ውብሸት ሰንደቁ
ተወልዶ ያደገው ድሬደዋ ከዚራ አካባቢ ነው። ኑሮውን አዲስ አበባ ካደረገ ከ10 ዓመት በላይ አስቆጥሯል።የተሰማራበትን የእጅ ጥበብ ዘርፍ ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል። ሀሁ አርት የተሰኘ የጌጣጌጥ አምራችና ዕቃዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ድርጅት ባለቤት ነው- አቶ ይማጅ መሀመድ።
‹‹አጠቃላይ ሥራዎችን የምሠራው ቆሻሻ ተብለው ተጥለው አካባቢን ከሚበክሉ ነገሮች ነው። ቆሻሻ ተብለው የሚጣሉ ነገሮችን በመጠቀም ለቤት፣ ለቢሮና ለተለያዩ ቦታዎች ውብ ጌጣጌጦችን መሥራት ያስደስተዋል። የአካባቢ ብክለት ነገር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ቢያስጨንቀኝም የምሠራው ጌጣጌጥ ከነዚሁ ቆሻሻ ተብለው ከሚጣሉ ዕቃዎች መሆኑ ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ከሚባለው አባባል ጋር የተሰናሰለ ነው›› ይላል። አንድም ቆሻሻን ወደ ጌጥነት ይቀይራል ሁለትም ፅዱ አካባቢን ፈጥሮ የገቢ ምንጭ ያገኛል።
ከግለሰብ ቤት ጀምሮ በየመንግሥትና የግል ተቋማት ብዙ ዕቃዎች አያስፈልጉም ተብለው ተጥለው የአካባቢውን ውበት ያበላሻሉ፤ ነዋሪውንም ለበሽታ ያጋልጣሉ፤ እንዲሁም አካባቢ ላይ ከፍተኛ የሆነ ብክለት ያስከትላሉ። እነዚህን ዓይነት ዕቃዎችን ለቤት ጌጥና ማስዋቢያነት አልፎ ተርፎም ለመልሶ ግልጋሎት እንዲውሉ እያስቻለ መሆኑ በስራው ደስተኛ ነው። በአብዛኛው ወጣት ‹‹ሥራ የለም›› የሚል አመለካከት አለው። በተቻለ መጠን ሥራ ፈጣሪ የሆነ ትውልድ ለማፍራት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወጣቶች ከአካባቢያቸው ያሉ ነገሮች ላይ ዓይናቸውን እንዲገልጡ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑ ይሰማዋል። ‹‹ወጣቱ ትውልድ የዕይታ አድማሱን ማስፋት ከቻለ ለሥራ መጀመሪያ የሚሆን የመነሻ ካፒታል ያስፈልገዋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በእኛ ሀገር ደረጃ ብዙ የተጣሉና ዝቅ ብለን ማንሳት ከቻልን ገንዘብ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ውዳቂ ናቸው ተብለው የሚጣሉ ነገሮች ወደ ገንዘብ የሚቀየሩበት ትልቅ ማዕከል መፍጠር ነው የምፈልገው። ሰው አልፈልገውም ብሎ የጣለውን ነገር መልሶ እንዲገዛው አደርጋለሁ። ቆሻሻ የሚለው ቃል ያለው አእምሯችን ውስጥ እንጂ ቆሻሻ የሚባል ነገር በምድር ላይ የለም። ሁሉንም በአግባቡ ከተጠቀምንበት ሀብት ነው›› ይላል።
መነሻ ካፒታሉ ለማጣበቂያ እና ለቀለም ያወጣው ጥቂት ገንዘብ እና የወዳደቁ የመኪና ጎማዎች፤ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፤ ላንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ ማንኪያዎች፤ የጁስ መምጠጫ ፕላስቲኮችና የመሳሰሉት የወዳደቁ ነገሮች ናቸው። እነዚህን የወደቁ ቁሶች ወደ ሰዓት፣ መስታወት ጌጥነት እና ወደመሳሰሉት የቤት ማስዋቢያነት በመቀየር ለሽያጭ አቅርቧል። የስራ ውጤቱን ሰዎች በሚገዙበት ጊዜ እነሱ ጥለዋቸው የነበሩ ዕቃዎች እንደነበሩ አያስተውሉም። ከመሬት የተለቃቀሙ ነገሮችን በቀላሉ አስውቦ መሸጥ ማለት በቀጥታ ሲነገር ገንዘብን ከመሬት መልቀም እንደማለት መሆኑን ይናገራል። ‹‹በበኩሌ ተጠቅሜ የምጥላቸው ዕቃዎች የሉኝም፤ አንድ ዕቃ አገልግሎቱ ካበቃ በሌላ መልክ አገልግሎት ላይ እንዲውል አደርገዋለሁ። ካለኝ የመሥሪያ ቦታ እጥረት አንፃር አስፍቼ መሥራት አልቻልኩም እንጂ ከዚህ በላይም መራመድ እችል ነበር።›› ሲል ስራውን በኩራት ይገልጻል።
