ኢያሱ መሰለ
ይህን አርቲክል ለመጻፍ ሳስብ ‹‹የፍልስፍና ሀሁ እራስንና ህይወትን ማወቅ ነው።›› የሚለው አባባል በአዕምሮዬ ይመላለስ ጀመር። ግን ምን ያህል እራሴንና ሕይወቴን አውቄ ነው ስለሌላው ጉዳይ ለመጻፍ የተነሳሁት ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ወድጄ አይደለም የፍልስፍና አንዱ ባህሪው ማሰላሰል ነው።
ቆየት ስል ሌላ የፍልስፍና አባባል ትዝ አለኝ ‹‹ትችትን አጥብቀህ የምትጠላ ከሆነ ምንም አትናገር፤ ምንም አትስራ ከዚያ ለምንም የማትሆን ሰው ትሆናለህ›› ይላል። አያችሁ? የፍልስፍና ጥቅሙ ይህ ነው፤ አንድ ነገር ላይ አይቆምም፤ አንዱን አንስቶ፤ አንዱን ይጥላል። ነጻነት ይሰጣል።
ፍልስፍና ነገሮች በጥልቀት የሚመረመሩበት፣ እውነት፣ ጥበብ፣ ፍቅር፣ በአመክንዮ የሚቀርቡበት ነው። ሰዎች ያዩትን ወይም የተነገሯቸውን እንዳለ ትክልል ነው ብለው ከመቀበል ይልቅ አዳዲስ ጉዳዮችን እያመጡ በአመክንዮ የሚያስረዱበት ጥበብ ነው። ሰዎችን ወደተሻለ ነገር ሊያሸጋግሩ የሚችሉ ንድፈ ሃሳቦችና ተግባሮች መገኛም ነው።
ፍልስፍና የማይዳስሳቸው ጉዳዮች የሉም። ሰው ከራሱ ጋር፤ ሰው ከሰው ጋር፤ ሰው ከተፈጥሮ ጋር፤ ሰው ከፈጣሪው ጋር ወዘተ ባለው ተፈጥሯዊ ግንኙነት በርካታ ጉዳዮችን ያነሳል፤ ይጥላል። በምናቡ የሚያመላልሳቸውንም ጉዳዮች በቃል ይገልጻቸዋል። በቃል የሚገለጹ ጥልቅ መልእክቶች ደግሞ በሚያምር ቋንቋ እየተከሸኑ ሲቀርቡ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና የማጎልበትና አቅጣጫን የማሳየት ሚና ይጫወታሉ።
በፍልስፍናው ዘርፍ አሻራቸውን ጥለው ያለፉት የሀገራችን ሊቃውንት በርካታ ናቸው። በተለይም በ13ኛው ክፍለዘመን ለየት ያሉ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን እያፈለቀ ሰዎችን ሲያስደምም የነበረውን ዘርዓያዕቆብ ዛሬ ላይ ሆነን የአስተሳሰቡን ምጥቀት ስንመረምረው የሚያስደንቅ ነው። ለምሳሌ ከሚያራምዳቸው አስተሳሰቦች ውስጥ ልቦና የማይደርስበት ሃይማኖታዊ አስተምሮት እንደሌለና እጅግ የተዋጣው ትክክለኛ የአኗኗር ዘዴ ከተፈጥሮ ህግና ስርዓት ጋር መስማማት እንደሆነ የሚያምን ነው። ከፍልስፍና ጋር የተያያዙትን የሀገራችንን ምሳሌዊ ንግግሮች፣ ፈሊጣዊ አባባሎች፣ ተረቶች፣ ስነጽሁፎች ወዘተ እንዘርዝር ብንል ቆጥረን አንዘልቃቸውም። ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌ መጽሃፋቸው የጻፏቸው እንደ ‹‹የሸክላ ድስትና የብረት ድስት፣ ላሜ ቦራ ›› የመሳሰሉት በስነጽሁፍ እድገት ላያ ካበረከቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የደራሲውን የህይወት ፍልስፍና ያሳዩ እና በማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ላይ አንዳች ቁም ነገር ያስቀመጡ ናቸው።
የክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልቦለድ መጽሃፍም ደራሲው በወቅቱ የነበረው የአስተዳደር ስርዓት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ የጠቆመ፤ በፊውዳሉ ስርዓት በላይኛውና በታችኛው መደቦች መካከል ወይም በሰዎች መካከል ያለው ከመጠን ያለፈ ርቀት መጥበብ እንዳለበት ያስተማረ ነው። ደራሲው እየጻፈ ብቻ ሳይሆን በራሱ እይታ ሁኔታዎችን እየመረመረ መለወጥ ያለባቸውን ኋላ ቀር አስተሳሰቦች እያስተማረም ጭምር ነው። እነዚህና ሌሎችም ካለፈው ዘመን የቀዳናቸው ተራማጅ አስተሳሰቦች በማህበረሰቡ አእምሮ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። እንዲህ አይነት እሴቶቻችንን ትኩረት ሰጥተን ከተጠቀምንባቸው በዛሬውም በነገውም ህይወታችን ላይ ብርሃን ይፈነጥቁበታል።
የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ከታሪክ ጋር ትስስር ያላቸውን የፍልስፍና አባባሎች ከወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ አንጻር በመፈተሽ ላይ ያለመ በመሆኑ ከመጻህፍትና ከዌብ ሳይት የተገኙ የፍልስፍና አባባሎችን መነሻ በማድረግ ለመተንተን የሞከረ ነው።
ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብራቸው ወይም በግል ህይወታቸው ቢጠቀሙባቸው የሚያተርፉባቸው በርካታ የታሪክ ትሩፋት አሉ። ታሪክ ያለፈ ሁኔታን የሚያሳይ መስታወት ነው። በታሪክ መስታወትነት የተመለከትናቸው አሉታዊና አዎንታዊ ክስተቶች ቀጣዩን ማህበረሰብ ወይም ትውልድ በቀና መንገድ የመምራት ሚናቸው ከፍ ያለ ነው።
በተለይ በሀገራችን አሁን የሚታየው ምስቅልቅል አስተሳሰብ የታሪክን ግብ ካለመረዳት የመጣ መሆኑ ሲታሰብ እና ታሪክ ወደፊት ማራመዱን ትቶ ወደ ኋላ የሚጎትት ሲሆን፤ ወይም ማስተማሪያ መሆኑ ቀርቶ መጠቀሚያ ሲሆን ተዳፍኖ ቢቀር ያሰኛል። የታሪክ እውቀት ዓላማው አንድና አንድ ነው። እርሱም ከታሪኩ መማር ። ምናልባት በበቂ መረጃ የተረጋገጠ ነው ቢባል እንኳን በዚያን ባልሰለጠነ ዘመን የተሰራን ስህተት በዚህ በሰለጠነ ዘመን እንዳይደገም ማድረግ ሲገባ ጥፋትን በጥፋት ለማካካስ መሞከር ከሰለጠነ ሰው የማይጠበቅ ነው።
ባለንበት ዘመን ሰዎች ታሪክን ለፖለቲካ ትርፍና ለግል ህይወታቸው መጠቀሚያ ለማድረግ በማሰብ የተዛቡ ትርክቶችን እየተናገሩ ሀገሪቱን ወደ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ለማስገባት ሲሞከር አይተናል። ማነው የተሳሳተ ታሪክ የሚያወራው ? ለምን ዓላማነው የሚያወራው? የሚለውን መመርመር ደግሞ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል።
