አስቴር ኤልያስ
የአስር ዓመት የልማት እቅድ ርዕዩ በ2022 ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሆነ በተለያዩ የውይይት መድረኮች በማስተዋወቁ፣ ግንዛቤ በመፍጠሩና ግብዓት በመሰብሰቡ ወቅት ተደጋግሞ ሲነሳ የቆየ ነው። ብልጽግና ሲባልም የቁሳዊ፣ የክብር፣ የእኩልነትና ነጻነት መረጋገጥ እንደሆነም እየተነገረ ነው። አነዚህን የዜጎች ፍላጎት ለማሟላትና አገሪቱንም የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል አቅዳ ከነበረው የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተገኘ ተሞክሮና በቀጣይ የዜጎችን ህይወት የተቃና ሊያደርግ የሚችል ተግባር እንዴት ሊከናወን እንደታሰበ እንዲሁም የክትትልና የግምገማ ስርዓት ምን መሆን እንዳለበት ከፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የአስር ዓመት የስትራቴጂክ እቅድ አውጥታ እንደነበር ይታወሳል፤ ለመሆኑ የዚህ እቅድ አፈጻጸም ምን ይመስላል? ከዚህ የተገኙ ተሞክሮዎችስ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ፍጹም፡– ኢትዮጵያ እቅድ በማቀድ በጣም ረጅም ጊዜ ሆኗታል። ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለ60 ዓመታት ያህል ኢኮኖሚዋን በማቀድ የመምራት ልምድ ነበራት። በተለይ ደግሞ ባለፈው አስር ዓመት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ እና ሁለት ተብሎ የአምስት የአምስት ዓመት የእቅድ ጊዜ ነበር።
አሁን በተለይ የአስር ዓመቱን እቅድ ስናቅድ እንደመነሻ የወሰድነው የየአምስት ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምን ነው። አፈጻጸሙ ጥሩ የሚባል ነገር እንዳለው ሁሉ ባቀድነው መጠን ያላሳካናቸው ብዙ ነገሮችም ነበሩት።
ጥሩ ተሞክሮ ተገኝቶበታል ከሚባለው ውስጥ አንዱና በቀጣይ ብንሄድበት ብለን ያሰብነው የኢኮኖሚው ዘርፍ ነው፣ ይህም ሲያድግ የቆየ መሆኑ አይካድም። ከእድገቱ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር ሁሉም ኢትዮጵያ ተገኘ የተባለው እድገት ተሰምቶታል ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢኮኖሚው ግን በአጠቃላይ በተለይ በመንግስት በተደረገ ኢንቨስትመንት እንደ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የጤና ተቋማት ማስፋፋት፣ ትምርት ቤት ማስፋፋትና መሰል ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ለውጦች ማምጣት አስችሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመጣው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይም ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ አንዱ መልካም ተሞክሮ የተገኘበት ነው ብለን የምናነሳው ጉዳይ ነው።
በእርግጥም አሁንም ቢሆን በርካታ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ቢገኝም ከአስር ዓመት በፊት ከድህነት ወለል በታች ከነበረው 30 በመቶ ህዝብ በ2012 ዓ.ም ወደ 19 በመቶ መቀነስ ተችሏል። ይህ እንደ አንድ መልካም አፈጻጸም ሊያዝ የሚችል ነው። ሌሎችም መልካም አፈጻጸም አላቸው የሚባሉ አሉ። ለምሳሌ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከነክፍተቶቹ መንገድ፣ ኢነርጂ፣ ባቡር ዝርጋታና መሰል ስራዎችን ስናስትውል ጥሩ የሚባሉ አፈጻጸሞች ነበሩ። ነገር ግን የጥራት ጉድለት ነበረባቸው።
ተያይዘውም የፍትሃዊነት ጥያቄዎችም ይነሳሉ። በተለያዩ አካቢዎች ወይም ወረዳዎች እኩል የመሰረተ ልማት ተደራሽነት አልነበራቸውም። አንዱ ክልል ከአንዱ ክልል የሚለያይበት፤ በጣም በትልቁ እንኳንም ባይሆንም አሁንም በልማት ወደኋላ የቀሩ አካባቢዎች ስለመሆናቸው፤ የአርብቶ አደሩን አካባቢም ስንመለከት የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ወይም ተደራሽነታቸው እንደሌላው አካባቢ አለመሆኑ በክፍተት የሚታይ ቢሆንም በጥሩ የሚጠቀስ ነገር መኖሩ እርግጥ ነው። በመሆኑም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ግን ከፍተኛ ስራ ነው የተሰራው።
ሌላው በማህበራዊ ዘርፍ በምንላቸው ለምሳሌ በትምህርትና በጤና ተደራሽነት አሁንም ቢሆን ከነክፍተቶቹ ትልቅ እና የተመሰከረለት ስራ ተሰርቷል። በጤናውም የአገልግሎት ጥራት ችግር በትምህርትም እንዲሁ የጥራት ችግር መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ለማለት ነው። በዚህ በኩልም የፍትሃዊነት ችግር አለ። ደግሞ የአርብቶ አደሩን አካባቢ ብጠቅስ የአኗኗር ሁኔታው የተለየ በመሆኑ ምክንያት ያንን ያማከለ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ክፍተት ነበረበት። እሱ እንዳለ ሆኖ ግን በጥቅሉ በኢትዮጵያ ደረጃ ስናየው በዚህም ዘርፍ ጥሩ የሚባሉ አፈጻጸሞች ነበሩ።
ክፍተቱ አካታች አለመሆኑ እንዲሁም ዜጋው እድገቱን በየቤቱ ገብቶ አለማግኘቱ ማለትም ሁሉም ሰው ኢትዮጵያ አድጋለች ሲባል ሊሰማው የሚችለው አይነት ስሜት አለመኖሩ የራሱ የሆነ እክል ነው። እድገቱ በአንድ ወገን ቢኖርም በሌላ ወገን ደግሞ የኑሮ ውድነቱ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፤ ምክንያቱም ምርትና ማርታማነት ላይ የተመሰረተ እድገት አልነበረም። መንግስት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ባደረገው ኢንቨስትመንት የመጣ እድገት እንጂ ግብርና ላይ፣ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ በተደረጉ ኢንቨስትመንቶችና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የተገኘ እድገት ባለመሆኑ የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ሆኗል። ምክንያቱም ገበያ ላይ በጣም ብዙ ፍላጎት አለ፤ ነገር ግን በሌላኛው በኩል ስናይ ግብርናው ዘርፍ እምብዛም አልተንቀሳቀሰም።
አምራች ኢንዱስትሪው ደግሞ እንዲያውም ብዙ ለውጥ ያላሳየ ዘርፍ ነውና ገበያው ላይ የኑሮ ውድነት እንዲስተዋል አድርጓል፤ አምርተን፣ ሸጠን፣ ብድር አግኝተን ብድራችንን መክፈል አለመቻላችንና በዛው መጠን እነዛን የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹን ለመስራት መንግስት የአገር ውስጥም የውጪም በጣም ብዙ ብድር በመበደሩ፤ በመንግስት የልማት ድርጅቶችም ሆነ በተለያዩ ተቋማቱ በኩል ብዙ ብድሮች በመጠቀሙ የብድር ጫናው ከፍተኛ ነበር። የማክሮ ኢኮኖሚው ጭምር መዛባት አመጣ። በአጭሩ ይህ የመጣው እድገት እና ልማት ችግሮችን ይዞ መጣ ማለት ነው።
ማኔጅ የተደረገበት መንገድ ክፍተት ነበረበት። በጥቅሉ ጥሩ የሚባሉ ተሞክሮዎችም ቢኖሩ የመጣው ልማት እና የራሱን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት አመጣ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ስትራቴጂክ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ የተሳኩና ያልተሳኩ ወይም ከእቅዱ አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም የነበራቸው ዘርፎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ እንደሱ ሆነ?
