ተገኝ ብሩ
“መጎንተል” አሉታዊ ሀሳብ ያለው ቃል ነው፤ ታዲያ ይህ ጉንተላ በአካል ብቻ ሳይሆን በሳይበር ወይም በማህበራዊ ትስስር ገጽ መከሰት ከጀመረ ሰነቧብቷል። ታዲያ በሳይበሩ መንደር ላይ ለክፋት የተሳሉ ፍላጻዎች፤ መልካም ስብዕናን የሚንዱ ውንጀላዎች የሚፈፀሙ ልቅነቶች ይበረክታሉ። ወገን ወደዚህ መንደር ስትገቡ እራሳችሁን ጠብቁ።
እዚያ ስድብ በየዓይነቱ፣ ዘለፋ በብዛት፣ ትችት በገፍ ይቀርባል። በመንደሩ የሚመረመር እውነት የለም። ለሽያጭ የሚሆን ሰዎች በጉጉት ገብተው የሚያነቡት ርዕሰ ጉዳይ ማቅረብ እንጂ በዚያ ምክንያት የሚመጣው ችግር፤ በቀረበው ጉዳይ የሚያስከትለው ጉዳት አይታሰብም።
የሳይበር ገበያው ደርቷል፤ ውሸት ይቸረቸራል። በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚነገር እውነት ትንሽ የሚቀጠፍ ሀሰት ግን በርክቷል። እውነት ይዘው ወደዚያ ከቀረቡ የሚከተሉ ትንሽ የሚሞልጮት ደግሞ ይበረክታል። ወገን ይህን የትስስር ሜዳ መግራት ካልቻልን መንደሩን ለቆ መውጣት ሰላም ይሰጣል ሞክሩት። በትክክለኛ ስብዕና ላይ ለመቆም ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለለመልከት እንድንችል ሳይበር በትክክለኛ መንገድ መጠቀም ግድ ይላል።
ባለፈው አንዱ ወዳጄ በማህበራዊ ትስስር ገጹ “እናቴ እወድሻለው!” የሚል የአድናቆት ቃል ይለጥፋል፤ ታዲያ በዚሁ መንደር ላይ የሚርመሰመሱት እነዚህ የሳይበር ጎንታዮች ምን ለማለት ፈልገህ ነው ከሚለው ጥያቄያቸው እስከ አንተን ብሎ ባለ እናት ይህኔ አቃጠለህ ልደፋት የደረስክ ነህ፣ አስመሳይ … ብቻ ምን አለፋችሁ እስከ ዶቃ ማሰሪያው ነገሩት!
ውሎ አድሮ ሲጣራ የሚያሳፍር እውነቱ ሲታወቅ የሚያስገምት ይሆናል የሚል ግምት በዚህ መንደር ያሉ ነጋዴዎች አያሳስባቸውም። ብቻ በምንም መልኩ የሚቸረችር ጉዳይ ሰዎች ትኩረት የሚሰጡበት አዳንች ነገር ማስተላለፍ እንጂ ውጤቱ አያሳስባቸውም። ሰሞኑ አንዲት አርቲስት በራስዋ ገፅ የለጠፈችው ተበደልኩ የሚል አብግን የሆነ ማስታወቂያ ነበር፤ አይታችሁታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። የለጠፈችው ማስታወቂያ እጅግ አሳፋሪ ነበር፤ ለንግድ በዚህ መጠን ዝቅ ማለት አያስነውርም። የማህበራዊ ትስስር ገጽን ለማስተዋወቅ በዚህ ልክ መውረድ የሚያስነውር ተግባር ነው።
በኢትዮጵያ የፊልም ከፍተኛ ተከፋይ ወንድ ተዋኒያን ቢሆኑም ወንድ ተዋንያን የሴቶቹ ያህል በኑሮዋቸው በምቾት የሚንፈላሰሱ ግን አይደሉም። ለምሳሌ እጅግ ስሙ የገነነና በተመልካች ዘንድ ተቀባይነት ያለው በስራውም አንቱ የተባለ ወንድ ተዋናይ ጠቅሳቹ የሚኖርበትን የኑሮ ሁኔታ ብትጠይቁ ያስደነግጣችኋል። ሴት ተዋንያን የሚለወጡት በሰሩት ፊልምና ማስታወቂያ አይደለም (እንድትረሱ ወገን የማይመለከታት የተከበረች ሴት ተዋናይት እንዳለች አሁንም አልረሳሁም) ማንነታቸውን ሽጠው ባገኙት እውቅና ተጠቅመው የቅንጦት ኑሮን የተቀላቀሉት።
