ውብሸት ሰንደቁ
የዛሬን አያድርገውና ድሮ ድሮ ገንዘብ የሚባል የስምምነት ወረቀት ሳይመጣ ንግድ ዕቃን በዕቃ በመለወጥ ግብይት (bartering) ቀጥሎም እንደ አሞሌ ባሉ ሰው ዕለት በዕለት በሚፈልጋቸው ነገሮች መገበያየት፤ ሰው ያለውን እየሰጠ የሌለውን የሚገበይበት መንገድ እንደነበረ ይነገራል።
በኢትዮጵያ የዘመነ ሥርዓት ተብሎ ጠገራ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበረም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዛሬ ዛሬ የንግድ ግብይት ሥርዓት እንዲይዝ ታስቦ በሙያና በሕይወት ምርጫነት ተወስኖ ከመንግሥት ፈቃድ ተወስዶ የሚገባበት ዘርፍ ነው።
መንግሥትም ሥርዓቱን ለማዘመን የበይነ መረብ ሽያጭን ጨምሮ የተለያዩ የግብይት ሥርዓቶች እንዲበረታቱ ድጋፎች ቢደረጉም ዛሬም ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት፤ ነጋዴውን ከግብር ተጫነኝ አቤቱታ፤ ግብር ሰብሳቢው ከተጭበረበርኩኝ ዋይታ ማዳን የሚችል ሥርዓት አለመዘርጋቱ የሚያሳዝንና መሬት ላይ ያለ የሚጨበጥ ዕውነታ ነው።
በርግጥ ሕዝቡ እዚህም እዚያም በተንጠባጠቡና በኮሚቴ (በአብዛኛው ሙያዊ ክህሎት በሌላቸው) በሚመሩ የሸማች ማህበራት አማካኝነት ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በትንሹም ቢሆን ራሱን ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ ይታያል።
ዳሩ ሽር ጉዱ የሚበዛው በክብረ በዕላት ጊዜ በመሆኑ በቀጣይነት ራሱን የሚያድንና አባላቱን ሊታደግ የቻለ የሸማች ማህበር አለ ቢባል እጅግ ጥቂት ነው የሚሆነው ነው። እንዲያውም የቅብብሎሽ መረብ በመዘርጋት ከሸማች ማህበር ሱቆች በርካሽ ተገዝተው በየሸቃጩ ሱቅ በውድ ለሽያጭ የሚቀርቡ የዘይትና ስኳር ምርቶች መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ቆይቷል። የራሱን ወገን ለቤሳቢስቴን ሳንቲም ሲል ለዋጋ ንረት አሳልፎ የሚሰጠውን ቤት ይቁጠረው።
በተለይ እጥረት በሚከሰትበት ጊዜ ነጋዴው ሁሉ የመክበሪያው ጊዜህ አሁን ነው ተብሎ ነጋሪት ተጎስሞ የተነገረው ይመስል የዋጋ ንረቱ እና ሽሚያው የትዬለሌ ይሆናል። አሳዛኙ ነገር ደግሞ በአብዛኛው እጥቶትም ሆነ ሆን ተብሎ በሰው ሠራሽ መንገድ ተፈጥሮ መገኘቱ ነው። ኮሮና የመጣ ጊዜ ፒያሳ አካባቢ የሆነ ሱቅ ዕቃ እየገበየሁ ነበር። የሆነ ሰው ከመኪና ወርዶ ዕቃ እየገበየሁበት ወደነበረው ሱቅ በፍጥነት ገባ።
“ወዲያው ባለሱቅ ፓስታ አለህ” ሲል ጠየቀው፤ አዎ የባለሱቁ ምላሽ ነበር። ሰውየው በፍጥነት “አጠቃላይ ያለው ፓስታ የስንት ብር ይሆናል” ሲል ጠየቀ የ10 ሺህ ብር ይሆናል አለ ባለሱቁ ግራ ተጋብቶ ትንሽ ካሰበ በኋላ። “በቃ ሁሉንም ገዝቸሃለሁ እሺ!” አለዋ። በዚያች ቀውጢ ሰዓት እና ፒያሳን በመሰለች ቀውጢ ምድር ውስጥ ለመጀመሪ ጊዜ መልካም ነጋዴ ያየሁበት ቀን ነውና አልረሳሁትም።
ነጋዴው አንገቱን ነቅንቆ “በፍፁም አላደርገውም፤ ላንተ ሽጨልህ ሌሎቹ ደንበኞቼ ምን ይብሉ” ብሎ መለሰለት። በወቅቱ ሰውየው ነጋዴውን ለመለማመጥ ቢሞክርም አልተሳካለትምና ሌላ ራሱን መሰል ስግብግቦችን ፍለጋ ሮጦ ወጣ።
ከዚህ ገጠመኝ መረዳት የምንችለው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም አንዱ ቁምነገር ለነጋዴው ባልተገባ መልኩ ሸቀጥን ማናር ዋና ምክንያት በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ “ለእኔ ብቻ” ባይ ግለሰቦች መሆናቸውን ነው። በነጋዴዎች በኩልም በብዙ ክፉዎች የተዋጡ መልካሞች መኖራቸውን ማሳያ ይሆናል።
