
በሀገሪቱ አብዛኛዎቹ ቡና አምራች አካባቢዎች በተለይ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና የሚፈለፍሉት በባሕላዊ መንገድ ነው። በድንጋይ በመፍጨት ወይም በሙቀጫ በመውቀጥ እንዲሁም መሬት ላይ በማሸት ቡናውን ከገለባው ይለያሉ። እንደ እዚህ ዓይነቱ ሂደት ብዙ ጊዜን የሚወስድ ከመሆኑም በላይ አድካሚና አሰልቺ ስለሆነ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ሊኖር ግድ ይላል።
በሀገሪቱ ቡና በብዛት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል በዋነኛው ይርጋጨፌ አካባቢ፤ የቡና ማምረት ሂደቱ በተለምዶ አሠራር የሚካሄድ ነው። ይህንን አሠራር የሚያዘምን መፍትሔም ከዚሁ አካባቢ ብቅ ብሏል። ይህንን ችግር በሚገባ ያጠናው የዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ አሰልጣኝ ቸርነት ማሞ፤ የመፍትሔ ሀሳብ ያለውን የደረቅ ቡና መፈልፈያ ቴክኖሎጂ መሥራት ችሏል።
በየጊዜው የሚመለከተው የቡና አመራረት ሂደት በእጅጉ ያሳሰበው አሰልጣኝ ቸርነት፤ ያለውን እውቀትና አቅም ተጠቅሞ ቡናን በዘመናዊ ዘዴ ማምረት የሚያስችል አነስተኛ ማሽን ለመሥራት አቅዶ፤ ሀሳቡን ወደ ተግባር ቀይሮታል።
አሰልጣኝ ቸርነት ቡና መፈልፈያ ማሽን ለመሥራት ሀሳብ ስለመጣላት ብቻ በቀጥታ ማሽን ወደ መሥራት አልገባም። ይልቁንም የሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ቡና በማምረት የሚታወቁ ሀገራትን ተሞክሮ ለመውሰድ መረጃ ማሰባሰብ ጀመረ። ብራዚልንና ቻይና የሚጠቀሙባቸውን ማሽኖች በመመልከት ተሞክሮ ለመውሰድ ጥረት አደረገ፡፡
ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከእነዚህ ሁለት ሀገራት መጥተው ሀገር ውስጥ የሚገቡት ማሽኖች በጣም ትልልቅና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ መረዳት ቻለ። ዋጋቸውም እንዲሁ ከሁለት ሚሊዮን ብር እስከ አራት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መሆናቸውን ተረዳ። ይህንን ካወቀ በኋላ ከውጭ የሚመጣውን ማሽን በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት እንደሚቻል በመረዳት ወደ ሥራ ገባ።
በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት በሀገር ውስጥ ተሠርቶ በቀላሉ ሕብረተሰቡ ሊጠቀምበት የሚችል ማሽን መሥራት እንዳለበት ወስኖ ሥራውን ጀመረ። ያሰበው እውን ሆኖ የፈለገውን አይነት ማሽን መሥራት ቻለ። ማሽኑ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ አነስተኛ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ በመሥራት በቀላሉ ቡና መፈልፈል የሚያስችል ነው፡፡
አሰልጣኝ ቸርነት ማሽን ለመሥራት ሙከራ ሲያደርግ መጀመሪያ ላይ የተመለከተው ከኢጣሊያን የመጣውን ስለነበረ የእነርሱን አይነት ማሽን መሥራት መቻሉን ይገልጻል። ይህ ለሙከራ የሠራው ማሽን ቡናን እየፈለፈለ ከነ ገለባው የሚያወጣ ነበር። ቡናውንና ገለባው ለየብቻ የሚለይ አልነበረም። ገለባውን ከቡና ለመለየትም ሌላ ማጣራት ሥራ ወይም ማሽን ያስፈልግ ነበር። ይህንን መነሻ በማድረግ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ የሌሎች ሀገራትን ማሽንንም ሲመለከት ውጫዊ ክፍሎችን እንጂ ውስጣዊ ክፍሎች ማየት ስላልቻለ ውጪያዊውን መሠረት አድርጎ ውስጣዊ ክፍሉን በራሱ እሳቤና እይታ ለመሥራት መንቀሳቀስ ጀመረ። በየጊዜው ከሚያየው ነገር በመነሳትም እያሻሻለ ሁለቱንም ተግባራት በአንድ ጊዜ መሥራት የሚችል ማሽን ለመፈብረክ በቃ። አዲሱ ማሽን ቡናውን ከገለባው ለየብቻ እየለየ የሚያወጣ ነው።
