዎቹን ምስክርነት ተመስርቶ ፍርድ ቤቱ ይርጋ እንደማያግደኝ አስታወቀ። ፍርድ ቤቱም ከዚያም በእኔና በድርጅቱ መካካል ያለው ክርክር ቀጥሎ በሂደት ላይ እያለ የገንዘቡን መጥፋት ምስክር መስማት አለብን አለ። ከሳሽ ድርጅቱና ተከሳሽ እኔም በየበኩላችን የየራሳችንን ምስክሮች አቀረብን። የእኔም ሆነ የድርጅቱ ምስክሮች የሞባይል ካርዱ እንደጠፋብኝ መሰከሩ። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ምክንያቱን በማላውቀውና እኔም ባልተከሰስኩበት፤ከሳሽም ባልጠየቀበት ጉዳይ አምስት ቀን ሥራ በመቅረትህ ከሥራ መሰናበትህ አግባብ ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ ወሰነብኝ›› ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
confusing incorporates are now the commonalities pertaining to better rolex.find great home you like.fulfill the hopes and dreams and desires epidermis persons in the modern world is a search for the best click to read more in the world.
‹‹ይህ አግባብ ውሳኔ አይደለም ብዬ ይግባኝ ለማለት የደቡብ ወሎ ዞኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ሄድኩ። ለዞኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረብኩትን የፍርድ መቃዋሚያ ዳኛው በደንብ መዝገቡን ሳያይ ሁለት መቶ ሺህ ብር አጎድሎ ወደ ሥራ መመለስ አይችልም የሚል ፍርድ ሲሰጥ ጠበቃዬም ሁለት መቶ ሺህ ብር አይደለም ክሱ ላይ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚል የተጻፈ አለ ወይ? ብሎ ሲጠይቀው ዳኛው ደነገጠ። ዳኛው ደግጦ መዝገቡን እንደገና አየው። ሆኖም አንዴ ስለፈረዱ በዚያው ፍርዱን አጸኑት። ይህ ዳኞች ፍርድ ሲሰጡ ጉዳዩን በጥልቀት እንደማያዩትና የአቤት ባዮችን ችግር ሳይረዱ ፣መዝገብ ሳይመረምሩ ውሳኔ መስጠታቸውን ያሳያል›› ሲሉ ይናገራሉ።
‹‹ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አቤት ልል ስመጣ የህግ ስህተት አለበት ለማለት አይቻልም ብሎ ነው ምልሽ የሰጠኝ። እውነት የህግ ስህተት ከሌለበት የህግ ስህተት የለበትም ብሎ ነው መወሰን ያለበት እንጂ ‹ለማለት አይቻልም› የሚል ምላሽ መስጠጥ ለምን አስፈለገ።
“እኔ ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር የምኖር ሰው ነኝ፤ ሦስተኛ ደረጃ የደረሰ የውስጥ ኪታሮት አለብኝ፤በዚህ ምክንያት ሞዴስ አድርጊ ነው የምሄደው፤ ስድስት ቤቴሰብ አስተዳድራለሁ። ተገቢ ባልሆነ ፍርድና የፍትህ እጦት 27 ዓመታት ሠርቼ ሜዳ ላይ ወድቄያለሁ። ምን ያህል ያጋደል ፍርድ እንደተወሰነብኝ ህዝብና መንግሥት ይወቅልኝ“ ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል።
‹‹ይህን የፍርድ መዛነፍ አቤት ለማለት ወደ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሄጀ ነበር። ፍርድ የተሠጠበትን ጉዳይ ማየት አንችልም ብለውኛል። አሁን ወዴት ሄጄ አቤት ልበል ሲሉ ሁሉም በሮች እንደተዘጉባቸው›› በምሬት ይናገራሉ። ሠራተኛውን ከሥራ የሚያስናብትና ማስጠንቀቂያ የሚያሰጥ የዲሲፒሊን ችግር ሲፈጠር የድርጅቱ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚያየው ቢሆንም ኮሜቴው ምንም ያለኝ ነገር የለም›› ብለዋል።
እኔም ሆነ ሌሎች ሠራተኞች ከመስመር ወደ ሽያጭ የተዛወርነው ያለፍላጎታችን ነው የሚሉት አቶ ኡመር፤ አንድ ጊዜ ቢሮ የሞባይል ካርድ እየሸጥኩ እያለ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ጓደኞቼ ስወድቅ የተበተነውን የሞባይል ካርድ ሰብስበው ሰጥተውኝ የዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያጅ በመኪና ወደ ቤቴ እንዲያደርሰኝ አዘውልኝ በድርጅቱ መኪና ወደ ቤቴ ሄጃለሁ። በዚህ ምክንያት ከሽያጭ ሥራ ወደ ሌላ ሥራ ቀይሩኝ እያልኩ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቤያለሁ›› ሲሉ በሽታቸው የቆየ መሆኑን ያስታውሳሉ።
‹‹ይህኛው አንድ መቶ ሺህ 652 ከሃምሳ ሳንቲም የሞባይል ካርድ የጠፋብኝ ታክሲ ላይ እየሄዱኩ ሳለ ራሴን ስቼ በመውደቄ ነው። ታክሲው ላይ ይውደቅ ፤ሌባ አንስቶ ይውሰደው የማውቀው ጉዳይ የለም። እኔ ከአምስትና ስድስት ቀን በኋላ ነው የነቃሁት። በዚህ ሁኔታ ነው ይህ ጉድለት ያጋጠመኝ። ለስምንት ዓመታት የሞባይል ካርድ ስሸጥ ቆይቻለሁ። ፍርድ ቤቱ ለድርጅቱ አንድ መቶ ሺህ 652 ከሃምሳ ሳንቲምና ዘጠኝ በመቶ ወለድ ተሰልቶ እንድከፍል ወሰነብኝ። በአንጻሩ የእኔ ሁለት ዓመታት ሙሉ 42ሺህ ብር ድርጅቱ ያልሰጠኝ ገንዘብ አለ። ፍርድ ቤቱ እኔ ከእነ ወለዱ እንድከፍል ነው ውሳኔ የሰጠው። የእኔ ግን ወለድ እንዲከፈለኝ አልወሰነልኝም። ይህስ ፍትሐዊ ፍርድ ነው፤ከህግ አንጻርስ እንዴት ይታያል? እኔ የአክሲዮን ማህበሩ176ሺህ ብር በላይ ካፒታል አለኝ። ይህ ሁሉ ታሳቢ መደረግ ነበረበት›› ሲሉ ይጠይቃሉ።
ከሥራ መሰናበትዎና ገንዘብ የማጉደሉ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በዲሲፕሊን ታይቷል ወይ የሚል ጥያቄ ለአቶ ዑመር አንስተንልቻው ነበር። አቶ ዑመርም ‹‹በዲሲፕሊን ኮሜቴ ስለመታየቱ የማውቀው ጉዳይ የለም። ኃላፊዎቹ ጠርተው ያጎደልከውን ገንዘብ ክፈል አሉኝ። እኔም ጊዜ ስጡኝና ከደሞዜ እየተቆረጠ ልክፈል ብያቸዋለሁ። ዛሬ ካልከፈልክ ብለው ነው ከሥራ ያስናበቱኝ። የሰጡኝ የስንብት ደብዳቤ ግን አምስት ቀን ስለቀረ ከሥራ አሰናብተኛዋል የሚል ነው›› ሲሉ ጉዳያቸውን ነግረውናል።
እኝህን ግለሰብ ድርጅቱ በሽያጭ ካርድ የተሰጠዎትን አንድ መቶ ሺህ 652 ብር ከሃምሳ ሳንቲም አጥፋተዋል ተብለው ከሥራ አሰናብቷቸዋል። እሳቸውም እየሠራሁ መክፈል አለብኝ፣ከተባረርኩም የሁለት ዓመት ዕረፍቴ፣ የሰባት ዓመት የአገልግሎት ክፍያ በገንዘብ ተሰልቶ ይሰጠኝ ሲሉ ለፍርድ ቤቶችና ለድርጅቱ አቤት ቢሉም ፍትህ ላገኝ አልቻልኩም ይላሉ።
የአቶ ኡመር የፍርድ ክርክር ጉዳይ ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ሰበር ችሎት ድረስ ሄዷል። በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ወሎ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እሳቸው ከሥራ መስናበታቸውን ውሳኔ