ለዚህ ደግሞ መነሻዬ! የአንዲት ተዋናይ ድርጊት አብሽቆኝ ነው። እውነት የልጅትዋ ተራ የቧልት ቪዲዮ ይሁን እንጂ ኑሮአቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ አሁን ልብ ይባል ሙያውን አክበረው የሚሰሩትን አይመለከትም።
ታዲያ ሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነ አንድ ጉዳይ ላንሳ። አንዲት በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ እየቀረበች ሙያዊ ክብርን ያላገናዘበ ባህላዊ ስርዓትን ያልጠበቀ አለባበስና በድርት (በእኔ አተያይ ለእስዋ ትዕይንት ነው) እና በእንባ ተሞልታ ተበደልኩ ትንኮሳ ተፈፀመብኝ ብላ ምክንያት አልባ ለሆኑ ተከታዮችዋ መልዕክት አስተላለፈች።
ወዲያው ተቀብለው አራገቡላት ትንሽ የነበረው እውቅናዋ በዚህ ምክንያት አልባ በበዛበት ገፅ ላይ ናኘ። እርግጥም የፈለገችው እውቅናን ተላበሰች። ነገር ግን በብዙኋኑ ህዝብ እና ምክንያታዊያን ትዝብት ውስጥ ወደቀች።
የተናገረችው ንግግር ውስጥ ቢቆጠር ከ4 ያላነሱ ትልልቅ ውሸቶች ማውጣት ይቻላል። ዱባይ ላይ ትንኮሳ ተፈፀመብን ባለች በሰዓታት ልዩነት እዚያ ህግ የሚጠብቅበት አገር ላይ ማነው እንዲህ ያረገሽ ተናገሪ ሰውየው ይቀጣ የሚል ጥያቄ ሊቀርብላት መሆኑ ስትረዳ እንዲህ የሆንኩት አገሬ ላይ ነው አለች። የአገርዋን ክብር በሚነካ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ህግ የለም ማንም ምንም ሊያደርግ ይችላል አለች።
በነገራችን ላይ አርቲስተዋ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ እየቀረበች ታስተላልፋቸው የነበሩ መልዕክቶች፤ልቅ በሆነ አለባበስ ለመግለፅ እንኳን በሚያሳፍር አለባበስ የምትፖስታቸው ፎቶዎችዋና የምትሰራቸው ቪዲዮዎች በደለኝ ያለችው ሰው በግድ እንድናገር አደረገኝ ያለችው ቃላት ወይም እዳደርግ አደረገኝ የምትለው ድርጊት በእጥፍ ያለችውን የሚያጥፉ አሳፋሪዎች ናቸው። ስርዓት የቀረባት ሁላ አትመስልም።
ልጅትዋ በራስዋ ገፅ የለጠፈችው አሳፋሪ ቧልቷ በብዙዎች ሲተላለፍ የነበረው ቪዲዮ፤ የሰራችው የገፅዋን ማስተዋወቅ ስራ ነው። ለማትረፍ ብላ የከሰረችበት ከፍ ለመሰኘት አስባ የወደቀችበት ተግባር። በነገራችን ላይ ብዙ አርቲስቶቻችን የበሰለ ምግብ ስለማይበሉ መሰለች ብስል ያ ሀሳብ የማይቀርባቸው። ጥሬ ተው በሉልኝ።
እርግጥ ቀርባ ስትናገር በሰማሁት መሳቅ ብፈልግም የእውነት እንደዚያ የሚደረግ እኮ ሊኖር ይችላል የሚል ሀሳብ ብልጭ አለብኝና ሳቄን አፈንኩት። አቤት ተቀባበሉት የአዛኝ ቅቤ አንጓቾች። ፍላትዋ ስውር ነው። ነገር ግን ንግግርዋ ለማስረዳት የሞከረችው ጉዳይ እውነት አለመሆኑ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ብዙ ብል በወደድኩ ነገር ግን በዚህ መልክ መውረድ ተገቢ አይደለምና መስመር ባትስቱ። ከራሳችሁ ክብር ይልቅ ቤተሰብ ከዝናና እውቅና ይልቅ ህሊና መተዳደሪያችሁ ብታደርጉ ሰላም የበረከተበት ህይወት ወደናንተ ይቀርባልና ኑሮን በትክክል ኑሩ።
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013