አሸብር ኃይሉ
በአለም ላይ የተለያዩ የመንግስት አወቃቀሮች መኖራቸው ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የፌደራላዊ ስርዓት አንዱ ነው ። እንደ ሌሎች የፖለቲካ ጭብጦች ሁሉ ፌደራሊዝም የሚለው ጭብጥ አንድ አይነት ምሁራንን የሚያስማማ ትርጓሜ የለውም። በአለማችን ከሚገኙት ሃገራት መካከል ወደ 60 በመቶ ያክሉ የአህዳዊ መንግስት አወቃቀር እንደሚከተሉ ጥናቶች ያመላክታሉ ።
የአለም ሃገራት ወደ ፌደራላዊ ስርዓት ሲመጡ አብዛኛውን ጊዜ በሁለት መንገዶች አንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። አንደኛው “aggregation” የሚባለው ሲሆን፤ በዚህም እራሳቸውን የቻሉ ሃገራት በመስማማት ወደ አንድ ሀገርነት በሚለወጡበት ሰዓት የሚፈጠር ፌደራሊዝም ነው። ለምሳሌ የታላቋ ብርታኒያ ኮሎኒ የነበሩት የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በስምምነት ዩናይትድ ስቴስ ኦፍ አሜሪካን እንደመሰረቱት አይነት ማለት ነው ።
ሁለተኛው ደግሞ “disaggregation”የ ሚባለው ነው ። ይህ ደግሞ የአንድ ሃገር መጀመሪያ ላይ አሃዳዊ የነበረች እና ማዕከላዊ መንግስቱ በፍላጎት ወይም በሌላ አስገዳጅ ሁኔታዎች ለክልሎች ስልጣን ሊያካፍል በፈለገ ጊዜ የሚፈጠር የፌደራሊዝም አይነት ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ጥሩ ምሳሌ ማንሳት የሚቻለው ምንም እንኳን ትክክለኛ ፌደራሊዝም ባይሆንም የኢህአዴግ መንግስት የማዕከላዊ መንግስት ስልጣኑን ለክልሎች በማካፈል እንደተፈጠረው የፌደራሊዝም አይነት ማለት ነው ።
የፌደራላዊ ስርዓት በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከ18ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የተፈጠረ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ። የእኛ ሃገር ኢትዮጵያም የፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር መከተል ከጀመረች ውላ አድራለች ። የፌደራሊዝም ስርዓት በሃገራችን በአፄ ዮሃንስ አራተኛ መጀመሩን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ እንደ ሃገር የፌደራላዊ አወቃቀር በመርህ የሚመራ እና በመዋቅር ደረጃ ስርዓት ተበጅቶለት የሃገሪቱ የፖለቲካ አምድ ለማድረግ የተሞከረው
በኢህአዴግ መንግስት መሆኑ የሚታወስ ነው ። ነገር ግን በኢህአዴግ የተጀመረው የፌደራላዊ ስርዓት ከፌደራላዊ አወቃቀር መርህ ይልቅ ወደ ኮንፌደሬሽን አወቃቀር መርህ ያዘነበለ ነው። ይህን ስል ዝም ብየ በግብዝነት እንዳልሆነ በአመክንዮ ማየቱ ተገቢ ነው ። ለምሳሌ በሀገሪቱ የሚገኙ የክልል የፀጥታ አካላት ከሃገሪቱ የመከላከያ ሃይል ምናልባትም በትጥቅ ጥራት ያንስ እንደሆን እንጂ በቁጥር ግን የሚበልጥ
ይመስለኛል ። የክልሎች የጸጥታ ሃይል ደግሞ ከማዕከላዊ መንግስት የሚገዳደር ከሆነ የክልል መንግስታት በህገ መንግስቱ ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ በመሻት ውሎ አድሮ ለማዕከላዊ መንግስቱ አልገዛም ላለማለታቸው ምን ማረጋገጫ አለን ? ለምሳሌ በቅርቡ የትግራይ ክልል አስተዳደር የነበረውን የጁንታውን ተግባር ማየቱ በቂ ነው ። ይህ ደግሞ በፌደራላዊ ስርዓት ለምትተደዳር ሃገር ከፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር መርህ ውጭ ነው ።
ሌላው አሁን ያለው የመንግስት አወቃቀር ኮንፌደራለዊ ነው እንድል ያስገደደኝ የክልሎች ህግ መንግስት አፈጣጠር ዜጎችን በደረጃ ለያይቶ የሚያስተዳር አፓርታዳዊ አካሄድ መሆኑ ነው ። ለምሳሌ አሁን ባለው የመንግስት አወቃቀር አንድ የአፋር ክልል ተወላጅ የሆነ ሰው በኦሮሚያ ወይም በአማራ ወይም በሌሎች ክልሎች ሂዶ ለአመራርነት መወዳደር አይችልም ። ለምን? ምክንያቱም የክልሎች ህገ መንግስት ለአመራርነት የሚበቃው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ሳይሆን የክልሉ ተወላጅ የሆነን ብቻ መሆኑን በደማቅ በመፃፉ ነው ። በየትኛው ፌደራሊዝም ስርዓት ነው እንደዚህ አይነት አግላይ እና ከፋፋይ የፌደራሊዝም ያያነው። ምነው ኢትዮጵያ ሌሎች ተሞክሮችን ከውጭ አለማት እንደምትወስድ ሁሉ ይህን ተሞክሮ መውሰድ ተሳናት!?