‹‹ተማሪ ሆኜ ጀምሮ የፈጠራ ሀሳብ ተሰጥኦ እንዳለኝ አውቃለሁ›› የሚለው ቸርነት በተለይ ሀሳቡን ከንግግር ይልቅ በተግባር መግለጽ እንደሚቀናው ይናገራል። አንድ ነገር በተግባር ለመግለጽ ሲያሰብ ደግሞ የፈጠራ ሀሳቦች እንደሚፈልቁለት ይገልጻል። ማሽኑን አስመስሎ ለመሥራት ሲታሰብ ውጫዊ ክፍሎቹን ብቻ በማየት መሥራት እጅግ አዳጋች ነው። አሰልጣኝ ቸርነት ግን በቻይና የተሠሩ ማሽኖችን ውስጣዊ ክፍሎች ሳይመለከት ውጫዊውን አካል በመመልከት ብቻ የውስጡን በራሱ ፈጠራ መሥራት መቻሉን አመላክቷል፡፡
አሰልጣኝ ቸርነት እንዳብራራው፤ ከውጭ የሚገባ ማሽን የአምስት ፈረስ ጉልበት አቅም አለው። በሰዓት እስከ 400 ኪሎ ግራም ቡና ይፈለፍላል። በሀገር ውስጥ የተሠራ አዲሱ ማሽን ግን በሦስት የፈረስ ጉልበት በሰዓት ከ200 እስከ 250 ኪሎ ግራም ቡና ይፈለፍላል። ቡናው ደረቅ ከሆነ ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ግራም ይፈለፍላል። ማሽኑ ቡናን ሲፈለፍል ቡናውና ገለባውን ለየብቻ ይለያል፤ የተፈለፈለው ንጹህ ቡና በአንድ በኩል ሲወጣ፤ ገለባው በሌላ በኩል እንዲወጣ ያደርጋል፡፡
ማሽኑ ቡናውን እንዲፈለፈል ሲደረግ ያልደረስ ቡና ብቻ ከውስጡ መልቀም እንደሚያስፈልግ ገልጾ፤ ያልደረሰው ቡና ከተለቀመ ሌላ ምንም አይነት ሂደት ሳያስፈልገው ቡናውን ደረጃውን ጠብቆ ለመፈልፈል ያስችላል፡፡
ቡና ከተፈለፈለ በኋላ ገለባው ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላል። ገለባውን አንዳንድ አካባቢዎች ልክ እንደ ቡና አፍልቶ ለመጠጣት ይጠቀሙበታል። ሌሎች ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ‹‹ለአብነት እኛ አካባቢ በተለይ የስፔሻል ቡና (የእሸት፤ የቀላው) ገለባ ተሰብሰቦ ለመጠጥ ይውላል›› የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ የቡና ገለባ ለኮምፖስትና ለከሰል አገልግሎት የሚውልበትም አካባቢ አለ። በመሆኑም ቡናው ከተፈለፈለ በኋላ የስፔሻል የቡና ገለባ ከሆነ ለመጠጥነት ይከማቻል፤ በተለምዶ የሚታወቀው የኖርማል ቡና ገለባ ሆኖ መሬት ላይ የሚነጠፈው ከሆነ ደግሞ ኮምፖስትና ለከሰል ማምረቻነት እንዲውል ይደረጋል ሲል አስረድቷል፡፡
ማሽኑ በቀላሉ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተሠራ መሆኑን የሚናገረው አሰልጣኝ ቸርነት። ማሽኑ ከተገጠመለት ኩሽኔታና ዲናሞ በስተቀር የተቀሩት አካባቢያችን ካሉ ቁሳቁሶች የተመረተው ነው። አሰልጣኝ ቸርነትም አሮጌ ላሜራዎችንም በመሰብሰብ ቀጥቅጦ ማሽኑን መሥራቱ ገልጾ፤ ማሽኑን በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲያመች አልሙኒየም ማቅለጫ በራሱ ሰርቶ እንደሚጠቀምም ይገልጻል፡፡
ማሽኑን ለመሥራት ብዙ ሙከራዎችና ልምምዶችን እያደረገ በስተመጨረሻም ይሄንኛውን ማሽን መሥራቱን አጫውቶናል። ‹‹ይህ የፈጠራ ሥራ የመጀመሪያዬ አይደለም፤ ማሽኑን በተለያዩ ጊዜያት እያሻሻልኩ ሠርቻለሁ ብዙ ልምድም አካብቻለሁ፤ ከዚህ ቀደም 20 ማሽኖችን ሰርቼ ዲላና አርባምንጭ አካባቢ እያንዳንዱን በ153ሺ ብር ሸጫለሁ›› የሚለው አሠልጣኝ ቸርነት፤ ይሄኛው ማሽን ልምድ ያካበተበት በመሆኑ ለመሥራት ብዙ ጊዜ እንዳልወሰደበት ይናገራል። እንደዚህ አይነቱን ማሽን ለመሥራት በሙሉ ጊዜ ተጠቅሞ ከተሠራ በሁለት ሳምንት ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ጠቁሟል።