ዶክተር ፍጹም፡– አቅደን ያልፈጸምናቸው ብዙ ናቸው፤ ለምሳሌ በዋናነት የማነሳው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር አልተረጋገጠም። እንዲህም ሲባል ባህላዊና ፕራይመሪ ከምንላቸው ዘርፎች ዘመናዊ ወደሆኑትና እሴት ወደሚጨምሩ ዘርፎች ኢኮኖሚው አልተሸጋገረም። እንዲህም ሲባል ለምሳሌ ግብርና አሁንም ትልቁን የኢኮኖሚውን ድርሻ ይወስዳል። መሆን የነበረበት ግብርና ሁሌ ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ ግን ስንሸጥም፣ ወደውጭ ስንልክም የግብርና ምርታችንን ለምሳሌ ቡና ጥሬውን መሸጥ ሳይሆን ቆልተንና ፈጭተን መቻል አለብን። ከቡና የሚሰሩ ሌሎች ምርቶችን በማምረት መሸጥም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።
አቡካዶን እንደሁ ከምንሸጥ ወደዘይትነት ቀይረን መሸጥ ብንችል፤ እንዲሁም የቅባት እህሎቻችንን በጥሬው ከምንልካቸው ዘይት አምርተን ቢያንስ እንኳ ከውጭ የሚመጣውን መተካት ብንችል በተጨማሪም ወደውጭ መላክ የምንችል ከሆነ ሽግግር የምንለው ይህንን ነው። ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ምርታማነት ወዳላቸው ዘርፎች መሸጋገር ቢቻል የተሻለ ነው። ለምሳሌ ግብርና ውስጥም ቢሆን ወደሆርቲካልቸር፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት እና መሰል ወደሆነው የምናደርገው ሽግግር በጣም ትንሽ ነው። አሁንም ድረስ ይዘን የቀጠልነው በተለመዱት ምርቶች ብቻ ነው። እነሱም ደግሞ ዝቅተኛ ምርት አላቸው የምንላቸው ናቸው።
የእንስሳት ሀብታችን በጣም ከፍተኛ ሆኖ አሁንም ያልተጠቀምንበትና ምንም እሴት ያልጨመርንበት ነውና ከግብርና ወደኢንዱስትሪ ቀጥሎም ደግሞ ዘመናዊ ወደሆኑ የአገልግሎት ዘርፎች ወደሆኑትን እነአይ.ሲ.ቲን ጨምሮ የመሸጋገሩ ነገር በጣም ካልተሳኩት ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
ወደዝርዝር ዘርፎች ስንመጣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በተለይ አቅሙን አሟጦ ከመጠቀም አኳያ ያለው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው። ለምሳሌ አንድ ፋብሪካ ካለው አቅም የሚጠቀመው 50 በመቶና ከዛ በታች ነው እየተጠቀመ ያለው። ፋብሪካዎቹ ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም እንዳይችሉ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት ሙሉ አቅማቸው መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርጋቸውን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ባለመቻላችን ነው። ይኸውም አንዱ ኢነርጂ ነው፤ ኢነርጂ ላይ መሰረተ ልማቱ መዘርጋት ቢጀምርም ፕሮጀክቶቻችንን ጀምረን መጨረስ አልቻልንም።
ለምሳሌ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁን ወቅት ማለቅ የነበረበትም ቢሆን አንዱ ትልቁ ማነቆ ፋብሪካዎቻችን በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ከሚያደርጋቸው ውስጥ የኃይል አቅርቦት ነው። የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት ፋብሪካዎች በተራ መስራት ተገደዋል። የኃይል መቆራረጥ ያስቸግራቸዋል። በዚህም ራሱ ያለንን እቅም አሟጠን እንዳንጠቀም የኃይል ጉዳዩ ማነቆ ሆኗል። ይህ የኢነርጂ ጉዳይ ካልተሳኩ ነገሮች መካከል የሚቆጠር ጉዳይ ነው። የኢነርጂ ጉዳይ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ታቅዶ የነበረው 17 ሺህ ሜጋ ዋት ነበር። አሁን ላይ ያለነው ው 4 ነጥብ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ላይ ነው። ስለዚህም ይህ ካልተሳኩ ነገሮች ውስጥ ይካተታል።
ሌሎች ያልተሳኩ ብለን የምንላቸው ደግሞ ዝርዝር ግቦች አሉ። በተለይ ደግም ግቡን ከመሰብሰብ አኳያ ታቅደው የነበሩ፣ የዋጋ ግሽበትን ወደ አንድ አኃዝ የማውረድ እቅድ እና ከማክሮ ኢኮኖሚው ጋር የተያያዙ አመላካቾች የምንላቸው ሳይሳኩ ቀርተዋል። በዩራፕ የመንገዱ ስራ እንዲሁ እንደታሰቡት ሳይሳኩ የቀሩ ጉዳዮች ናቸው። በመንገድ ዝርጋታው በጥሩ ሁኔታ የተጓዝንባቸው ነገሮች ቢኖሩም አሁንም ገጠር አካባቢ ያሉ አገናኝ መንገዶች በአግባቡ እየተሰሩ አለመሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
ከመዋቅራዊ ሽግግሩ በተጨማሪ ወደዝርዝሩ ዘርፍ ስንመጣ ደግሞ ያላሳካናቸው በርካታ ግቦች አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም በነበረው የስትራቴጂክ እቅድ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንደምትሸጋገር ማቀዱ ይታወሳል። ይህ ምን ያህል መስመር ውስጥ ገብቷል?
