አሊሴሮ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተለያዩ መልኮች ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮችና ውይይቶች ቀጥለዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃው ተነስቶላቸው በአገሪቱ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ላይ ተሠልፈዋል።
ከእነዚህ ድርጅቶች መካከልም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነት)፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የሚጠቀሱ ናቸው።
ከውጭ የመጡትን የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ በአገሪቱ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካው ሲሳተፉ የነበሩ ድርጅቶች፣ አሁን ላለው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አዋጭ መፍትሔ ነው ብለው የሚያስቡትን የመፍትሔ ሐሳብ በየፊናቸው መሰንዘራቸውንም እንዲሁ ቀጥለዋል። አንዳንዶቹም ይህ ካልተደረገልኝ በምርጫው አልሳተፍም፤ይህ ሁኔ መጀመርያ መደረግ አለበት ወዘተ እያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲደረድሩ ይታያሉ። የሆኖ ሆኖ ግን ዴሞክራሲ ያለምርጫ አይታሰብምና የዘንድሮ ህጋዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከቅድመ ሁኔታ ወጥተው ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊወጡ ይገባል።
በበርካታ ፖለቲከኞች የተሳሳት ግምት ሚሊዮኖች ዜጎችን የታቀፈች ሀገር የምትፈረጀው “ከእኔና ከእኔ መሰሎች ውጪ ከቶውንም ሀገር ሀገር አትሆንም” ከሚል ድምዳሜ መውጣትና ኢትዮጵያ ሁሉም ሀገር መሆኗን ማመን ይገባል። ሁሉም ነገር ውስጥ አለሁበት ሁሉም የእኔ ነው ከሚለው ኋላቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥተን የህዝብን ድምፅ ሊገዙ የሚያስችሉ ሃሳቦችን በመሸጥ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብን ሸጦ ተወዳድሮ ከማሸነፍ ይልቅ ስሜት ቀስቃሽ ነገሮችን በማንሳትና የበዳይና የተበዳይ የፖለቲካ ትርክትን በማጎን በአቋራጭ ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲታትሩ ይታያሉ። ለይህ አካሄድ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከመጉዳቱም በሻገር የጥላቻ ፖለቲካን በማንገስ ሀገሪቱን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነው። የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዳኙት የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ በሚታሰበው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ ከመውጣታቸው በፊት፣ የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይጠበቅባቸዋል። ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈለገውን ዲሲፕሊን ያላሟላ የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ብያኔ መቅረብ አይችልም። የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያስፈልጋቸዋል።
ራሳቸውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ጨዋታ ሕግ ማስገዛት የማይችሉና ግልጽና የተብራራ አጀንዳ የሌላቸው ፓርቲዎች፣ ሕዝብ ፊት በመውጣታቸው የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል። ሕዝብን በጉልበት፣ በማታለል፣ የማይጨበጥ ቃል በመግባት ወይም አገር በማተራመስ ሥልጣን መሻት እንደማያዋጣ መረዳት ይገባል።
ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሐሳብ ልዩነትን የሚያከብር የፖለቲካ ምኅዳር ነው። የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄ መነሻም ይኼ ነው። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከብሯል ከሚባልባቸው መሥፈርቶች አንዱ፣ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ነው። በሐሳብ የሚለይ ግለሰብም ሆነ ቡድን የሌሎችን መብት ማክበር መቻል አለበት። የሐሳብ ገበያው የሚፈልገው አንድን ሐሳብ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ሐሳብ ይዞ መገኘትን ጭምር ነው። ዴሞክራሲ መለምለም የሚጀምረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
