ለምለም መንግሥቱ
መሬት ላይ ያረፈና ግቢ ያለው የመኖሪያ ቤት መመኘት ለብዙዎች ምርጫቸው ነው። ለዚህ ከሚሰጡ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም በእርጅና ዘመን አለያም በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ የአካል ጉዳት ቢያጋጥምና የአካል ድጋፍ ቢያሥፈልግ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዲሆን የሚለው አይታሰብም። ነገር ግን ከቤተሰብ አባል በአንዱ ላይ የአካል ጉዳት ሊከሰትና የአካል ድጋፍ መጠቀም ግድ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ወደላይ እንጂ ወደ ጎን ግንባታ እየቀነሰ በመጣበት፣ መኖሪያ ቤትም ሆነ የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ረጃጅም ፎቆች በሆነበት በዚህ ጊዜ ደግሞ ለአካል ድጋፍ መወጣጫ ደረጃ (ራፕ) ከህንፃ ግንባታው ጋር ታሳቢ ተደርጎ መገንባት ግድ ይላል። የጋራ መኖሪያ ቤት ለመግዛትም ሲታሰብ እንደዚሁ ለአካል ጉዳተኞች መወጣጫ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላል።
የመወጣጫ ደረጃ አሥፈላጊነት በሀገሪቷ የህንፃ አዋጅ ህግ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። ነገር ግን አስፈፃሚው አካል መንግሥት እራሱ ህጉን እየተገበረው አይደለም። ለአብነትም በሺዎች የሚቆጠር የጋራ መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለዜጎች እያስተላለፈ ቢገኝም አንዳቸውም የአካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ መወጣጫ የላቸውም። ይብሱንም ደረጃ ያልተሠራላቸውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመታዘብ ይቻላል። የግንባታ ሥራውን በወሰደው ተቋራጭ በጎ ፈቃድ ተሟልቶ ተሠርቶ እንደሆን እንጂ ተከታትሎ መሟላቱን ያረጋገጠ አካል እንዳልነበር ማሳያ ነው።
የአካል ጉዳተኞች መወጣጫን በተመለከተ ህጉን ያወጣው መንግሥት ካልተገበረ በግል ተሠርተው ለሽያጭ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶች አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ አድርገው ባይሠሩ አይገርምም። የአገልግሎት መስጫዎችም ቢሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ካልሆኑ በስተቀር የደንበኞቻቸውን ምቾት የጠበቁ አይደሉም። ብዛት ያላቸው አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በኪራይ ቤት ውስጥ የሚሠሩ በመሆናቸው አማራጭ ያላቸው አይመስሉም። ችግሩን በተደጋጋሚ ከማንሳት ያለፈ መፍትሄ እንዲያገኝ አለመደረጉ ደግሞ ነገሩን አባብሶታል። አልፎ አልፎ የተገነቡትም ቢሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው የበለጠ ለጉዳት አጋላጭ በመሆናቸው ቅሬታ ይቀርብባቸዋል። ህንፃውን ለመገንባት የወሰደው አካል ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ተከትሎ ለምን እንደማይሠራ ምክንያቱ ግራ ያጋባል። እርሱም የማህበረሰቡ አካል ከመሆኑ በተጨማሪ ለአካል ጉዳትም ተጋላጭ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። መልካም ሥም ከመቃብር በላይ ይውላል እንደሚባለው የሚያስመሰግን ጥሩ ነገር ሠርቶ ማለፍ በግል ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም የሚያኮራ ተግባር መሆኑ በግዴለሽነት ካልተወሰደ በስተቀር ማንም አይጠፋውም።
‹‹ማን ያርዳ የነበረ፣ ማን ይናገር የቀበረ›› እንደሚባለው በየቀኑ የሚፈተኑት በአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እነዚህ ክፍተቶች ለሚያስከትሉት ጉዳት እማኞች ናቸው። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ጉዳዩን በምሬት ያነሳሉ። በሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞች የህንፃ ተደራሽነት አዋጅ ወጥቷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ ህንፃና መንገድ ለመገንባት የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነት ፈርማ ወደ ሥራ ከገባች ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚሁ መሠረት በአዋጁ ሦስተኛና ከዚያ በላይ የሆኑ ህንፃዎች መወጣጫና አሳንሰር እንዲኖራቸው ይደነግጋል። ህንፃ በስፋት በሚገነባበትና የሀገሪቱ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ግን ይህ እየሆነ አይደለም። በመንግሥት ተገንብተው ለዜጎች በመተላለፍ ላይ ያሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ። እንደ ዓለም አቀፍ ሆቴል ቤቶች ያሉ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር አብዛኞቹ የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡም ለአካል ጉዳተኛው ተደራሽ አይደሉም። የተሠሩትም በቁጥር ከሚጠቀሱት በስተቀር ከፍታ ያላቸውና የሚያንሸራትት ሴራሚክ የለበሱ በመሆናቸው ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል።
ማህበሩ ችግሩን በተደጋጋሚ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብና ማህበራቸው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በተለያየ መድረክ ላይም በመገኘት ችግሩን ቢያሳውቅም ከንግግር ባለፈ ወደ ተግባር የተለወጠ ነገር አለመኖሩን አቶ አባይነህ ያስረዳሉ። ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ፍቃደኝነቱ አለ ብለውም እንደማያምኑ በተስፋ መቁረጥ ነው የገለጹት።
ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነም አቶ አባይ ሲያስረዱ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም 18 ሚሊየን የሚሆን አካል ጉዳተኛ እንደሚኖር ይገመታል። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የአካል ድጋፍ የሚያሥፈልጋቸው የሚታይ (ፊዚካል) አካል ጉዳተኞች ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ እንዲሁም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግሮች ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። ጉዳቱን መቀነስ ባይቻል እንኳን ለተጎጂዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኮንሥትራክሽን ኮንትራክተር ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚደንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማርያም የማህበሩን ቅሬታ ይጋራሉ። በተለያየ መድረክ ሲገናኙ የሚያነሱት እንደሆነም ተናግረዋል። ችግሩ ከዲዛይን (ንድፍ) ይጀምራል ይላሉ። ንድፉን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። እርሳቸው እንዳሉት በመንግሥትም ሆነ በግል የሚገነቡ በአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ ተግባር እያከናወኑ እንዳልሆነ የተሠሩትም ቢሆኑ የአካል ጉዳት ለሌለባቸውም የሚሆን እንዳልሆነ ታዝበዋል። አካል ጉዳተኞቹ በራሳቸው የአካል ድጋፋቸውን እየገፉ መሄድ ሲገባቸው የሚያግዛቸው ሰው ሊያሥፈልጋቸው ነው። ሰው የሚረዳቸው ከሆነ መወጣጫውን መገንባት አያሥፈልግም። በተሠራው መወጣጫ ላይ የሚያንሸራትት ግብዓት መጠቀም ደግሞ ተጎጂው ለተጨማሪ ጉዳት እንዲጋለጥ ማድረግ በመሆኑ ያለዕውቀት የሚሠራው ሥራ መቆም ይኖርበታል።
እንደማህበርም እንደ ባለሙያም ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ሲሠራ እንዴት እየታየ ነው? ለሚለው ጥያቄም ኢንጂነር ግርማ ‹‹እውነት ለመናገር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በማህበር ደረጃ አንስተን ከአባላቶቻችን ጋር ተወያይተን አናውቅም። ማህበሩ የሥነ ምግባር መመሪያ አለው። ሙያውን ያገናዘበ ሥራ ላይ ነው ትኩረቱ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። አንድ ተቋራጭ በዲዛይኑ መሠረት ኃላፊነቱን ሳይወጣ ሥራውን ቢያስረክብ እንኳን እስከ አሥር ዓመት ድረስ የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበትም አመልክተዋል። ተቋራጩ በቅድመ ንድፉ ላይ አስተያየት መሥጠት እንዳለበትና ይህንኑ የሚያረጋግጥ ባለሙያ ሊኖረው እንደሚገባ በህግ የተቀመጠ መመሪያ መኖሩን ያስታወሱት ኢንጂነር ግርማ ነገር ግን ንድፍ የሚያወጣውም ሆነ ተቋራጩ የሚጠበቅባቸውን የየራሳቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸውና ግዴለሽነትም በመኖሩ የሚፈጠር ችግር እንደሆነ አስረድተዋል። እርሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ የግንባታ ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ሥራው ቀሏል። እንደርሳቸው ገለፃ አሠሪው አካልም ህግ የሚፈቅድለትን መብት ተጠቅሞ እንዲስተካከል በማድረግ ላይም ክፍተት ይታያል።
መፍትሄዎችን ከማምጣት ይልቅ ችግሮች ላይ ብቻ ማተኮሩ ምን ያህል ያስኬዳል ለሚለው ጥያቄም ኢንጂነር ግርማ በሰጡት ምላሽ በግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋለው ችግር የቆየና በመንግሥትም ይታወቃል። ችግሩ የመፍትሄ እርምጃ ላይ ነው። አሁንም ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ መሥጠት ከመንግሥት ይጠበቃል። በዘርፉ ውስጥ ያለውም ቢሆን የመፍትሄው አካል መሆን ይኖርበታል።
በአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በተመለከተ በህንፃ አዋጁ ላይ በግልጽ መቀመጡን የተናገሩት ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት በፌዴራል ኮንሥትራክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን የህንፃ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት ተዘራ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት የአካል ድጋፍ ለሚጠቀሙ ወገኖች የሚውለውን መወጣጫ (ራፕ) ብቻ ሳይሆን በህንጻዎች ውስጥ የሚገጠሙት አሳንሰሮች ዓይነሥውራንን ታሳቢ ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል። እነርሱ የሚጠቀሙበት የብሬል ምልክትና ድምጽ አብሮ እንዲኖረው በማድረግ ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ እንደሀገር የቤቶች ልማትም ሆነ በሌሎች ግንባታዎች ላይ እነዚህ ነገሮች ታሳቢ ተደርገው እየተሰሩ አለመሆናቸው እየተነሱ ያሉት ችግሮች ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ተቋማቸው ከተቋቋመ ገና የሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ባከናወነው ተግባር ትልቁ ክፍተት የህንፃ አዋጁን በትክክል ካለመተግበር የመነጨ መሆኑን ደርሶበታል። የትኛውም የህንፃ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በህንፃ አዋጅ ሹሞች ውስጥ አልፈው መጽደቅ አለባቸው። በዚህ ሂደት ታሳቢ መሆን ያለበት የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ አንዱ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ተቋማቸው በሁለት ዓመት ቆይታው 63 የተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ቁጥጥር አድርጓል። ከቁጥጥር ሥራዎች አንዱ የሚገነቡ ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ወይም ተደራሽ ያደረጉ መሆናቸውን የመለየት ሥራ ነው። ክትትል ከተደረገባቸውም የተወሰኑት መወጣጫ ሠርተዋል፤ የተወሰኑት ደግሞ አልሰሩም። ተቋሙ ከለያቸው መካከልም የዲዛይን ማስተካከያ የተሠራላቸውም ይገኙበታል። ያልጸደቁ ግንባታዎች ግን የአካል ድጋፍ ለሚጠቀሙ መወጣጫ በግንባታው ውስጥ ማካተታቸው ተረጋግጦ ነው ፍቃድ የሚሰጣቸው።
እንደ አቶ በረከት ገለፃ ቀድመው መወጣጫ ከህንፃው ጋር ያልሠሩ ቢኖሩም ማስተካከል የሚቻልበት ዕድል ዝግ አይደለም። ለአብነትም የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት በመግቢያ በሩ ላይ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ ግን ተቋማቸው በሰጠው ጥቆማ እንዲስተካከል ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። ስለዚህ ህንፃው ተሠርቶ ቢጠናቀቅም እንደገና ለማረም የሚከለክል ነገር የለም። ግን የአቅም ጉዳይ ወሳኝ ነው። ተቋሙ መልሶ ለማረም የወጭ አቅም ከሌለው በሚፈለገው ፍጥነት ሊታረምና ሊጓተት ይችላል።
በጥራት ወይንም ደረጃውን ጠብቆ አለማከናወን ጉዳይ ላይም ለተነሳው ቅሬታ አግባብ እንደሆነ ያወሱት አቶ በረከት በሀገር አቀፍና በዓለምአቀፍ የተቀመጠውን የግንባታ መሥፈርት አሟልቶ መተግበር ግድ ነው። ተጠቃሚው በቀላሉ የአካል ድጋፉን ካልተጠቀመበት ግንባታው መኖሩ ህንፃው አሟልቷል ለማለት አያስችለውም። ተቋማቸው ጥራቱንም በመቆጣጠር ችግሩን መቅረፍ አንዱ ተልዕኮው ነው። በእርሳቸው እምነት ብዙዎች ትኩረት ያልሰጡት በህንጻ አዋጁ ላይ መቀጮ ቢኖርም የገንዘቡ መጠን አነስተኛ በመሆኑ አስተማሪ አይደለም። ያም ቢሆን እየተተገበረ አይደለም። በመሆኑም ክፍተት ተፈጥሯል።
ተቋማቸው ከጥር አጋማሽ ጀምሮ በስድስት ከተሞች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ ግንዛቤ በመፍጠር የንቅናቄ መድረክ ላይ በግንባታ ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ክፍተቶች ይዳሰሳሉ።
ክፍተቱ የበዛ ቢሆንም በመልካም የሚነሱ መኖራቸውን አቶ በረከት ይጠቅሳሉ። ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የአካል ድጋፍ ለሚጠቀሙ ዜጎች የሚሆን መወጣጫ (ራፕ) በጥሩ ሁኔታ በመሥራት ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታልን፣ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ደግሞ የአፄዮሃንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጠቅሰዋል።
ተቋሙ እያካሄደ ባለው የንቅናቄ መድረክና በያዘው ዕቅድ በቀጣይ የተሻለ ሥራ የሚጠበቅ ቢሆንም እስካሁን የህንፃ አዋጁን መሰረት አድርገው አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ባላደረገ መልኩ የተከናወኑት የህንፃ ሥራዎች ሊታረሙ የሚችሉበት ዕድል ስለመኖሩ አቶ በረከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከአንደኛ ፎቅ በላይ እንደቦታቸው ሁኔታ ነው የሚወሰነው። ያም ሆኖ ግን የሚስተካከልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል እንደባለሙያ ይገመታል። ህንፃውን ከገነቡት ጋር በመመካከር ነገሮች የሚመቻቹበትን በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013