እዚህ ጋር ‹‹ብልህ ሰው ከሰው ስህተት ይማራል፤ ሞኝ ሰው ከራሱም ስህተት አይማርም›› የሚለውን የሀገራችንን ብሂል ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ‹‹ስህተት›› ቀጣይ ዘመናችንን ለማሳመር ግብዓት ሆኖ ሊጠቅመን እንደሚችል የሚያስረዳ ነው። ስለዚህ በስህተት የተመዘገቡ ታሪኮች ካሉን እነዚያን ታሪኮች ማስታወስ ያለብን ቀጣይ ስህተት ላለመስራት መሆን አለበት ምክንያቱም ህይወት ሙሉ ስዕል የሚኖረው የትናንትናው የዛሬውና የነገው ተደምረው ጤናማ ስሌት ሲሰራላቸው ብቻ ነውና።
የግሪክን ፍልስፍናን ለአውሮፓ ያስተዋወቀውና ከክርስቶስ ልደት በፊት በኢጣልያ ሀገር ስሙ ገኖ የነበረው ፈላስፋና የስነጽሁፍ ሰው ቱሊየስ ሲሴሮ /Tullius Cicero/ ታሪክን እንዲህ ይገልጸዋል። ‹‹ ታሪክ የዘመን ምስክር፣ የእውነታ ብርሃን፣ የኑሮ ማስታወሻ፣ የህይወት ማስተማሪያ እንዲሁም የጥንት ስራ መልእክተኛ ነው። ›› ይህ ሰው በሮማ ታሪክ ውስጥ ታላቁ የስነጽሁፍና የፍልስፍና ሰው ተብሎም ይጠራል።
በተለይም በላቲን ቋንቋ ውስጥ አዳዲስ የፍልስፍና ሀሳቦችን በማንጸባረቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም ይነገራል። ሲሴሮ ታሪክ የዘመን ምስክር ነው ሲል ባልነበርንበት ዘመን የተከሰተን ጥሩም ይሁን መጥፎ ጉዳይ እንዲህ ሆኖ ነበር እንዲህ ተከስቶ ነበር እያለ የሚያስረዳ መሆኑን እንገነዘባለን። ታሪክ የጥንት ስራ መልእክተኛ የሚያስብለውም በጥንት ዘመን የተከሰቱ ኩነቶችን መዝግቦ በማቆየት አሁን ላለው ትውልድ ስለሚያቀብል ነው። ይዞ የሚመጣው ታሪክ ግን የሚያቃቅር ወይም የሚያጠፋፋ ሳይሆን የሚያስተምርና የምንጓዘውን መንገድም በብርሃን አጅቦ ወደፊት የሚያራምደን ማለት ነው።
የታሪክ ትምህርት በስርዓት ትምህርት ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ዋናው ምክንያት ሰዎች የዓለምንም ይሁን የሀገራቸውን ታሪክ በሚገባ እንዲያውቁ ነው። ከመጥፎ ታሪኮች ይማራሉ፤ ጥሩዎቹን ልምዶችና ተግባሮች ያስቀጥላሉ። በ1966 ዓ.ም የወሎ ህዝብ ሲራብ በወቅቱ የነበረው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠም በሚል ተተችቷል። የችግሩን አስከፊነት በፍጥነት ተረድቶ አስፈላጊውን ምላሽ ባለመስጠቱ በርካታ ወገኖቻችን በረሃብ ሞተዋል። ይህ መጥፎ ታሪክ ሲታወስ ያስቆጫል።
ጉዳዩ ታሪክ ሆኖ አልፏል። ይህ የሚያስቆጭ መጥፎ ታሪክ እንዳይደገም ግን ተምረንበታል። ስለዚህ ረሀብ እንዳይከሰት አስቀድመን እናመርታለን፤ በአየር መዛባት ወይም በሌላ ምክንያት ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ ከሌለ ግን ሰዎች እንዳይራቡ አስቀድመን እንዘጋጃለን። በ1966 ዓ.ም በሀገራችን ከተከሰተው ረሃብ በኋላ በ1977 ዓ.ም ሌላ የድርቅ ወቅት ተከስቶ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል። ያስከተለው አደጋና እልቂት ግን አንዳለፈው አልነበረም። ምክንያቱም ከዚያኛው ተምረን ስለነበር ነው።