ዶክተር ፍጹም፡– መስመር ውስጥ ስለመግባቱ ጥርጥር የለውም፤ የኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግር የሚባለው ነው በሌላ ቋንቋ ግብርናው በሚፈለገው ፍጥነት ባይሆንም እየቀነሰ መጥቷል። 47 ነጥብ 5 በመቶ ከነበረበት አሁን ላይ ከአገር ውስጥ ምርት ወደ 32 በመቶ ቀንሷል። ይህ ተፈጥሯዊ መቀነስ ያለበትን መንገዱን ይዟል ያስብላል። ችግሩ ግን ፍጥነቱ ላይ ነው። እንዲያም ቢሆን ግብርና የቀነሰበት ፍጥነት በጣም መጥፎ የሚባል አይደለም።
ነገር ግን ከዛ የወጣውን ማን ነው የተረከበው ስንል መዋቅራዊ ሽግግር በትክክል ሆኖ ቢሆን ኖሮ መረከብ የነበረበት ከኢንዱስትሪው ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው ነበር። ከኢንዱስትሪው ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው፣ ማዕድን በተጨማሪ ደግሞ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አለ። ባለፉት አስር ዓመታት ከግብርና የወጣውን መጋራት የተቀበለው ኮንስትራከሽን ነው።
ተከታታይ ወይም ደግሞ ጤናማ ያልሆነ ልውውጥ ነው። መዋቅራዊ ሽግግሩን በትክክኛው መንገድ አይደለም። ማለትም ግብርናው እየቀነሰ ኢንዱስትሪው እየተረከበ ቢሆንም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍፍል ነጣጥለን ስናየው ግን ማኑፋክቸሪንግ አይደለም እየተቀበለ ያለው። ወይም አምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ሳይሆን የተቀበለው ኮንስትራክሽኑ ነው። ስለሆነም በትክክለኛ መስመር ላይ ቢሆንም በጣም ቀርፋፋ ነበር ማለት ይቻላል።
ይህን ጉዳይ በተለያዩ አመላካቾች ማየት ይቻላል። አንደኛው በኤክስፖርት ምርቶቻችን ውስጥ ወደ ውጭ የምንልካቸው እቃዎች ምንድን ናቸው ብለን ዘርዝረን ብናይ አሁንም ወደ 77 በመቶ ግብርና ነው ትልቁን ድርሻ የሚወስደው። እንዲህም ሲባል አሁንም እየሸጥን ያለው ጥሬ ምርቶችን ነው ማለት ነው። በተጨማሪም በሰው ኃይል ስምሪትም ስንመለከት አሁንም በጣም ብዙ ሰራተኛ ቀጥሮ ያለው ግብርና ነው። ይህ የሚያመላክተን ትክክለኛ መንገድ ላይ ብንሆንም ግን በጣም እየተንቀረፈፈ መሆኑን ነው። በመሆኑም እቅዳችን እንዳልተሳካ ነው የሚያሳየው።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የፕላን ኮሚሽን የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት የተሳተፉበት የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፤ የዚህ እቅድ ዋና ግቡ በዋናነት አገሪቷን ወደየት ለማድረስ ነው?
ዶክተር ፍጹም፡– ስለዚህ ጉዳይ ጠቅለል አድርጌ ስነግርሽ ርዕዩ ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ነው። እንዲህ ሲባል እዚህ ውስጥ ሁለት ገዢ ቃሎች አሉ። አንዱ አፍሪካ የሚለው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ብልጽግና የሚል ነው። አፍሪካዊት ያልንበት ምክንያት በዓለም ላይ ማንኛውም አገር ልምድ ሲቀምር የሚሄድባቸው ኮርነሮች አሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማልማት፣ ህዝቧን ካለበት የኑሮ ሁኔታ ለማሸጋገርና አገሪቱ ወደተሻለ መንገድ ለመምራት የአገራት ልምድ ብላ የምትቀምራቸው ነገሮች አሉ። ከቻይና፣ ከቬትናም፣ ከኮሪያና ከሌሎችም አገራት ልምድ ለመቀመር ጥረት ይደረጋል።
ከአፍሪካ ብለን ብናይ ግን ተስፋ ሰጪ የሆነና ተምሳሌት ሊሆን የሚችል አልተፈጠረም፤ ዓለምም የሚረዳው እንደዛ ነው። ስለዚህም ይህ ታሪክ መቀየር አለበት። አንዲት ጥቁር አፍሪካዊት አገር ለመልማት የወሰደችው መንገድ ለሌሎች አገራት ተምሳሌት መሆን ይችላል የሚል አንደኛው እንድምታው አንዱ ገዢ ቃል አፍሪካ የምንለው።
ብልጽግና የምንለው ደግሞ በአስር ዓመት ውስጥ ተሳክቶና ጨርሰን ጫፍ እንደርሳለን ማለት አይደለም። ርዕያችንም ጊዜ የሚገድበውም አይደለም። ይህ የአስር ዓመት እቅድ ግን በዛ በትክክለኛ መስመር ውስጥ የሚያስገባን ነው። ከአስር ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ትክክለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፤ ያንንም አቅም ፈጥራ ትደርሳለች የሚል ነው።
ርዕዩ ይህ ሆኖ ዋናው ነገር ግን ግቡ ብዙዎች የሚጋሩትና ሰዎች ሁሉ የሚያጣጥሙት አካታች የሆነ ልማት ተረጋግጦ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት መጥቶ ህዝቡ ሁሉ በሚመለከተው ደረጃ የልማቱ ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ ሆኖ የጋራ ብልጽግና መረጋገጥ የሚችልባት አገርን ማየት መቻል ነው። ነገር ግን ብልጽግና አሁንም በኢኮኖሚ ወይም ቁሳዊ በሆነ ነገር ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የለመድነውን አይነት የነፍስ ወከፍ እድገት ገቢ በዚህን ያህል በመቶ እድገት የሚለውን ብቻ ሳይሆን የሰውን ህይወት በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ለምሳሌ እኩልት፣ ነጻነት፣ የፍትህ ተደራሽነት፣ መልካም አስተዳደርና መሰል የሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተሰርተው ለህዝብ አገልግሎት መቆሙን የሚያረጋግጥበት ነው።
ዘላቂ ሰላምም የሚረጋገጥበትና ከጎረቤት አገሮችም ጋር በልማት የምንተሳሰርበት እና አጠቃላይ የኢኮኖሚው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊና የተለያዩ ስርዓቶችም እንዲሁም የመንግስትና የግሉንም ሚና የሚዳኙ የማህበረሰባዊ አመለካከቶች ሁሉ ትራንስፎርም አድርገው ለአገር ብልጽግና በሚያገለግሉበት እና ቁርጠኝነታቸውን በሚያሳዩበት መልኩ እንዲዳብሩ ግቦች ተይዘዋል።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ የዜጎችስ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ምን ታቅዷል?
ዶክተር ፍጹም፡– ከኢኮኖሚ አንጻር የሰው ልጅ ኑሮ መሻሻሉ አስፈላጊ ነው። የሰው ልጅ ገቢ የሆነ ደረጃ ላይ መድረስ መቻል አለበት። አንድ ሰው ገቢ ካለው ደግሞ ጥሪት ይኖረዋል። ጥሪቱ ሲተረጎም ደግሞ ኑሮው የተሻሻለ ይሆናል። ዓለም በሚለካበት በነፍሰ ወከፍ ገቢ ብንገልጸው በአስር ዓመቱ መጨረሻ የነፍስ ወከፉ ገቢ ሁለት ሺህ 200 የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ነው የሚታሰበው። እሱ ብቻ በቂ አይሆንም። ብልጽግና ፈርጀ ብዙ ነው። ለዚህም ነው እንደመንግስትም ቃል ስንገባ የገባነውን ቃል ማሳካታችንንና ቃላችንን መጠበቃችንን የምንለካው በነፍስ ወከፍ ገቢያችን ይሆናል።
የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን ለማሳደግ በሚደረገው የልማት ጥረት ውስጥ የዜጎች ተሳታፊነት በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው። ልማቱም እድገቱም የመጣው ሁሉም ዜጋ ተሳትፎበት ነው። በመሆኑም ዜጎች በልማት ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆን የሚያስችላቸው ነገር አንዱ አቅማቸውን አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች ጤናቸው መጠበቅና መማር መቻል አለባቸው። እነዚህን ጉዳዮች በነጻ የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። እነዚህን አገልግሎቶች መንግስት ለህዝቡ ማድረስ አለበት።
ሌላው የዜጎች የኑሮ ሁኔታ የት ይደርሳል ካልን አንድ ሰው የተሟላ ነገር ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ስለሰላምና ስለደህንነቱ ሊሰማው የሚችለው ስሜት ያለውን እንኳ ማጣጣም እንዲችል በጣም ወሳኝ ነው፡ ስለዚህ የአንድ ሰው የእርካታ ደረጃ የሚለካው በዚህም ጭምር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ማህበራዊ መስተጋብራቸው በጾታ፣ በብሄርና፣ በእድሜ መለያየት ሳይኖርና እነዚህ ነገሮች ሳይገድቧቸው በአገሪቱ ባለው በማንኛውም ልማት መሳተፍ መቻል አለባቸው። ይህም ከአስር ዓመት በኋላ በእነዚህ አይነት ነገሮች ያሉ ችግሮች ተፈትተው በሁሉም አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በእኩልነት መንቀሳቀስ ወደሚያስችል ሂደት የሚስያገባ ይሆናል። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የዜጎችን ህይወት ተጨባጭ በሆነ መልኩ መቀየር ይቻላል ብለን ነው በአስር ዓመት ውስጥ የያዝነው እቅድ የሚያሳየው።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም በነበረው የስትራቴጂክ እቅድ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ እንደምትሸጋገር ማቀዱ ይታወሳል፤ በቀጣይስ?
ዶክተር ፍጹም፡– በቀጣይ የተያዘው ያለብንን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለማስወገድ የኢኮኖሚው የአቅርቦት ዘርፉ ላይ ስራ መሰራት አለበት። ይህ ማለት ግብርና ድርሻው እየቀነሰ ይሂድ አንደማለት ነው። ግብርናው በሚቀጥረው የሰው ኃይል በኢኮኖሚው ውስጥ ለምሳሌ ኤክስፖርት በምናደርጋቸው ምርቶች ውስጥ ጥሬ ምርቶቹ እየተቀነሱና እሴት እየተጨመረባቸው የሚሄዱበት ሁኔታ በአግባቡ መጀመር አለበት ከማለት አኳያ ነው እንጂ ግብርና በራሱ ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ ገና ብዙ የቤት ስራ የሚቀረን ጉዳይ ነው።
ግብርና እሱን እያደረገ ለምሳሌ ከውጭ የሚመጡ አንድ ስንዴ አይነቶቹን ምርቶች በመተካት እንከፍል የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የውጭ ምንዛሬውን ወሳኝ ለሆኑ ለሌሎች ዘርፎች እንዲውሉ የራሱን አስተዋጽዖ ደያርጋል። ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት ያቀብላል። በአሁን ወቅት ለገነባናቸው ብዙ አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት ግብርናው መስጠት መቻል አለብን። ይህ የሚያሳየን በግብርናው በኩል አሁንም በጣም ብዙ የሚሰራ ስራ እንዳለ አመላካች ነው።
ከመሸጋገር አኳያ ግን ግብርና ራሱ በውስጡ ከፍተኛ ምርታማነት ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ወደ እንስሳት አካባቢ የሚሰሩ ስራዎች ላይ በደንብ መስራት ይኖርበታል። በተጨማሪም ኢንዱስትሪው ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪው ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት። የኢኮኖሚ እድገቱ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በአማካይ አስር በመቶ እንዲሆን ነው የታቀደው። ያንን የኢኮኖሚ እድገት ከዚህ በፊት እንደተለመደው ኮንስትራክሽን፣ ግብርናና የመሳሰሉት የጅምላና ችርቻሮ ንግዶች ናቸው እድገቱን ሲመሩት የቆየው። አሁን ግን በሚቀጥለው አስር ዓመት በየዓመቱ በአማካይ በማደግ ከ20 በመቶ በላይ የሚመራው አምራች ኢንዱስትሪው ነው።
እንዲህም ሲባል ሽግግሩ ኢኮኖሚውን በመምራት ከሌሎቹ ዘርፎች አምራች ኢንዱስትሪው ይቀበላል።
ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው ቢባል ብዙ ስራ አጥ ቁጥር አለ። አምራች ኢንዱስትሪው ደግሞ በጣም ብዙ ሰራተኞችን በመቅጠር ይታወቃል። በተጨማሪም ዘላቂ የሆነ ስራ መስጠት የሚችል ዘርፍ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪው እሴት የተጨመረበት ነገር አምርቶ ለውጭ ሸጦ ገንዘብ ማግኘት መቻል አለብን። በተለይ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶ በዋናነት የሚሰራው በምግብ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በአልባሳት እንዲሁም በመድኃኒት ኢንዱስትሪው ላይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ትኩረት ይደረጋል። ቀጥሎ ደግሞ ኬሚካልና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት ይደረጋልና መዋቅራዊ ሽግግሩን ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ እቅድ ተይዟል።
በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ውስጥ የግብርና ድርሻ ወደ 22 በመቶ ይቀንሳል። የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው 35 ነጥብ 9 በመቶ ይጨምራል። ከኤክስፖርት ውስጥም እንደዚሁ የግብርና ድርሻ ቀንሶ በጥሬው መሸጥ አቁመን እሴት ተጨምሮባቸው የሚሸጡ ምርቶቻችን ናቸው ብዙውን ድርሻ የሚወስዱት። በሰው ኃይል ስምሪትም ግብርና ይቀንስና በተለይ አምራች ኢንዱስትሪው 15 በመቶውን የሰው ኃይል ስምሪት ይወስዳል። እዛ ውስጥ ሌላም ዘርፍ አለ። በመሆኑም መዋቅራዊ ሽግግሩ በእነዚህ ሁሉ በተቀመጡ ግቦች እንደሚሳካ የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ወይም ዘላቂ እቅድን ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች አንዱ ካፒታል ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ አንጻር በቂ የካፒታል አቅም የላትም፤ ይህ ክፍተት በምን ይሸፈናል?
ዶክተር ፍጹም፡– ትክክል፤ ፋይናንስ በጣም ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ነው። ፋይናንስ ለምናስበው ልማትና ብልጽግና የኦክሲጂን ያህል አስፈላጊ ነው። ነገር ግን እንደ አገር በጣም ብዙ ምንጮችን ማሰቡ አስፈላጊ ነው። ከዚህ የነበረው አንዱ ድክመታችን ባለፉት አስር ዓመታት እድገታችንና ልማታችንን ፋይናንስ ያደረግንበት መንገድ ዘላቂ አልነበረም። ይህ በመሆኑም ነው ብዙ እዳ ተሸክመን ያለነው። የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች እንኳ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ቆመው የነበሩት ብዙ ጥረት በማድረግ ወደስራ የገቡ ናቸው። ስለዚህም በሚቀጥለው አስር ዓመት እንደዛ መቀጠል አይችልም። ብዙ ካፒታልን የሚጠይቅ ነው። ግን ይህ የአስር ዓመት እቅድ የኢንቨስትመንቱን ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የግሉ ዘርፍ ነው፤ ያ የግሉ ዘርፍ በጣም ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል።
ነገር ግን እስካሁን የግሉ ዘርፍም ቢወስድ ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፋይናንስ መመቻቸት መቻል አለበት። ያንን ለማድረግ ያለን የፋይናንስ ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነው። ወደ አርብቶ አደሩ አካባቢ ስንሄድ ገና የባንክና የፋይናንስ ተቋማት አልደረሱም። ስለዚህ በጣም ብዙ ካፒታል ሊሰበሰብ የሚችል በቁጠባ መልክ ንቅናቄ ተደርጎ ነው ወደኢንቨስትመንት የሚዞረው። ነገር ግን ያንን ሳናደርግ የቆየን በመሆኑ አሁን እሱን መስራት አለብን።
በዚህ በአስር ዓመቱ አንዱ ስትራቴጂክ የሆነው አንኳሩ ነገር ዘላቂ የልማት ፋይናንስ የሚለው ነው። ከዘላቂ የልማት ፋይናንስ ለማመንጨት አንዱ የተያዘው ስትራቴጂ የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነትን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ያሉ አርብቶ አደሮች እንዲሁም በአርሶአደሩም አካባቢ የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነትን በማጠናከር እዛ አካባቢ ያለው ሰው የሚገለገልበት ማድረግ ነው። ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር በዓመት ከሚጠቀምበት በላይ ቢያመርት የሚያስቀምጠው ጎተራ ውስጥ ነው። የፋይናንስ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ባለመኖሩ አርብቶ አደሩ እንስሳትን በብዛት ይይዛል እንጂ ጥራት ላይ አያተኩርም።
የተወሰነውን መቀነስ ሲኖርበት ያንን አያደርግም። ይህንን በትምህርትም በማሰልጠንም ግንዛቤው እንዲኖረው ማድረግ አለብን። በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማትን ተደራሽነት በማረጋገጥ ቁጠባን እንዲቆጥቡ ማነሳሳት ነው። ይህን በማድረግ የግል ዘርፉ ብድርን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
ሌላው ደግሞ በቅርቡ የጸደቀው የካፒታል ገበያ የመመስረቻ አዋጅ የሚያደርገው ነገር ከዚህ በፊት የፋይናንስ አማራጮች በአገሪቱ በጣም ውስን ነበሩ። በአክሲዮን ገበያ ላይ የአክሲዮን ሼር ሸጦ የሚገኝ በየጊዜው የሚንቀሳቀስ የካፒታል ገበያ አልነበረም። ለምሳሌ ሼር ካምፓኒዎች ሲመሰረቱ ሼራቸውን የሚሸጡት አንዴ ነው። እንደምናውቃቸው እንደምዕራባውያን አገሮች ፈጣን የሆነ የካፒታል ገበያ አልነበረንም፤ አልተመሰረተምም።