አሠልጣኝ ቸርነት እንዳብራራው፤ ማሽኑን ባለሦስት፣ ባለ አራት፣ ባለ አምስት እና እስከ ሰባት ነጥብ አምስት የፈረስ ጉልበት እንዲኖረው ተደርጎ መሥራት ይቻላል። ማሽኑ ለመኖሪያ ቤት በሚያገለግለው ነጠላ ፌዝ የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም የሚሠራ ነው። ሦስት የፈረስ ጉልበት ያለው ማሽን 200 እስከ 250 ኪሎ ግራም ቡና መፈልፈል ያስችላል። አራት የፈረስ ጉልበት እንዲኖረው ከተደረገ 250 እስከ 300 ኪሎ ግራም ቡና የሚፈለፍል ሲሆን አምስት ነጥብ አምስት የፈረስ ጉልበት እንዲኖረው ከተደረገ ደግሞ ከ350 ኪሎ ግራም ቡና በላይ መፈልፈል ይችላል። ማሽኑ ሲሠራ በሚፈለፍለው ቡና በመጠን የውስጣዊ ክፍሎች እና የጉልበት መጠኑን በመጨመርና በመቀነስ በዲናሞውም መጠን በዚያው ልክ እንዲሰፋ መደረግ እንደሚቻል ተናግሯል።
ከውጭ የሚገባው ማሽን ትልቅና ቁመቱ እስከ ሦስት ሜትር የሚደርስ ነው። በዚህም በጣም ግዙፍ እና ለማንሳት በእጅጉ የሚከብድ እና ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቃስ ማንሻ ይፈልጋል። የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት «እኔ ባመረትኩት ማሽን መጠን ከውጪ የመጣ እስካሁን አላየሁም። ይሄ ማሽን በመጠን አነስተኛ ሆኖ ከውጭ ከሚገቡ ማሽኖች ያልተናነስ የሚሠራ ነው። መጠኑም ሜትር ከ50 በሜትር ከ50 የሆነ አነስተኛ መጠን ያለው ሲሆን፤ 200 እስከ 250 ኪሎ ግራም ክብደት ያለውና ሰፊ ቦታ የማይፈልግ በመሆኑ በተፈለገው ቦታ እንደልብ ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ተናግሯል።
ማሽኑ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ነው የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ ቡና ማሳዎች ያሉበት በገጠራማ አካባቢ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው አካባቢ የመብራት ኃይል ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል። በተለይ ጌዲዮ ዞን አብዛኛው አካባቢዎች የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል። የመብራት ኃይል በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በጀነሬተር እንዲሠራ ማድረግ ይቻላል። ለአብነትም መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች ለባለ ሦስት የፈረስ ጉልበት ማሽን አራት ኪሎ ዋት ጀነሬተር ቢገዛለት በጀነሬተሩ ኃይል መንቀሳቀስ ይችላል። ለአራት ኪሎዋት ጀነሬተር ለመጠቀም ዋጋውም ብዙ የሚባል አይደለም ሲል ያስረዳል።
ቀደም ሲል የሠራኋቸው ማሽኖች 90 በመቶ ያህሉ በይርጋጨፌ አካባቢ ተደራሽ ተደርገዋል የሚለው አሰልጣኙ፤ እዚያ አካባቢ ያሉ ተጠቃሚዎችም ማሽኑን እየተጠቀሙበት ይገኛል። ተጠቃሚዎቹ ‹ማሽኑ በተባለው መጠን አገልግሎት እየሰጠ መሆንና ቡና ሲፈለፍልም ሳይሰባበር ቡናና ገለባውን በትክክል እንደሚለይ፣ የቡናን ጥራትና ጣዕም እንዳይበላሽ የሚያደርግ ጥራት ያለው ማሽን ነው› በማለት በተለያዩ ጊዜያት ከሚሰጧቸው ግብረ መልሶች በብዙ መልኩ እንደጠቀማቸው መረዳት መቻሉን ይገልጻል፡፡