ሲያጸና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ ታኅሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም የሰበር መ.ቁ፣199312 በሰጠው ውሳኔ አንድ መዝገብ ለሰበር ችሎት ሊቀርብ የሚችለው ቅሬታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተገኘበት ብቻ መሆኑን አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጸ 22/1 ይደነግጋል። በዚህ መሰረት ችሎቱ አቤቱታውን መነሻ በማድረግ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉትን ውሳኔዎች አግባብ ካለው ህግ እና በየፍርድ ቤቱ ከተደረጉት ክርክሮች ጋር መርምሮ በቀረበው ጉዳይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተሠርቷል ማለት አይቻለም። በመሆኑም መዝገቡ ለሰበር ችሎት አይቀርብም ብሎ ውሳኔ እንደሰተጠበት መረጃዎቹን አይተናል።
የአክሲዮን ማህበሩ የሠራተኞች ግንኙነትና የዲሲፕሊን ፖሊሲና አፈጻጸም መመሪያ ማህበሩ የቆመለትን ዓላማ በቅልጥፍና እና ባስተማማኝነት ለመውጣት እንዲቻል በመግባባትና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ሰላም የሰፈነበትና የማህበሩ ህልውና የተረጋገጠበትን ተቋምና ጤናማ የሥራ ግንኙነት የሚታይበት የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ስነ ስርዓት (ዲሲፕሊንን) አክብሮ መገኘት ወሳኝ መሆኑን ይገልጻል። በመመሪያው መሰረት የድርጅቱ ሠራተኞች ከባድ ጥፋት ከፈጸሙ በመጀመሪያ ጥፋት ብቻ አጥፊውን ሠራተኛ ከሥራ ሊባረር እንደሚችል ይገልጻል።
ከሥራ የሚያሰናብቱ ጥፋት ናቸው ካላቸው መካከል የአክሲዮን ማህበሩን ምስጢር ማባከን፣ በኩባንያው ንብረቶች ላይ ሆን ብሎ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ዶክመንቶችን መሰረዝ፣መደለዝ ወይም ትክክል ያልሆነ ምስክር ወረቀት ማስያዝ ይገኙበታል። በተለይ እምነት በማጉደል የማህበሩን ገንዘብ ወይም ንብረት ለግል ጥቅም መዋል ከሥራ ለማሰናበት በቂ ምክንያት እንደሆነ በመመሪያው ውስጥ ሰፍሯል። እኝህ አቤት ባይ ግለሰብ ግን ገንዘቡ የጠፋባቸው ራሳቸውን ስተው በመውደቃቸው ነው እንጂ በእንዝህላልነት እንዳልሆነ ምስክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ከሥራ ላይ ስለመጥፋትና ከሥራ ስለመቅረት የሚወሰኑ የዲሲፕሊን ዕርምጃዎች በሚለው ርዕስ ስርም አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ አምስት ቀን በተከታታይ ያለ በቂ ምክንያት ከቀረ ከሥራ ሊሰናበት እንደሚችል ስፍሯል። አቶ ኡመር ሰይድ ከሥራ የቀሩት በህመም ምክንያት መሆኑንና ከህመሜ ተሽሎኝ ከገባሁ በኋላም አምስት ቀን ከሥራ አልቀረሁም ይላሉ። ይህንንም በምስክሮቼ አስረጋግጫለሁ ባይ ናቸው።
የህዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማህበር የሠራተኛ ግንኙነት መመሪያ አንድ ሠራተኛ ከአቅም በላይ ወይም ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምክንያት ከሥራ ሲጠፋና የጠፋበት ምክንያት በቅድሚያ በኩባንያው ታውቆ ምክንያቱ አጥጋቢ ከሆነ ድርጅቱ ለሦስት ወራት ይጠብቀዋል ይላል።
በአቶ ኡመር ሳይድ ስም የተመዘገበ የአክሲዮን መጠን በጠቅላላ ብር 176 ሺህ 481 ብር ከ89 ሳንቲም ያላቸው መሆኑን ህዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ለደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው መረጃ ያመለክታል።