አቶ ይማጅ ለራሱ በሰራው ስራና ባገኘው ገቢ ብቻ ተደስቶ መኖርን አልመረጠም። ይልቁንም ልምዱን ለማካፈልና ስራ አጥ ወጣቶች ስራ መስራትና በቀላል ገንዘብ እንደሚገኝ ለማነቃቃት ድሬዳዋ ድረስ ተጉዟል። አዲስ አበባ ላይ በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና በከተማ ደረጃ በሚካሄዱ ኢግዚቢሽኖች ሥራዎችን አሳይቷል። በኢግዚቢሽኑ ላይ የሠራቸውን ሥራዎች እና ሥራው የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል በተመለከተ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ለማስገንዘብ ሞክሯል። የመሥሪያ ቦታ ጥያቄው ግን እስካሁን ሊፈታለት እንዳልቻለ ይናገራል። ‹‹የዕይታ አድማስህን ስታሰፋ ብዙ ሥራ የመፍጠር አቅም ይኖርሃል፤ ይህ ደግሞ በተራው ብዙ የገቢ ምንጮችን ይዞ ይመጣል። ለዚህም ነው ከሚጣሉ ቆሻሻዎች ውስጥ ጌጥ መፍጠር የቻልኩት፤ እግረ መንገዴንም አካባቢዎች ፅዱ እና ንፁህ አደረኩ ማለት ነው።›› ይላል።
አንድ ቀን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄጄ እያለ ድንገተኛ ታማሚ መጣ፤ ያሉት የህሙማን ማንሻ ስትሬቸሮች በጣም ውስን ስለነበሩ ታማሚውን ቶሎ አንስቶ ወደ ሕክምና ማስገባት አልተቻለም። ወጣ ሲባል ግን በግቢው በርካታ አልጋዎች፣ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ወንበሮችና ሌሎች ቁሳቁሶች ተሰባብረው ተጥለዋል። እነዚህ የወዳደቁት ቀላል ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት ሊሰጡ እና ጌጥ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ባየሁት ሁኔታ የሰው ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል በማሰቤና እንደዚህ ዓይነት በርካታ ክስተቶች ለሕይወት መጥፋት መንስኤ እየሆኑና የአካባቢን ገፅታ እያጠለሹ መሆኑን በመገንዘቤ ወደጀመርኩት ሥራ ልገባ ችያለሁ።የተጣለ አንስተን የቆሸሸውን አፅድተንና የሥራ ዕድሎችን ፈጥረን አካባቢያችንን ውብና ፅዱ እናደርጋለን።
የሚሠራቸውን ጌጦች ከ100 ጀምሮ እስከ አምስት ሺህ ብር እየተሸጠ ነው። በምሠራው ስራ የውጪ ምንዛሪን ከማስቀረቴ በተጨማሪ ሀገርኛ የሆኑ ዕሴቶች ስለሚጨመርባቸው ወደ ውጪ ኤክስፖርት ቢደረጉ አይን የሚገቡ ጥበቦች ናቸው።
አቶ ይማጅ በማህበራዊ ተሳትፎዎችም ጠንካራ የሚባሉ አይነት ሰው ናቸው። ለምሳሌ ሞጣ የተቃጠለውን መስጊጅ ለማሠራት ሰዓት ሰርቼ በማበርከት ሰዓቱ በጨረታ ከ35 ሺህ ብር በላይ ተሽጦ ለመስጂዱ ገቢ እድሳት ውሏል። ለመቄዶንያ የአረጋዊያን መርጃ ድርጅት፤ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ዓባይ ግድብ ዋንጫ ወረዳ 14 በመጣበት ጊዜ ‹‹ግድቡ ዓይኔ ነው›› በሚል ሰዓት ሰርቼ በጨረታ ተሸጦ ገቢ ተደርጓል።
ከግለሰብ ጀምሮ በመንግሥት ተቋማት ጭምር የሚባክኑና አይጠቅሙም ተብለው ተጥለው ቆሻሻ የሚሆኑ በርካታ ምርቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ ትልቅ ፀጋ አለ። እነዚህን ፀጋዎች መጠቀም እንድችልና የአካባቢውን ውበት አስጠብቄ በርካታ የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጮች እንድፈጥር ዕድሉ እንዲመቻችልኝ እጠይቃለሁ። በዚህ ሁኔታ እንኳን በየክፍለ ከተማው አንዳንድ ቆሻሻን መልሶ መጠቀም የሚያስችሉ ማዕከላት ብንገነባ በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013