ከሶስት ሳምንት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካፒታል ገበያ መመስረቻ አዋጅ ጸድቋል። ይህ ማለት የፋይናንስ ምንጮቻችን ከብድርና ከመሳሰሉት ውስን ከሆኑት ሰፋ እንዲል የማድረግ እድል ይሰጣል ማለት ነው። የትኛውም ካምፓኒ ትንሽም ሆነ ትልቅ ገበያ ላይ እንደማንኛውም ምርት ገበያ ነውና የሚሰራው ገበያ ላይ ሼሩን አቅርቦ ገንዘብ ሊሰበስብ ይችላል። ስለዚህ ትንሽም ብር ያለው ብዙም ብር ያለው ሁሉም ዜጋ እዛ የካፒታል ገበያ ውስጥ መሳተፍ ይችላል። ይሁንና የዚያን ሁሉ የህዝቡን አቅም መጠቀም አንችልም፤ ምክንያቱም የዚያ አይነት ገበያ የለንም።
በተጨማሪም መንግስትም የራሱ የሆነ በልማት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። ምክንያቱም በመሰረተ ልማት ተደራሽነት በኩል አሁንም ድረስ ክፍተት አለ። መንግስት እንደድሮው ብድር የሚበደርበት አካሄድ ሳይሆን የሚኖረው የአገር ውስጥ ገቢን ከፍ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቁጥር ስናየው የአገር
ውስጥ እድገቱ በጣም ብዙ ነው። የሚያመነጨው ገቢ ግን በጣም ትንሽ ነው። ያ ማለት በጣም ብዙ ኢ-መደበኛ ዘርፍ አለ ማለት ነው። በዛ ላይ በጣም ብዙ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች አሉ። በተጨማሪም አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን የሚከፍል ቢሆንም በዛው ልክ ደግሞ ግብር በአግባቡ የማይከፍል አሉ የሚለውን የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ልክ እንኳ ስትታይ በግብር ክፍያው ወደኋላ የምትቀር አገር ናት። ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት 18 በመቶ አካባቢ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ አሁንም 10 በመቶ እና ከዛ በታች ናት። እንዲህም ሆኖ ኢኮኖሚው እያደገ ነው። ነገር ግን የሚያመነጨው ከቀረጥ የሚገኝ ገቢ በዛ ልክ አይደለም። ስለዚህ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት መንግስት የሚያደርገውን የራሱን ኢንቨስትመንቶች ከብድር ይልቅ ዘላቂ ወደሆነው ከአገር ውስጥ ገቢ ከግብር በሚገኙ ገቢዎች ላይ የበለጠ ለመመስረት ነው እቅዱ።በተጨማሪም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም አለ። ከውጭ አገር የሚላኩ ፋይናንሶች አሉ። በእርግጥም ደግሞ ብድርና እርዳታም አለ።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ይገኛል። ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም የራሱ ጉዳት አለውና በአስር ዓመቱ እቅድ ውስጥ ከዚህ አንጻር የታሰቡ ነገሮች ምን ይመስላሉ?
ዶክተር ፍጹም፡– የሰው ሀብት ከተጠቀምንበት ትልቅ አቅም ነው። በዛው ልክ ደግሞ መጠቀም ካልቻልንና አሰልጥነነው የስራ እድል ካልፈጠርንለት ወጣቱ አደጋ የሚሆንበትም እድል ሰፊ ነው። ለአሁኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት እንደ አቅም እንደ ገበያ የምንቆጥረው ሆኖ ነገር ግን ብዙ ስራ ይጠይቃል። ገበያ ሊሆን የሚችለው ገንዘብ አግኝቶ መግዛት ሲችል በመሆኑ ለዛ የስራ እድል መፍጠር መቻል አለብን። ወይም ነግዶ ማትረፍ መቻል አለበት። ይህንን ለማድረግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ኃይል በቂ ስልጠና ሰጥታ ጤናማ እንዲሆን በማድረግ የስራ እድል መፍጠር መቻል አለባት። የስትራቴጂክ አንኳር ጉዳይ ከምንላቸው አንዱ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብና የጋራ የሆነን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚል አለ፤ የጋራ ብልጽግና የሚረጋገጠው የስራ እድልን መፍጠር ሲቻል ነው። እንዲሁም አካታች የሆነ ልማትን ማምጣት ሲቻል ነው። አሁን ያለንን የሰው ኃይል በአግባቡ ወደ ልማት ለመቀየር መንግስት ሚናውን መጫወት መቻል አለበት።
ከዛ በተጨማሪ ግን በቀጣይስ ብለሽ ላነሳሽው ጥያቄ የሕዝብ ቁጥር እድገታችን ከልማታችን ጋር የተመጣጠነ መሆን መቻል አለበት። በእርግጥም ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት በርካታ ስራ ተሰርቷል። ለምሳሌ የአንድ እናት ውልደት መጠን ከነበረበት ሰባት በመቶ አካባቢ ወደ አራት ነጥብ አምስት በመቶ አካባቢ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። አሁንም ግን ብዙ ስራ ይጠይቃል። ከፖሊሲ ጀምሮ ነው ስራ መሰራት ያለበት። የስነ ህዝብ ፖሊሲው በፕላንና ልማት ኮሚሽን እና ከሚመለከታቸው ሌሎች ተዋናይ ጋር ጥናት ተጠንቶ ፖሊሲው መሻሻል አለበት የሚል እይታ መጥቶ በፖሊሲው መሰረት ወደማሻሻል ስራ ገብተናል። ስለዚህም ያለንን የህዝብ መጠን በተሻሻለው ፖሊሲ አማካይነት በደንብ እንድንመራ ያደርገናል። ያለንን የህዝብ ቁጥር መጨመርን ከልማት ጋር ማመጣጠን በሚል እሳቤ ነው የፖሊሲው መሻሻል ያለበት። ባለፉት አስር ዓመታት የስነ ህዝብን ጉዳይ ብዙ ያላነሳነው ቢሆንም ከአሁን በኋላ እንደዛ አድርገን አንዘልቅምና ከልማታችን ጋር የሚጣጣም እንዲሆን እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ይህንን የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን አፈጻጸሙን ለመከታተል የሚያደርገው ጥረት በምን መልኩ ነው?