አቶ ኡመር ከህዳሴ ቴሌ ኮም ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። ማህበሩ ከሥራ ሲያባርራቸው አንቀፅ 2.1.6.4.1 ንዑስ አንቀጸ “ሠ“ ጠቅሶ ሲሆን ይህም እምነት በማጉደል የማህበሩን ገንዘብ ወይም ንብረት ለግል ጥቅም ማዋል የሚል ነው። ሆኖም በዚህ ጉዳይ ተከሰው እያለ ድርጅቱ ከሥራ የተሰናበቱት አምስት ቀን ተከታታይ በመቅረታቸው ነው ሲል ጉዳዩን ቀይሮ ፍርድ ቤት እንደተከራከረ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
እንዲሁም እሳቸውም አንድ መቶ ሺህ 652 ብር ከሃምሳ ሳንቲም የሂሳብ ጉድለቱን አምነው ጉድለቱ የተከሰተው ሆን ብዬ ሳይሆን በተደራራቢ በሽታ ምክንያት የከፋ የጤና ችግር አጋጥሞኝ ነው፤እንዲሁም በእንዝህላልነት ገንዘብ ማጉደል በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 መሰረት ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ሊያሰናብት አይችልም ይላሉ።
‹‹በአዋጅ ቁጥር 1156 አንቀፅ 27-1(መ እና ሸ) ላይ እንደተደነገገው ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ሊያሰናብት የሚችለው ሆነ ብሎ ወይም አስቦ በአሠሪው ንብረት ያለአግባብ መገልገል ወይም ጉዳት ማድረስ እንጂ በእንዝላልነት ገንዘብ ማጉደል አይደለም። ስለዚህ ድርጅቱ ያለ ማስጠንቀቂያ ከሥራ ያስናበተኝ በእንዝላልነት ገንዘብ ማጉደል ስለሆነ ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም። ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጁና ከድርጅቱ መመሪያ ውጪ ነው። ፍርድ ቤቱም ከሥራ የተሰናበትኩት በህገ ወጥ መልኩ ሆኖ እያለና የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን የሚቃረን ሆኖ እያለ ስንብቱ ህጋዊ ነው ብሎ የሰጠው ውሳኔ ፍትሐዊ አይደለም ብለው ቢከራክሩም ፍርድ ተጓሎብኛል›› ብለዋል።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት የደቡብ ወሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ኡመር አንድ መቶ ሺህ 652 ከሃምሳ ሳንቲም ከታኅሣሥ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር በአንድነትና በነጠላ ይክፍሉ ብሎ ወስኗል። ከሥራ የተሰናበቱበት መንገድ ህጋዊ በመሆኑ የሥራ ስንብት እና የአገልግሎት ክፍያ ሊከፈለው አይችልም። ወደ ሥራ ልመለስ ብለው የጠየቁት ዳኝነትም ተቀባይነት የለውም ሲል ወስኗል።
‹‹ያልተጠቀምኩበት የ2009 እና 20010 ዓ.ም የዓመት ዕረፍትም ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ይከፈላቸው ሲል የወሰነውን ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲል ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አቤቱታ ባቀርብም በትዕዛዝ ውድቅ ተደርጎብኛል።›› ሲሉ ይናገራሉ።
ድርጅቱ ከሥራ ያሰናበታቸው በእንዝላልነት ገንዘብ አጉድለዋል በሚል ምክንያት ሲሆን፤ እሳቸው እንደሚሉትም በእንዝላልነት ገንዘብ ማጉደል በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 መሰረት ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ሊያሰናብት አይችልም።