ኢትዮጵያ እንደሀገር ከመመስረቷ በፊትም ይሁን በኋላ በህዝቦች መካከል አለመግባባት፣ ግጭት፣ የመደብ ልዩነት የተፈጠረባቸው መጥፎ ታሪኮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተዛዘን፣ መደጋገፍ የታዩባቸው ረዥም የታሪክ ዘመናት ነበሩ። እንዲህ ስል ዛሬ የሉንም ማለቴ እንዳልሆነ ተረዱኝ። የሚያቀራርቡ ታሪኮቻችንን እየደፈቅን የሚያለያዩንን ብቻ እየመዘዝን ማራገቡ፤ ሌላ መጥፎ ታሪክ እንዲደገም ከማድረግ ውጭ ጥቅም የለውም። እንደሀገርም እንደህዝብም እንደማህበረሰብም እንደግለሰብም ያለፈውን ታሪካዊ ስህተት ማስታወስ የሚጠቅመው ዳግም ስህተት ላለመስራት ብቻ መሆን አለበት። እንዲህ ካልሆነ ግን ሲሴሮ እንደሚለው ‹‹ ከታሪክ ምንም አንማርም፤ የምንማረው ከታሪክ ምንም መማር አለመቻላችንን ብቻ ይሆናል ማለት ነው።››
ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሸጋገረች ባለችበት ዘመን ስለመፈጸማቸው እርግጠኛ ያልተሆነባቸው መጥፎ ታሪኮች ላይ ትኩረት እያደረጉ በፍቅርና በሰላም በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚጥሩ ተማርን ባዮች በዝተዋል። እነዚህ ሰዎች ለምን የአባቶቻችንን ተጋድሎ፤ ማለትም ደማቸውን አፍስሰው ህይወታቸውን ሰጥተው ሀገራችንን ያቆዩበትን የጋራ ታሪካችንን አጉልተው እንደማይናገሩ አይገባኝም።
ይባስ ብለው ታሪክ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ በመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ ተካቶ እንዳይቀርብ ይሰራሉ። ባለንበት ዘመን የታሪክ ሽሚያ፣ የታሪክ ቅሚያ፣ የታሪክ ውጊያ ውስጥ ተገብቷል። ለመልካም ቢሆን ባልከፋ።
አንድ ሀገር የበዳይና የተበዳይ ትርክቶችን እየዘመረ እድገት ማምጣት አይችልም። ማነው የተበደለው? ማንነው የበደለው? ማን ነው ያልተበደለው? ይልቁንስ ለበዳዩም ለተበዳዩም የሚጠቅመው የበደል ስህተቶች እንዳይደገሙ በማድረግ መጪውን ዘመን ለመጪው ትውልድ ሰርቶ ማስረከብ ነበር። በቃ ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ነው።
ይህ ባይሆንማ ኖሮ ውቅያኖስን ተሻግሮ መጥቶ አያት ቅድመአያቶቻችንን በግፍ ከጨፈጨፈው ፋሺስት ጋር ዛሬ በትብብር ባልሰራን ነበር። ጣሊያንና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገሮች ናቸው:: በዚህም ላይ ጥሩ ታሪክ አልነበራቸውም። እኛ ኢትዮጵያውያን በደም የተሳሰርን የአንድ ሀገር ህዝቦች ነን፤ ተወራራሽ ባህል፤ ተወራራሽ ቋንቋና ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ የምንከተል። እንደኢጣሊያ ካለው ሀገር ጋር ተስማምተን እየሰራን እርስ በእርሳችን እንዳንግባባ መጥፎ ታሪኮችን እያነሱ ሊያለያዩን ለሚፈልጉ ሰዎች ጆሯችንን የምንሰጣቸው ለምን ይሆን ?