ዶክተር ፍጹም፡- እቅድ ሙሉ የሚሆነው አፈጻጸሙን የምንከታተልበትና የምንገመግምበት ስርዓት መዘርጋትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ስንችል ነው። ቃል እየገባን ሳንፈጽም ስንቀርና ተጠያቂነት የማይረጋገጥ ከሆነ ጥቅም የለውም። ባለፉት አስር ዓመታት ካየናቸው ድክመቶች ውስጥ አንዱ ይህ ነው። አሁን ግን ይህን ድክመት ይዞ መቀጠል አይቻልም። ኢትዮጵያ ሁሌ እያቀደች የማይሳካላት አገር ሆና መቀጠል አትችልም፤ አይገባትምም።
ህዝቡም ይጠይቃል፤ እኛም መስራት መቻል አለብን። ስለዚህ ያን ለማድረግ እቅዱን ማዘጋጀት ስንጀምር በቅድሚያ የተደረገው ነገር የክትትልና ግምገማ ስርዓታችን ሂደቶችን ከሚለካው አካሄዱ ውጤት ወደሚለካ አካሄድ መሻገር መቻል አለበት፤ ያንን ለማድረግ አንደኛ የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ነበረ። ስለሆነም በ2010 ዓ.ም የጸደቀ የአፈጻጸም፣ ክትትልና ግምገማ መመሪያ አለ። መመሪያው አጠቃላይ ክትትልና ግምገማ ስርዓታችንን ወደውጤት መለካትና ማሻገር የሚችል ነው።
እዛ ውስጥ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሚሰጠው ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት አለ። በዛ ውስጥ ደግሞ በዋናነት የፕላንና ልማት ኮሚሽን ትልቅ ኃላፊነት አለበት። አጠቃላይ የልማት እቅድን መፈጸሙን መከታተል፣ መገምገምና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ለሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን መረጃ የመስጠት ኃላፊነትም አለበት፤ እሱን ለማረጋገጥ ደግሞ እንዳለ የውጤት አመላካቾችን ሂደት ከሚለኩ ውጤት ወደሚለኩ መቀየር አለበት። ከእያንዳንዱ ፈጻሚ ጋር ቁጭ ብለን ተነጋግረን ነው የውጤት አመላካቾቻችንን በአዲስ ያዋቀርናቸው። ስለዚህ ግብርና የሚለካው ማዳበሪያ በማከፋፈል ሳይሆን ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ነው። ማዳበሪያው ለገበሬው ቢደርስም ገበሬው ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነቱ ማደግ መቻል አለበት። የመስኖ ተቋሞቻችን የመስኖ ግድብና ወይም ቦይ በመስራት ሳይሆን አሁንም ያ ውሃ ከመሬት ጋር ተገናኝቶ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ሲያስችል ነው።
መለኪያውን ያዘጋጀነው በዚህ መሰረት ነው። እቅድ ያቀዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተቋማቱ ግቦቻቸውን ያስቀመጡት በውጤት አመላካቾቻቸው ነው። አመላካቾቻቸውን ብቻቸውን አስቀምጠን መተው የለብንም። ቀጥሎ ክትትልና ግምገማው ግለጸኝነትን መፍጠር መቻል አለበት። ህዝብም መረጃ ማየት እንዲችል ዲጂታል የሆነ የቁጥጥርና የሪፖርቲንግ ሲስተም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት ይፋ አድርገናል። በዚህም ሲስተም አንድ መስሪያ ቤት ምን ያህል በመቶ እቅዱን እንዳሳካ እንከታተልበታለን። ይህን አካሄድ ህዝቡም በሚያይበት ሁኔታ የምናከናውነውን ሲስተም ተደራሽ እንዲሆን እየሰራነው ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግምገማ ስርዓቱን የተሻለ የሚያደርጉ ለምሳሌ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለስድስት መስሪያ ቤቶች ነበር ቀደም ሲል ሪፖርት የሚያደርገው። ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለፕላንና ልማት ኮሚሽን፣ ለኦዲተር ጄነራል፣ ለፓርላማ እንዲሁም ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሪፖርት ያደርግ ነበር፤ ይህ ሁሉ ሰው ላይ በየሩብ ዓመቱ ሲሰማ የማይሆን ነገር ይፈጥራል። ሪፖርቱን በየጊዜው ማዘጋጀቱም በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ይህን ሁሉ ወደ አንድ የማምጣት ስራውን ፕላንና ልማት ኮሚሽን አስተባብሮ በዚህ ዓመት ወደ እዛ ሲስተም እየገባ ነው ማለት ይቻላል። ሪፖርቱ ቀላል የሖነ፣ ዘመናዊነትን የሚያረጋገጥና ውጤትን የሚለካ የማድረግ ስርዓትን አብረን እየዘረጋን ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ አሁን ካሉባት ተግዳሮቶች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ የውጭ ንግዱ ከገቢ ጋር ያለመመጣጠን እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የታሰቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ፍጹም፡– እውነት ነው የውጭ ምንዛሬ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ኢትዮጵያ ገና ብዙ ከውጭ ገዝታ የምታስገባቸው ግብዓት አሉ። ወደ አምራች ኢንዱስትሪው እንሸጋገራለን ስንል ገና ነው፤ ከውጭ የምናመጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። በመሆኑም ዶላር ያስፈልገናል። ያንን ለማድረግ እንደ ኤክስፖርት ለረጅም ጊዜ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ነገር ግን በኮቪድ ምክንያት ካልተቀዛቀዙ ነገሮች አንዱ ኤክስፖርታችን ነው። እንዲያውም በዓለም ላይ የየአገራቱ ገበያ በተቀዛቀዘበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከነበሯት አፈጻጸም ሁሉ ከኤክስፖርት አግኝታ የምታውቀውን ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው ትልቁ፤ አሁን በዚህ በኮቪድ ዘመንም ሶስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ችላለች።
ነገር ግን የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ዋናው ነገር የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ለምሳሌ የኢነርጂ ፕሮጀክቶች ከምንላቸው ለአብነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ኃይል ማምረት ጀምሮ አምራች ኢንዱስትሪዎቻችን በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ትርፍ አምርተን ደግሞ መሸጥ እንጀምራለን። ዋናው ነገር የውጭ ምንዛሪ ሸጠን በዘላቂነት የምናመጣው ነው። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ኢነርጂ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምረናል።