‹‹የኪንታሮት፣የልብ፣የአንጀትና የጨጓራ ህመምተኛ በመሆናቸውና ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር የምኖር በመሆኔ ተደጋጋሚ ህመም ያጋጥመኛል። በዚህ ሁኔታ እያለሁ አንድ መቶ ሺህ 652 ብር ከሃምሳ ሳንቲም ከድርጅቱ ተረክቤ ለሽያጭ ያወጣሁት የሞባይል ካርድ የት እንደጣልኩት ሳላውቀው ስለጠፋብኝ የድርጅቱ ገንዘብ ጎሎብኛል። ጉድለቱ ከደሞዜና ከትርፍ ድርሻዬ እየተቀነሰ እንድከፍል በተደጋጋሚ ብጠይቅም ከአቅሜ በላይ በሆነ የጤና እክል ጉድለቱ ተከስቶ እያለ ታስቦ የተፈጸመ በማስመሰልና ያለ ማስጠንቀቂያ ከሥራ አስናብተውኛል፤አሁን ወዴት ልግባ ፣ብዙ ቤተሰቦቼ ይጠብቁኛል፤በአሁኑ ጊዜ ከእነ ቤተሰቦቼ የከፋ ችግር ውስጥ ወድቄያለሁ›› ሲሉ መሬታቸውን ነግረውናል።
‹‹እኤአ በ1/12/2018 ጀምሮ ከሥራ ተሰናብቻለሁ፤አሁን ምንም ገቢ የለኝም፤ የማውቃቸውን ሰዎች እየለመንኩ ነበር ፍርድ ቤት ስከራከር የቆየሁት፤አዲስ አበባ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስመጣም እንዲሁ የትራንስፖርት ለምኜ ነው። ይህን የምሠራበት ድርጅት ያውቃል። ሆኖም በዚህ ሁኔታ እያለሁ ያለግባብ ከሥራ አሰናብቶናል::›› በማለት ህይወታቸውን በችግር እየመሩ መሆኑን አጫውተውናል።
‹‹አምስት ቀን ቀርቶ ነው ያባረርነው የሚለውን ጭብጥ ፍርድ ቤቱ ያንን ሳይዝ እኔ ባልተከራከርኩበትና ምለሽ ባልሰጠሁበት አምስት ቀን ከሥራ ገበታህ ቀርተሀል በሚል ከሥራ መሰናበቴ ትክክል ነው ብሎ ፈረደብኝ። ወደ ጉዳዩን በጥልቀት ሳያዩ የህግ ስህተት የለበትም በሚል አሰናበቱኝ›› ይላሉ።
‹‹የጠፋውን ገንዘብ አልካድኩም። መሰረታዊ ጥያቄዬ ወደ ሥራዬ ልመለስና እየሠራሁ ከደሞዜ እየተቆረጠ ልክፈል ነው ያልኩት የሚሉት አቶ ዑመር ፤አምስት ቀን ተከታታይ ከሥራ የቀረ ይሰናበታል የሚለው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የተሻሻለው ነሐሴ 2011 ዓ.ም ነው። እኔ ከሥራ የተባረርኩት ህዳር 2011 ዓ.ም ነው። ስለዚህ በወቅቱ ባልነበረ አዋጅ ነው የተዳኘሁት። ፍርድ ቤቱም ሊሰማኝ ያልቻለው ይህንን ነው›› ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
‹‹በተጨማሪም ፍርድ ቤቶቹ ከጤና ፤ከቤተሰብ አስተዳዳሪነቴ፣ከሰብዓዊነት አኳያ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ጭብጥ ባልተያዘበት ሁኔታ ነው የተፈረደብኝ ባይ ናቸው። ፍርድ ቤቱ የወሰነልኝን የትርፍ ክፍፍል ድርሻዬ 42 ሺ ብር እንዲሰጠኝ ቢወስንልኝም እስከአሁን አልተሰጠኝም።ይህንን የተዛባ ፍርድ ህዝብና መንግሥት ይወቅልኝ›› ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስረድተዋል።
‹‹ፍርድ ቤቱም ከዚያም በእኔና በድርጅቱ መካከል ያለው ክርክር ቀጠሎ በሂደት ላይ እያለ የገንዘቡን መጥፋት ምስክር መስማት አለብን አለ። ሁላታችንም ምስክሮችን አቀረብን ፤የእኔም ሆነ የድርጅቱ ምስክሮች የሞባይል ካርዱ እንደጠፋብኝ መሰከሩ። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ምክንያቱን በማላውቀውና እኔም ባልተከሰስኩበት፤ከሳሽም ባልጠየቀበት ጉዳይ አምስት ቀን ሥራ በመቅረትህ ከሥራ መሰናበትህ አግባብ ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ ወሰነብኝ ።
ይህ አግባብ ውሳኔ አይደለም ብዬ ይግባኝ ለማለት የዞኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ሄድኩ። ለዞኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረብኩትን የፍርድ መቃወሚያ ዳኛው ሳያነብ ሁለት መቶ ሺህ አጎድሎ ወደ ሥራ መመለስ አይችልም ሲል ጠበቃዬ ሁለት መቶ ሺህ ብር አይደለም። ክሱ ላይ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚል የተጻፈ አለ ብሎ ሲጠይቀው ዳኛው ደነገጠ። ሆኖም አንዴ ስለፈረዱ በዚያው አጸኑት። ይህ ዳኞች ፍርድ ሲሰጡ ጉዳዩን በጥልቀት አንደማያዩትና የአቤት ባዮችን ችግር ሳይረዱ ፣መዝገብ ሳይመረምሩ ውሳኔ መስጠታቸውን ያሳያል›› ሲሉ ይናገራሉ።
‹‹የአገልግሎቴ፣የሥራ ማፈላላጊያና የሞራል ካሳ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛው ይህንን ውሳኔ ሲሰጥ ና ብሎ ካስጠራኝ በኋላ የሁለት ዓመት የዓመት ዕረፍትህ ስንት ቀናት ይሆናሉ ብሎ ጠየቀኝ። ዳኛ ክስ በቀረበበት ጉዳይን አይቶ መወሰን እንጂ ምን ይህ ከጀርባው ሌላ ጉዳይ አለው የሚል ጥርጣሬ ፍጥሮብኛል ነው ያሉት። ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሄጀ ነበር። በፍርድ ቤት የተሠጠበትን ጉዳይ ማየት አንችልም ብለውኛል። በሠራተኛ ከሥራ የሚያስናብትና ማስጠንቀቂያ የሚያሰጥ የዲሲፒሊን ችግር ሲፈጠር የድርጅቱ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ምንም ያለኝ ነገር የለም። ከመስመር ወደ ሽያጭ የተዛወርነው ያለፍላጎታችን ነው።
ከሽያጭ ሥራ ወደ ሌላ ሥራ ቀይሩኝ እያልኩ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቤያለሁ። እንዲያውም አንድ ጊዜ ቢሮ የሞባይል ካርድ እየሸጥኩ እያለ ራሴን ስቼ ወድቄ የዲስትሪክቱን ሥራ አስኪያጅ በጣም አሞኝ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ጓደኞቼ ስወድቅ የተበተነውን የሞባይል ካርድ ሰብስበው ሰጥተውኝ በድርጅቱ መኪና ወደ ቤቴ ሄጃለሁ። ይኼኛው ካርድ የጠፋብኝ ታክሲ ላይ እየሄዱኩ ሳለ ራሴን ስቼ በመውደቄ ነው። ታክሲው ላይ ይውደቅ ሌባ አንስቶ ይውሰደው የማውቀው ጉዳይ የለም። እኔ ከአምስትና ስድስት ቀን በኋላ ነው የነቃሁት።
በዚህ ሁኔታ ነው ይህ ጉድለት ያጋጠመኝ። ለስምንት ዓመታት የሞባይል ካርድ ስሸጥ ቆይቻለሁ። ለድርጅቱ ፍርድ ቤቱ የወሰነልኝን የትርፍ ክፍፍል ድርሻዬ 42 ሺ ብር እንዲሰጠኝ ቢወስንልኝም እስከአሁን አልተሰጠኝም። ለ100 ሺህ 666 ዘጠኝ በመቶ ወለድ እንድከፍል ወሰነብኝ። በአንጻሩ የእኔ ሁለት ዓመታት ሙሉ 42 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ በድርጅቱ ያልሰጠኝ ገንዘብ አለ። እኔ ከእነ ወለዱን እንድከፍል ነው ውሳኔ የሰጠው። የእኔ ግን ወለድ እንዲከፈለኝ አልወሰነልኝም። ይህስ ፍትሐዊ ፍርድ ነው፤ከህግ አንጻርስ እንዴት ይታያል›› ሲሉ ይጠይቃሉ።
‹‹እኔ የአክሲዮን ባለድርሻ ነኝ። ከ176 ሺህ ብር በላይ ካፒታል አለኝ። ይህ ሁሉ ታሳቢ መደረግ አለበት። ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት በዲሲፕሊን ስለመታየቱ የማውቀው ጉዳይ የለም። ኃላፊዎቹ ጠርተው ያጎደልከውን ገንዘብ ክፈል አሉኝ እኔም ጊዜ ስጡኝኛ ከደሞዜ እየተቆረጠ ልክፈል ብያቸዋለሁ። ዛሬ ካልከፈልክ ብለው ነው ከሥራ ያስናበቱኝ። የስንበት ደብዳቤው አምስት ቀን ስለቀረ አሰናብተነዋል የሚል ነው። እና እኔን ለመበደል የተደረገ ነው እንጂ ህጉን ጠብቆ የተወሰነ አይደለም›› ሲሉ ያብራራሉ።
በህዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማህበር የሠራተኛ ግንኙነት መመሪያ መሰረት በተከታታይ ለአምስት የሥራ ቀናት ያለበቂ ምክንያት ከሥራ የሚቀርን ሠራተኛ ኩባንያው ከሥራ ያስናብተዋል ይላል። ሆኖም የተጠቀሰው የ5 ቀን ገደብ ከመድረሱ በፊት ኩባንያው የመጨረሻ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ በአምስተኛው ቀን መሰጠት አለበት። ሠራተኛው የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆን ወይንም ሠራተኛው ባለመገኘቱ ምክንያት አስፈርሞ መስጠት ባይቻል በሚሠራበት አካባቢ ወይም ክፍል ውስጥ ግልጽ በሆነ ስፍራ ላይ የሠራተኛው የቅርብ አለቃ ወይም ተቆጣጣሪ ባለበት እንዲለጠፍ ይደረጋል። የተለጠፈው የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ቢያንስ ለ10 ቀናት በማስታወቂያ ሰሌዳ ወይም በተለጠፈበት ስፍራ ላይ ይቆያል ይላል። ይህን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ ያረጋገጥበት ጉዳይ እንደሌለ ውሳኔ ከሰጠባቸው ሰነዶች መረዳት ችለናል።
አንድ ሠራተኛ ከአቅም በላይ ወይም ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምክንያት ከሥራ ሲጠፋና የጠፋበት ምክንያት በቅድሚያ በኩባንያው ታውቆ ምክንያቱ አጥጋቢ ከሆነ ድርጅቱ ለሦስት ወራት ይጠብቀዋል ይላል። አንድ ሠራተኛ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት የማህበሩን ገንዘብ ወይም ንብረት ያጎደለ ወይም ያለአግባብ የተጠቀመ፣ በድርጅቱ ላይ ኪሳራ የሚያስከትል ድርጊት የፈጸመ ወይም በገንዘብ ሊተመን የሚችል ዶክሜንት ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም ያጠፋ በዚህ መመሪያ ከተመለከተው የዲሲፕሊን ዕርምጃ በተጨማሪ ባደረሰው የጉዳት መጠን በሚዘጋጀው የጉዳት ግምት መሰረት ማህበሩ ከደመወዙ በየወሩ ተመጣጠኝ ገንዘብ እየተቆረጠ ለድርጅቱ ገቢ ይደረጋል ቢልም የአቶ ኡመርን ጉዳይ በዚህ መመሪያ ማስተናገድ እንደሚቻል በህዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማህበር የሠራተኛ ግንኙነት መመሪያ መረዳት ይቻላል።
በአክሲዮን ማህበሩ የስነ – ስርዓት(ዲሲፕሊን) መመሪያ መሰረት ቅጣት የሚያቀሉ ጉዳዮች ብሎ ከጠቀሳቸው መካከልም ከዚህ በፊት መሰል ድርጊት ያልፈጸመ የሚለውን ጉዳይም አልታየላቸውም።
የአገልግሎት ክፍያ፣የሥራ ማፈላላጊያና የሞራል ካሳም ሳይሰጣቸው ሰባት ዓመት ከሠሩበት መስሪያቤት ከሥራ መሰናበታቸው በኑሯቸውና በቤተሳባቸው ላይ ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን ነግረውናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የህዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማህበር ደሴ ከተማ የሚገኘውን የሰሜን ምዕራብ ዲስትሪክ ምልሽ እንዲሰጡበት ተደጋጋሚ በስልክ ያደረግነው ሙከራ ስልኩ ሊነሳ ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም። የዲስትሪክቱ ኃላፊዎች በአቶ ኡመር ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ በቀጣይ የምናስተናግድ መሆኑን እየገለጽን የዛሬውን በዚሁ እንቋጫለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013