ታምራት ተስፋዬ
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ኢኖቬተሮችን ለማፍራት ያግዝ ዘንድ ያሰናዳው የቅድመ-ኢንኪዩቤሽን ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ተጠናቀዋል። ከረቡዕ ጥር 26 አንስቶ ለስስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዝግጅቱ ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ 26 ኢኖቬተሮች ተሳትፈውበታል።
በመድረኩ የስታርት አፕ እና የኢኖቬሽን ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት አባይነህ፣ ዝግጅቱ የተሳታፊዎችን ክህሎት ለማዳበር፣ ዕውቀትን ለመጨመር፣ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ከጠበቁት በላይ ትልልቅ ሀሳብን ያነገቡ ሆነው እንዳገኟቸውና ከእነርሱም ብዙ መማራቸውን ከቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
‹‹ለኢኖቬሽን ትልቁና አስፈላጊ ጉዳይ ክህሎት እና ትስስር ነው›› ያሉት አቶ በረከት፣ ተሳታፊዎች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመሻገር በይበልጥ ወደ ራሳቸው እንዲመለከቱና ከመደበኛ ትምህርት ባሻገርም በንባብና ሌሎች መንገዶች እራሳቸውን እንዲያበቁ አስገንዝበዋል።
በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለሚዘጋጀውና የሦስት ወራት ቆይታ ለሚኖረው የሙሉ ኢንኪዩቤሽን መርሃ ግብር መሰናዶዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ያስታወቁት አቶ በረከት ይህ ዝግጅትም ለዚህ መንደርደሪያ እንደሚሆን ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ሲያበረክቱ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የተወከሉት አቶ በኃይሉ መልከፃዲቅ በአዕምሮ ንብረት እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ስልጠና ሰጥተዋል። ስልጠናው በምን በምን ጉዳዮች ላይ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ እንደሚደረግ በዝርዝር የተገለፀበት ሲሆን በፓተንት ምዝገባ ረገድም ተሳታፊዎቹ ፈጠራቸውን በፓተንት የማስመዝገባቸው ትልቅ ፋይዳና በምንም መልኩ አስመዝግበው ለፈጠራቸው ጥበቃ ማግኘት እንደሚችሉም አብራርተዋል። ያለ አዕምሮ ንብረት ጥበቃ ፈጠራዎች ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ አፅእኖት የሰጡት አቶ በኃይሉ፣ አስፈላጊውን ነገር ከማሟላትና ፈጠራቸውን ከማስመዝገብ ወደኋላ እንዳይሉ ለፈጠራ ባለሙያዎቹ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ዝግጅቱ የተለያዩ ቁም ነገሮችን ማግኘታቸውን የተናገሩት ተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ዝግጅቱ በተለይም በአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ረገድ ቀድሞ የነበራቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ የለወጠና ጉዳዩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትምህርት የሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013