አንዳንድ ፖለቲከኞች ታሪክን የስልጣን መወጣጫ እርካብ ለማድረግ በማሰብ ለመጡበት ብሄረሰብ እነርሱ ብቻ ተቆርቋሪ እነርሱ ብቻ አድራጊ ፈጣሪ ሆነው ያልሆነ የሆነውን ይቀበጣጥራሉ። ይህን ሳይ ቂመኛ፣ ጨካኝ፣ ስርዓተ አልበኛ፣ አጥፊ፣ እራስ ወዳድ ትውልድ በኢትዮጵያ ምድር እንዲፈጠር የሚያደርጉት ስልጣን ወዳድ ፖለቲከኞች ናቸው እንድል እገደዳለሁ። ለሀገር እድገት፣ ለህዝቦች ብልጽግና የሚያስብ እውነተኛ ፖለቲከኛ መሰረቱን የሚጥለው በህዝቦች መፈቃቀር ላይ ነው። ምናልባት ቀንቶት የተመኘውን ስልጣን ቢያገኝ እንኳ ማስተዳዳር የሚችለው የሚቻቻል፣ የሚፋቀር አንድነቱ የተጠበቀ ህዝብ ሲኖር ነው።
ምንጩን ‹‹የአሸዋና የድንጋይ ላይ ጹፎች›› አድርጎ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያገኘሁትን ሀገር በቀል ብሂል ላጋራችሁ። ‹‹ የሚያደርጉልህን መልካም ነገሮች በልብህ አለታማ ቦታዎች ላይ ጻፋቸው። የሚሰሩብህን የክፋትና የተንኮል ስራዎች ደግሞ በአሸዋማ ቦታ ላይ ጻፋቸው። ምክንያቱም አንድን ሰው የምትወደው መልካም ነገሮቹን ባሰብክ ቁጥር ነውና። በአለቱ ላይ የጻፍከው ደግነት ብዙ ጊዜ ሳይረሳ ይቆያል፤ በአሸዋ ላይ የጻፍከው ክፋት ግን በቀላሉ በነፋስ ተጠርጎ ይጠፋል። ››
በልባቸው ቂምና በቀልን ማስቀመጥ የማይፈልጉ ቅን ሰዎች መጥፎ ታሪኮችን በአለት ላይ ጽፈው አያስቀምጡም። ተበድለውም ቢሆን እንኳ ለሰው ያላቸው ፍቅር እንዳይጠፋ በመጠንቀቅ መጥፎው ነገር ቶሎ ብሎ ከውስጣቸው እንዲወጣና እንዲረሱት ይፈልጋሉ። ክፉ ሰዎች ግን ዘመናትን ወደ ኋላ ሄደው የታሪክ ሰነዶችን እያገለባበጡ የተፈጸሙትንም ያልተፈጸሙትንም መጥፎ መጥፎ ታሪኮች እያስታወሱ አንዳንዶቹንም እየፈጠሩ ህዝቦችን ያለያያሉ።
በአሉታዊ አስተሳብ ጫና ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁል ግዜም የሚታያቸው መጥፎ መጥፎ አስተሳሰብ ነው። አይናቸው ከብርሃን ይልቅ ጨለማውን መመልከት ይፈልጋል። የራሳቸው በጨለማ ውስጥ መዳከር ሳያንስ ሌሎችንም ለመክተት ይፈልጋሉ።
አስተውለን ከሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም በተነሱ ጸረሰላም ሃይሎች አደጋ ውስጥ ወድቃለች። የውጭ ሃይሎች ለኢትዮጵያ ጠላት የሆኑት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር በማሰብ ነው ብለን እናስብ። የሀገር ተቆርቋሪ፣ የህዝብ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ ፖለቲከኞቻችን የውጭ ሃይሎችን አጀንዳ ለማስፈጸም የሚያጋጨንን ታሪክ እየፈለጉ ወይም እየፈጠሩ እርስ በእርስ እንድንናከስ ያርጉናል። ፍቅራችንን ለማጥፋት፣ አንድነታችንን ለማላላት፣ ታሪካችንን ለመድፈቅ ተግተው ይሰራሉ። ታሪክ የትናቱን የሚነግረን የነገውን በተሻለ መንገድ እንድንሰራ እንጂ የትናንቱ ላይ እንድንቆም አይደለም።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013