የአሜሪካን ፌደራሊዝም ስንመለከት አንድ አሜሪካዊ ዜጋ እስከ ሆነ ድረስ የትኛውም የአሜሪካ ግዛት በመሄድ ለአስተዳደርነት መወዳደር ይችላል ። ኸረ እንዴውም ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ የሄዱ ስደተኞች ሁሉ በምርጫ ሲወዳደሩና ሲያሸንፉ ተመልክተናል። የእኛ ሃገር ግን አይደለም ባልተወለድንበት ክልል ለመሪነት መወዳደር ይቅር እና ለመኖርም ተቸግረናል ።
እንደሚታወቀው ኢጋድ፣ ኔቶ ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ አውሮፓ ህብረት ፣ የአረብ ሊግ ወዘተ በአለማችን የሚገኙ የኮንፌደሬሽን ምሳሌዎች ናቸው ። በነዚህም ኮንፌደሬሽኖች ውስጥ የተለያዩ ሃገራት ይገኛሉ። ለምሳሌ ኢጋድን ብንወስድ በውስጡ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ይገኛሉ ። እነኝህ ሃገራት ምንም እንኳን በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አባልነት ስር ይሁኑ እንጂ የጂቡቲ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ሊመረጥ አይችልም። ምክንያቱም ስርዓቱ ኮንፌደራላዊ ስለሆነ። ግን ለምንድን ነው ፌደራላዊ ስርዓት በምትከተለው ኢትዮጵያ የአንድ ክልል ተወላጅ ሌላ ክልል ሂዶ የማያስተዳድረው!? ለምርጫስ የማይወዳደረው !? በኢትዮጵያ በስመ ፌደራላዊ አወቃቀር ስር ሰዶ ያለው የኮንፌደራላዊ አካሄድ እንደኔ የብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ካደረጉ እጅግ አደገኛ የተንኮል መዋቅሮች መካከል አንዱ ይመስለኛል ።
ይህ ስርኣት የፈጠረው የብሄር ፖለቲከኞች አመለካከት ሰፍቶ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሀገር ከማሰብ እና ለሃገር እድገት ከመመራመር ይልቅ በጎሳ ተከፋፍለው እንዲበላሉ በቀላሉ ሊነቀል የማይችል እሾህ የተከለ ይመስለኛል ። በዚህም በሃገሪቱ ያለው ምሁር ተምሮ እና ተመራምሮ በሃገሩ እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መስራት እንዳይችል አድርጓል። በዚህም የተሰላቹት ኢትዮጵያዊያን ሃገራቸው በሌለ አቅሟ ስንት ወጭ አድርጋ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ስንት ችግር የሚፈታ ጭንቅላት እና ጉልበት ይዘው ለውጭ ሀገራት ሲሳይ መሆናቸው አልቀረም ። ይህ ደግሞ በሀገሩ ተስፋ እየቆረጠ ምሁራን እንዲበዙ በማድረግ ቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ጠል እንዲሆን የራሱ አሉታዊ አስተዋፆ ያሳደረ ይመስለኛል። ይህ አካሄድ ሀገርን ጉድጓድ ቆፍሮ እንደመቅበር የሚቆጠር ነው። ስለሆነም መንግስት እና ተወዳደሪ ፓርቲዎች ትክክለኛ የፌደራላዊ አወቃቀር በመመስረት ኢትዮጵያ ችግር ፈች ትወልድ እድትፈጥር የማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
በመጨረሻም ሁሉም ፖለቲከኛ ነኝ ባይ እውነት እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ እና የኢትዮጵያ ህልውና ያሳስበኛል የሚል ከሆነ ከእንደዚህ አይነት የመከፋፈል የጨለማ አዙሪት ውስጥ በመውጣት የሃገሪቱን እድገት እና ብልፅግና እውን ማድረግ ይገባችኋል። ስለሆነም የለውጡ መንግስት እና የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገሪቱን የፖለቲካ አካሄድ የተስተካከለ ለማድረግ ከኮንፌደራላዊ አወቃቀር በማላቀቅ ወደ ፌደራላዊ ስርዓት ለማምጣት መስራት ይጠበቅባችኋል መልዕክቴ ነው። ሰላም !!!
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013