ይህ ማሽን በአንድ ጊዜ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሳይሆን በየጊዜው እየተሻሻለ አሁን ያለበት ደረጃ መድረስ ችሏል። ለቀጣይም እንደገና መሻሻል ያለበትን ነገር ሁሉ በማሻሻል ላቅ ያለ ደረጃ እንዲደርስ አድርገዋለሁ የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ ‹‹በቀጣይም ማሽኑን አውቶማቲክ እንዲሆን በማድረግ ያለሰው በራሱ ሁሉንም ነገር እንዲያከናውን ለማድረግ አቅጃለሁ›› ብሏል። በተጨማሪ ከዚህ ማሽን ባሻገር ሌሎች ለሌላ አገልግሎት የሚውሉ ማሽኖችን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቋል። ‹‹በተለይ ቀደም ብዬ ለመሥራት ሞክሬ ሳይሳካልኝ ቀርቶ ተስፋ ቆርጬ የተውኩትን ማሽን በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስትቲዮት ተሰርቶ በማየቴ በድጋሚ እንደሞክረውና የተሻለ አድርጌ መሥራት እንደሚችል መነሳሳትን ፈጥሮብኛል። አሁን ለይ ማሽኑን ለመሥራት በራስ መተማመኔ ጨምሮ እንደምሰራውም እርግጠኛ ሆኛለሁ ›› ብሏል።
አሰልጣኙ እንዳብራራው፤ የቡና መፈልፈያ ማሽኑ ዋጋው ተመጣጣኝና የመግዛት አቅምን ያገናዘበ ከመሆኑም በላይ በትንሽ ሰዓት ብዙ ቡና በጥንቃቄ የሚፈለፍል ነው። በየቡና መፈልፈል አገልግሎት የሚሰጡ ከውጪ የሚገቡ ማሽኖችን የሚያስቀር ነው። ይህን በማሻሻልና በማሳደግ አውቶማቲክ ሆኖ ለቡና አምራቾች ተደራሽ ቢደረግ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ካማሟላትም ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎትም እንዳለው ጠቁሟል።
ማሽኑ ከውጪ ከምናስገባቸው ማሽኖች የበለጠ ጠቀሜታ ስላለው ከውጭ የሚገባውን በማስቀረት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት በሀገር ውስጥ የተመረተውን ምርት ልንጠቀም ይገባል፤ የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ ቡና አምራቾች ይህንን ማሽን ገዝተው ተጠቅመው ራሳቸውንም ሆነ ለሀገራቸው ጠቅመው በሀገራቸው ምርት ሊኮሩ ይገባል ሲልም አስገንዝቧል።
‹‹በውስጤ ገና ብዙ ያላወጣኋቸው የፈጠራ ሀሳቦች አሉኝ፤ የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንዳልተገብራቸው የሚገደብኝ ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ የሚፈልገው ጥግ እስክደርስ የማደርገውን ጥረት አላቋርጥም›› የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ አሰልጣኝ በመሆኑ ለተማሪዎች በብዙ መልኩ አርአያ የሆኑ ተግባራት ለመሥራት ሙያዊ ግዴታ እንዳለበት ይገልጻል። ‹‹የፈጠራ ሀሳቡ ያላቸው ተማሪዎች ውስጣቸው ያለውን ሀሳብ እንዲያወጡ አበረታታቸዋለሁ። ውስጣቸው ያለው ሀሳብ ለብዙዎች የሚተርፍ ሀሳብ ሊሆን ስለሚችል አውጥተው ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት ልክ ሀሳባቸው እውን እንዲያደርጉ እመክራለሁ›› ብሏል፡፡
በተለይ ወጣቶች ለቴክኖሎጂ ቅርብ እንደመሆናቸው መጠን የሕብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የፈጠራ ሀሳቦች ሊያፈልቁ ይገባል። የሚለው አሰልጣኝ ቸርነት፤ ሀሳብ ማፍለቅ ብቻ ሳይሆን ሀሳባቸው እውን እስኪሆን ድረስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙ ወጣውረድ ውስጥ ሊገጥማቸው እንደሚችል በማመን የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁሞ፤ «ከሁሉ በላይ እራሳችሁ የምታደርጉት ጥረትና ትግል ወደምታስቡት መንገድ ያደርሳችኋል» ሲልም የምክረ ሀሳቡን ለግሷል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም