ኸይረናስ አብደላ (ሳይኮሎጂስት)
ክፍል ሁለት
ባለፈው ሳምንት በኦቲዝምና በአዕምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ መክረናል። በዛሬው ዕትማችን ደግሞ በሁለቱ መካከል ስላለው ልዩነት በተመለከተ እንዳስሳለን።
በአዕምሮ እድገት ውስንነት እና በኦቲዝም መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድ ሰው ላይ በአንድ ጊዜ ሊከሰቱ እንደሚችሉ መረዳት በጤናው ዘርፍ እና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ በላቀ እና ሰፋ ባለ መልኩ ልዩነታቸውን መረዳት የተሳሳቱ አመለካከቶችን እና ማግለልን ለመቀነስ ያግዛል፤ ይልቁንም በይበልጥ ትኩረታችንን እንዴት ልዩ የሆነውን ፍላጎታችውን ተረድተን ማገዝ እንችላለን የሚለው ላይ ተኩረት እንድናደርግ ያስችለናል።
የሁለቱን ልዩነት ግልጽ ለማድረግ ያህል በተደጋጋሚ የምንጠቀማቸውን ቃላት እንመልከት
1.የአዕምሮ ብስለት/ልህቀት(Intellectual Ability)፡-የአንድን ሰው የመማር፤ የማመዛዘን፤ ችግር የመፍታት፤ የማቀድ፤ የማይዳሰሱ ነገሮችን የማሰብ እና የተማሩትን ነገር ማስተላለፍ (ይዞ ማቆየት) የመሳሰሉትን የሚያመላክት ነው።
2.የመልመድ ብቃት (Adaptive Ability)፡- ይህ ደግሞ ክህሎት ሲሆን፤ እራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ እንደ ተግባቦት፤ እራስን ማገዝ፤ እና ማህበራዊ ክህሎቶችን የሚገልጽ ነው።
“ብስለት/ልህቀት” (Intelligence)፡- አንድን ነገር የመማር እና ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በአንድ ሰው የህይወት ቆይታ ተለዋዋጭ አይደለም ተብሎ ይታሰባል።
“እድገት” (Developmental)- ተለዋዋጭ የሆነ የሕፃን ወይም የአዋቂ የዕድገት ሂደትን የሚያሳይ ነው።
በኦቲዝም እና በአዕምሮ እድገት ወስንነት መካከል ያሉ መሰረታዊ ልዩነቶች
- የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው (ቀደም ብለን የአዕምሮ ብስለታቸው ሰባ እና ከዚያ በታች የሆኑ ብለን የገለጽናቸው) የአዕምሮ ብቃት እና የመልመድ ብቃት ላይ ተግዳሮት ሲኖራቸው፤ ኦትስቲክ ልጆች ግን በዚህ ረገድ ያለባችው ተግዳሮት እምብዛም ነው።
- የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያላችው ሰዎች የክህሎት እድገታቸው በሁሉም ዘርፍ አዝጋሚ የሚባል ነው።
- የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ግን የተለየ፤ ያልተስተካከለ የክህሎት እድገት ሲኖራቸው ይህም ማለት
ለምሳሌ፡- ተግባቦት፤ ማህበራዊ እና የቋንቋ እድገታችውን ስንመለከት የተወሰኑ ክህሎቶች ላይ ፈጣን እድገት ሲያሳዩ ሌሎቹ ላይ ደግሞ አዝጋሚ እድገት ሊያሳዩ ይችላሉ።
- መናገር አለመቻል ማለት ማሰብ እና መማር አለመቻል ማለት አይደለም፤ መናገር መቻል እና አለመቻል በራሱ የአዕምሮ ብቃትን ሊያሳይ አይችልምና። በከፍተኛ ሁኔታ መናገር የሚችሉ ሰዎች(Highly verbal individuals) የአዕምሮ ብስለታቸው አማካይ ላይ ሊሆን ይችላል። አልያም ከአማካይ ያነሰና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ሊኖራቸው ይችላል። እዚህ ጋር ሌላው መታየት ያለበት ነገር መናገር የማይችሉ (ቃል አልባ) (Non-verbal Autistic) የአዕምሮ ብስለታችው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
- በኦቲዝም የተለየ (Diagnose) የተደረገ ግለሰብ በአዕምሮ እድገት ውስንነት ከተለየ (ከዕድሜ እኩዮቹ ያነሰ የአዕምሮ ብቃት ካለው) ሰው ጋር እኩል (ተመሳሳይ) አይደለም።
- ኦትስቲክ የሆኑ እና በተጨማሪ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ልጆች ላይ ችግሩ የሚገለጽበት መንገድ የተለየ ሲሆን፤ የሚማሩበት መንገድም የተለየ ይሆናል፤ የሚፈልጉትም ከፍተኛ የሆነ የግል ድጋፍ ነው፤ ኦትስቲክ ሆነው በተጓዳኝነት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ከሌላቸው ጋር ሲነፃፀሩ።
- ኦትስቲክ በሆኑ ልጆች ላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት መኖሩን መለየት ተገቢ የሆነ እራስን ችሎ ለመኖር የሚያግዛቸውን እና መማር የሚያስችላችውን ድጋፍ ለመስጠት የጎላ ጠቀሜታ አለው።
- ተገቢውን ድጋፍ ካገኘ ሁሉም ሰው ማደግ፤መማር እና መሻሻል ይችላል፤ ሌላው ከሚስተዋልባቸው ተግዳሮት ባሻገር የራሳቸው የሆነ ሊከበርላችው የሚገባ ምርጫም እንዳላቸው ማሰብ ተገቢ ነው።
እሳቤዎች
- ኦቲዝም ማለት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ማለት አይደለም፤ የአዕምሮ ብቃት ዝቅተኛ መሆን ኦቲዝምን ለመለየት መስፈርት አይሆንም።
- የአዕምሮ እድገት እክል መኖር አንድን ሰው የአዕምሮ ብቃትን የሚጠይቁ እንደትምህርት፤ ክህሎት ማዳበር እና ተግባር ላይ ለማዋል ተግዳሮት እንዲገጥመው ቢያደርግም፤ ነገር ግን ይህ ማለት መማር አይችልም ማለት አይደለም።
- ኦቲዝም ያላቸው ልጆች እድገታችውን ተከትሎ የሚመጣ የመልመድ ብቃት ላይ ብዙ ያዘግማሉ ተብሎ አይታሰብም፤ ነገር ግን እድገታቸው የሚገለጸው በተለይ እና በአጠቃላይ ባልተለመደ ማህበራዊ፤ ተግባቦት፤ ቋንቋ እና እራስን የመርዳት ክህሎት ሂደት ነው። እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ነገር እድገት ተለዋዋጭ መሆኑን ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ April 2 የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ሲሆን፤ ወሩ ደግሞ የኦቲዝም ወር በመባል ይታወቃል። ኦቲዝም (Autism spectrum disorder) ዋነኛ መነሻ ምክንያቱ አሁንም ድረስ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ መታወቅ ያልቻለ ሲሆን፤ አንዳንድ ከባቢያዊ እና ሥነ-ባህሪያዊ ምክንያቶች (Genetical causes) አጋላጭ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ መላምታቸውን አስቀምጠዋል።
ሁላችንም ስለ ኦቲዝም እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ትክክለኛውን አመለካከት ይኑረን፤ እንዲሁም በቂ ድጋፍ ከተደረገላቸው እንደ ማንኛውም ሰው መማር፤ መለወጥ እና መሻሻል ይችላሉ በማለት ፅሑፌን ለማጠቃለል እውዳለሁ::
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013