የወርቅ ኤክስፖርትም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ማለትም በዚህ ዓመት ብቻ ከ600 በመቶ በላይ ነው ያደገው። አንዱ የሪፎርም ስራ ከተሰራበት ስራ የማዕድን ዘርፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ስለዚህ ይህ ተጠናክሮ ሲቀጥል ሸጠን የምናገኘው ዘላቂ ይሆናል።
ግብርናም እንዲሁ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ለምሳሌ ከውጭ የምናመጣን ስንዴ ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራ በጣም ትልቅና ተዓምራዊ የምንለው ስራ ነው። ከዛ በፊት ቡና ሸጠን የምናገኘውን ዶላር ሁሉ ለስንዴ መግዣ ነበር ስናውለው የነበረው። አሁን በመጪው ዓመት ስንዴ መግዛት እናቆማለን። ሁኔታዎች አልሆን ብለው እንጂ በዚህ ዓመት ራሱ መሳካት እንዲችል ነበር እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው።
ሌሎች የኮንስትራክሽን እቃዎች አገር ውስጥ ማምረት እየቻልን ከውጭ የምንገዛቸው አሉ። ለምሳሌ የፊኒሺንግ ማቴሪያሎች አይነት። የማዳበሪያ ፋብሪኮቻችንም ወደስራ ሲገቡ ማስመጣትን እናቆማለን። ማዳበሪያ ኤክስፖርት ይደረግበት የነበረው ገንዘብ ወደቁጠባ ሲገባ በውጭ ምንዛሬ ላይ ያለው ጫና እየቀነሰ ገቢያችን ደግሞ እየጨመረ ይመጣል። በተጨማሪም ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚመጣ ገቢ በዛው መጠን እያደገ ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡– አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በቀጣዩ አስር ዓመት በምን አግባብ ተግባራዊ ይደረጋል? በምን በምን ጉዳዮችስ ላይ ያተኩራል?
ዶክተር ፍጹም፡– የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሶስት ዓመት መርሃግብር ነው፤ መተግበር ከጀመርን አሁን አንድ ዓመት ተኩል ሆኖናል። ይህ መርሃግብር ከአስር ዓመቱ ጋር ያለው ትስስር ለአስር ዓመቱ እቅድ መሳካት አስፈላጊ የሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። ከምን አኳያ ቢባል የፖሊሲዎችን፣ የህግ ማዕቀፎችን እና የመሳሰሉ ነገሮችን በማሻሻል ማነቆ ሆነው የነበሩ ህጎችንና ያልነበሩን ህጎች በማምጣት በተጨማሪም የማይነበቡ ህጎችን በማሻሻል የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በሩን ክፍት ማድረግ አቅማቸውንም መጠቀም እንዲችሉ የማድረግ ነው።
የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋናነት ሶስት ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፣ አንደኛ ማክሮ የምንለው የገንዘብ ፖሊሲ ፊስካል ፖሊሲዎችን የማሻሻል ነው። አንዱ ለምሳሌ የወርቅ ገቢ በ600 በመቶ የጨመረበት ምክንያት በብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ነው። እሱ አንድ የፖሊሲ ማሻሻያ ነው። ይህ በሌሎችም ዘርፎች እየተደረገ ያለ ነው። የግብርና እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተደርገዋል። ከትራክተሮች ጀምሮ እስከ ወተት ማለቢያዎች ድረስ ድሮ ታክስ ይጣልባቸው ነበር። ይህም ግብርና ትኩረታችን ነው እያልን በሚገቡ አቃዎች ላይ ታክስ የመጣሉ ነገር ትርጉም አይሰጥም ነበር። ለግብርና እና አምራች ናቸው ለምንላቸው ኢንዱስትሪዎች የሚሰጠው ብድር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ለዘርፎቹ ማነቆ የሆኑ ለምሳሌ ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ግብርና ላይ ኩታ ገጠም ስራ መሰራት ትልቅ ማሻሻያ ነው። ቀደም ሲል ለምን አላሰብነውም ነበር በሚል የሚያስቆጭ ስራ ነው በመሰራት ላይ ያለነው። በጥቅሉ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደ እነዚህ አይነት ተግባራትን ሁሉ የያዘ ነው። አሰራሮችን፣ የህግ ማዕቀፎችንና ፖሊሲዎችን ማሻሻልን ይይዛል። እነዚህ ነገሮች ሲሻሻሉ ደግሞ ለአስር ዓመቱ እቅድ መተግበር ምቹ መደላድልን ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡– የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ምን ይሆናል ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር ፍጹም፡– ማክሮ ኢኮኖሚው አሁን ካለበት ሁኔታ አነጻጽሬ ስነግርሽ አሁን ያለበት ሁኔታ በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት በመንግስት ውስጥ ለውጥ ሲደረግ አስፈሪ የነበረ የኢኮኖሚ መዛባቱ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደለየለት ቀውስ ውስጥ ሊከት የሚችል የነበረ ነው። ከዛ በኋላ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች አሁንም ማክሮ ኢኮኖሚውን ወደሚዛናዊነት እና መረጋጋት እንዲመለስ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተዋል። ከዛ ውስጥ የብድር ጫናን መውሰድ እንችላለን። የብድር ጫና ከአገር ውስጥ ምርት አኳያ ስናይ ትልቅ መቀነስ ነው ያሳየው። እሱ ደግሞ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ መረጋጋት መፍጠር የቻለ ነው።
ሌላኛው አሁንም መስራት ያለብን የቤት ስራ ደግሞ የዋጋ ንረት ጉዳይ ነው። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የዋጋ ንረት በአንድ አኃዝ ውስጥ ሆኖ እንዲቀጥልና የተረጋጋ እና ጤናማ የሆነ እንዲሆን ነው ለማድረግ የሚሰራው። ስራ አጥነት በከተማ ውስጥ 18 ነጥብ 7 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ ወደ 9 በመቶና ከዛ በታች እንዲቀንስ ነውና ይህም የማክሮ አንዱ አመላካች ነው። የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን አድጎ መዋቅራዊ ሽግግር ተረጋግጦ አጠቃላይ በአስር ዓመት ውስጥ በምናደርገው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚው በሚረጋገጥበት ሁኔታ እንዲሆን ነው የታቀደው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ፍጹም፡– እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013