በሌላ በኩል በነጋዴው ላይ ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች አንዱ በተሰላ ትርፍ አለመሸጥ ነው። በርግጥ ለችግሩ መበርታት የትርፍ ስሌት ባለማውጣትና ባለማስተግበር መንግሥትም የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ነጋዴው ለሸማች ልቡ በፈቀደው ዋጋ አንስቶ መሸጥ ባሕላችን ሆኗል፤ ገዢም ግፋ ቢል ከመነጫነጭ ያለፈ የትም እንደማይደርስ ያውቀዋልና በነጋዴው መልካም ፈቃድ የተጠራለትን ዋጋ ከፍሎ ይወስዳል። ንግድ ልጓም የሚያሥፈልገው ሥርዓት ነው።
ልጓሙ ከተለቀቀ የበላዩንም የበታቹንም ረጋግጦ እና ጨፈላልቆ መጣሉ አይቀሬ ነው። ንግድ ገዢና ሻጭ በሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ተስማምተው የሚያደርጉት የዕቃ ልውውጥ ብቻ አይደለም። ሻጭ እንደሚያተርፈው ሁሉ ገዢም ከኑሮው ደሥታውንና ከወጪው ቀሪውን ማትረፍ ይፈልጋል። መንግሥትም በበኩሉ ከሂደቱ የሚያተርፈውን ግብር ይፈልጋል።
በነገራችን ላይ ብዙ ሰው መታዘብ ከቻለውና የእኔም ትዝብት የሆነው ነገር አንዱ ከንግድ የሚሰበሰበው ግብር ከነጋዴ የሚሰበሰብ አለመሆኑ ነው። ነጋዴው ለመንግሥት ግብር እየሰበሰበ ያለው ከሸማች ኪስ ነው። ለዚህ አጋላጩ መንገድ አንደኛው የትርፍ ስሌት አለመኖሩ ነው።
አንድ ነጋዴ ከአንድ ዕቃ ማግኘት የሚገባው የትርፍ ስሌት ባለመኖሩ መንግሥት ነጋዴው ላይ ግብር ከፍ በሚያደርበት ጊዜ ነጋዴው በሸማቹ ላይ ዋጋ ከፍ በማድረግ የሚያገኘውን ያልተገባ ትርፍ እንዳስጠበቀ ይቀጥላል።
ተገቢ ያልሆነው የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ እንኳን የሥነልክ ተግባሪነት ኢምንት መሆን ሌላው የግብይት ሥርዓቱ ላይ የተተከለ ሳንካ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆን ቀልደኛ ጓደኛዬ ትዝብቱን የገለፀበትን መንገድ ልናገር። ጓደኛየ ለሥራ ከተላከበት ጅማ ከተማ ሁለት ኪሎ ቡና እንዲያመጣልኝ ደውዬ ስነግረው “ሁለት ኪሎ ማለት በአዲስ አበባ ነው በጅማ ኪሎ” ሲል ፈገግ አሰኝቶኛል። ልክ አይደለ! ያለን የሥነልክ ቁጥጥርና ሳይንስ ዕውቀት እምብዛም ስለሆንን የአዲስ አበባ አንድ ኪሎ ከሌሎች አካባቢዎች ተነፃፃሪ ምጣኔ ጋር እኩል ይሆናል ብሎ ማስብ ዘበት ነው።
የግብይት ዘያችን ያደረሰብን ተፅዕኖ አይደለም ሀገር ውስጥ ከሀገር ወጥተን አንኳን አይለቀንም። ውጭ ሀገር በዘመነ የንግድ ሥርዓት ሸቀጦች በዓይነት በዓይነት የተደረደሩበት ሞል ውስጥ ገብቶ “ቀንስልኝ” ብሎና ተከራክሮ ሊገዛ የሚያምረው ሀበሻ በርካታ እንደሆነ አንድ ወዳጄ አጫውታኛለች።
ምን ያድርጉ በመርካቶ የለመደ ልማድ በፀበል እንኳን ላይለቅ እኮ የተጋባ ነው። እና አንድ ሺህ ብር ለሽያጭ የተጠራ ዕቃ ልብ ውልቅ በሚያደርግ ክርክር ሦስት መቶ ብር ሲገዛ ለኖረ በዕቃው ላይ በተጻፈ አይነቃነቄ ዋጋ ገዝቶ ቢሄድ የተታለልኩ አይስለውምን?
ይህን ዘመን ያላላቀውን የግብይት ሥርአዓት ህፀፅ አለማረም የከፋ ጉዳት ያስከትላል። ሥርዓቱ መንግሥትንና ሕዝብን እየጎዳ አጭበርባሪ ነጋዴዎችን እየጠቀመ የሚገኝ ነውና ሁለት አማራጮች አሉን ብዬ አስባለሁ፤ ወይ እኛ ዘምነን ሥርዓታችንን ማዘመን ወይም ሥርዓታችንን አዘምነን እኛን ማዘመን። አበቃሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013