የአገሪቱ ኋላ ቀር የፖለቲካ ምኅዳር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አጀንዳ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገጽታው መለወጥ አለበት። የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲለወጥ ደግሞ፣ የጨዋታው ሕግ በአግባቡ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል። የጨዋታው ሕግ ምን ይላል? ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት መላበስ፣ ልዩነት አብሮ ለመሥራት አያመችም ከሚል ቅዠት ውስጥ መውጣት፣ ያልተገደበ የሕዝብ ውይይትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ማድረግ፣ ዝምታን አስፍኖ አሉባልታንና ሹክሹክታን የሚያባዛ የተወጠረ አየርን ማስተንፈስ ነው። ዴሞክራሲያዊነት ደግሞ በመብቶችና በልዩነቶች ውስጥ አብሮ ለመኖር መቻል ማለት መሆኑን፣ ይኼንንም መሠረት ለማስያዝ በመረባረብ ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ውጤቱንም መቀበል የጨዋታው ሕግ አካል ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሰላም፣ በነፃነትና በእኩልነት የሚያኖረው ሥርዓት እንዲገነባለት ነው። የተሻለ ገቢ፣ ለኑሮ አመቺ የሆነ መኖሪያ፣ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ፍትሕና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል አጀንዳ ያለው ፓርቲ የሕዝብን ቀልብ ይስባል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር መሆን ያለበትም ይህንን ፍላጎት ለማርካት ነው።
ባለፉት አአምስት ምርጫዎች ያካሄድናቸው አምስት ‹‹ምርጫዎች›› የይስሙላ መሆናቸውን ሁሉንም የሚያስማማ ነው። ሆኖም ግን እነዚህ የይስሙላ ምርጫዎች እንዲካሄዱ ሁሉም ባይባል እንኳን እንደአሸን የፈሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን ጡብ ማስቀመጣቸውን ግን መካድ አይቻልም።
ምርጫ በመጣ ቁጥር ሀገርን ወደ አንድ ትልቅ ግብ ለማሸጋገር ከማቀድ ይልቅ እንደ አንድ ገቢ ማስገኛ ዘርፍ መቁጠር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ ተግባር መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ስለሆነም አሁንም በዚህ አባዜ ውስጥ የሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲ ካለ ጊዜው አያስኬድምና ከተቻለ አቋምን አስተካክሎ ለህዝብና ለወገን የሚጠቅሙ ሃሳቦችን አንግቦ በምርጫው መወዳደር ካልሆነም በጊዜ ከፖለቲካ ምህዳሩ ገሸሽ ማለት ለራስም ለሀገርም ይጠቅማል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ እንዳደረገው መልክታቸውን ሲገቡና ለምርጫው ዝግጁ የሆኑ ፓርቲዎች ቁጥር 49ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 10 ሀገራዊ ቀሪዎቹ ደግሞ 39ኙ የክልል ፓርቲዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ እንደሚስተዋለውም ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ስለኢትዮጵያ የሚጨነቁና ትኩረታቸውም አንድነትንና ህብረትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይራመናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ብሄርን መሰረት አድርገው የተቋቋሙት የክልል ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደማያገባቸውና ትኩረታቸውም ብሄራቸውና ክልላቸው እንደሆነ ተደርጎ ይሳበል። ሃሳቡን ሙሉ ለሙሉ ማጣጣል ባይቻልም በዘንድሮ ምርጫ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህብረብሄራዊነት ትኩረት መስጠት ኢትዮጵያንም ለማስቀጠል የተሻለ ድምፅም ለማግኘት አዋጭ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ብሄርተኞች ምንም ቢጮሁ የአብዛኛው ህዝብ ፍላጎትና ሞኞት ኢትዮጵያዊነት አብቦ፤ወንድማማችነት በልጽጎ ማየት ነው።
በኢትዮጵያ አንድነትና በሕዝቡ አብሮነት ላይ የጋራ ራዕይ ሊኖር የግድ ይላል። ኢትዮጵያ ሲባል የሚከፋቸውና የሕዝቡን አብሮነት መስማት የማይፈልጉ ወገኖች አሁንም አሉ። ከሥልጣን በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የሚላቸው ፖለቲከኞች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር ራሳቸውን ዝግጁ ያድርጉ። ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ የአገር ህልውና መቅደም አለበት።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013